Wednesday, April 15, 2015

የኤርትራ ነገር የኛ ጉዳይ ፣ ትችትን በቅኝት ( ሄኖክ የሺጥላ )

ወዳጄ ልጅ ተክሌ የጻፈውን ” የኤርትራ ነገር ፣ የኛ ችግር ፣ መርህ አልባ ፍቅር ” የምትለዋን አየሁ ። መስመር በመስመር ደግሜ ደጋግሜ አነበብኩ ። ከዚያ ተመለሼ ወዳጄ መሳይ መኮንን በዳላስ ስለ ኤርትራ ቆይታው ያደረገውን ውይይት ተመለከትኩ ፣ እኔ በነበርኩበት በሲያትል ላይ ስላደረገው ውይይትም ለማስታወስ ሞከርኩ ፣ ከዚያ የፕሮፌሰር መስፍን ወለደማርያምን ጽሑፍ በድጋሚ አነበብኩ ፣ ከዚያ ስለ ጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወለድ እና በጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወለድ የተነገሩ እና የተከተቡ ነገሮችን አነበብኩ ፣ ከዚያ ያንዳርጋቸው ጽጌን ንግግር ( ስለ ኢሳያስ አፈወርቂ የተናገረውን ) ቪዲዮ ሄጄ ተመለከትኩ ፣ ከዚያ ባንድ ወቅት ( ምናልባት ከ 3 ወይም አራት ወር በፊት ) ዔፍሬም ማዴቦ ከውህደቱ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ በ ሎስ አንጀለስ አድጎት የነበረውን ንግግር ለማስታወስ ሞከርኩ ( ስለ አርበኞች ግንቦት ሰባት ውህደት ) ፣ ከዚያ እኔ ስለ እውነት ስለ ኤርትራ መንግስት የሚሰማኝን አሰብኩ ። ባንድ ወቅት ከወዳጄ መሳይ መኮንን ጋ ባደረኩት ቃለ መጠይቅ እንዲህ ነበር ያልኩት ። ” እኔ ተኩላ ሊበላኝ ነው ብዬ ለጅብ አላመለክትም !” ፣ ይህንንም ስል ወያኔ ተኩላ ሻቢያ ደሞ ጅብ ነው ማለቴ ነበር ።
ታዲያ ዛሬ በኤርትራ በኩል የሚደረገውን ትግል ትደግፋለህ ሆይ ? አዎ ! ለምን ” ሻእብያዎች መላእኮች እንዳልሆኑ ስለማውቅ ፣ ይህም ማለት ሰይጣንነታቸውም የሚያረጅ እና የሚጃጅ መሆኑን ስለምረዳም ጭምር ። የትግሉ አካሄድ ላይ ስህተት አለ ወይ ፣ በደንብ ። ለምሳሌ ወዳጄ ተክለሚካዔል በዚህ ከላይ ባነሳሁት ጽሑፉ ላይ ያለው በሙሉ ፣ እደግመዋለሁ በሙሉ ልክ ነው !!!! ግን ሕዝቡን አያለሁ ። እደግመዋለሁ ከሻዕቢያና ከኛ ብሶት ባሻገር ዔርትራውያኖችን አስባለሁ ፣ ኢትዮጵያውያኖችን አስባለሁ ። ሰው ጥላቻን ለምዶ ነው ጠይ የሆነው ፣ ወይ ብዙ በደል ደርሶበት ወይም ብዙ የጥላቻ ወሬ ተመግቦ ፣ ስለዚህ ያ ሰው ኢ- ጥላቻን ሊማር የማይችልበት ምክንያት አይታየኝም ።
