Saturday, October 18, 2014

ሥነ-ኪን ወይስ ኪነ-ጥበብ? ሥነ-ጥበብስ ምንድን ናት? ዓላማ ግቧና ጥቅም አገልግሎቷስ?

art-music-dance-photo
ብዙውን ጊዜ ሥነ-ኪን ወይም የጥበብ ሥራ፣ ነገረ-ጥበብ ማለት እንፈልግና ኪነ-ጥበብ የሚለውን ቃልና ሥነ-ጥበብ የሚለውን ቃል እያጣረስን ስንጠቀም እንስተዋላለን፡፡ ኪነ-ጥበብ ወይም ኪነ-ጥበባት የሚለው ቃል ራሱ ግራ የተጋባ ቃል ነው፡፡ ልንጠቀምበት ፈልገን በምንጠቀምበት ቦታ ሁሉ ሰዋስዉ የተሳሳተ (Grammatically wrong) በሆነ መንገድ ነው፡፡ ቃሉ የግዕዝ ቃል ቢሆንም እነኝህን ሁለት ቃላት ማጣመር ግን የሰዋስው ስሕተትን ይፈጥራል፡፡ ምክንያቱም ኪን የሚለው ቃል ትርጉም ራሱ ጥበብ ማለት ነውና፡፡

ስለዚህም ኪነ-ጥበባት ስንል ጥበበ ጥበባት ማለታችን ነው ማለት ነው፡፡ ይሄም ማለት የጥበቦች ጥበብ ወይም ከጥበቦች ሁሉ የበላይ ጥበብ የሚል ትርጉምን ይሰጣል እንጅ አጠቃላይ የጥበብ ሥራ ዘርፍ ማለት አይደለም፡፡ ንጉሠ ነገሥታት ማለት የነገሥታት ንጉሥ ማለት እንደ ሆነ ሁሉ ማለት ነው፡፡ ስሕተቱ ይሄ አይደለም ይሄንን ቃል ጠቅሰን ልንገልጽ የምንፈልገው ጉዳይ ቃሉን ስሕተት ያደርገዋል፡፡ ስለሆነም ቃሉ የተሳሳተ ነው፡፡ እናም ይስተካከል ቢባል ሊሆን የሚችለው “ሥነ-ኪን” ወይም ሲተረጎም “ነገረ-ጥበብ፣ የጥበብ ሥራ ባጭሩ ደግሞ ኪነት” ይሆናል ማለት ነው፡፡
ነገር ግን ብዙዎቻችን “ኪነት” ሲባል የሚመስለን ቃሉ የሚያመለክተው ዜማንና ግጥሙን ወይም ዘፈንን ብቻ ይመስለናል፡፡ እንደተረዳሁት ብዙ ሰዎች እንዲህ ብለው እንዲያስቡ ያደረጋቸው ደርግ በተለይ በወጣቱ አቀጣጣይነት የተነሣውን የወቅቱን አቢዮት ወጣቱን ለመያዝ ወጣቱን በሚስብና በሚቀሰቅስ ብሎም ወደሚፈልገው አቅጣጫ ለመውሰድ ወጣቱን የሚያሳትፍ በየቦታው በየክፍላተ ሀገሩ የኪነት ማዕከል አቋቋመ፡፡ በእነዚህ የኪነት ማዕከላት ውስጥ በርከት ያሉ የሥነ-ኪን ወይም ሲተረጎም የጥበብ ሥራ ወይም ደግሞ በአጭሩ የኪነት ዘርፎች የሆኑ የጥበብ ሥራዎች እንዲከወኑ እንዲሠሩ ሙከራ አድርጓል፡፡
ከነዚህም ውስጥ ለምሳሌ ያህል ብንጠቃቅስ ተውኔት ወይም ቴአትር፣ ሥነ-ጽሑፍ፣ ሥነ-ጥበብ (ሥዕልና ቅርጻቅርጽ)፣ ዘፈን ወይም ሙዚቃ (በነገራችን ላይ ሙዚቃ አማርኛ አይደለም ሚዩዚክ የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል በአገርኛ ለዛ ሲጠራ ነው ሙዚቃ የተባለው ልክ school የሚለው ቃል አስኳላ እንደተባለው ሁሉ ማለት ነው) ነበሩ፡፡ ነገር ግን የአጋጣሚ ጉዳይ ሆኖ ይሁን የሌላ አላውቅም ከእነኝህ ሁሉ ዘርፎች ዘፈን ወይም ሙዚቃ ገኖና ጎልቶ ሌሎቹን ውጦ በመውጣቱ ለአጠቃላይ ዘርፉ የሚያገለግለው ሥያሜ ማለትም ኪነት የሚለው ቃል ዘፈንንና ዘፋኝነትን የሚያመለክት ብቻ ተደርጎ በስሕተት ሊቆጠር ቻለ፡፡
