Tuesday, August 27, 2013

ጽንፈኞቹ (2)

ውድ አንባቢያን እንደተለመደው ዛሬም ወደዋናው ርዕሴ ከመግባቴ በፊት ትንሽ ስለ ጎንደር ስለ ጀግናው የአጼ ቴዎድሮስን ሀገር ትንሽ ልበላችሁ ጎንደር የነአጼ ፋሲልም ሀገር ነው። ዛሬ ትንሽ ስለጎርጎራ ልንገራችሁና ወደፊት ስለ ጎንደር ከተማ እናወጋለን፡፡ መኪናዎትን እያሽከረከሩ ጎንደር ሊደርሱ ጥቂት ሲቀርዎት የጎንደርን የአጼ ቴዎድሮስን አየር ማረፊያ አጥር እንደጨረሱ አዘዞ ከተማ ሳይገቡ ወደ ግራ ይታጠፋሉ። ከዚያም ቅድም ከበላይዎ የነበረው አየር ማረፊያ ከበታችዎ አርገው ዳገቱን እየገፉ የባህር ዳር ሌላኛው ገጽታ (the other face of Bahirdar) ወደ ጎርጎራ ያቀናሉ። ሁለት ኪ/ሜ የማትሞላውን ዳገት ከጨረሱ በሁዋላ ለጥ ያለውን የመኪና መንገድ ይዘው ቆላ ድባን ጯሂትን አልፈው ጎርጎራ ይገባሉ።

ጎርጎራ ጣና ሀይቅ ከአጠገቡዋ ተኝቶ ሲያዩት እና ከዚህ ከጣና ሀይቅ የሚመጣው ቀዝቃዛ አየር አጠገበዎ ዳረሶ ሲነካዎ ሲያስደስት ግሩም ነው። በዚህ በጎርጎራ ደርግ ሰርቶታል የሚባለው የመዝናኛ ቦታ በአሳዛኝ ሁኔታ አልጋዎቹ ፈራርሰው ሲያዩ በእጅጉ ያዝናሉ ያለቅሱማል። በጎርጎራ የመዝናኛ ቦታ በርካታ የስፖርት ሜዳዎች አሉ፡፡ ግራውንድ ቴኒስ፣ የቅርጫት ኩዋስ መጫዎቻ፣ የመረብ ኩዋስ መጨወቻ፣ የእጅ ኩዋስ መጫወቻና የመሳሰሉት ያሉ ሲሆን ግን ደርግ ስለሰራቸው ሊሆን ይችል የሆናል አገልግሎት ግን አይሰጡም፡፡ በአሁኑ ሰዓት የአያያዝ ጉድለት ችግር ቢኖርም ነገር ግን የግልና የጋራ የእንግዳ ማረፊያዎችም በጎርጎራ መዝናኛ ቦታ አሉ።
በዙሪያው ያለው ጥቅጥቅ ያለው ደን ከሚዛን ቦንጋና ቴፒ ጋር የሚያመሳስለው የጎርጎራ መዝናኛን ላየ ሰው አገራችንን አረንጉዋዴ ማድረግ እንደሚቻል አስተማሪ ነው። በዚያ ጭው ባለው ቆላ ምንም ዛፍ ከማይታይበት መንገድ እየነዱ ሄደው ጎርጎራ መዝናኛ ክበብ ከደኑ ሲገቡ ቅጽበታዊ ለውጥ (sudden change) ይሆንብዎታል። በዚህ በጎርጎራ የመዝናኛ ክበብ የሌለ የአበባና የዛፍ አይነት የለም። የተዋበው ጊቢ በእንክብካቤ ጉድለት ትንሽ ተጎሳቁሎአል። ብአዴን ለክልሉ በርካታ የቱሪስት መስህብ ያለውን ይህንን ቦታ ችላ ማለቱ የቆመለት ዓላማ ከሀገር እደገት አኳያ ቸለተኛ መሆኑን ላይ ያሳብቅበታል። የተሰራን ጠግኖና አስተከክሎ ከጥቅም ላይ ማዋል አዲስ ከመስራት ይቀላል። ብአዴን ይህንን ማድረግ ግን አልቻለም።

