Tuesday, August 27, 2013

የኢህአዴግ ስውር ሴራ በሮቤ ከተማ ተጋለጠ!!! ሐገሪቷን የሚያስተዳድራት ማነው? የባሌ ሮቤ ሰላማዊ ሰልፍ ለምን ተደናቀፈ? -አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)

ከአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ ማብራሪያ
የሚሊየኖች ድምፅ ለነፃነት ንቅናቄ በአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት የነፃነት ድምፅ ማስተጋባት ከጀመረ እንሆ ዛሬ ስልሳ ሰባተኛ(67) ቀኑን ይዟል፡፡ ፓርቲያችን በእዚህ ታላቅ ሕዝባዊ የነፃነት ንቅናቄ መሪር የሆነ ውድ ዋጋ እየከፈለ ድምፅ አልባ ለሆኑት ሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን ድምፅ በመሆኑ ታላቅ ደስታ ይሰማዋል፡፡
ላለፋት ስምንት ዓመታት ሰቆቃ እና ግፍ በገዢዎቻችን ሲፈፀምበት የኖረው የገጠሩም ሆነ የከተማው ታላቁ ህዝባችን ‹አንድነት ፓርቲአችን አስትንፋሳችን› በማለት አንድነት ፓርቲ ባመቻቸለት ህዝባዊ ስብሰባዎች እና ሠላማዊ ሠልፎች በነቂስ በመውጣት የታፈነ ብሶቱን በግልፅ በአደባባይ ላይ በማሰማቱ ኢህአዴግ እና ህዝቡ ዛሬም ድረስ ተለያይተው እንዳሉ አንድነት ፓርቲ በማያወላዳ ሁኔታ በሚሊዮኖች ድምፅ ንቅናቄ በህዝባችን መሀል በመገኘት አረጋግጧል፡፡