ባለፈው ጊዜ የሥነ-ኪን ወይም የኪነት ባሙያዎች ከሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር አድርገውት በነበረው ውይይት ላይ ይህ ስሕተት በጉልህ ተስተውሏል ሁሉም ይጠቀሙት የነበረው ቃል ስሕተት ነበር፡፡ የመገናኛ ብዙኃንም ሥነ-ጥበብን የተመለከተ ውይይት እያሉ ሲዘግቡ ዓይተናል ሰምተናል፡፡ ሥነ-ጥበብ የሚለው ቃል ግን የእንግሊዘኛውን fine Art እንዲወክል በየመዝገበ ቃላቶቻችን ጭምር የሰፈረ ቃል ነው፡፡ ብቸኛው መንግሥታዊ የfine art ወይም የሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት የሚጠራውም በዚሁ ሥያሜ ነው የሚወክለውም ሥዕልና ቅርጻቅርጽን ብቻ ነው፡፡ በዚያ ውይይት ተጋብዘው የተገኙት ግን ሠዓልያንና ቀራጽያን ብቻ ሳይሆኑ ዘፋኞች ወይም ሙዚቀኞችም፣ በተውኔት ወይም በቴአትር ሥራ ዘርፍ የተሰማሩ ተዋንያንና ደራሲያን እና በሌሎች የሥነ-ኪን (የጥበብ ሥራዎች) ወይም የኪነት ዘርፎች የተሠማሩ ከያኔያን (Artists) በሙሉ ነበሩ፡፡
ይህ ጽሑፍ የተሳሳተውን “ኪነ-ጥበብ” የሚለውን ቃል በማረም የሥነ-ኪንን (የጥበብን ሥራዎችን) ወይም ደሞ ባጭሩ የኪነትን እና የሥነ-ጥበብን ልዩነትና አጠቃቀም የጥበቡንም አገልግሎትና  መቸት ያብራራል፡፡
ኪነ-ጥበብ ስለሚለው ቃል ትርጉምና ከሰዋስው ሕግ አንጻርና ልንለው ከምንፈልገው ነገር ጋር ያለውን ነገር ከላይ ዐይተናልና አሁን ደግሞ ሥነ-ጥበብ የሚለው ቃል በአጠቃቀምና በትርጉም ልንለው ከምንፈልገው ጋር ያለውን ችግር ዕንይ፡- ሥነ-ጥበብ ብለን በድምፅ ስንል ሦስት ነገር እንዳልን መረዳት ይኖርብናል፡፡
  1. ሥነ-ጥበብ ስንል ጉዳዬ፣ ጥናተ፣ ነገረ፣ ተግባረ “ጥበብ” ማለታችን ሲሆን
ምሳሌ፡- ecology ሥነ-ምኅዳር፣ psychology ሥነ-ልቡና፣ psychiatry ሥነ-እእምሮ፣ biology ሥነ-ሕይዎት፣ literature ሥነ-ጽሑፍ፡፡ በዚህ አገባብ “ሥነ” የሚለው ቃል logy ጥናት የሚለውን ይወክላል፡፡
  1. ሌላኛው አጠቃቀም ደግሞ ለምሳሌ ሥነ-ጥበብ ስንል ውበተ-ጥበብ ማለታችን ነው፡፡ በዚህኛው አገባብ “ሥን” የሚለው ቃል ሌላኛው ትርጉም ማለትም “ውበት” የሚለውን ተጠቅመናል ማለት ነው፡፡
  2. ስነ የሚለው ቃል በእሳቱ ሰ ሳድሱ ስነ-ጥበብ ተብሎ ቢጻፍ የሚሰጠው ትርጉም ጥርሰ-ጥበብ ወይም የጥበብ ጥርስ የሚል ይሆናል፡፡