በዚህ በጎርጎራ መዝናኛ ቦሌ አየር ማረፊያን ሳይረግጡ የሚመጡ ቱሪስቶች አሉ። በግብጽና በሱዳን አድርገው በሞተርና በመኪና ሀገርን የሚጎበኙ ኦቨር ላንደሮች አዲሳባ ሳይደርሱ ግን ጎረጎራ ይገባሉ፡፡ እንዚ መንገደኞች አርፈው ዶላራቸውን ትተው የሚሄዱበት መዝናኛና መስተንግዶ ደግሞ ያስፈልጋል። የጣና ሀይቅ በጎርጎራ በኩል ገና ምንም አልተሰራበትም። ደቡብ አፍሪካና ኬኒያ ሞምባሳ የህንድ ውቅያኖስን ጠርዝ በሙሉ ሎጅ ሰርተው ተጠቅመውበታል። እኛ የበሬ ግንባር የምታክለውን ጣና ሀይቅ ገና አልተጠቅምንባትም። በዚህም ሀገራችን ማግኘት ያለባትን ዶላር ማግኘት አልቻለችም። 

የጣና ሀይቅ ከጎጃም ይልቅ ሰፊው ቦታ ያለው ጎንደር ነው። በአንገታቸው የመስቀል ምልክትና ጥቁር ማተብ የሚያንጠለጥሉት ጎንደሮች ኩሩነታቸውና ታማኝነታቸው ከፊታቸው ይነበባል። ሁሉንም እንግዳ የማክበር ባህል ያላቸው ጎንደሮች እነሱ ቢያበሉ እንጂ ሄደው የመብላት ፍላጎቱ የላቸውም። ጎንደሮች ቆንጆዎች ኩሩና ግድርድሮች ናቸው።በርካታ ታሪካዊ ቦታዎች ያሉዋት ጎንደር ከታሪካዊ ቦታዋ ማግኘት የሚገባትን ገቢ አግኝታለች የሚል እምነቱ የለኝም። 

በበርካታ የአማራ ክልሎች የሚታየው ችግር በጎንደር ቆላድባና አካበቢዋም ይታያል። የካድሬዎቹ የበላይ ነኝ ባይነት ጽንፍ መያዝ ከካድሬው አመለካከት ውጭ ያሉትን ማግለል የእኛ አይደሉም ማለትና እንደበዳይ ማየት በብአዴን ካድሬዎች ዘንድ የሚታይ ሲሆን በሽተኞችን ወደክሊኒክ በአልጋ ተሸክሞ መሔድና የትራንስፖርት ችግሩ በጎንደር ይታያል። ሌላው በጎንደሮች ዘንድ አበረታች ያለው ባህል በሙስሊሙና በክርስቲያኑ ዘንድ ያለው ተፋቅሮና ተከባብሮ የመኖር ባህሉ በእጅጉ አስደሳች ነው። እኔ በዚያ በነበርኩበት ጊዜ በጎርጎራ መዝናኛ ግቢ ውስጥ አንድ ሰርግ ነበር። የዚያን ቀን አይቻቸው ያማላውቀው የወጥ ቤት ሰራትኞች መጡ ነገሩን በጥሞና እከታተል ነበር፡፡ እንግዶቹ የመጡት ከድርጅቱ ውጭ ሲሆን የሚያገባው ሙስሊም ስለነበረ ለሙሽሮቹና ለሙስሊም አጃባዎች የሙስሊም ምግብ ለማዘጋጀት የመጡ ሙስሊሞች ናቸው።

ምግቡ በየፈርጁ ከተዘጋጀ በኋላ ሙሽሮቹ መጡ በዚህም የተዘጋጀው ምግብ ቀረበ ከሙሽራው ሚዜዎች ውስጥ አንድ ሙስሊምና ሁለት ክርስቲያኖች አሉ የያዙትን የየሀይማኖቱን ምግብ ለራሳቸው እየበሉ ከባለ ሀይማኖቱ ምግብ ሳህን ላይ ለባለቤቱ ያጎርሳሉ። የሀይማኖት ልዩነት ያልፈታው ፍቅር ይገርማል። ፍቅር ሁሉን እንደሚያደርግ ያይሁት ያን ቀን ነው። ምክንያቱም በእጁ የክርስቲያን ምግብ ከክርስቲያኑ ሳህን አንስቶ ለክርስቲያን ጉዋደኛው ያጎረሰው ሰው እጄን ልታጠብ የክርስቲያን ስጋ በነካ እጄ ለራሴ አልጎርስም ሳይል የራሱን ምግብ ደግሞ በዚያው እጁ አንስቶ ይበላል። አብሮ ላለመብላት ያልቻሉት በሀገራችን ባለው ባህል ገደብ ብቻ ይመስለኛል። እኔን የሚገርመኝ ይህ የሙስሊም የክርስቲያን የሚባል የተለየ ምግብ ያለው ሀገራችን ብቻ መሆኑ አስገራሚ ነው። የሙስሊም መዲና ነን የሚሉት የአረብ ሀገራት የፍየልና የበግ ስጋ ተዘጋጅቶ የሚሄደው ከሀገራችን ነው። በተቻለው ሁሉ እኛን ለመለያየት ስለሚፈለግ እንጂ የመግብ ለዩነት ቢኖርማ መች ክረሰቲያን ካቋቋማው ቄራ የታረደ ሥጋ አረብ ይገባ ነበር፡፡ ዋናው የወዳጆቻችን ተግባር በተቻለው ሁሉ በጽንፍ እንድንለያይ ማድረግ ነው።

