Friday, March 20, 2015

United Ethiopian Muslims Peaceful Movement Support Group የኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች ሰላማዊ ንቅናቄ ደጋፊዎች ህብረት

 በመስሊሙ ማህበረሰብ ላይ ህወሃት የዘረጋውን የጥላቻና የበቀል ዘመቻ ለመከላከል የወጣ የአቋም መግለጫ የኢትዮጵያውያን ሙሰሊሞች ሰላማዊ ንቅናቄ ደጋፊዎች ህብረት ሰሜን አሜሪካ March 19, 2015
ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች የተጣሰውን ህገመንግስታዊ መብት በህግ ለማስከበር የጀመሩት ሰላማዊ ትግል ድፍን ሶስት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ይህ ትግል በመላው አለም ሰላማዊ ትግልን መታገል ለሚሹ አርአያ ከመሆኑም ባሻገር በተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት እውቅናን ያገኘም ነው፡፡ በነዚህ መራራ ሶስት የትግል አመታት ህዝቡ በፊርማው የመረጣቸው የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች የእስር ብቻ ሳይሆን የድብደባ፣ የግርፋት፣ የማዋረድ፣ የሰብዓዊ መብትም መገፈፍ ሰለባ ሆነዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ሲታሰሩ፣ ሲገረፉ፣ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ደግሞ ለመሰደድ በቅተዋል፡፡ሰላማዊ ዜጎች በግፍ ጥይት እየተደበደቡ ለሞት መዳረጋቸው ሊካድ የማይችል የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

የዜጎች መብትን የሚገፈው ህወሃት መራሹ የኢትዮጵያ መንግስት ሀገርን እንደሚመራ ኃላፊነት እንደሚሰማው አካል ሳይሆን በቡድን እንደተደራጀ የቀበሌ ማፊያ ዝቅ ብሎ በአለማችን እንደሚታወቁ አሸባሪ አካላት ዜጎችን እያሸበረ የስልጣን እድሜውን ለማራዘም የሚያደርገው ሴራ ለመታደግና ለመመከት የኢትዮጵያን ሙስሊሞች ሰላማዊ ንቅናዌ ደጋፊዎች ህብረት ማንኛውንም አለማቀፋዊ እውቅና ያለው ህጋዊ የቅዋሜ መንገድ ከመተግበር የማይቆጠብ መሆኑን በአጽንኦት ለመግለጽ ይሻል፡፡
አሳፋሪ በሆነ የኋላቀር የጥላቻ ስሜት የታነጸው ህወሃት መራሹ የአሸባሪዎች ቡድን ሰላም ወዳዱን፣ለሀገሩ ልማት ደፋ ቀና የሚለውን፣ ሀገሩን ለመጠበቅ የህይወት መስዋእትነት የሚከፍለውን፣በሀገር ፍቅር ስሜት ለሀገሩ ታማኝ የሆነውን የሙስሊም ማህበረሰብ ጫንቃ ላይ የሚጭነው የጭቆና ሸክም የሚያንገፈግፍና ለመሸከም የሚያስቸግር ነዉ። ህብረቱ ይህንን ህዝብን የማገንፈልና ሀገርን የማወክ ህወሃታዊ የማሸበር ተግባር ጠንቅቆ የሚያውቅ በመሆኑ ለሀገሪቷ ሰላምና መረጋጋት ድከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ይሰራል።