እንግዲህ በቁጥር አንድ ላይ የተገለጸውን ትርጉሙን መሠረት በማድረግ “ሥነ-ጥበብ” ብለን በአጠቃላይ የሁሉንም የጥበብ ሥራዎች ወክሎ የጥቅል መጠሪያ እንዲሆን ከፈለግን ለንዑስ ዘዝፍም እየተጠቀምንበት በመሆኑ በአገልግሎት ላይ መምታታትና መወናበድ እንዳይፈጥር በቅድሚያ ከዚህ በፊት fine Art ማለትም “ሥዕልና ቅርጻቅርጽ” ልብ በሉ ሌሎቹን አያካትትም ሥዕልና ቅርጻቅርጽ ለሚለው ንዑስ ዘርፍ ትርጉም እንዲሆን የተሰጠውን መዝገበ-ቃላታዊ ትርጉም በቀየር ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም በተመሳሳይ አሁንም “ሥነ-ጥበብ” የሚለውን ቃል የጥቅል ሥያሜም ልናደርገው አንችልምና፡፡
በመሆኑም ሥነ-ጥበብ የሚለው ቃል ከዚህ በፊት እንደነበረው ሁሉ fine art  ወይም ሥዕልና ቅርፃቅርጽን እንጂ የጥበብ ሥራዎች ሁሉ የጥቅል ሥያሜ ወይም መጠሪያ ሊሆን አይችልም ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ቀደም ሲል ስንጠቀምበት የነበረውንና በተሳሳተ ግንዛቤ ያስቀረነውን ቃል ማለትም ኪነት የሚለውን ቃል መመለስ ይኖርብናል ማለት ነው፡፡ ወይም ደግሞ ይሄው ቃል ደበረኝ የሚል ካለ ሥነ-ኪን የሚለውንና ሲተረጎም የጥበብ ሥራዎች የሚል ቃል የያዘውን የጠራ ቃል መጠቀም ይኖርብናል ማለት ነው፡፡
“ኪን” ማለት ምን ማለት ነው?
ኪን ቃሉ ግዕዝ ነው እንደሚታወቀው አማርኛ የግዕዝ የበኩር ልጅ ምናልባትም አባት እንደመሆኑ የግዕዝን ቃላት በባለቤትነት ሲጠቀም ይስተዋላል፡፡ “ለአማርኛ ግዕዝ ነው ዳኛ” እየተባለም ይተረታል፡፡
ኪን፡- ጥሬ ዘር ሲሆን ጥበብ፣ የጥበብ ሥራ፣ የጥበብ ሙያ ማለት ነው፡፡
ኬንያ፡- የሚለውም ቃል ስም ነው ጥሬ ዘሩ “ኪን” ሆኖ ማለት ነው፡፡ ትርጉሙም ጥበበኛ ማለት ነው “ዘኢገብራ እደ ኬንያ ዘሰብእ” እንዲል፡፡ ትርጉም የጥበበኛ ሰው እጅ ያልሠራት ወይም ያልተጠበበባት ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ሥነ-ኪን ማለት የጥበብ ሥራ የጥበብ ሞያ ማለት ይሆናል፡፡
በሌላም በኩል “ከያኔ” ለነጠላ “ከያኔያን” ለብዙ አሁንም ስም ሲሆኑ ጥሬ ዘሩም “ኪን” ነው ትርጉሙም የጥበብ ሥራ ሠራተኛ ወይም ሙያተኛ ማለት ነው፡፡
ሥነ-ኪን ወይም ኪነት  የተለያዩ ዘርፎች ሲኖሯት ከእነርሱ ዋና ዋናዎቹም፡-
  1. ሥነ-ዜማ (Music or Song) መግለጽ ወይም ማለት የተፈለገን ነገር በጥዑመ ዜማ መግለጽን ይመለከታል፡፡