የሀይማኖት ጽንፍ

ባለፈው ሳምንት ስለጽንፍ ለመነጋገር የሞከርን ሲሆን በዚህ ጽንፍ በመንግስት በአንዳንድ ጋዜጠኞችንና በአንዳንድ ዲየስፖራዎች እያስከተለ የለውን መዘዝ ለማየት ሞክረናል። ጽንፍ ወይም አንድ ጥግ መያዝ በሀይመኖትና በፖለቲካ መሪዎች ዘንድ ይስትዋላል።

በየትኛውም መመዘኛ የትኛውም ሀይማኖት የሚያስተምረው ፍቅርን ነው። በዚህ በሀይማኖት ዙሪያ የሚያዙ ሌላው ጫፎች የሚመጡት የኔ ሀይማኖት ከአንተ ይበልጣል፡፡ በሚሉ ካልተሻለ አስተሳሰብ የሚመንጭ ሲሆን ይህኛው መዘዙ ከባድና ሀገርና ህዝብን ለከፍተኛ ዕልቂት የሚዳርግ ነው። የቅኝ ገዥዎች አፍሪካን ለመበተታንም ይሁን ዝም ብለው እንዲገዙ ለማድረግ ይህንኛውን አማራጭ ይጠቀማሉ። ሀይማኖትን በተመለከተ በተለይ የህይማኖት መምህራን የተሻለ ፍቅር አዘል ትምትህርት ለተከታዮቻቸው ያስተምሩ ዘንድ ግድ ነው። ሀይማኖተኛው በሀይማኖቱ ለሚመጣ ነገር በሞት ጽድቅን እንደሚቀበል ስለሚገነዘብ ሀይማኖት ላይ ጥንቃቄ ይደረግ ዘንድ ግድ ይላል።

በመጀመሪያው ክ/ዘመን የክርስቶስ ተከታዮች ሀይመኖታቸውን እንዲተው የሮማ ነገስተታት የተለያየ ዘዴን ለመጠቀም ቢሞክሩም እነርሱ ባሰቡት ክርስቲያኖች ሀይማኖታቸውን ከመተው ይልቅ ፈጽሞ የበለጠ ሀይማኖቱ ተስፋፋ እንጂ እንዲዳደክም ማድረግ አልቻሉም። ለአንበሳ ቢሰጡዋቸው በእሳት ቢያቃጥሉአቸው አንዱ ሲሞት ሌለው እየተተካ ከፍተኛ እልቂት ደርሶ እንደነበረ ይታወቃል። በሀገረችን በኢትዮጵየም አጼ ሱስኒዮስ ካቶሊክን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሀይመኖት እንዲሆን ባወጁ ወቅት ግጭት ተቀስቅሶ እጅግ በርካታ ህዝብ በግጭቱ እንዳለቀ ታሪክ ያትታል።

ቅኝ ገዥዎች እኛን ለመከፋፈል ይህችኛዋን መንገድ በተደጋጋሚ ተጠቅመውባታል። አሁንም እየተጠቀሙበት ይገኛል። ሲቻላቸው እንድንጋጭ ሳይቻላቸው ተከፋፍለን እየተከራከርን ስራ ሳንሰራ ጊዜ እንድናሳልፍ በርካታ ጊዜ እነርሱ የማያውቁትን እኛ እንድናምነው በማድረግ ብዙ ፈተና እምጥተውብን ያውቃሉ። ለምሳሌ የጎጃሙን ቅባትና ጸጋ የፈጠረውና በርካታና ምስኪን የጎጃም ገበሬ እርስ በርሱ እንዲተላለቅበት የሆነውን ቅባትና ጸጋን ለሁለት ምስኪን ገበሬዎች እንዱን ሀይማኖት ለያይቶ ያስተማራውና የመለያያ ሀሳቡን የፈጠረው አንድ አውሮፓዊ ዜጋ ነው።

