Tuesday, March 17, 2015

“ስሉሱ” ዞረ እንዴ?! የምዕራቡ ሚዲያና ኢህአዴግ

eprdf and western media
ከጥቂት ሳምንታት ወዲህ ባልተለመደ ሁኔታ ኢህአዴግ ላይ ታዋቂ የዓለማችን ጋዜጦች የጀመሩት ተከታታይ ትችት፣ ማሳሰቢያና መፍትሔ ጠቋሚ ዘገባዎች መነጋገሪያ አጀንዳ ሆነዋል፡፡ ሚዲያዎቹ በዘገባቸው ኢህአዴግን ከቻይና አምባገነናዊና አክራሪ አገዛዝ ጋር አመሳስለዋል፡፡ ኢህአዴግ እከተለዋለሁ የሚለውን የኢኮኖሚ መርህ ከቻይና የተኮረጀ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ውጤቱም ሆነ መድረሻው ግራ የሚያጋባና የማይታወቅ እንደሆነ ዘግበዋል፡፡ ጋዜጦቹ ኢህአዴግን በሚንከባከቡት መንግሥቶቻቸው እና በራሱ ኢህአዴግ ላይ የሰላ ሒስ መሰዘንዘር መጀመራቸው የፖሊሲ አውጭዎችን አስተሳሰብ የሚያስቀይር ከመሆን አልፎ ኢህአዴግ ላይ “ስሉሱ” ዞሯል የሚያስብል እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡

ጋዜጠኝነት ወንጀል አይደለም” በሚል ርዕስ የሰብዓዊ መብት ተመልካች የሆነው ድርጅት (ሂዩማን ራይትስ ዎች) ኢህአዴግ በሚያደርስባቸው ስልታዊ አፈና፣ ማስፈራሪያ፣ ህይወት የማጥፋት ዛቻ፣ … ምክንያት ኢትዮጵያ በጋዜጠኞች ላይ አፈና በማድረግ የቀዳሚነቱን ስፍራ መያዟን ባለ 76 ገጽ ዘገባ ካወጣ በኋላ በምዕራቡ ዓለም ያሉ ሚዲያዎች በኢህአዴግ አፋኝነት ላይ ጠንከር ያሉ ዘገባዎችን ማውጣታቸውን ይፋ እየሆነ መጥቷል፡፡
በዚህ ረገድ ቀዳሚውን ቦታ የወሰደው በዋሽንግቶን ዲሲ የአሜሪካ ፖሊሲና ሕግ አውጪዎችን አቅጣጫ በማመላከት የሚታወቀው “ዋሽንግቶን ፖስት” የዛሬ ወር አካባቢ የሰብዓዊ መብት ድርጅቱን ዘገባ ተተርሶ (የታፈነው የኢትዮጵያ ፕሬስ) “Ethiopia’s stifled press” በሚል ርዕስ አቋም የያዘበት ርዕሰ አንቀጽ ነው፡፡ ጋዜጣው እንዳለው በሟቹ መለስ የተጀመረው አፈና በቀጣዩ ሃይለማርያም አገዛዝም በይበልጥ እየከረረ መሄዱን ጠቁሟል፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ከባላንጣዋ ኤርትራ እየባሰች መምጣቷን እንዲያው በተሻለ ሁኔታ ኤርትራ በጥር ወር ውስጥ በርካታ ጋዜጠኞችን ከእስር መፍታቷን ጨምሮ ገልጾዋል፡፡ ጋዜጣው ግልጽና የጠነከረ አቋም በወሰደበት በዚህ ርዕሰ አንቀጽ ማብቂያ ላይ አሜሪካ ለኢህአዴግ ዋንኛ ድጋፍ ሰጪ መሆኗን በመናገር በ2014 ለልማት ዕርዳታ በሚል 373 ሚሊዮን ዶላር መስጠቷን አስረድቷል፡፡ በአንጻሩ አሜሪካ ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብት ጥበቃ ማስፋፊያ ለኢትዮጵያ የምትሰጠው ዕርዳታ በ2012ዓም 3.4ሚሊዮን ዶላር የነበረው በ2014ዓም ወደ 163ሺህ ዶላር ማሽቆልቆሉን ተናግሯል፡፡ ይህ የሆነበት ዋንኛ ምክንያት ኢህአዴግ ያወጣው የመያዶች ሕግ እንደሆነ ጋዜጣው ጨምሮ ገልጾዋል፡፡