  2. ሥነ-ጥበብ (Fine art) ሥዕልና ቅርጻቅርጽን ይመለከታል፡፡
  3. ሥነ-ጽሑፍ (Literature) ግጥምን ጨምሮ አጭር ረጅም ልብ ወለድና ኢልብ ወለድ ድርሰቶችን ወግን የጽሑፍ ሥራዎችን ይመለከታል፡፡
  4. ተውኔት ወይም ትውንተ-ድርሰት (Theatre or Drama) የተለያዩ ጭብጦችን ይዞ በሕዝብ ወይም በተመልካቶች (Audience) ፊት በመድረክ ላይ ወይም በብዙኃን መገናኛ የሚተወን ድርሰትን ይመለከታል፡፡
  5. ምትርኢት (film or movie) በቴሌቪዥን (በምርዓየ-ኩነት) ወይም በማንኛውም ሰሌዳ (screen) ላይ የሚታይ የትውንተ ድርሰት (Drama) ሥራን ይመለከታል፡፡
  6. ሥነ-ሕንፃ ወይም ኪነ-ሕንፃ (Architecture) የሕንፃዎችን ንድፎች ከነ መዋቅሩ የሚመለከት ነው፡፡
የተውኩት የሥነ-ኪን ዘርፍ ያለ አይመስለኝም ነገር ግን በስራቸው የሚካተቱ የየራሳቸው ዘርፎች ይኖራሉ ለምሳሌ ጭፈራና ድንከራ ወይም ውዝዋዜ በሥነ-ዜማ ውስጥ፣ ሥነ-ውበት በሥዕልና ቅርጻ ቅርጽ ወዘተ.
ሥነ-ኪን ወይም ኪነት መቼና የት ተጀመረ፡-
ሥነ-ኪንን ወይም የኪነትን መቸት በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም የሰው ልጆች በማኅበራዊ የሕይወት መስተጋብር ምክንያት በጣም በቆየ ዘመን በተለይም በቤተ አምልኮዎች እንደተጀመረ ይታመናል፡፡
ሥነ-ኪን (ኪነት) ለምንና እንዴት ተጀመረ፡-
  1. ሰዎች የወደዱትን ነገር መውደዳቸውን በተሻለ መንገድ ለመግለጽ በሚጥሩበት ጊዜ፡፡
  2. በጥንት ዘመን በተለያዩ የአምልኮ ቦታዎች ያሉ ምእመናን ወይም አማኞች ማለት ማድረግ የሚፈልጉትን (ጸሎታቸውንና አገልግሎታቸውን) በውበትና በተመስጦ ለማቅረብ በሚሞክሩበት ጊዜ፡፡
  3. የሰው ልጆች ሕይወትን በተሻለ መንገድ ለመኖር ለማስቀጠል ብሎም ለማሳመር በሚያደረጉት ጥረት፡፡
  4. አማልክቶቻችን የሚሏቸውን በሚታዩ በሚጨበጡና በሚዳሰሱ ምስሎች ለመወከል ከመነጨ ፍላጎት፡፡
  5. አማልክቶቻችን ናቸው ከሚሏቸው ማግኘት የፈለጉትን ነገር ለማግኘት ጸሎታቸውና ሌላው አገልግሎታቸው በተዋቡ ሥራዎችና በጥዑመ ዜማ ማታጀቡ የአማልክቶቻችንን ልብ ያባብልልናል፣ ያስደስትልናል፣ ፈቃዳችንንም ያስፈጽምልናል፣ ዋጋን ያሰጠናል ከሚል የጸና እምነት ሥነ-ኪንን ወይም ኪነትን ጀመሯት፡፡
ተግባረ ኪን (ኪነት) ምን ምን ጥቅሞች አሏት፡-
  1. ሥልጣኔን ትከስታለች፡፡
  2. ደስታና ኀዘንን አይረሴ በሆነ መንገድ ትገልጻለች፡፡
  3. ባሕልን ትፈጥራለች ትቀርጻለች ከነ እሴቱም ጠብቃ ታቆያለች፡፡
  4. ታሪክን በተለያየ መንገድ መዝግባ ለተከታታይ ትውልዶች ታሻግራለች፡፡