የሀይማኖት ጽንፍ በተመሳሳይ ሀይመኖትም ይሁን በተለያየ ሀይመኖት ሊከሰት ይችላል። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስን ሰው ሁሉ እንደተረዳው አረደድ ሊረዳው ይችላል። የተማረው ሁሉ እኩል ይረዳል ማለት አይደልም። ስለዚህ በአንድ መምህር ስለትማሩ እኩል እውቀት ሊኖር አይችልም። በዚህም ብእንድ ክፍል በአንድ አስተማሪ ተምረው ሁሉም ተመሪ አንዳይነት ፈተና ተፈትነው እኩል ውጤት አለማምጣት አንዱ ምሳሌ ነው። አንዱ በራሱ በተረዳው መልኩ ስለተረዳ የተሻል ዕውቀት እንደሌለው ያነሰ አመለካከት አልው ብሎ መገመት ትክክል አይደለም። የኔ ካንተ የተሻለ ነው ብሎ ለመፍረድ ሚዛኑ ምንድን ነው? የሚለካው እና አንዱ ካንዱ ለመብለጡ ማስረጃው ምንሊሆን ይችላል። በዚህ ረገድ አንድ ምሳሌ ማቅረብ ይቻላል። ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ እጅግ በርካታ ሰዎች ከዋለበት እየዋሉ ካደረበት እያደሩ የተማሩ ቢሆንም ሁሉም የትምህርቱ ተጠቃሚ መሆን ግን አልቻሉም። አንዳንዶቹ እንደውም ምንም የገንዘብ ያዥ ሆነው ቢሾሙም ቅሉ መምህራቸውን አሳልፎ በመሸጥ የመጀመሪያ ሆነዋል። ክፉ ላደረጉባችሁ ደግ መልሱ ሲባሉ የነበሩትም በሰይፍ የጠላታቸውን ጆሮ እስከመቁረጥ ደርሰዋል። በየትኘውም ሚዛን ሀይማኖትን በተመለከተ አንዱ ሀይማኖት ከአንዱ እንደሚበልጥ አድርጎ ለማሳመን አይቻልም። ሁሉም የሚየምነው ለእርሱ የበላይ ነው። የኔ ካንተ ይበልጣልና የኔን ተከተል ብሎ ማስገደድ ትርፉ ግጭትና ግጭት ብቻ ነው።

በዚህ በሀይማኖት በኩል በርካታ ጽንፍ የሚፈጥሩ ጉዳዮች አሉ። አንዳንዶች የንግድ ድርጅታቸውን የሀይማኖት ተከታያቸው እንዲሆን ሲያደርጉ በንግድ ድርጅታቸው የሚጠቀሙ ደንበኞችም የእምነታቸውን ህግ እንዲከተሉ ይፈልጋሉ። ይህንን የማያደርግ ተስተናገጅ በንግድ ድርጅታቸው ውስጥ የሚፈልገውን አግልግሎት እንዳያገኝ ሲደረግ ይታያል። በዚህም ሁሉም ደምበኛ እነርሱ ለሚከተሉት እምነት ህግ ተገዢ እንዲሆን ይፈልጋሉ። በዚህም የሀገሪቱን የንግድ ህግ ጥሰው ከሆነ እንኩዋን ጠያቂ የለም። በአንዳንድ ቦታ ከባለቤቱ ጋር ወደዚያ ክልል ቢሄድ አልጋ ተከራይቶ ለማደር የሰመኒያ ወረቀት ወይም የጋብቻ ሰርተፍኬት ካልያዘ የማይታደርበት ቦታ አለ። በሌላ መልኩ ሶስት ኮከብ ሆቴል ከፍቶ አንድ ሳጥን ቢራ በሆቴሉ እንዳይገባ የሚከለክል ባለ ሆቴል አለ። ሌላው ደግሞ በሆቴሉ ውስጥ እርሱ የሚከተለው ሀይማኖትን የሚያነጸባርቅ ነገር ይከፍታል። ምሳሌ ሙስሊም ከሆነ መንዙማ ወይም ቁርዓን ሲያስቀራ ክርስቲያን ከሆነ ደግሞ መዝሙር ይከፍታል። ይህ ዓይነቱ ከቁጥጥር ማነስና ክግንዛቤ እጥረት የሚመጣ ጽንፈኝነት መጨረሻው አስቸጋሪ ነው። አንድ ሰው የከፈተው ሆቴልም ይሁን የከፈተው ሱቅ፣ ሱፐር ማርኬት፣ እንዲሁም ይህዝብ አገልግሎት ስጪ ምኪና የሾፌሩ ወይም መኪናውን የገዛው ግለሰብ ሳይሆን የሚገለገልበት ህዝብ ነው። የተገልጋይ እንጂ የእርሱ አይደለም። በሰው ቤት ደግሞ አንድ ቤቱ ያልሆነ ሰው ሊያዝበት አይችልም። ሁለት ነገር መውደድ ደግሞ አይቻልም። ንግድና ሀይማኖት ክርስቶስ ሲያስተምር አንድ ሰው ለሁለት ጌታ አይገዛም ይላል። ለገንዘብና ለአምላኩ።