ዋሽንግቶን ፖስት ርዕሰ አንቀጹን ሲጠቃልል ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ዕርዳታ በማግኘት ቀዳሚ እንደመሆኗ በዴሞክራሲ ዕድገት እየሄደችበት ያለው ጎዳና አጠያያቂ እንደሆነ እንደምታ ያለው ሃሳብ ከሰነዘረ በኋላ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚ/ር መ/ቤት (ስቴት ዲፓርትመንት) እና የኦባማ አስተዳደር እንዲሁም ባጠቃላይ ምዕራባውያን ማድረግ የሚገባቸውን በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ስቴት ዲፓርትመንት በኢትዮጵያ እየተደረገ ባለው የሚዲያ አፈና ላይ ተቃውሞውን ማሰማት አለበት፤ ይህም ግን ከቃላት ማለፍ አለበት፤ የኦባማ አስተዳደር የሚሰጠውን ዕርዳታ ጋዜጠኞችና ጦማሪዎች እንዲፈቱ ከመጠየቅ ጋር ማቆራኘት አለበት (የማይፈቱ ከሆነ ዕርዳታ እስከመከልከል)፤ ሌሎች ምዕራባዊ ለጋስ አገራትም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ ማድረግ አለበት፤ ምዕራባዊ አገራት በአጠቃላይ ጋዜጠኞችን በማሰር በዓለም ታዋቂ ለሆነ አገዛዝ የሚያደርጉትን ዕገዛ ማቆም አለባቸው የሚል በዓይነቱ ተጠቃሽ የሆነና የምዕራቡ ዓለም በኢትዮጵያ ላይ የፖሊሲ ለውጥ እንዲያደርግ ግፊት የሚያደርግ ርዕሰ አንቀጽ ነበር፡፡
anuak woman aboboበቀጣይ የእንግሊዙ “ዘ ጋርዲያን” ኢህአዴግ በምዕራባውያን ዕርዳታ ከዓለም ባንክ የሚያገኘው 98ቢሊዮን ብር እንደነጠፈበት በመዘገብ “በመብት ረገጣ ምክንያት ብሪታኒያ ለኢትዮጵያ ከምትሰጠው ዕርዳታ አፈገፈገች” (British support for Ethiopia scheme withdrawn amid abuse allegations) በሚል ርዕስ ያወጣው ነው፡፡ ኢህአዴግን ከማንገስ ጀምራ በሥልጣን እንዲቆይ እንዲሁም በርካታ ድጋፍ ስትሰጥ የቆየችው እንግሊዝ እንዲህ ዓይነቱን እርምጃ ለመውሰድ መቻሏን ጋዜጣው በሰበር ዜና መልክ ማተሙ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ከተወሰኑ ጊዜያት በስተቀር በኢህአዴግ አገዛዝ ላይ የሰላ ሒስ ከመሰንዘር ከሚቆጠቡት የእንግሊዝ ሚዲያዎች አንጻር ዘጋርዲያን የወሰደው አቋም ለየት ያለ ነው፡፡ የእንግሊዙ የልማት ተራድዖ መ/ቤት “ኢትዮጵያ አድጋለች” በማለት ዕርዳታውን