  5. ለተፈለገው ዓላማ ውጤታማ በሆነ መንገድ ማለትም ሕዝብን ለማስተማር፣ ለመቀስቀስ፣ ለማነሣሣት የማይተካ ሚናን ትጫዋታለች፡፡
  6. መሠላል በመሆን አማኞችን ከአምላክ ጋር ታገናኛለች፡፡
  7. የግለሰቦችን ወይም የሕዝብን ሕይወት እራሷን በመግለጥ አዎንታዊ በሆነ መንገድ ትለውጣለች ማለትም ታሳድጋለች ታንጻለች ትገነባለች፡፡
  8. መፍትሔንና አቅጣጫን ትጠቁማለች፡፡
  9. ጤናማ እና የተረጋጋ ሰብእናን ትገነባለች፡፡
10. በሥራ የደከመን አእምሮ ዘና ታደርጋለች አዲስ ጉልበትንም ትሰጣለች፡፡
  1. 11.  ኀዘንንና ጭንቀትን ታስረሳለች ታጽናናለች ታረጋጋለች መንፈስን ታድሳለች፡፡
  2. 12.  ከተለያየ ዓይነት በሽታ ትፈውሳለች፡፡
  3. 13.  ፍቅርን ትፈጥራለች ታሰማምራለች ታበጃጃለች ታቆነጃጃለች፡፡
  4. 14.  ጸብንና ክርክርን አርቃ ታስታርቃለች ሰላምን የማስፈን ትልቅ ጉልበት አላት፡፡
  5. 15.  ቀቢጸ ተስፋን አርቃ በተስፋ ትሞላለች፡፡
  6. 16.  እንደ ማቅረቢያ መነጽር (Telescope) እና እንደ ማጉያ መነጽር (microscope) ሩቁን አቅርባ፣ ሥውርና ረቂቁን አጉልታና ገልጣ ታሳያለች፡፡
  7. 17.  በማኅበራዊና እምነተ አሥተዳደራዊ (ፖለቲካዊ) ጉዳዮች ያሉ ጉድፎችን እንደ መስታውት ቁልጭ አድርጋ ታሳያለች፡፡
  8. 18.  ብሶት መተንፈሻና እንዲደርሰው ለተፈለገው አካል በታማኝነት በሚገባ ታደርሳለች፡፡
ባጠቃላይ ያለ ሥነ-ኪን ወይም ያለ ጥበብ ሥራ አንዳችም የሚከወን ነገር የለም፡፡ ከነዚህ ጥቅሞቿ አንጻር በተለይም በዘመናችን እኛ እንደ ሕዝብ ሥነ-ኪንን ምን ያህል ተጠቅመንባታል? ለመጠቀምስ ምን ያህል ምቹ ሁኔታን ፈጥረንላታል? ሀገራችን ኢትዮጵያ አንጻራዊ በሆነ መልኩ እስከ 20ኛው መቶ ክ/ን አጋማሽ ድረስ ክብሯን ዓላማዋን ግቧንና ጥቅሟን በጠበቀ መልኩ ኪነትን ተጠቅማባታለች የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ለውጪው ዓለም ካለን ተጋላጭነት የተነሣ እነሱ ጋር ያለው በሽታ እዚህም መጥቶ የሥነ-ኪንን እጅ በመጠምዘዝ ለግል ፍላጎታችን መጠቀሚያ ለማድረግ በምንፈልግ ወገኖች ጫና የተነሣ ሥነ-ኪን በተለያዩ አካላት ስትገዛ ኖራለች ትኖራለችም፡፡ በእኔ ግምት ከዚህ በኋላ ሥነ-ኪንን ከዚህ ባርነቷ መቸም የትም ነጻ ትወጣለች ብየ አላስብም፡፡ ኪነት የትም መቸም ቢሆን አላግባብ መጠቀሚያ ከመሆን ትድናለች ብሎ ማሰብ ሲበዛ ጅልነት ይመስለኛል፡፡ ኪነት በአንባ ገነን መንግሥታት ከሚደርስባት ፈተና ጫና ውክቢያና ብዝበዛ ባለተናነሰ ወደታች በምገልጻቸው አካላት መብት እንደልብ አለበት በሚባለው የምዕራቡ የዓለም ክፍልም ከዓላማዋ ከግቧና አቋሟ ውጪ ወይም በተፃራሪ መንገድ እየተበዘበዘች በባርነት ግዞት ውስጥ ትገኛለች፡፡
