Saturday, August 31, 2013

መንግስት ዘንድ ከፍተኛ መደናገጥ ተፈጥሯል!

ለዛሬ ታቅደው የነበሩ ግዙፍ የቅስቀሳ መድረኮች ተሰርዘዋል!
የሃይማቶች ጉባኤ ያዘጋጀው ነው ተብሎ በሚዲያ የተገለጸው የነገው ሰልፍ ሙስሊሙ ህብረተሰብ በነቂስ እንደሚሳተፍበት ካሳወቀ በኋላ እጣ ፈንታው ምን እንደሆነ ማወቅ አልተቻለም፡፡ ይህ ከፍተኛ ዝግጅት እና ወጪ ተደረጎለት የሰነበተውን ሰላማዊ ሰልፍ ድንገት ሙስሊሙ ህብረተሰብ በስፋት እንደሚገኝበት መታወቁን ተከትሎ በመንግስት ወገን አካባቢ ከፍተኛ ድንጋጤ በመፍጠሩ የሰልፉ እጣ ፈንታ አልተለየም፡፡ ትናንት አመሻሹ ላይ ሊካሄዱ ታስበው የነበሩ የሰልፍ ዝግጅት ግምገማዎች በዚሁ ምክንያት ሙሉበሙሉ መሰረዛቸው የታወቀ ሲሆን በወረዳና በክፍለ ከተማ አካባቢ ያሉ የመንግሰት ሀላፊዎችም ለከፍተኛ ጭንቀት ተዳርገዋል፡፡

‹‹አክራሪነትን ለማውገዝ›› በሚል መሪ አላማ በተዘጋጀው ሰልፍ መንግስት አዘጋጅ እንዳልሆ ሲገልጽ መሰንበቱ ይታወቃል፡፡ ሆኖም የሰልፉን አጠቃላይ ዝግጅት ከአጀንዳ መረጣ ጀምሮ በፋይናንስ እና በቅድመ ዝግጅት በኩል እንዲሁም ከፍተኛ ሚዲያ ሽፋን በመስጠት ዝግጅቱን ሲመራ ቆይቷል፡፡ በክፍለ ከተማ እና ወረዳ ደረጃ ያሉ የመንግስተ ሀላፊዎችና ቢሮዎች በዚሁ ሰልፍ ላይ ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው የከረሙ ሲሆን በመንግስት ስር የተደራጁ የጥቃቅን እና አነስተኛ፣ የሴቶችና ወጣት ሊጎች፣ የኮብልስቶን ሰልጣኞችና የመንግስት ሰራተኞች እንዲሁም ሌሎችም በሰለፉ እንዲሳተፉና ቅስቀሳ እንዲደርጉ ሲደረግ ሰንብቷል፡፡
ሙስሊሙ ህብረተሰብ አክራሪነትን እንደሚያወግዝና እንደማይቀበል ለሁለት ዓመት በቆየው ሰላማዊ እንቅስቃሴው ደጋግሞ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ ኮሚቴዎቻችን ሕገ መንግስቱ ቢፈቅድ አንኳ አክራሪነትንና ጽንፈኝነትን ፈጽመው እንደማይቀበሉ በተለያዩ መድረኮች ላይ ተናግረዋል፡፡ በተቃራኒው መንግስት መብት የጠየቀውንና አክራሪነትን የሚቃወመውን ሙስሊም ህብረተሰብ በአክራነት በመወንጀል ለመብት ጥያቄው ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ቆይቷል፡፡ መንግስት በእምነቶች መካከል መቃቃር እንዲፈጠር በማሰብ ሲነዛ የቆየውን ፕሮፖጋንዳ ሃለፊነት በጎደለው መልኩ በመንግስት ሚዲያዎች ሲያሰራጭም ሰንብቷል፡፡
በክልልሎች በግዳጅ ህብረተሰቡን ወደ ጎዳና በማስወጣት ያካሄዳቸውን ሰልፎች ተከትሎ በአዲስ አበባ ደረጃ አክራሪነትን በመቃወም ስም ሙስሊሙን የሚያወግዝና መብት ጠያቂውን ህብረተሰብ በተራ የፖለቲካ ስሌት ለማንጣጣት የሚጥር መድረክ ቢጠራም ሙስሊሙ ሁሉንም አይነት አክራሪነት በመቃወም ጭምር ሰልፉ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ የሙስሊሙ ህብረተሰብ በሰልፉ በስፋት መገኘት ውሳኔ ስጋት ያሳደረበት መንግስት ከፍተኛ ድንጋጤ እና መረበሽ ውስጥ ገብቷል፡፡ በዚህም ምክንያት ለዛሬ በከተማዋ ሊካሄዱ ታስበው ነበሩ ግዙፍ ቅስቀሳዎች ተሰርዘዋል፡፡ በመኪናዎችና በግዙፍ ሜጋ ስፒከሮች በከተማዋ ሊካሄዱ ታስበው የነበሩ የዛሬ ዋና ዋና ቅስቀሳዎች ከላይ በወረደ ትእዛዝ ምክንያት ከመሰረዛቸውም በላይ ለሰልፉ ተሳታፊዎች ይዘጋጃሉ የተባሉ የሕዝብ ማመላለሻ ነጻ ተሸከርካሪዎችም እንደማይኖሩ ተነግሯል፡፡ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ነገ በሚደረገው ሰልፍ በስፋት ነቅሎ በመውጣት ፍጹም ዲሲፕሊን በታከለበት መልኩ አክራሪነትን እንደሚያወግዝ ይጠበቃል፡፡ ለዚህም ከፍተኛ የቅስቀሳ ስራዎች በመሰራት ላይ ናቸው፡፡
ድምፃችን ይሰማ

No comments:

Post a Comment