ከማቆም በማይተናነስ መልኩ ወደ 5በመቶ ማውረዱን ጋዜጣው ቢጠቅስም “ለዕድገቷ ማስረጃ” እንዲሆን ዜናውን ሲያትም በገዢነት ያወጣው የፎቶ ምስል በድንግዝግዝ ጸሃይ በአቧራ የተሰራ ቤት አቅራቢያ አቧራ ሲጠርጉ የሚታዩ ደካማ የአኙዋክ ሴትን ነው፡፡ የእርዳታው ገንዘብ ይሰጥ የነበረው መሠረታዊ አገልግሎቶችን ማለትም ትምህርት፣ ጤና፣ ንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ መንገድ ሥራ፣ ወዘተ ለመሳሰሉ የዜጎችን ኑሮ ለሚያሻሽሉ አስፈላጊ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያነት ነበር፡፡
ያለፈው ሳምንት አጋማሽ ኒው ዮርክ ታይምስ “በድህነት ተዳክማ የነበረችው ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ፍንዳታ እየጋለበች ነው” (Ethiopia, Long Mired in Poverty, Rides an Economic Boom) በሚል ርዕስ በርካታ ጉዳዮችን በመዳሰስ ያወጣው የዜና ዘገባ ሌላው ተጠቃሽ ነው፡፡ ለኢኮኖሚ ዕድገቱ አብነት እንዲሆኑ የዘመኑን ሰዎች እና ባለሃብቶች ጋዜጣው ቃለመጠይቅ በማድረግ በቂ ሽፋን ሰጥቷል፡፡ በአዲስ አበባ ውስጥ ጎልተው የሚታዩ እና “ከዕድገቱ” ጋር በንጽጽር ሊቀርቡ የሚገባቸውን ጉዳዮችንም ዳስሷል፡፡ በከተማዋ የተንሰራፋው ድህነት፣ የመገናኛ ዕጥረት፣ የኤሌክትሪክ መቋረጥ፣ የኢንተርኔት ኤሊነት፣ የቴሌኮሙኒኬሸን ኢተዓማኒነት፣ ወዘተ ላይ ጋዜጣው የሰላ ሒስ ሳያነሳ አላለፈም፡፡ ኢህአዴግ የሚታመንበትን የዓለም ባንክ ኃላፊንም አነጋግሯል፡፡ በኢትዮጵያ የባንኩ ዳይሬክተር የሆኑት ጉዋንግ ቼን አሁን አጠቃላይ ያለው አሠራር ተጠቃሽ መሆኑ ከገለጹ በኋላ ሲቀጥሉ “እንዲህ ያለው የኢኮኖሚ ሞዴል ለኢትዮጵያ ሰርቷል፤ ጥያቄው ቀጣይነት አለው? የሚለው ነው፤ ባንኩም ይህንኑ በመጠየቅ የኢኮኖሚው ሞዴል ለሚቀጥሉት 10 ዓመታት መቀጠል ይችላል ወይ? በማለት ይጠይቃል፤ በእኛ አመለካከት መልሱ አይችልም ነው” ማለታቸውን ጋዜጣው ጨምሮ ዘግቧል፡፡
ለማመዛዘን የተቃዋሚዎችን ሃሳብ ያቀረበው ጋዜጣ በፖለቲካው ረገድ ቀልብ የሚስቡ ሃሳቦችን አስፍሯል፡፡ ተቺዎች ያሉት ነው በማለት የመንግሥት አስተዳደር በትግሬዎች የበላይነት ቁጥጥር ሥር መውደቁን፣ ህወሃት ምንም ዓይነት ተቃውሞ መስማት የተሳነው መሆኑን፣ የተቃዋሚው እንቅስቃሴ (በትግሬዎች) የቁጥጥር መረብ ውስጥ የወደቀ መሆኑን፤ ፓርላማው በኢህአዴግ የበላይነት “የሚነዳ” መሆኑን፤ ማንኛውም የተቃውሞ ድምጽ የታፈነ መሆኑን፤ ጋዜጣው ማስረጃዎችን በማጣቀስ ሃተታውን ሰጥቷል፡፡ ሲያጠቃልልም የዞን 9 