ህዝባችን ውስጡ ላይ የሚፍለቀለቀውን የመጨቆን ስሜት አሸባሪው ህወሃት በሚፈልገው መልኩ ሳይሆን ላይቀሬው እና ለተገቢው ህብረተሰባዊ ለውጥ አምቆ ያቆየው ዘንድ ህብረቱ ጥሪውን ለሰፊው ህዝብ ያቀርባል፡፡ዜጎችን በመጨቆን አምባገነናዊ እስትንፋሱን የሚያራዝመው አሸባሪው ህወሃት ያሰማራቸውና የቀጠራቸው ለህዝብ ስጋት የሆኑ ደህንነቶች በሚያዟቸው ማረሚያ ቤቶች ውስጥ የሚሰቃዩት የሙስሊሙ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎችም ሆኑ ሌሎች እስረኞች ከእስር ቤት ወደ እስር ቤት እንዲቀያየሩ መደረጋቸው የእስረኞቹን መንፈስ ለመስበር የሚደረግ ከንቱ ሴራ በመሆኑ ህብረቱ በጽኑ የሚቃወመው ተግባር ነው፡፡በታራሚዎች ዘንድ ተወዳጅ፣ምስጉን ለመልካም ተግባራቸው አርአያ የሆኑትን የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎችና ባልደረቦቻቸውን በካቴና ጠፍሮ በማሰር፣በጨለማ ክፍል የመቀመጣቸው እውነታን ህብረቱ በጽኑ የሚቃወመው ብቻ ሳይሆን የዚህን የረብየለሽ ማፊያ ተግባር መሪዎች እንደሌሎች አሸባሪ አካላት በአለምአቀፋዊ የህግና የተጠያቂነት መድረክ አቅርቦ ተጠየቂ ለማድረግ ሌት ተቀን የሚሰራ መሆኑን ህብረቱ ለመግለጽ ይወዳል፡፡
የታሰሩ የሙስሊም የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎችና ባልደረቦቻቸውን ለማሸማቀቅ በታሰሩበት የማጎሪያና የማሰቃያ ክፍል በድንገት በመግባት፤መጽሀፍትን፣ ንብረትን፣ የህግ ሰነድን፣ የፍርድ ቤት ማስታወሻን ብሎም የጀግና ታሳሪዎች የጭንቅላት ውጤት የሆኑ የስነጽሀፍ ስራዎችን መዝረፉ የአሸባሪው ህወሃት ቅሌትን የሚያመለክት የረከሰ ተግባር ቢሆንም ህወሃት በእጁ ያሉ እስረኞችን በማሰቃየት ከሚያደርገው ቅሌት ይታቀብ ዘንድ ህብረቱ ያስገነዝባል፡፡
በህግ ጥላ ስር ያለን እስረኛን በማሸማቀቅና የተለያዩ የማሰቃያ ዘዴዎችን በመጠቀም ፍትህ አልባ በሆነው የካንጋሮው ፍርድ ቤት ሚዛን የማይደፋ ውጤትን ለማስመዝገብ ጨቋኙ መንግስት እየጣረ ነዉ። ህወሃት የሙስሊም የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎችንና የባልደረቦቻቸውን የቤተሰብ አባላትና የትዳር አጋሮችን ሒጃብ (ጸጉር መሸፈኛን) ሳታወልቁ እስር ቤት ታሳሪዎችን ለመጠየቅ አትገቡም ብሎ የተከበሩ ሴቶችን ክብር ለመግፈፍ የሚያደርገው ሙከራ የሀገሪቱን ህገ መንግስት የጣሰ ነዉ። የሴቶች ሐይማኖታዊ አልባሳት በኢስላም መለኮታዊ መመሪያ የተድነገገ በመሆኑ ይህ በሴቶች ላይ ያነጣጠረዉ ጥቃት የሀይማኖት መመሪያችንን ቅዱስ ቁርዓንን እንደማራከስና እንደማዋረድ የሚቆጠር ነው፡፡ ህብረቱ ይህ ድርጊት በሀገራችን ላይ የተንሰራፋ ብሔራዊ ዉርደት ነዉ ብሎ ያምናል።በዚህ ፈታኝ መከራ መካከልም ህብረቱ የታሳሪ ቤተሰቦችን