ኢህአዴግ የቀረው በውሸት እና በሴራ የተሞላ የቅጥፈት ፕሮፖጋንዳ ብቻ መሆኑን ይበልጥ ያረጋገጠልን የባሌ ዞን አስተዳደር እና የሮቤ ከተማ አስተዳደር ያዘጋጁት በሀገር ሽማግሌዎች ስም የተቀነባበረው የእናደራድራችሁ አሳፋሪ ድራማ ለኦሆዴድም ሆነ ለኢህአዴግ ታላቅ ውድቀት ነው፡፡
አንድነት ፓርቲ በባሌ ሮቤ ከተማ ሠላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ህጉ በሚያዘው መሰረት ነሐሴ 13/2005 የሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ደብዳቤ ለከተማዋ አስተዳደር አስገባ፡፡ ጉዳዩን የሚከታተሉት የፓርቲው ተወካዮች ደብዳቤው ከገባ ከ48 ሠዓት በኋላ ወደ መደበኛ ቅስቀሳቸው መግባት እንደሚችሉ ህጉ እንደሚፈቅድላቸው የተረዱት የፓርቲያችን ትንታግ ታጋዮች ጊዜ ሳያባክኑ የተዘጋጀውን የቅስቀሳ በራሪ ወረቀት በከተማ ውስጥ ማሰራጨት ጀመሩ፡፡
ሁኔታውን በቅርብ ሲከታተሉት የነበሩት የፌደራል መንግስት እና የክልሉ መንግስት ከሮቤ ከተማ አስተዳደር ጋር በመቀናጀት አንድነት ፓርቲ ላይ ያጠመዱት ሴራ ለመተግበር የከተማው ከንቲባ አቶ አብዱል ላጥፍ ነሓሴ 13/2005 ለገባላቸው የፓርቲው ደብዳቤ መልስ ያሉትን ነሓሴ 13/2005 ቀን እንደ ተፃፈ ተደርጎ ፓርቲው አላማ ያሉትን ዘርዝረው ነሓሴ 17/2005 ዓ.ም ደብዳቤ ለፓርቲው ተወካዮች ሰጡ፡፡ የተባሉትን ሰበቦች እና ምክንያቶችን በሙሉ አሟልቶ ፓርቲው የእዚያኑ ዕለት በደብዳቤ ምላሽ ቢሰጥም የከተማው አስተዳደር ባለስልጣኖች ከንቲባውም ጭምር ቢሮአቸውን ዘግተው ጠፉ፡፡ መዝገብቤትም ለማስገባት የተደረገው ጥረት በመዝገብ ቤት ሰራተኞች እምቢ ባይነት ሳይሳካ ቀረ፡፡ የአምባ ገነኑን የኢህአድግ ባለስልጣኖችን ነውረኛ ስራ ቀድሞ የሚያውቀው የአንድነት ፓርቲ የተዘጋጀውን ደብዳቤ በሪኮማንዴ በፓስታ ቤት በኩል አንዲደርሳቸው በማድረግ ምንም መፈናፈኛ ሰበብ እንዳያገኙ አደረገ፡፡
ግራ የገባቸው የከተማው አስተዳዳሪዎች ተሰባስበው ከላይ በተሰጣቸው ትእዛዝ መሰረት አንድነትን የማጥቅያ ሌላ ሴራ ተጠቅመው መጥታችሁ የሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያውን ቅፅ ሙሉ በማለት ለተወካዮቻችን ጥሪ አደረጉ፡፡ የፓርቲው ተወካዮች ስራቸውን እየሰሩ ቅፁን የሚሞሉ እና የሚፈርሙ አባላትን በመመደብ ተወካይ ብቻ ወደ ወስተዳድሩ ፅ/ቤት ላኩ፡፡ የጠበቃቸው ግን የተቀናጀ ሴራ ነው፡፡ አንድነት ፓርቲን በህግ የሚያስጠይቅ እንዲሁም ያዘጋጁትን የሀይል ርምጃ ህጋዊ የሚያደርግ፤ ደብዳቤ ካስገባን 48 ሰዓታት ባነሰ ጊዜ ሰልፍ እወጣለሁ ብሎ ፓርቲው ነሓሴ 17/2005 ደብዳቤ እንዳስገባ ተደርጎ ይህንኑ ቀን የጠቀሰ ቅፅ አዘጋጅተው የአንድነትን ተወካዮች አንዲፈርሙ ተጠየቁ፡፡ ቀድሞውኑ ሴራው የገባው የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራር በሰጠው መመርያ መሰረት ቅፁ ላይ የምንፈርመው ደብዳቤአችንን ያስገባንበትን ነሐሴ 13/2005 ቀን ከጠቀሰ ብቻ ነው በማለት የአንድነት ተወካዮች አንፈርምም አሉ፡፡
አንድነት ፓርቲን በጉልበትም በህግም ለማኮላሸት ኢህአድግ ያዘጋጀውን ሴራ በጥበብ ማክሸፍ ተቻለ፡፡ ኢህአዴግ ለሌላ ሴራ ማቀንቀኑን ወድያውኑ ተያያዘው፡፡
የፓርቲው ቀስቃሽ ቡድን በ50.000 የሚገመት በራሪ ወረቀት መበተኑን እና ከ5.000 በላይ ፖስተር በእለቱ በመለጠፍ የፓርቲውን መልእክት ለታፈነው የሮቤ ከተማ ህዝብ አደረሰ፡፡ በሁለት መኪና መጠነኛ ቅስቀሳ ካደረገ ከ 1፡00 ሰዓት በኋላ መኪናዎቹ ከነቀስቃሽ ቡድኑ ከነሀሴ 18/2005 እስከ እሁድ ነሀሴ 19/2005 ድረስ በታጣቂዎች ከቆሙበት አንዳይንቀሳቀሱ ታገቱ፡፡ የትራፊክ ፖሊሶችም መኪናዎቻችንን በማገት ያለቆቻቸውን ትዕዛዝ ተግባራዊ አደረጉ፡፡ በዚህ መሀል ነው በሽማግሌ ስም ያደራጃቸውን 15 የሚሆኑ የኦህዴድ ካድሬዎች ‹‹ነገ የሚከሰተው ደም