ጠበቃ የሆኑትን አቶ አመሃ መኮንን የሰጡትን አስተያየት ጠቅሷል፡፡ “በመንግሥትና በሕዝብ መካከል መተማመን መኖሩ ለዕድገት ጠቃሚ ነው፤ ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱ መተማመን አለ ብዬ ለማመን አልችልም” በማለት የሕግ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡
ከጥቂት ቀናት በፊት ደግሞ “ዎል ስትሪት ጆርናል” ኢህአዴግ የሚከተለው የልማት ፕሮግራም የተቃዋሚውን ድምጽ እንዲታፈን ያደረገ መሆኑን በመጥቀስ “Ethiopia’s Growth Program Cuts Out Dissent” በሚል ርዕስ  ዘገባ አስነብቧል፡፡ በኢህአዴግ ፓርላማ ፓርቲ አልባ ብቸኛ “የተቃዋሚ ፓርቲ አባል” በሆኑትን አቶ ግርማ ሰይፉ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ “ገዢው ፓርቲ ምርጫውን ያጠናቀቀው” መሆኑን በመግለጽ መጪው ምርጫ አስቀድሞ የተወሰነ መሆኑን ዘግቧል፡፡ በቻይና ስልት ኢትዮጵያን እየገዛ ያለው ኢህአዴግ ተቃዋሚዎቹን ሁሉ በሚፈልገው መልኩ ጸጥ ያሰኘ መሆኑን ያተተው ጋዜጣ ስልቱን ሲተነትን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከጋዜጠኛ ጋር በፖለቲካ ጉዳዮች ለመነጋገር እንደሚፈሩ፤ የስልክ ጥሪዎች ክትትል እንደሚደረግባቸው፤ አገዛዙን የሚተቹ ድረገጾች ውታፍ የተደረገባቸው እንደሆነ፤ የኢህአዴግን አገዛዝ የሚተች ማንኛውም ሰው ሥራ ለማግኘት፣ ንግድ ለማከናወን፣ ጨረታ ለማሸነፍ፣ ወዘተ የሚቸገር መሆኑን፤ ከነዋሪዎች ቃርሞ ባገኘው መረጃ አስረድቷል፡፡girma seifu maru
ከኢህአዴግ ሹሞች ስለታሰሩት ጋዜጠኞች ጉዳይ የአጸፋ ምላሽ ያሰፈረው ዎል ስትሪት አፈቀላጤው ሽመልስ ከማል የታሰሩት “ጋዜጠኞች አለመሆናቸውን” የታሰሩትም ሃሳባቸውን በመግለጻቸው አለመሆኑን ጋዜጣው ለንጽጽር አቅርቧል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘየሰብዓዊ መብት ተመልካቹ መ/ቤት በሚዲያ እና ጋዜጠኞች ላይ ያወጣውን ዘገባ በማጣቀስ በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የሰብዓዊ መብት ረገጣና በጋዜጠኞች ላይ የሚፈጸመውን እንግልት ለአብነት አስፍሯል፡፡ በመልካም አስተዳደር እና በሌሎች ጉዳዮች አገሪቱ ወደታች እያሽቆለቆለች እንደሆነ የተናገረው ዎል ስትሪት ጆርናል በቅርቡ በተካሄዱ ሰላማዊ ሰልፎች የአገዛዙ ጥበቃ ኃይላት በሰልፈኞች ላይ ጥይቶች መተኮሳቸውን ዘግቧል፡፡