2 4324 Georgia Avenue NW – Washington, DC 20011 uempmsg@gmail.com
ጽናት እየጠየቀ፤ ህወሃት ካመጣዉ ብሔራዊ ዉርደት መዉጫዉ ድልን በህወሃት ላይ መቀዳጀት እንጂ ምንንም ሊሆን እንደማይችል ህብረቱ በቁርጠኝነት ያስገነዝባል።
በየ አምስት አመቱ በሚደረግ የይስሙላ ምርጫ “አሸናፊ” የሚለውን ስያሜ ለማግኘት የሚኳትነው ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ዲሞክራሲያዊ ሽንፈትን በመስጋት ከምርጫ በፊት የጀመረውን ሙስሊም ወጣቶችን የማመናመንና ማእከላዊ አስገብቶ የማሰቃየት ዘመቻ ህብረቱ በጽኑ ይቃወመዋል፡፡ በዚህም የከሸፈ የምርጫ ስሌት ህወሃት ዳግማዊ ሽንፈትን መከናነቡ አይቀርም።ህወሃት በወጣቶች ላይም የከፈተው ዘመቻ ግቡን እንደማይመታ ህብረቱ በጽኑ ያምናል።
ኢስላም ከሁሉ ሀገራት ቀድሞ የገባባትን ዉዷ አገራችንን ሰላም ለማናጋት፤ ነውጥ ከማያጣት ሊባኖስ የአህባሸን አንጃ ያመጣው ህወሃት በሶስት አመት ውስጥ አያሌ የፖለቲካ ኪሳራዎችን ተከናንቧል።ከዚህም የፖለቲካ ኪሳራ ለመዉጣት በሙስሊሙ ማህበረሰብ ውስጥ መንግስታዊ ሀይማኖትን አስርጾ ለማስገባት “ነባሩ እስልምናና አዲሱ እስልምና” በማለት የጀመረው የማከፋፈል ሴራ ከጅማሮው በፊት የከሸፈም ነው፡፡ ለዚሁ ስንኩል ተግባር ያሰማራቸው የሀገር ውስጥም ይሁን የዲያስፖራው ወኪሎቹ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ ቅሌትን እየተከናነቡ ነዉ።እነዚህ ካድሬዎችም ከሰፊዉ ህዝብ ሰርቆ ሊመጸዉታቸዉ ከተዘረጋዉ ረጅም የመንግስት እጅ ይልቅ ወደ ህዝባዊዉ የፍቅር እቅፍ ዉስጥ ይገቡ ዘንድ ህብረቱ ጥሪዉን ያቀርባል።
የዛሬን ትውልድ በመኮትኮት ለአለማዊና ለመንፈሳዊ ህይወት ቤዛነታቸዉ የተረጋገጠዉ መተኪያ አልባ የሆኑ ኡለሞቻችንን (የሐይማኖት ሊቃዉንት) ህወሃት ከቦታ ቦታ እያንቀሳቀሰ በመንግስታዊ የሀይማኖት ስልጠና ስም የሚፈጸምባቸው እንግልት የሚቀረፍበት ቀን ሩቅ አይሆንም፡፡ አይደለም ለሀገራችን ለምስራቅ አፍሪካ ብርሃን የሆኑት ኡለሞቻችን (የሐይማኖት ሊቃዉንት) ይሰልጥኑ ማለቱ የ1400 ዓመታት የእምነት ዘለበት በታጠቀችው ሀገራችን ላይ ስላቅ ቢሆንም፤ ለዚህ ውርደት ያበቃን ህወሃት በአለም ህዝብ ፊት የሚዋረድበት ቀን ሩቅ እንደማይሆን ከታሪክ ተምረናል።ህወሃት የሚርድበትን ታሪካዊ ዉርደት ለማፋጠንና የኡለሞቻችንን ክብር ለመመለስ በህብረትና በአንድነት መነሳቱ የሚኖረን ሁነኛ ምርጫና ከቀደምት የብርቅ ሰብእና ባሌቤት ከሆኑት ውድ ኡለሞቻችን (የሐይማኖት ሊቃዉንት) የቀሰምነዉ የማንነታችን ነጸብራቅ ነዉ።