መፋሰስ አሳስቦን ነው የመጣነው እናወያያችሁ›› በማለት ከምሽቱ 1፡30 ባረፍንበተ ሆቴል ተሰባስበው የመጡት፡፡ ለሀገር ሽማግሌ ክብር የሚሰጠው አንድነት ፓርቲ ሽማግሌዎች የተላኩበትን ዝርዝር መልእክት ካዳመጠ በኋላ የእሁዱን ሰላማዊ ሰልፍ በምንም ተአምር እንደማንሰርዘው፤ ይልቁንም የከተማው መስተዳድር ለፖሊስ የሀይል እርምጃ ውሰዱ ብሎ ያስተላለፈውን መመሪያ እንዲስብና ህገመንግስቱን እንዲያከብር ሽማግሌዎቹ ምክራቸውን ለገዢው ፓርቲ ባለ ስልጣኖች እንዲለግሱ መልእክት በመንገር ውይይቱ ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት ተጠናቀቀ፡፡ በኢህአድግ የተለመደ ቀመር የቅስቀሳ ጊዜያችንን በጉልበት እና በማስመሰል ለመስረቅ የተደረገውን የተለመደ ቅንብር አንድነት ፓርቲ ቀድሞ የሚያውቀው ጉዳይ በመሆኑ ሁለት ተደራዳሪዎችን ብቻ በመመደቡ ሌላው ግብረኃይል ሳይዘናጋ የቅስቀሳ ወረቀቱን በማሰራጨቱ ኢህአዴግ ያሰበውን አንድነትን የመነጠል ሴራ ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡
እነዚያው የሀገር ሽማግሌዎች የተባሉ ግለሰቦች ‹‹መስተዳድሩ አሁን ሊያነጋግራችሁ ዝግጁ ነው፡፡ ቢሮ ድረስ ኑ እና ተወያዩ›› በማለት በሰላማዊ ሰልፉ ቀን እሁድ ከጥዋቱ 1፡00 ሰዓት እኛን ቀጥረውን በሰዓቱ ስንደርስ የኦሆዴድ ባለስልጣኖች ግን የጠዋቱ የቅስቀሳ ስዓታችንን ለመስረቅ ከጠዋቱ 1፡40 በሁለት ኮብራ መኪና እና ታርጋ በሌላት በአንድ መኪና በደህንነት ባለ ስልጣኖች ታጅበው መጡ፡፡
ውይይቱ በዞኑ ም/አስተዳዳሪ አቶ ሰሎሞን አወያይነት የከተማው ከንቲባ፣ የኦሆዴድ ተጠሪ የኮምኒኬሽን ሀላፊ ሌሎችም ከ15 ያላነሱ ባለ ስልጣኖች እንዲሁም በርካታ የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት ሦስት የመንግስት ካሜራዎች ተጠምደው ውይይቱ ተጀመረ፡፡
የሽማግሌ ካባ የለበሱት የኦሆዴድ ካድሬ የሆኑት የሀገር ሽማግሌዎች ተወካይ ነኝ ያሉት ግለሰብ ውይይቱን በንግግር ሲጀምሩ ‹‹እናንተ የነፍጠኛን ስርዓት ልታመጡብን ነው፡፡ እኛን ሳታነጋግሩ ሳንፈቅድላችሁ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ እንዴት አሰባችሁ? አሁንም ይህንን ሰላማዊ ሰልፍ አታደርጓትም፡፡ የሮቤ ህዝብ እኛን ዎክሎናል መንግስት እንኳን ቢፈቅድላችሁ እኛ ሽማግሌዎች አይደረግም ብለናል አቁሙ›› በማለት የተጫኑትን ዉሳኔ በሚደንቅ ሁኔታ አስተላለፉ፡፡ በእዚያው መድረክ የኢህአዴግ/ኦህዴድ ማንነት እና ጭንብል ለዓለም ህዝብ ተጋለጠ፡፡ አንድነት ፓርቲም ይህንን ከላይ እስከታች ባሉ ባለስልጣኖች የተቀነባበረውን ድራማ በካሜራ ቀርፆ ያስቀረ በመሆኑ በእጃችን የሚገኘውን የውይይቱን ይዘት የያዘውን ቨድዮ እንድትመለከቱ በአክብሮት እየጋበዝን አንድነት ፓርቲ የኢህአዴግን እውነተኛ ገፅታ በመረጃ ማጋለጡን አጠናክሮ ዛሬም ነገም ይቀጥላል፡፡
በሮቤ ከተማ ለቅስቀሳ የተላከው ቡድን በመስተዳድሩ ባለስልጣናት ትእዛዝ ከምሽቱ 4፡00 ስዓት አልጋ ከያዙበት ታይታኒክ ሆቴል በግፍ ተባረው፤ የያዙትን ቦርሳ እንኳን ከመኝታ ክፍላችው ሳያወጡ በግፍ አውላላ ሜዳ ላይ ወንጀል እንዲፈፀምባቻው የከተማው መስተዳድር የፍፀመውን መንግስታዊ ውንብድና ፓርቲአችን በዝምታ የሚያልፈው ጉዳይ አይደለም፡፡ የመኪና ሹፊሮቻችንን በውድቅት ሌሊት ጭንብል ባጠለቁ ከ 20 በላይ ታጣቂዎችን በማሰማራት በማስወረር በጉልበት ክፍላቸው ውስጥ በመግባት ስለተፈፀመው ወንጀል አንድነት ፓርቲ በህግ የሚጠይቅ ሲሆን ታላቁ የሮቤ ከተማ ነዋሪ ህዝብ መብቱን ለማስከበር ያደረገውን ትንቅንቅ አንድነት ፓርቲ ከልብ ያደንቃል፡፡ ምስጋናውንም በእዚህ አጋጣሚ ያቀርባል፡፡
ድል ለታፈነው የኢትዮጵያ ህዝብ!!!
አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)UDJ

No comments:

Post a Comment