Monday, October 13, 2014

‹‹በሚዲያ ካውንስሉ›› መንግስት ይግባ መባሉ አከራከረ

(ነገረ ኢትዮጵያ) ‹‹የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት የምክክር ጉባዔ›› በሚል የሚዲያ ካውንስ ለመመስረት እየተደረገ በሚገኘው ስብሰባ መንግስት ይግባ መባሉ አከራካሪ ሆኗል፡፡ ለሁለት ቀን የሚቆየው ስብሰባ ትናንት መስከረም 29/2007 ዓ.ም በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ የተጀመረ ሲሆን ‹‹የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት የምክክር ጉባዔ›› በሚኖረው 15 የቅሬታ ሰሚ አባላት የመንግስት ተወካይ ሊኖር ይገባል መባሉ ተቃውሞ አስነስቷል፡፡ በእነ ሚሚ ስብሃቱ የሚመራው አደራጅ ኮሚቴ ቅድመ ጥናቱ ላይ ‹‹የመንግስት ተወካይ መኖር አለበት›› ብሎ ቢያቀርብም ከተሰብሳቢዎቹ መካከል ‹‹የመንግስት ተወካይ ካለ መንግስት ማህበሩን ይቆጣጠረዋል›› በሚል ቅድመ ጥናቱን ተቃውመዋል፡፡ ‹‹የመንግስት ተወካይ ይኑር አይኑር›› የሚለው ክርክር ረዥም ጊዜ የፈጀ ሲሆን ውሳኔ ሳይሰጥበት ታልፏል፡፡

Lomi-magazine-
በተመሳሳይ የገቢ ምንጩ ከየት ይሁን የሚለው አጀንዳም አከራካሪና ውሳኔ ያልተሰጠበት ሲሆን አደራጅ ኮሚቴው በቅድመ ጥናቱ የ‹‹ዴሞክራሲ ፈንድ›› በሚል የገቢ ምንጩ ከመንግስት መሆን እንዳለበት አስቀምጧል፡፡ በሌላ በኩል ግን ተሰብሳቢዎቹ ካውንስሉ ነጻ ሆኖ መቀጠል ካለበት አባል የሚሆኑት ሚዲያዎች በሚያዋጡትና በሌሎች መንገዶች በሚሰበሰብ ገቢ መቀጠል እንዳለበት፣ የገንዘብ ምንጩ ከመንግስት ከሆነ መንግስት ሊቆጣጠረው እንደሚችል ተከራክረዋል፡፡

ወይዘሮ ሚሚ ስብሃቱና ባለቤቷ አቶ ዘሪሁን ተሾመ የሚመሩት ቡድን የመንግስት ተወካይ በቅሬታ ሰሚው መካተት አለበት፣ ‹‹የዴሞክራሲ ፈንድ›› በሚል የገቢ ምንጩ ከመንግስት መሆን አለበት በሚል የተከራከሩ ሲሆን የፎርቹን ጋዜጣ ባለቤት አቶ ታምራት ገ/ጊዎርጊስንና ሌሎች በስብሰባው የተገኙ የሚዲያ ባለቤቶችና ተወካዮች ከእነ ሚሚን አቋም በተቃራኒ ቆመዋል፡፡ በሁለቱ አከራካሪ ጉዳዮች ምክንያት ዛሬ መስከረም 30/2007 ዓ.ም በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ይደረጋል ተብሎ የነበረው ፕሮግራም ለሰዓት ተላልፏል፡፡
ካውንስሉን ለማቋቋም የቅድመ ጥናት ያደረጉት የገዥውን ፓርቲ አቋም የሚደግፉና በገዥው ፓርቲ የሚደገፉ ሚዲያዎች ሲሆን በስብሰባውም የእነዚህ አካላት አቋም ጎላ ብሎ ተንጸባርቆበታል፡፡

No comments:

Post a Comment