መጪው ምርጫ ብዙም ተስፋ የሚጣልበት እንዳልሆነ በሃተታው እንደምታ የገለጸው ጋዜጣ የምዕራባውያንን ዝምታ ሳይጠቅስ አላለፈም፡፡ አሜሪካ ከኢህአዴግ ጋር ባላት የአካባቢው ጸጥታና የሰላም ጥበቃ ውል ምክንያት የራሷን ጥቅም የምታይ ብቻ መሆኗን ጋዜጣው ያስረዳል፡፡ በመሆኑም አቶ ግርማ እንዳሉት ምርጫው አስቀድሞ የተጠናቀቀ መሆኑን ጋዜጣው በመጥቀስ የምዕራብ ፖሊሲ አውጪዎች እንዲህ ዓይነቱን ዝምታ በመምረጥ ከኢህአዴግ አፋኝ አገዛዝ ጋር መሞዳሞድ መቀጠላቸው የራሳቸውን አገር ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ እየጣሉት እንደሆነ ሊገባቸው በሚችል ቋንቋ አስረድቷል፡፡
የምዕራቡ ዓለም ሚዲያ ውጤቶች በኢህአዴግ ላይ ይህንን መሰሉ ትችት ሲያቀርቡ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም፡፡ እንዲህ ባለው አጭር ጊዜ ውስጥ ታዋቂ የሆኑ ጋዜጦች በተደጋጋሚ ኢህአዴግን ሲተቹ ግን በዓይነቱ የመጀመሪያው ነው ሊባል ይችላል፡፡ ከዚህ ቀደም አንድ የምዕራብ ሚዲያ በኢህአዴግ ላይ የሰላ ትችት ሲደርስ ኢህአዴግ “በእጅም በእግርም” በማለት በሌላ ተመጣጣኝ ሚዲያ የአጸፋ ምላሽ ሲሰጥ በተደጋጋሚ የተከሰተ እውነታ ነው፡፡ አሁን ግን ከአንድ ጊዜ በላይ ይህንን ዓይነት ተደራራቢ ትችት ሲቀርብበት ሊያስተባብልለት የሚችል ተመጣጣኝ ሚዲያ አለማግኘቱ ወይም ሞክሮ እምቢ መባሉ “የስሉሱን” መዞር እውነተኛነት የሚያጠናክር እንደሆነ አብሮ የሚጠቀስ ነው፡፡
በጥቂት ሳምንታት ውስጥ አራት የምዕራብ አገራት ታዋቂ ጋዜጦች ይህንን ዓይነት ዘገባ ማቅረባቸው የምዕራቡ ዓለም የፖለቲካ ዘዋሪዎች በኢህአዴግ ላይ አቋም እንዲወስዱ ተገቢውን ግብዓት በይፋ እየሰጡ እንደሆነ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል እና ድርጊቱም ያለምክንያት እንዳልሆነ የፖለቲካ ተንታኞች የሚስማሙበት ሃሳብ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በሚገኝ አንድ የትምህርት ተቋም የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር የሆኑ ለጎልጉል ይህንን ጉዳይ ሲገልጹ “የምዕራብ ፖለቲከኞችና ጋዜጦች በቁርኝት ነው የሚሰሩት፤ ፖለቲከኞች የሚፈልጉትን ለማድረግ ሲፈልጉ በጋዜጦች በኩል ሃተታ እንዲሰራ ያደርጋሉ ከዚያ ያንኑ ዘገባ መልሰው እንደማስረጃ በመጠቀም የፖሊሲ ለውጥ ለማድረግ ይጠቀሙበታል፤ ሰሞኑን የምዕራብ ጋዜጦች እየወሰዱ ያለውን የተለየ አቋም ከዚህ አንጻር ከተመለከትነው በእርግጥ ምዕራባውያን በኢህአዴግ ላይ ስሉሱን ሊያዞሩ ነው እንዴ በሚል ሊታይ የሚችል ሲሆን ይህ አካሄድ ምን ያህል ለውጥ ሊያመጣ ይችላል የሚለው በሂደት የሚገለጽ ነው፤ በውጭ አገር ያለው ኢትዮጵያዊ የሚያደርገው ግፊትና ተጽዕኖም ከዚሁ ጋር በተዛማጅ ሊጠቀስ የሚገባው ነው” ብለዋል፡፡