አሁን አሁን ሁኔታውች ግር ማሰኘት ጀምረዋል። በርካታ ሰዎች በሚቻልበት ሁኔታ በተለይ ታክሲዎች እና የህዝብ አገልግሎት ሰጪ ትራንስፖፕርት ላይ የተለያዩ የራሳቸውን ህይማኖት የሚገልጽ ጽሁፍ ይለጥፋሉ በዚህ በኩል እነርሱ በሚያምኑት የማያምን ሰው ደስተኛ ላይሆንበት ይችላል። አንዚህን የግል ሀይማኖት የሚገልጹ የሁሉም እኩል ያልሆኑ ጽሁፎች ቅዱሳን ጽዕሎች የሚዘጋጁት ደግሞ ለንግድ ለትርፍ እንጂ በቅዱሳን በጸሎት የተዝጋጁ አይደሉም። አንዳንዶቹ የቤተክርስቲያንንም ይሁን የሌላውን ሀይማኖት ትውፊት የጠበቁ አይደሉም። በዚህም አንዳንዶቹ ለትርፍ ያዘጋጃሉ አንደንዶች በየዋህነት ይለጥፋሉ በዚህም ሌሎች ይበሳጫሉ ጽንፍም ይይዛሉ።

እኔ በእንድ ወቅት ቻይና ሂጄ በነበርኩበትጊዜ በሀገራችን በየመኪናው ላይ የሚለጠፉ የቅዱሳን ስዕሎች፣ የሚለጠፉ ቅዱሳን ጥቅሶች በቁርዓንና በአማርኛ የሚሰሩት በቻይና ሀገር ባለ አንድ የህትመት ድርጅት ነው። እኔ ያየሁትን ነው። ሌላም ሊኖር ይችላል። በዚህ ቦታ የሚለጠፉ ስዕሎችን የሚያሰሩት የየዕምነቱ ተከታዮች አለመሆን ደግሞ ግርምትን ይፈጥራል። እኔ በነበርኩበት አንዱ ከቅዱስ ቁርዓን የተጠውጣጡ ጥቅሶችን የሚያሰራ ሲሆን ልጁ በእምነቱ ደግሞ ክርስቲያን ነበር። ዋናው ቁም ነገር ማንም ምንም ሊያሰራ ይችላል። ያመነበትን ለራሱ ለሚያምነው ማዋል ሲገበው በሌላው ላይ ተጽዕኖ ማሳደሪያ መሆን ግን የለበትም። በተለይ በህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ በአጠቃላይ የህዝብ አገልግሎት መስጫ በሆኑ ተቁዋማት ላይ እንደ ኢትዮጵያ ባለችና የበርካታ ብሔርና እምነት ባለባት ሀገር የአንዱን ብቻ ለማንጸባረቅ መሞከር አደጋው የከፋ ነው።

