Monday, April 20, 2015

“ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ለማረጋገጥ እንሞክራለን”

እንደ ሚዲያ ወይም እንደ ጋዜጠኛ ሳይሆን እንደ ሰብዓዊ ፍጡር ይህን እንጽፋለን፡፡ እንደ ክርስቲያን ወይም እንደ ሙስሊም ሳይሆን እንደ አንድ ሰው ይህን እንናገራለን፡፡
ሰብዓዊነት ከሙያ በላይ ነው፡፡ ሰብዓዊነት ከሃይማኖት በላይ ነው፡፡ ሰብዓዊነት ከዘር በላይ ነው፡፡ ሰብዓዊነት ከምን ዓይነት መጠሪያ በላይ ነው፡፡
በሊቢያ የሚገኘው የአይሲስ ተወካይ ቡድን 30 ኢትዮጵያውያንን አረደ፤ በጥይት ረሸነ፡፡ የዓለም ዜና ማሰራጫዎች ዘገባውን አቀረቡ፤ ኢትዮጵያውያን መታረዳቸውን አወጁ፤ ዓለም ቪዲዮውን ተመለከተው፤ ዜናውን አነበበው፡፡ እኛም በሃዘንና በእንባ አንብበነዋል፤ ተመልክተነዋል፤ (ፎቶም ሆነ ቪዲዮውን እዚህ ላይ አንለጥፍም)፡፡