እነዚህ ወገኖች ከ20ኛው መቶ ክ/ዘ አስቀድሞ የራሳቸውን አቢዮትና ፈሊጥ ይዘው በመምጣትና እንቅስቃሴያቸውንም መገለጥ (expressionism) ብለው በመሠየም ሥዕልን፣ ቅርጻቅርጽን፣ ተውኔትን፣ ምትርኢትን (ሲኒማን ወይም ፊልምን) እና ዘፈንን (ሙዚቃን) “የሰዎችን ስሜትና ፍላጎትን እንደወረደ መግለጥ አለባቸው አንጂ ስሜትና ፍላጎት አልባ ድርጊትንና አካልን የሚገልጡ ብቻ መሆን የለባቸውም” በማለት ከደካማነታቸው የመነጨውን ድብቅ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ይጥራሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ኪነት ለኪነት (Art for Art’s sake) የሚል በግል ፍላጎታቸው የተቀፈደደና የተቀረጸ አንድ መፎክር አላቸው፡፡ ይሄን መንገድ በመያዝ ኪነትን የዋልጌነታቸው መጠቀሚያ ባሪያ እያደረጓት ይገኛሉ፡፡
እንደነሱ ግንዛቤ ኪነት ነጻ የምትሆነው በዚህ አውድ ነው፡፡ ለእነሱ ነጻነት ማለት ያለ ገደብ ሁሉንም ነገር በነጻነት የማድረግ ነጻ ፈቃድ ማለት ይመስላቸዋል፡፡ ነጻነትን እንዲህ በተረዳ ሰው ሕይዎት ውስጥ ኪነት ዓላማና አቋም አልባ ለመሆን ትገደዳለች፡፡ ዓላማ አላት ከተባለም እነሱ “ደስታ” ብለው የሚሉትን ግን ያልሆነውን ማስገኘት ይሆናል፡፡ አቋሟ ደስታ በተባለው ስም የሰውን ልጅ ማባለግ፤ ግቧም ባለጌ ዋልጌ ማኅበረሰብ መፍጠር ይሆናል ማለት ነው፡፡
ምን ያህል እንደተሳሳቱ አያቹህ? ይህ እብደት እንጅ ነጻነት አይደለም፡፡ እብደትነቱን የምናረጋግጠው በገዛ ራሳቸው ትርጓሜ ነው፡፡ ኪነት ለኪነት (Art for Art’s sake) ብለው ለማድረግ የሚፈልጉትንና የሚያደርጉትን ድርጊት ሁሉ እነሱ እራሳቸው የትም መቸም በማንኛውም ሰው ፊት አያደርጉትምና፡፡ ይህ ድርጊታቸው ጤናማና ችግር የሌለበት ቦታና ሰዓት ሊለይለት የማይገባ ከሆነ የትም መቸም ሲያደርጉት በተስተዋሉ ወይም ሊያደርጉት በተገባ ነበርና፡፡ ይህ ጉዳይ ለእነሱም እንኳ የማይታሰብ የማይሞከርም ነው፡፡ ጨርሶ አላበዱምና እብደታቸው ገና በከፊል ነውና በመሆኑም በከፊሉ እብደታቸው እነሱ በመረጡት ቦታና ጊዜ “ኪነት ለኪነት” እያሉ ከባሕል ከሞራል (ከግብረ-ገብ) ድንጋጌዎችና ከሃይማኖታዊ አስተምህሮ ተጻራሪ ድርጊቶችን እየፈጸሙ የዋልጌነት ስሜታቸውንና ፍላጎታቸውን ያረካሉ፡፡