የሀይማኖትን ጽንፍ ስንስመለከት በተመሳሳይ ሀይማኖት የሚከሰቱ ጽንፎች አሉ። በክርስቲያንም ይሁን በእስልምናው እንዲሁም በሌሎች እምነቶች ዘንድ በተመሳሳይ ሀይማኖቶች የሚከሰቱ ልዩነቶች በቀጥታ ወደ ጽንፍ ወይም ሌላኛው ጫፍ መፈጠር ይሄዳሉ። ለዚህ ጽንፍ መፈጠር ደግሞ የየግለስቡ የራሱን እምነት የተረዳበት አንዱ ምክንያት ሲሆን ሌላኛው ከሌላ አካባቢ የሚመጡ ረጃጅም እጆች ሁለተኛው ምክንያት ነው። በዚህ ረገድ ማንም ለራሱ በተረዳው አረዳድ ሀይማኖቱን ማስፋፋት ይችላል። ለራሱ ለሚከተለውና የግሉ በሆነው ሀይማኖት ከሌላ በኩል የሚመጣ ተጽእኖ ሊኖርበት አይገባም። አንድ ሰው ለራሱ ለሚድንበትም ይሁን ለሚኮነንበት የሌላው ተፅዕኖ ለምን አስፈለገ የሚለውን ሁሉም ሊያጤነው ይገባል።

በዚህ ረገድ የክርስትና ዕምነት እንከተላለን ለሚሉት ክርስቶስ በዚህ ምድር ተመላልሶ ባስተማረበት ጊዜ ማንንም ማስገደድ አልፈለገም የፈቀደ እንዲከተለው ሲመክር የወደደኝ እናቱን አባቱን እህት ወንድሞቹን ትቶ ይምጣ ነው ያለው ሁሉንም ሰብስቦ መጥቶ ተከታይ ይብዛልኝ አላለም። ምክንያቱም ተከታይ ለማብዛት የሚደረጉ ሂደቶች ጥፋትን ያመጣሉና ነው። ዘመድ አዝማድ ይዘህ ና ቢል ኖሮ ና አልመጣም ላይ ግብግብና ግጭት ይፈጠር ነበር። በጸብና በጉልበት የተፈጠረ ነግር ደግሞ ረዥም ጊዜ አይኖርም እድሜ የለውም። ስለዚህ ሁሉም ነገር በፍቅርና በፍላጎት እንዲሆን አስተማረ የወደዱት ተከትሉት። አሁን ያለው የማሳመን ሁኔታ ስንመለከተው የኔ ብቻ ትክክል ስለሆነ እኔን ተከተል የሚል ጽንፍ ይዞ መሄድን አንዳንድ ሰዎች እንደሥራ ተያይዘውት ሲታይ የወደፊቱን ተቻችሎ የመኖር ሁኔታ አደጋ ላይ ይጥለዋል የሚል ስጋት አለ። 

በእስልምናውም በኩል በመጀመሪያ ነብዩ መሐመድ አንድ ሀይማኖት እንዳስተማሩ ይገባኛል። የሰዎች አረደድ ግን አንድምታን ሊፈጥር ይችላል። ነቢዩ መሐመድ ይህንን የተናገሩት ይህን ለማለት ፈልገው ነው በሚል ይተረጉሙታል። በዚህም ሰው ለራሱ በተረዳው አረዳድ የመረዳት መብቱ ሊጠበቅለት ይገባል። ይህንን የቁርዓንም ይሁን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በተመለከተ የእኔ ትክክል ስለሆነ የእኔን ብቻ ተከተሉ ብሎ ተጽዕኖ ከመፍጠር ሰው እንደተረዳው እንዲያምን ቢተው የተሻለ ነው የሚል እምነት አለኝ። በዚህ በሀገራችን በተለይ በአፍሪካ ልዩነት የሚፈጥሩ የሀይማኖት ክርክሮች መነሻቸውን ማወቁ ተገቢ ይመስለኛል። ለምሳሌ በሀገራችን በቅርቡ የተፈጠረው የህይማኖት ልዩነት አነድ ዓይነት ሀይማኖት ያላቸውን ሰዎች በሁለት ዓመለካከት ከፍሎ ይገኛል።