ለምሳሌ እሳት ያድበሰበሰው ግን የሻቢያን ቁርጠኛነት ወይም ኢ-ቁርጠኛነት ሊነግረን ወይም ሊያስረዳን የሚችሉ ብዙ ተጠይቀው ያልተመለሱ ፣ ወይም ያልተጠየቁ ጉዳዮች አሉ ። ለምሳሌ የአሰብ ጉዳይ አንዱ ነው ፣ የ ኮ/ል ታደሰ ሙሉነህ ነገር ሌላው ነው ፣ ስለ ደሚት የሰማነው ነገር የህጻን ልጅ ወሬ ነው የሚመስለው ፣ ኢሳያስ ካሳ ይገባኛል ያለው ስህተት ባይሆንም ፣ ለምንድን ነው ካሳ ይገባኛል ያልከው ? እና ወዘተ ብሎ መጠየቅ ነበረበት ። ግን ይሄንንስ ማን አየበት ከሆነ ነገሩ ፣ መዝለሉ ብልህነት ባይሆንም እንደ ብልጠት ነው የማየው ። ያም ሆኖ ትግሉን እደግፋለሁ ! ለምን አሁንም እደግመዋለሁ ” እኛ ኢትዮጵያውያኖች መሆናችንን ስለማውቅ !” ፣ ታሪክ ራሱን እንደሚደግም ስለማውቅ ፣ የበለጡንን መብለጥ ፣ ያመኑንን ማመን እና መታመን ፣ ያሴሩብን ላይ ማሴር እንደምንችል ስለማውቅ ። ከምንም በላይ ሻዕቢያ ይህንን ለውጥ ለራሱ ሲል እንደሚፈልገው ስለማውቅ ። ለምን ? ” ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የነጻነት ፈላጊነት ባሮ ሜትር ምን እያነበበ እንደሆነ ስለሚረዳ እና ባይፈልገውም እጁን እዚህ ላይ ካልዶለ ፣ እንደሚጎዳ በደንብ ስለሚያውቅ ። ይሄ ኢሳያስ ኢትዮጵያን ይወዳል ፣ ምናምን የሚሉትን ታሪክ ” ተናጋሪውም የተነገረለትም ” ሁለቱም እንደማያምኑበት መናገር ጠቃሚ አይመስለኝም ።
ታዲያ ይሄም ሆኖ ሳለ ትግሉን እደግፋለሁ ! ለምን ? ያለም ታሪክ በአጋጣሚዎች ላይ የተጎለተ ድማሚት ስለሚመስለኝ ። የማልደግፈው ግን ፣ ትግሉ ከዔርትራ ብቻ መነሳት አለበት የሚለውን ነው ። አቅሙ ያላቸው ሰዎች አማራጭ እንዲያዩ እመክራለሁ ። ሰሞኑን ሱዳን አካባቢ አንዳንድ ጠቋሚ እና ጠቃሚ ነገር እያየሁ ነው ። ሌላም ነገሮች ይኖራሉ ። እርግጥ የኤርትራ መንግስት ወዳጄ መሳይ እንደነገረን ተቃዋሚዎች አንድ ሁኑ ሲባሉ አንድ አንሆንም ብለው ስላስቸገሩት ነው አንድ ሳይሆኑ የቀሩት የሚለውን ” እቃቃ መሰል ወሬ ” ፣ እራሴን እየነቀነቅሁ ልክ ነው ልል ስብናዬ አይፈቅድም ፣ ግን ከኛ ባሀሪ ስነሳ ፣ አንድ ሆኖ መስራት ድሮም ስለማይሆንልን ፣ እኛን ማፍረስ ቀላል ቀላል መሆኑን በደንብ እገነዘባለሁ ። ለዚህም ነው በልጅ ተክሌ ጽሑፍ ሙሉ በሙሉ ለመስማማት የፈለኩት ።
በነገራችን ላይ ልጅ ተክሌን ለማታውቁት ፣ እስከማውቀው ድረስ ” ለአፉ ለከት የሌለው የሚመስል ግን ያልሆነ ፣ የራሱ ሰው ነው “። አንዳንዴ ዝም ብሎ ሲያፈነዳም አስተውያለሁ ፣ ግን ለክፉ የሚሰጡ ናቸው ብዬ አላምንም ። ባጭሩ ፣ ባለ ብሩህ አእምሮ እና ፣ ጨዋታ የሚወድ ሰው መሆኑን ሳላውቅ አልቀርም ። እንደውም ወደፊት ግንቦት ሰባትን ከኔ ጋ ሆነን ገልብጠን ሌላ ድርጅት ለመመስረት እያሰብን ነው ። መነሻው የሃንሽ ደሴቶች ላይ የሆነ ባህር ኃይል ፣ በሁለት ዓመት አዲስ አበባ የሚገባ ምናምን ልበል ? እስቲ ተዉት !