የማስተማርና የመማማር መብትን ተነፍገው ከሀገር የተሰደዱ ኡለሞች (የሐይማኖት ሊቃዉንት) በክብር ወደ ሀገር እስኪመለሱ ብሎም በሌሊት እጆቻቸዉ ለጸሎት ተዘርግተዉ አይኖቻቸው የፈጣሪ ምህረትና እዝነት ይወርድ ዘንድ የሚያነቡ፤ በቀን የሐዘን የእንባ ዘለላን ከጨቋኙ ሸሽገዉ በልቦቻቸዉ የሚያለቅሱ ኡለሞቻችን (የሐይማኖት ሊቃዉንት) እንባን በድል ለመጥረግ የተላያየ የጣት አሻራ ያለዉ የወገን እጅ በአንድነት ተያይዞ የኡለሞቻችን ደጀን ሊሆን ይገባል።
የሴቶችን መብት አስከበርኩ በማለት የሚመጻደቀው ህወሃት፤ ለሴቶች አደጋና ጠንቅ እንደሆነ በገሀድ አሳይቷል፡፡ የሚንሰፈሰፍ የወላድ አንጀት ባለቤት የሆኑትን እናትና እህቶችን በቆመጥ ደብድቧል፡፡ በከስክስ ጫማው ረግጧል፡፡ ፈንክቷል፣ አቁስሏል፣ ነፍሰጡር ሴቶች የጸነሱት ጽንስ በዱላ አውርዷል፡፡ ሴቶችን ለእርቃን በተቃረበ መልኩ በገማ ወንዝ እንዲገቡና እንዲነከሩ ካደረገ በኋላ፤ በጭቃ ላይ እንዲንከባለሉ በማድረግ በሌሊትም የአውሬ እራት አንዲሆኑ ከማጎሪያ እስር ቤት አባሯል፡፡ ቁርዓንን፣ ሂጃብን፣ ተስቢህ መቁጠሪያን፣ የእስላም ኮፍያን፣ አማይምና የተለያዩ አልባሳትን ከምሮ እየተሳለቀ ህወሃት አቃጥሏል፡፡ በማእከላዊ የምርመራ ማእከል ሴቶችን እርቃን አቁሞ በመሳለቅ ደብድቧል።
ይህ የሴቶች ስቃይና መከራ “ድረሱልኝ!”በሚል ፈታኝ የሰቆቃ ድምጽ ቢያስተጋባም፤ እንክብካቤ የሚገባቸው እናትና እህቶችን በማሰቃየት ሁከትን ፈጥሮ የስልጣን እድሜዉን ለማራዘም በደም የተጠማዉን የህወሃትን ሰይጣናዊ ሴራ ህዝባችን በታጋሽነቱ አክሽፏል።ሀገር ወዳድና አርቆ አሳቢ የሆነዉ ህዝባችን ቁርዓንን ጨምሮ አያሌ የሐይማኖት መለዮዎች፤ የሐይማኖት ጸብ አጫሪ በሆነዉ ህወሃት ቢቃጠልበትም የነዚህን መለኮታዊ መለዮዎች የትዬለሌ የዋጋ ስሌት ለፈጣሪው በመተዉ ትእግስት የሚባል ሽልማትን በመቀዳጀት ጨቋኞችን ከስር እራሱን ከላይ በማድረግ ፍጹማዊ የህሊና የበላይነትን ተጎናጽፏል።
ነገ በድል ማግስት ሴቶቻችን በክብር እርከን መላቃቸዉ ሲታወስ የዛሬዉ መከፋት ኢምንት ነዉ።ህወሃት በሴቶቻችን ላይ በፈጸመዉ ጭካኔ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ትጉህ ያገሪቷ ዜጎች ላይ ያጫረ ስሜት አለ። ይኸዉም ሴቶች ሲደፈሩ ሀገር የመደፈሯ እዉነታ የማይካድ መሆኑን ነዉ። ሀገር ደግሞ በመደፈሯ ይህንን አምባገነናዊ ስርዓት ለመሻርና በምትኩ
3 4324 Georgia Avenue NW – Washington, DC 20011 uempmsg@gmail.com
ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመተካት በቁርጠኝነት ተነስተናል።የተደራጀ ህዝባዊ አቅም ባለቤቶችም መሆናችንን ህወሃት ቢያዉቀዉም ዉስጡ በእብሪት ስልተሞላ እዉነታዉን የመረዳት አቅም ያጣ ይመስለናል። የኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች ሰላማዊ ንቅናቄ ደጋፊዎች ህብረት በእብሪት የተወጠረዉ አምባገነኑ መንግስት በለዉጥ እስኪተነፍስ ድረስ እረፍት አልባ መሆኑን በቁርጠኝነት ይፋ ሊያደርግም ይሻል።
በሙስና የፋፋው ህወሃት መነገድን እንደመኖር አማራጭ የያዘውን ነጋዴዉን ወገናችን ከጨዋታ ውጭ እያደረገ ነው፡፡ ዘመናዊ ንግድን በመመርኮዝ ውጤት ያስመገቡና ተጽኖ ፈጣሪ የሆኑ ነጋዴዎችን በማሽመድመድ በኢኮኖሚ የደቀቀ ማህበረሰብን ለመፍጠር የሚቻለውን ሁሉ ጥቃት እየፈጸመ ነው፡፡ ህዝባችን ይህንን ኢኮኖሚያዊ ጦርነት ጠንቅቆ በማወቅ አቅሙ በቻለዉ መጠን በኦኮኖሚ ለመብቃቃትና የህወሃትን ሴራ ለመቋቋም ወደ ጠንካራና የላቀ የኢኮኖሚ እርከን ራሱን ለማሳደግ መጣር አለበት።
ኢስላማዊ አልባሳትንና ሶላትን ማመካኛ በማድረግ ህብረተሰባችንን የበይ ተመልካች እንዲሆን ከየመንግስት መስሪያ ቤቱ ከስራ ገበታው እንዲፈናቀል የማድረጉ ጥረት የአገሪቱን ሚዛን በማዛባት የቀድሞው ስረዓተ ማህበሮችን ተሞክሮ ለመድገም የሚደረግ ፈተና ነዉ ቢባል ማጋነን አይሆንም። ይህን በታሪክ ብቻ የሚወሳዉን ግዜ ጥሎት የነጎደዉን ኋላ ቀር ስርዓት ዳግም እንዳይመለስ የማድረግ ብቃት በህዝባችን ላይ ያለ በመሆኑ የህወሀትን የተናጠል ጥቃት እንደጋራ ጥቃት አርጎ መረዳቱ ወደ ድል የሚያዳርስ ያሸናፊነት ፈለግ ነዉ።
በከፍተኛ የትምርት ተቋማት ዉስጥ ተማሪዎች በሐይማኖታዊ አልባሳትና በሶላት ለፈተና ይዳረጋሉ።ተማሪዎች በሚደርስባቸዉ የማይቋረጥ ትንኮሳ ዝቅተኛ ዉጤት እንዲያመጡና ከትምርት ገበታቸዉ እንዲፈናቀሉ አድሎአዊ አሰራር ይተገበራል።ይህም የአንዱን የህብረተሰብ ክፍል በመነጠል በቀጣዮቹ ክፍለ ዘመናት ፍሬ አልባ የሆነ ትውልድ እንዲወጣ የማድረግ ሴራ መሆኑን ተማሪው ጠንቅቆ ማወቁ ግዴታ ነዉ።ነገ አገርን ተረካቢ የሆነዉ ተማሪ ከትምርቱ ሊያሰናክሉት በፈለጉ ቁጥር ለመማር ያለው ፍላጎትና ጽናት ጨምሮ በእውቀቱ በመጎልበት ያገር ፍቅር ስሜቱን መግለጹ ብልህነት ነው።
ቀደም ሲል በአሸባሪነትና በብሔር አስገንጣይነት መዛግብት ላይ ሰፍሮ የነበረው ህዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ ዛሬም በነጠፈ ያገር ፍቅር ስሜት ኢትዮጵያዉያንን በዘር በሐይማኖት በመነጣጠል እያሸበረ ነዉ። ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች ህወሃትን የመሰሉ የፖለቲካ አሸባሪዎችንም ሆነ ሌሎች የሐማኖት ካባን የለበሱ አሸባሪዎችን በጽኑ ይቃወማሉ። ዜጎች ከመቻቻልም ባሻገር ተዋደው የሚኖሩባት ሀገር ሰላምና መረጋጋት እንደማንኛውም ዜጋ ለኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ያስጨንቃቸዋል።