ይህንን ሁኔታ ስንስመለከትና የኢራንን የሰሞኑን መግለጫ ስናዳምጥ በሀገራችን ምን እየተሰራ ሌሎች ምን እየሰሩ ነው ብለን ሁኔታውን እንድናጤን ሊያደርገን ይችላል። ከዚህ ቀደም ኢራን ስለኒኩሌር ማብለያ ጣቢያ ሲነሰባት አይኔን ግንባር ያድርገው ስትል እንደነበረ የሚታወቅ ሲሆን ዛሬ ላይ ግን ለሀይል ማመንጫየ ይሆነኝ ዘንድ እየተጠቀምኩ ነው የሚል መልስ እየሰጠች ሲሆን ከዚያም ባለፈ ብሔድ ማንም ሊገደው እይችልም። መንም ሊጠይቀኝም አይገባም በማለት የመለሰች ሲሆን በቅርቡ የሰራችው ምድር ለምድር የሚምዘገዘግ ሚሳኤል በእስራኤልና በአሜሪካን ላይ ከፍተኛ የሆነ ስጋትን ፈጥሮአል። ከዚህም በመቀጠል ኢራን ከጥቂት ቀናት በሁዋላ የኒኩሌር ባለቤት እንደምትሆንና የዓለም ስድስተኛ ሀገር ለመሆን እየተቃረበች ትገኛለች። ይህንን የኣለም ሀገራት አየሰሩ ያሉትን ሥራ ስንመለከትና 

ይህ የዓለም ነባራዊን ሁኔታ ተመልክተን አንዳንዶች ጽንፍ ይዘው እያደረጉ ያለውን ሁኔታ ስንገመግመው አረቦችም ይሁኑ አውሮፓዊያን ለእኛ እርስበርስ የምንገዳደርበትን አንዳችን በእንዳችን ላይ ጽንፍ ይዘን የማንቀራረብበትን የቤት ሥራ እየሰጡ ለራሳቸው በታላላቆቹ ሀገር ተርታ ለመሰለፍ እያደረጉት ያለውን ሁኔታ መመልከትን ተገቢም ጠቃሚም ነው። ለእኛ ለኢትይጵያውያን ከራሳችን ከወገናችን በቀር ማንም አይጠቅመንም። የሙስሊሙን ሀገር መካከለኛው ምስራቅን ብንመለከት ለቤት ሰራተኛነት የሄዱ ሙስሊም ልጆቻችን ከፎቅ የሚወረወሩባት በፈላ ዉሃ የሚገሽሩባት ሀገር ነች። ለእኛ የሚጠቅሙን ቢሆኑ ኖሮ በሀገራቸው ስንሄድ ተንከባክበው ያኖሩን ነበር። ግን እኛ እንዳናድግ የቤት ሥራ ከመስጠት የዘለለ አንዳች ጥቅም የሚሰጡን ነገር የለም። በሌላ በኩል አብዛኛው ክርስቲያን ይበዛበታል የሚባለው አውሮፓ ከሀገራችን የሚሄዱ ክርስቲያኖች ከተቀመጡበት እንዳይቀመቱ የሚደረግበት ሁኔታ የቆዳችን ቀለም መልቀቅ አለመልቀቁን በጣት አሸት አሽት የሚደረግበት ሀገር መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው።

ልጅም ይሁን ጎረቤት የሚወደደው የሚፈራው፣ የሚከበረው ራሱን ሲችል አቅም ሲኖረው ነው። አቅም የሚኖረው ደግሞ በመካከል ያለን ጽንፍ ማስወገድ ሲቻል ነው። አምባ ገነን መሪዎችን አስወግዶ ዴሞክራሲያዊ መሪዎችን መፍጠር የሚቻለው በመካከል ያለን ጽንፍ አስወግዶ አንድ ምሆን ሲቻል ነው። ሁሉም በራሱ መንገድ የሚሄድ ከሆነና የተለያየ አመለካከት ካለ እርስ በእርስ መተማመን ስለማይኖር ለውጥ ሊመጣ አይችልም። በዚህ ከራሱ ከህዝቡ ይልቅ ገዥዎች ይጠቀማሉ። ምክንያቱም ይህንን ሰው የራሱን ጽንፍ መያዝን እያሳዩ እገሌ ቢሆን እነገሌን እይወድም። እገሌ ቢሆን እነእገሌን ያጠፋል እያሉ ስለሚያፈርሱበት አብሮ እየታገለ የማይተማመን ህዝብ እንዲፈጠር ያደርጋሉ። ይህንን በመጠቀም ሀይማኖቶች የተለያዩ ጽንፎች በሌላው ላይ መያዝና በራሱ በውስጥ በአይዶሎጂ መከፋፈል ጽንፍ ለሀገርና ለወገን ፈጽሞ ጥቅም የለውም። ይልቁንም ወንድማመች የሆኑት እምነቶች ግን እርስ በርስ እንዳይተማመኑ ግን ያደርጋል። በሚቀጥለው የብሔር ጽንፍ ችግሩንና መዘዙን እናያለን ቸር ይግጠመ

No comments:

Post a Comment