እውነቱ እንዲህ በሆነበት ሁኔታ ኪነት በነጻነት ለራሷ ዓላማና አቋም እያገለገለች ነው ሳይሆን የምንለው ለእብዶች ባሪያ ሆናለች ነው ለማለት የምንችለው፡፡ እነዚህ ሰዎች ኪነት ወይም ጥበብ ይላሉ እንጅ ጥበብን ወይም ኪነትን ጨርሶ አያውቋትም፡፡ ኪነት የራሷ ዓላማና ግብ አላት፤ ኪነት የራሷ አቋም አላት፤ ኪነት ጽዩፍ ናት፤ ኪነት የጽድቅ የንጽሕና አገልጋይ ናት፤ ኪነት ግፍንና ወንጀልን ትጠላለች፡፡ የኪነት ዓላማ የሰው ልጆችን ሕይዎት ቀናና ምቹ ማድረግ ነው እንጅ አደጋና ችግር ላይ መጣል አይደለም፡፡ ሕይዎቱ እንዲመሰቃቀልና ችግር ላይ እንዲወድቅ ምቹ ሁኔታን መፍጠርና ወደዚያ መምራት አይደለም፡፡ እውነቱ ይሄ ከሆነ የጻድቋ የኪነት ዓላማ የሞራል (የግብረ-ገብ) እሴቶች እንዲጠበቁ በራሷ መንገድ እየሰበከች የሰው ልጆችን ሕይዎት ቀና ምቹ ሰላማዊና ጤናማ ማድረግ ከጥፋት መጠበቅ ይሆናል፡፡ አቋሟም ለእውነት ስለ እውነት ለሕዝብ ጥቅም መሥራት የማትደራደርበት አቋሟ ነው ማለት ነው፡፡
እንዳልኳቹህ በጣም ተጋኖ የሚወራ ባይሆን ቀደም ሲል ከጠቀስኩት ጊዜ ጊዜ ወዲህ ኪነትን የሞራል (የግብረ-ገብ) ድንጋጌዎቻችንን ለመደረማመስ እየተጠቀምንባት እንገኛለን፡፡ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ያሉ ዘፈኖቻችንን መለስ ብለን ብንፈትሽ የሚበዙቱ በፍቅር ስም ብልግናን ወይም ከባሕል፣ ከግብረ ገብና ከሃይማኖታዊ አስተምህሮ ውጪ ፆታዊ ግንኙነትን የሚሰብኩ ዋልጌነትን የሚያበረታቱ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ በአጭር አማርኛ ኪነትን የዝሙት ቃፊር አድርገናታል፡፡
ፍቅር ማለት ዝሙት ነው ካላልን በስተቀር ዝሙትን እየሰበክን እንዴት ስለ ፍቅር ልናወራ እንደምንችል ሊገባኝ አልቻለም፡፡ በዝሙት ሕይዎት ውስጥ የወሲብ ሱስ እንጂ ፍቅር ሊኖር አይችልምና፡፡ ፍቅር ማለት ፆታዊ ፍቅር በመተማመንና እራስን ለአንድ አሳልፎ በመስጠት ውስጥ ያለ ጸጋ ነው፡፡ ፍቅር መተማመንን ሳይይዝ መቸም የትም ሄዶ አያውቅም፡፡ መተማመን በሌለበት ፍቅር የለም፡፡ ዘፈኖቻችን በእርግጥ ዘፈኖቻችን ብቻ አይደሉም ከላይ የዘረዘርኳቸው የሥነ-ኪን ዘርፎቻችን በሙሉ በግልጽ የመተማመንን እሴት የሚያፈራርሱ ሆነዋል፡፡ የሚገርመው እነኝህን ዓይነት ሥራዎች በፍቅር የምናደምጣቸውና የምንመለከታቸው መሆናቸው ነው፡፡ ይህ ሁኔታም በምን ዓይነት የሞራል (የግብረ-ገብ) ውድቀት ውስጥ እንደገባን ያሳያል፡፡ ከከያኔያኖቻችን (አርቲስቶቻችን) የሚበዙቱ በፍቅር ስም እየሰበኩን ያለውን ድርጊት ፍቅር