ህወሃት ህገርን እያወከ ሲያከፋፍልና ሁከትን ለመፍጠር ሲጥር ያገሪቷ ሰላም፣መረጋጋት ለማስፈን ኢዮጵያዉያን ሙስሊሞች የዜግነት ቃልኪዳናቸዉን የማያዛንፉ መሆናቸዉን በገሃድ እያሳዩ ነዉ።ህብረቱም ያገሪቱ ዜጎች የህወሃትን የማከፋፈል ተውሳክን ቸል በማለት ለዘመናት ባስተሳሰራቸዉ ቃልኪዳን ይኖሩ ዘንድም ጥሪዉን ያቀርባል።
ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በተሰማሩበት በሳል የሰላማዊ የትግል ጎዳና አድናቆትን መቸር ብቻ ሳይሆን ለሌሎች አርአያ መሆን መቻላቸዉ የተመሰከረላቸዉ ነዉ። ድምጻችን ይሰማ በእለተ አርብ ሰላማዊ ተቃውሞን ሲጠራ ቀኑ ከጥምቀት ጋር በመገጣጠሙ ቦታን የመቀየር አዋጅ ማወጁ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በደሴ የአንድነትና የሰደቃ መርሃ ግብር ሲከናወን ሙስሊሞች ከአብያተ ክርስቲያናት ድንኳን ተውሰዋል፡፡ መንግስት ጥቃቅንና አነስተኛ እንጀራ ጋጋሪዎች ለአንድነትና ለሰደቃ እንጀራ እንዳይጋግሩ ሲከለክል የደሴ ሙስሊምና ክርስቲያኖች በመተባበር እንጀራውን ጋግረው የጋራ እንግዳቸውን ሸኝተዋል፡፡ በአዲስ አበባ አንዋር መስጂድ የአንድነትና የሰደቃ ዝግጅት ላይ አያሌ ክርስቲያን ወገኖች ተሳትፈዋል፡፡ ባህርማዶ የምትገኘዋ ሲኖዶስ የሙስሊሞችን የመብት ጥያቄ በመደገፍ መግለጫ አውጥታለች፡፡ ዛሬ ሙስሊሙና ክርስቲያኑ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ መልኩ በመጣመር ለለውጥ ተነሳሽነታቸውን ያሳዩበት ታሪካዊ ወቅት ላይ በመሆናችን ይህንን ሀገራዊ ቁርኝት ለማፍረስ የሚደረግ የማስፈራራት ሴራ ከንቱ መሆኑ አያጠራጥርም። ህብረቱ ከሌሎች የእምነት ተቋማት ጋር በመተባበር ብሔራዊ መግባባትንና መተማመንን ያጸናል። ህብረቱ ከሌሎች የሐማኖት፣የሲቪክና የፖለቲካ ማህበራት ጋር በመሆን የጋራ በሆነችዋ አገር ላይ የሚቃጣ ማንኛዉንም የፖለቲካም ይሁን የሐይማኖት አሸባሪነትን በመጋፈጥ የሀገር ሰላምና ደህንነትን ያስጠብቃል።
‘ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም’ እንደሚባለው ህወሃት መራሹ መንግስት የራሱን ጥቅም የሚያስከብሩ በህይወትና በስራ የከሸፉ የመጅሊስ ሹመኞችን በህዝበ ሙስሊሙ ላይ በግዳጅ መጫኑ ዝቅጠት ነው፡፡ ይህ ታሪካዊ ዝቅጠት የሙስሊሙን
4 4324 Georgia Avenue NW – Washington, DC 20011 uempmsg@gmail.com