ልጅ ተክሌ በአርበኞች ግንቦት ሰባት ስያሜ ላይ የሰጠው ነቀፋ ተገቢ ነው ፣ አንድም ሁለትም ናቸው የሚለው አባባል ፣ እንደኔ ሚስጥረ ስላሴ ለማይገባው ኩታራ አደገኛ አገላለጽ ቢሆንም ። በተጨማሪም የአርበኞች ግንቦት ሰባት መሪ ብርሃኑ ነጋ መሆኑን መቃወሙ አግባብ ይመስለኛል ። ይህንንም ስል ብርሃኑ የመምራት ብቃት የለውም ለማለት ሳይሆን ፣ የቄሳርን ለቄሳር ፣ የየሱስን ለየሱስ እንደተባለው ፣ የሜዳውን ለሜዳ ፣ የ እንትኑን ለእንትን ማለት ብንችል ብዬ ነው ። በተጨማሪ መሪ የሚለው ነገር ከአንድ በላይ ትርጉም ያለው ስለሚያስመስል ፣ ለሱም ሲባል ቢቀር ጥሩ ነበር ብዬ አምናለሁ ። ይህንን ስል ፣ እንደ ብላቴና ነው አስተያየቴን እየጻፍኩ ያለሁት ። ብዙ ውስብስብ ነገሮች እንዳሉ ይገባኛል ። ሲጀመር ኤርትራ ሆኖ መዋጋት በራሱ ውስብስብ ነው ፣ መሰንጠቅ ፣ መካድ ፣ አላስፈላጊ ውሳኔ መስጠት እና ወዘተ ሌላው ነው ። ግን መሪው በቅርብ የሌለበት የለት ተለት ተሰራዊት እንቅስቃሴ ፣ ጸብ ፣ የለት ተለት የትግል ውሎ ፣ ለሊቀመንበሩ ከርቀት በሚደርስ መርጃ መከወን ብዙ ጉዳቶች አሉት ። ከነዚህ ውስጥ አንዱ የመረጃ ፍሰት እና አጠባበቅ ነው ። ለምሳሌ ምክትል ሊቀመንበሩ ከሆነ ለ ዋናው ሊቀ መንበር መረጃ የሚያደረሰው ፣ በእርግጠኝነት በሁለቱ መሃከል ስለሚደረገው ማንኛው አይነት ግንኙነት ሌላ አካል ( ሻብያን ጨምሮ ) ሊሰማ ወይም ሊያውቅ ይችላል ። ምክትል ሊቀ መንበሩ ደሞ ምን ያህል በራሱ ነገሮችን መፈጸም ይችላል የሚለው ነገር ፣ ከፋሲል የኔ ዓለም ጋ ያደረገውን ቃለ መጠይቅ ከሰማሁ በሁዋላ ” በቃ አልተመቸኝም ” ( ቃለ መጠይቁ ላይ ፋሲል የኔ ዓለም ስለ ኮ/ ል ታደሰ ጥያቄ ሲጠይቅ ፣ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ምክትል ሊቀመንበር የሆነው አቶ መአዛው ጌጡ ” ስለዚህ ነገር አትጠይቁኝ ፣ ተወኝ ፣ እለፈኝ ” የሚል መልስ ነው የሰጠው ። ብዙ ያልተሩ ነገሮች አሉ ። የዚህ ጽሑፍ አላማውም ፣ ልጅ ተክሌ የጠየቀውን አስባችሁበታል ወይ ለማለት አይደለም ( ምክንያቱም በደንብ እንደምታውቁት ስለማውቅ ) ፣ የዚህ ጽሑፍ አላማው ፣ አርበኞች ግንቦት ሰባት መሰሪ ፖለቲከኞች ያስፈልጉታል ፣ ለዚህ ዘመን እና ትውልድ በሚመጥን መልኩ አይደለም አንዳንድ ውሸቶች እየተሰሩ ያሉት ፣ እውነትም ይሁን ውሸት ጥራቱን ይጠብቅልን ለማለት ። በተጨማሪ እኔም እንደ ተክሌ የፈለኩትን መናገር አልፈራም የሚልም መልክት ለማስተላለፍ ነው ።

No comments:

Post a Comment