ይበሉት እንጂ ፍቅር እንዳልሆነ እነሱም የሚያውቁ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን ለግብረ-ገብ እሴቶች ግድ የላቸውምና ምንም አይመስላቸውም፡፡ ባጠቃላይ ኪነትን የአጉራዘለልነት ባሪያ አድርገናታል፡፡ ይህ ተሞክሮ ሀገር በቀል አይደለም ከላይ እንደገለጽኩት በሥልጣኔ ስም የገባው ከባዕድ ነው፡፡
እርግጥ ነው አንድ ነገር መዘንጋት እንደሌለብን ይሰማኛል፡፡ ይህች ምድር የፊልሚያ ምድር ናት፡፡ የየራሱን ሕይዎት የሚኖረው ሁሉ የየራሱን ጥቅም ለማስከበር ለማስጠበቅ የሚፋለምባት፡፡ ከዚህ አንጻር እነዚህና ሌሎች የሰብእናና የምግባር ችግር ያለባቸው ሰዎች ኢግብረገባዊ ድርጊቶችን ሳይወቀሱና ሳይከሰሱ እንዳሻቸው የትም ለማድረግ እንደ “ኪነት ለኪነት” ያለ ለድርጊቶቻቸው መልካም ሥያሜዎችን ፈልገው እንደጭምብል ለመጠቀም በእነሱም ለመሸሸግ አስገራሚ ጥረት ሲያደርጉ ብናይ ሊገርመን አይገባም፡፡ ከዚህ የከፋ የሰብእናና የምግባር ችግር መላቀቅ እስካልቻሉ ጊዜ ድረስ ለእነሱ ከዚህ የተለየ ሌላ አማራጭ የላቸውም፡፡
እርግጥ ነው በስሜት ደረጃ የዋልጌነት ስሜት የሌለው ሰው የለም፡፡ ልዩነቱ እንደሰው እውስጡ ለሚፈታተነው ለዚህ ስሜት እጅ የመስጠቱና ያለመስጠቱ፣ የመሸነፉና ያለመሸነፉ፣ መቆጣጠር የመቻሉና ያለመቻሉ ጉዳይ ነው፡፡ ጠንካሮቹ ስሜቱ እውስጣቸው ጨርሶ የሌለ እስኪመስሉ ድረስ አሸንፈውት ተቆጣጥረውት የመልካም ሰብእናና ምግባር ባለቤት ሲሆኑ ተሸናፊዎቹ ደግሞ መቆጣጠር ካለመቻላቸው የተነሣ ገንፍሎ ይፈስባቸዋል፡፡ መሸነፍ እንዳይመስልባቸውም ከሰብአዊ መብትና ከጥበብ ከኪነት ነጻነትና መገለጫ ጋራ ለማጣበቅ ይጣጣራሉ፡፡ አሁንም ደረጃው ይለያይ እንጅ የዋልጌነት ስሜት የማያስተናግድ ሰው የለም በዚህም ምክንያት ነው ከስሕተት የጸዳ ፍጹም ሰው የለም መባሉ፡፡ ልዩነቱ የመጠን ነው በአንደኛው ላይ አምስት በመቶ በሌላኛው ላይ ደግሞ ዘጠና አምስት በመቶ፡፡ ባለ አምስት በመቶው ጨዋ ንጹሕ ሲባል ባለ ዘጠና አምስት በመቶው ደግሞ የመጨረሻ ዋልጌ፡፡ ዋልጌዎቹ (expressionists) ኪነትን በቁጥጥራቸው ስር አድርገው የጥቅማቸው አቀንቃኝ ለማድረግ በብርታት እየሠሩ ሲሆን ጨዋዎቹ (Moralists) ደግሞ የህልውናቸው መሠረት የሆነው ምግባር ሲደረማመስ ፈዘውና ደንዝዘው በዝምታ በመመልከት እየተዋጡ ይገኛሉ፡፡ የዚህ ውጤት ምን ይሆን? የትስ ያደርሰናል???
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ዕንቁ መጽሔት ቅጽ 113

No comments:

Post a Comment