ማህበረሰብ የነጻነት ጥማት የሚያንርም ነዉ።ቀደምት አባቶቻችን በደም እና በመስዋእትነት የገነቡት መጅሊስ የመንደር ቦዘኔና ዱርየዎች መፈንጫ እንደማይሆን ቁርጠኝነቱ የጎላ ነው፡፡ እያንዳንዱ ካድሬ ከመጅሊስ ወጥቶ ህዝብ የመረጣቸው ተወካዮች እስኪገቡ ድረስ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ደጋፊዎች ህብረት እረፍት የለውም፡፡
በየካቲት 26/2004 በፌደራል ጉዳዮች ሚስቴር ዉስጥ ህዝበ ሙስሊሙን በመወከል መንግስት እውቅና ሰጥቶ ያነጋገራቸው የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ዛሬም የህዝብ ወኪል ናቸዉ ሲል ህብረቱ ያረጋግጣል። መንግስት እንደ ህዝብ ወኪል አክብሮ ያነጋገራቸውን ብርቅ የኢትዮጵያ ልጆችን ስንኩል የፖለቲካ ጥቅሙን ለማሳካት “አሸባሪ” የሚል ፍረጃ ለጥፎባቸው እስር ቤት መወርመወሩ መላው የኢትዮጵያን ሙስሊምን ከመፈረጅ ተለይቶ የማይታይ ከንቱ የአንባገነናውያን ፈለግ ነው ብሎ ህብረቱ ያምናል፡፡ እነዚህ የህዝብ ተወካዮች የጠየቋቸው ጥያቄዎች በአስቸኳይ ምላሽ ያገኙ ዘንድም ህብረቱ ያስገነዝባል፡፡ጥያቄዎቹም፡-
1.የህዝበ ሙስሊሙ ብቸኛ ተቋም የሆነው መጅሊስ በህዝብ በተመረጡ የህዝብ ተወካዮች ይመራ፤
2.አህባሽን አስገድዶ መጫኑ ይቁም፤ 3. አወሊያ ትምርት ቤት በህዝብ በተመረጡ የቦርድ አመራሮች ይመራ
ለነዚህ ቀላል ጥያቄዎች ሀገርን ማተራመስ የመረጠው ህወሃት ጥያቄዎቹን አለመመለሱ የራሱን እድሜ የሚያሳጥርም ነዉ። በአንጻሩ ህዝባዊ ውክልናን ተጎናጽፈው፤ የህዝቡን ቅሬታ ለመንግስት ያሰሙ፤ ነጻና ንጹህ የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎችን አስሮ ማሰቃየቱ በሚሊየን የሚቆጠረውን የሀገሪቱን ዜጋ አስሮ ከማሰቃየት ተለይቶ የማይታይ ነው፡፡ ህወሃት ኮሚቴውን አስሮ የሚያሰቃይበት የእያንዳንዱ ሴኮንድ ዋጋ በእጅጉ የላቀ በመሆኑ በአለም ላይ መግቢያ አጥተው እርቃናቸውን የቀሩትን አምባገነናዉያን እጣ በማጤንና ከግምት ዉስጥ በማስገባት ህብረቱ ለህዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ ቀጣዩን መልእክት ያስተላልፋል።
1.የህዝበ ሙስሊሙ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ በአስኳይ ይፍታ፣ 2.በዚህ የአሰራር ግድፈት ውስጥ በመሳተፍ በኮሚቴው ላይ እና በህዝቡ ላይ ጥቃት የፈጸሙ ለፍርድ እንዲቀርቡ፣ 3.ለኮሚቴዎቹና ለቤተሰቦቸቸው ብሎም ለሌሎች በመንግስት የግፍ በትር የተጠቁ የሞራል ካሳ እንዲከፈላቸው፣ 4. ሀገሪቱ ዉስጥ ካሉት የካንጋሮ ፍርድ ቤቶች ፍትህ ባይጠበቅም፤ ለጨቋኙ መንግስት የሚኖረዉ አማራጭ ከላይ የቀረቡትን መጠይቆች ማሟላት ብቻ መሆኑን ህብረቱ አበክሮ ይገልጻል፡፡