ኋይት ሃውስ እንኳን መግለጫ ሰጠ፤ ድርጊቱን ኮነነ፤ ከሰብዓዊነት በታች፤ ዘግናኝ፣ ፍጹም አረመኔያዊ፣ ጨካኝና ስሜት አልባ በማለት አወገዘው፡፡ ኢትዮጵያውያኑ የተገደሉት በሃይማኖታቸው ምክንያት መሆኑን በግልጽ ተናገረ፤ ሆኖም ይህ የአሸባሪዎች ድርጊት የእምነት ተከታዮችን በአንድነት አሸባሪነትን እንዲታገሉ የሚያስተባብራቸው ሊሆን ይገባል በማለት በሃይማኖቶች መካከል ተጨማሪ ግጭትና መከፋፈል እንዳይፈጠር አሳሰበ፡፡
የመስቀል ማተብ ያሰሩ መልካቸው፣ ገጽታቸው፣ ሁለንተናቸው አበሻ መሆናቸውን በሚመሰክረው የ29 ድቂቃ ቪዲዮ ኢትዮጵያውያን ለዕርድ ሲሰለፉ፤ ለጥይት ሲማገዱ ተመልክተናል፡፡ ጎልጉል በቀጥታ ከቤተሰብ ማጣራት ባይችልም ባገኘው መረጃ መሠረት በቪዲዮው ላይ ወንድሟን የተመለከተች አትዮጵያዊት መኖሯን መረጃ ደርሶናል፡፡ ጥልቅ ሃዘናችንን ለወገኖቻችን እንገልጻለን፡፡ ይህ የሃይማኖት ጉዳይ አይደለም ሰብዓዊነትእንጂ!
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ የአይሲስ ተግባር እስልምናን ይወክላል ብሎ አያምንም፡፡ እስልምና ወይም ኢስላም ማለት “ለአላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ትዕዛዝ ሙሉ ለሙሉ እጅ መስጠት” መሆኑን እንዲሁም ሌላው ትርጉሙ “ሰላም ማለት” መሆኑን ሃይማኖቱ በሚያስተምረው ትምህርት መሠረት ይቀበላል። ጽንፈኝነትና አክራሪነት በሁሉም ሃይማኖት ውስጥ የሚንጸባረቅና ከራስ ቅድስና የሚመጣ የተሳሳተ አመለካከት እንደሆነ ጎልጉል ያምናል፡፡
ስለዚህ ይህ የአይሲስ ተግባር የእስልምና ተግባር ተደርጎ መወሰድ የለበትም፤ ይህም ድርጊት ለዘመናት በክፉም በደጉም ተቻችሎና ተከባብሮ የኖረውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ሊለያየው አይገባም፡፡ እዚህ ላይ አስተያየት የምትሰጡም ሁሉ በዚህ የተሳሳተና ሁሉን በጭፍን በሚያወግዝ መንፈስ አስተያየት እንዳትሰጡ ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
በህወሃት የሚመራው ኢህአዴግ በእሁድ ምሽት ዜናው ላይ በጣም ተዝናንቶ ጉዳዩን እንደ አንድ ተራ ዜና ከረጅሙ የዜና እወጃው ሰዓት ውስጥ ጥቂት ደቂቃዎችን ሰጥቶታል፡፡ ያውም የቀደመው ሌላ ዜና አለ – “የልማት ዜና!”
በዚህ ብቻ አላበቃም፤ ዜናውን እንደ ሁላችንም በዓለም የዜና ማሰራጫዎች መስማቱን ተናገረ፤ የኢህአዴግ አፈቀላጤ ሬድዋን ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ለማረጋገጥ እንሞክራለን አለ፡፡ ሃይለማርያም ደሳለኝ የተናገረው ነገር የለም፤ የዜናው ቀዳሚ የሆነው ሙላቱ ተሾመ ያለው ነገር የለም፡፡ “የፌስቡኩ ፍንዳታ” ቴድሮስ አድሃኖም አይሲስን ደውሎ ለመጠየቅ ያሰበ ይመስል “ድርጊቱን እያጣራነው ነው” ብሏል፡፡ ከጥቂት ቀናት በፊት በለቀቀው መልዕክት “ወያኔ ነኝ” ብሎ ነበር፡፡ እውነተኛ “ወያኔ ነው”! የህወሃትና ኢህአዴግ ደጋፊዎችና አሽቃባጮች “ታዲያ ምን ማለት ነበረበት?” ብላችሁ ባትጠይቁ መልካም ነው፡፡
ዜጎቻቸው በአይሲስ የተገደሉባቸው አገራት የአይሲስን ምሽጎች ደብድበዋል፤ በተገደሉባቸው ዜጎች ልክ ወይም የበለጠ ጥቃት በአይሲስ ላይ አድርሰዋል፡፡ የሞቱባቸውን ዜጎች ህይወት ለመመለስ ባይችሉም የዜጋቸውን ጥቃት የሚከላከል መንግሥት መኖሩን አስመስክረዋል፡፡ ባለቤትና መሪ የሌላት ኢትዮጵያስ? ሳይጠሩት አቤት ብሎ ሶማሊያን ያተራመሰው በህወሃት የሚመራው ኢህአዴግስ ምን ሊያደርግ ነው ያሰበው? ሃይለማርያም፣ ሙላቱ፣ ሬድዋን፣ ቴድሮስ፣ በረከት፣ አባይ፣ . . . ወያኔዎች ሁላችሁም አይሲስ የገደላቸው “ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን አጣርታችሁ” ስታበቁ ምን ልታደርጉ ነው ያሰባችሁት? “ቦንድ ልትሰበስቡ” ወይስ “ኢህአዴግን ምረጡ” ዘመቻችሁን ልትቀጥሉ? የፈለጋችሁትን ልታደርጉ ትችላላችሁ፡፡ የሃዘን ቀን ልታውጁ ትችላላችሁ፤ ዲስኩር ልትነፉም ትችላላችሁ፤ ባንዲራ የምትሉትን “ጨርቅ” ዝቅ አድርጋችሁ ልታውለበልቡ ትችላላችሁ፤ … የምታደርጉት ነገር በሙሉ ግን በቁም ያለነውን እንደ አይሲስ ካረዳችሁን በኋላ የምታደርጉት በመሆኑ እንደ ምንም አንቆጥረውም፡፡ በጣም ዘግይታችኋል፡፡ ምክንያቱም ሃዘናችሁንና የሃዘን መግለጫችሁን ሳንሰማ እኛ ሞተናል፤ ታርደናል፡፡
ስለዚህ እንደ ቴድሮስ አድሃኖም “ወያኔ ነን” የምትሉ፣ የወያኔ ደጋፊዎች፣ ካድሬዎች፣ ተላላኪዎች፣ የጥቅም ተጋሪዎችና ልክስክሶች ስሉሱ እስኪዞርባችሁ “መጪው ጊዜ ከኢህአዴግ ጋር ብሩህ ነው፤ ሥራ ላይ ነን” ማለታችሁን ቀጥሉ፡፡
ከላይ እንዳልነው እንደ ሚዲያ ወይም እንደ ጋዜጠኛ ሳይሆን ሰብዓዊ ፍጡር ነው ይህን የምንጽፈውና እኛም በፈጣሪ እናምናለን፡፡ ፍርድን የሚሰጥ ቅን ፈራጅ፤ ሁሉንም የሚመለከት፤ የሚመረምር፤ ዕንባን የሚያብስ፤ የበቀል በትሩን ከዘረጋ የማይመለስ ፈጣሪ አለ፡፡ ፕ/ር መስፍን እንዳሉት “የኢትዮጵያ ደሀዎች እንባ የእግዚአብሔርን ሰማይ አጨቀየው”፤ እንባ ብቻ አይደለም ደምም ተጨምሯል፡፡ እጅግ ርኅሩህ፣ እጅግ መሃሪ የሆነው ፈጣሪ ጊዜ የተሰጣችሁ “ህዳሴ፣ ውዳሴ፣ …” እያላችሁ ከበሮ እየደለቃችሁ እንድትዘፍኑ ሳይሆን ወደ ኅሊናችሁ እንድትመለሱ ነው፡፡
አበቃን!!

No comments:

Post a Comment