የምዕራቡ ዓለም ጋዜጦች በኢህአዴግ ላይ የጀመሩት “ዘመቻ” ወደ የትኛውም አቅጣጫ ይሂድ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ሁኔታ ግን “ስሉሱ” ቢዞርም ባይዞር የሕዝቡ ምሬት ከምንግዜውም በበለጠ እየጨመረ መምጣቱን ነው፡፡ ሁኔታውን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች የዕርቅን አማራጭ በተደጋጋሚ እያቀረቡ ያለ ቢሆንም ከኢህአዴግ በኩል የሚሰማው ግን “እንደጀመርን እንጨርሰዋል” የሚል ቀረርቶ ብቻ ነው፡፡
ፕ/ር መስፍን ወልደ-ማርያም “የወያኔ የጥላቻ ፍሬ” በሚል ርዕስ የዛሬ ዓመት አካባቢ ባወጡት ጽሁፍ ላይ እንደጠቆሙት ግፍ ማብቂያ እንደሚኖረውና አልሰማ የሚል ሁሉ ጊዜውን ጠብቆ በግድ እንዲሰማ እንደሚደረግ ይህም ደግሞ ለማንም እንደማይበጅ ሲገልጹ እንዲህ ብለው ነበር፡- “ወያኔ ከሀያ ዓመታት በላይ አፍንጫ እየያዘ ያስከፈለውን የሚመልስበት ጊዜ እየተቃረበ ነው፤ ጥያቄው ወያኔ እንዲመልስ የሚገደደው እንዴት ነው? የሚል ነው፤ ጥላቻ ወደ ንዴት፣ ንዴት ወደ ቁጣ ተለውጦ ሲገነፍል ምጽዓት ደረሰ ማለት ነው፤ ሁሉም ሰው ራቁቱን ይሆናል፤ አንደአውሬ ከጥፍሩና ከጥርሱ በቀር ሌላ መሣሪያ አይኖረውም፤ ሰው ሁሉ በክፋት ወደ አውሬነት ይለወጣል፤ ጠመንጃና ቦምብ አያገለግሉም፤ ሕንጻው ምሽግ አይሆንም፤ መኪናው፣ ባቡሩ፣ ታንኩ ከቆመበት አይነቃነቅም፤ የትም አያደርስም፤ ጭፍራ ሁሉ በየራሱ ፍዳ ታንቆ እንኳን ለሌላ ሊተርፍ ለራሱም የማይበቃ ይሆናል፤ ለነገሩ ጌታና ሎሌም የለም፤ ሁሉም በአውሬ እኩልነት የተፋጠጠ ነው፤ ርኅራኄ ተሟጦ፣ መግል ያዘለ ልብ ፈርጦ፣ ውይይትና ክርክር አብቅቶ፣ ጥርሱን ያገጠጠና ጥፍሩን የሳለ መንጋ በደም የሚራጭበት ሁኔታ ነው።”
በመጪው ግንቦት ወር ይካሄዳል ከሚባለው ምርጫ አኳያ ኢህአዴግ እየተጓዘበት ያለው የዕውር መንገድ፤ በልማትና ዕድገት ስም በሕዝቡ ላይ እየጫነ ያለው ቀንበር፤ “እኔ ከሌለሁ አገር ትፈርሳለች” የሚለው ቅኝት፤ በተቃዋሚዎች ላይ የሚያደርሰው ዓይን ያወጣ በደል፤ አፈና፣ እስራት፣ ግድያ፣ … የግፉን ሸክም እያገዘፈው ብቻ ሳይሆን የሚሄደው መሸከም የሚችል ወገብ እንዳይኖርም ያደርገዋል፡፡ የዚያን ጊዜ የግፉን ቀንበር ተሸካሚው መውደቁ የማይቀር ይሆናል፡፡ ይህ ሲሆን “ስሉሱ” ቢዞርም ባይዞርም አሸካሚው ግፈኛም ሚዛኑን ስቶ መውደቁ የማይቀር ነው፡፡

No comments:

Post a Comment