በመጨረሻም ህወሃትና መሰል ጨቋኞች ሊረዱት የሚገባ ነገር ቢኖር ጭቆናው በበረታ ቁጥር ለትግሉ የገባነው ቃል ኪዳን ጠብቆ ትግሉን መቀጠሉን ነዉ። ጠባቡ ህወሃት ካመጣዉ ምስቅልቅልታ የምንወጣበት ቅያስ ያቋራጭ ሽርፍራፊ መብትን መቀብል አይደለም።አማራጫችን በሰፊዉ የድል ጎዳና ተጉዘን መጪዉ ትዉልድ በተድላ የሚኖርበት ድልና ድልን መጎናጸፍ ብቻ ነዉ።ጨቋኞች በፈጠሩት ታሪካዊ ግድፈት በሌትም ይሁን በቀን የዉስጥ ሰላም ሲያጡ፤እኛ በተጻራሪዉ በምጎናጸፈዉ የትዬለሌ ምንዳ የትእግስት ፍሬን ከያለንበት እየተቋደስን፤መታሰሩንም፣መዘረፉንም፣ከሀገር መሰደዱንም ለነገዉ ትዉልድ የምንዘራዉ የተስፋ ዘር ነዉ ብለን እናምናለን። የዛሬን ዉርደት እንደ ክብር የምንቆጥር በመሆናችን ሰፊዉ ህዝባችን እንደሚያሸንፍ ቅንጣት ታህል ጥርጣሬ የለንም። በታነጽንበት መለኮታዊ ግብረገባዊነት ከጨቋኙ ህወሃት በላይ አያሌ የተስፋና የድል የበላይነትን ተቀዳጅተናል። በነዚያ በብሩህ የድል ደጃፎች ላይ በድል አድራጊነት እስክንጓዝ ድረስ ከድል ያነስ ድልን ዛሬ ብንቀበል የመጪዉን ትዉልድ የብሩህ ተስፋ ወጋገን ያፀለምን ስለሚመስለን የድል ጃኖ እንደደረብን ወደፊት እንጓዛለን። ጨቋኝነት ተሸናፊነት ነዉ! መጨቆን አሽናፊነት ነዉ! ህወሃት ህዝብን ያጠመደበት የጭቆና ቀንበር በሙስሊም የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች በመሰበሩ ቀሪዉ ግዜ በሽንፈቱ የሚዳክርበት ነዉና እስከመጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ከሰላማዊ ትግላችን አፈግፋጊዎችም አንሆንም።
በዚህ የድል ዋዜማ በመላው አለም የሚገኙ ወገኖቻችን በዘር በቋንቋ ሳይለያዩ የጋራ ጠላት በሆነው ጨቋኝ ስርዓት የጋራ ክንድን በማሳረፍ ይህንን ሰቆቃ ከወገናችን ጫንቃ ላይ ከማራገፍ በስተቀር አማራጭ ስለሌለን አንድ እንሁን፡፡ ኡለሞች፣

ዳኢዎች፣ የኮምዩኒቲ ማህበራት፣ የኮምዩኒቲ ተመራጮች፣ የመገናኛ ብዙሃን፣ ጸሀፍትና ገጣሚዎች፣ አርቲስቶች፣ አክቲቪስቶች፣ የኮምፒውተር ባለሙያዎች… ወዘተ ይህንን ህዝብ አንድ አንድርጎ ወደ ድል በማቅናቱ ረገድ ያላቸው ሚና ወሳኝ ነዉ።በመናበብ የመስራት ባህል ከነበረው በላይ ዳብሮ፤ የአንድነታችን ውጤት፣ የድላችን ስምረት፣ የጥረታችንን ስኬት ተቋድሰን የነጻነት አየርን ዉድ የሆነዉ ወገናችን ይተነፍስ ዘንድ አቅማችን በቻለዉ መጠን እንድንታገልና እንድንጥር የኢትዮጵያን ሙስሊሞች ሰላማዊ ንቅናቄ ደጋፊዎች ህብረት ጥሪውን ያቀርባል፡፡
የጨቋኞች ሽንፈት አይቀሬ ነው! ድልም ከአላህ እንጂ ከማንም አይደለም!
መውጫችን ድላችን ነው! አላሁ አክበር!
4324 Georgia Avenue NW – Washington, DC 20011 uempmsg@gmail.com
 4324 Georgia Avenue NW – Washington, DC 20011 uempmsg@gmail.com

No comments:

Post a Comment