ለተሳታፊዎች ዳጎስ ያለ አበል ተዘጋጅቷል!
የግል ድርጅት ሀላፊዎች ከእነ መኪናቸውና ሰራተኞቻቸው በሰልፉ እንዲገኙ ግዳጅ ተጥሎባቸዋል!
መንግስት በመጪው እሁድ ሰልፍ ሊያካሄድ ነው፡፡ መንግስት በክልሎች ሲያካሄድ ያቆየውን ይህንኑ የግዳጅ ሰልፍ በአዲስ አበባ ለማድረግ ለወራት ከፍተኛ ዝግጅት ሲያካሄድ ቆይቷል፡፡ የፊታችን እሁድ በአዲስ አበባ ለማካሄድ የታሰበው ሰልፍ በዋነኝት ሙስሊሙ ህብረተሰብ ያነሳውን የእምነት መብት ጥያቄ በክራሪነት ለመወንጀልና ‹‹ሕዝቡ መንግስት እርምጃ ይውሰድልን›› አለ በሚል ለሚዲያ ፍጆታ ለመጠቀም ነው፡፡
በዚህ ሰልፍ በርካታ ሰው እንዲገኝ ለማድረግ ያስችል ዘንድ የመንግስት ሰራተኞች፣ የፓርቲ አባላት፣ የሴቶች ሊግ፣ የወጣቶች ሊግ እንዲሁም በጥቃቅን እና አነስተኛ የተደራጁ ማህበራት አባሎች፣ በኮብል ስቶን የሰለጠኑ ወጣቶች እንዲገኙ የግዳጅ መመሪያ ተላልፏል፡፡ እነዚህ የተጠቀሱ ሁሉ በሰልፉ ላይ ለመገኘት ፊርማቸውን እንዲያኖሩ በዚሁ ሳምንት ሊጠየቁ እንደሚችሉ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
እሁድ ዕለት ነሐሴ 26/2005 ኢሕአዴግ በጠራውና ‹‹አክራሪነት››ን ማውገዝ ዋነኛው አጀንዳው ነው በተባለለት ሰልፍ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማትም እንዲሳተፉ መንግስት ጫና በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ከሃይማኖት ተቋማት በተጨማሪ የተለያዩ የግል ድርጅቶች በተለይም የጅምናስቲክ፣ የማርሻል አርትና የቴኳንዶ ስልጠና የሚሰጡ ድርጅቶች ሰልጣኝ ተማሪዎቻቸውን በሰልፉ ይዘው እንዲገኙ በየወረዳው አስተዳዳሪዎች ትእዛዝ ተላልፎላቸዋል፡፡
ከየክፍለ ከተማው አስከ አስር ሺ ሰው እንዲሳተፍበት በተላለፈው መመሪያ መሰረት የወረዳ ቢሮዎች ኮታውን ለመሙላት ይሄን ሳምንት ሙሉ ጊዜያቸውን ለዚሁ ስራ በመስጠት ከፍተኛ የቅስቀሳ እና የግደጅ ስራ ለመስራት ተዘጋጅተዋል፡፡ መንግስት በክልል ከተሞች ሲያካሄደው እንደነበረው ሁሉ ለዚህ ሰልፍም ከፍተኛ ባጀት መድቧል፡፡ ለሰልፉ ተሳታፊዎችም ዳጎስ ያለ አበል እንደሚቆረጥላቸው ቃል ተገብቶላቸዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ትናንት በአዲስ አበባ የሚገኙ የግል ድርጅት ሀላፊዎችን መንግስት በዚሁ አጀንዳ ጉዳይ ጠርቶ ማነጋገሩ ታውቋል፡፡ ድርጅቶቹ መኪኖቻቸውን ከእነሰራተኞቻቸው ይዘው ‹‹አሸባሪነትን እንቃወማለን›› በሚል በሰልፉ እንዲገኙ በየአካባቢው ያነጋገሯቸው የመንግስት ከፍተኛ ሀላፊዎች በማስጠንቀቂያ መልክ ገልጸውላቸዋል፡፡ የመንግስት ኋላፊዎቹ ቁጥጥር እንደሚያደርጉና አንድም ሰራተኛ መቅረት እንደሌለበት አሳስበዋልም፡፡
መንግስት መሰል ሰልፎችን በግዳጅ በመጥራት በሚዲያው ግን በተቃራኒው ‹‹ሕዝቡ በራሱ ፈቃደኝነት ሰልፍ ወጣ›› የሚል ዜና ሲሰራ ቆይቷል፡፡ የመሰል ሰልፎችና ስብሰባዎች የአቋም መግለጫዎች ከስብሰባውና ሰልፉ ቀናት በፊት ተዘጋጅተው የሰልፉ ተሳታፊዎች ያወጡት መግለጫ በሚል በእለቱ እንዲነበብና ለፕሮፖጋንዳነት እንዲውል ሲደረግ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
አላሁ አክበር!
No comments:
Post a Comment