በፍቅር ለይኩን
በአንድ ወቅት በደቡብ አፍሪካዊቷ ከተማ በኬፕታውን የሚኖር አንድ በንግድ ሥራ የሚተዳደር ኢትዮጵያዊ ጎልማሳ አንድ አሳዛኝ ገጠመኙን እንዲህ አጫውቶኝ ነበር፡፡ ይህን ታሪኩን ያካፈለኝ ኢትዮጵያዊ ጎልማሳ የሥራ ቦታው ላይ ከአንድ ከኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ጋር በተነሳ ጠብ በተፈጠረ ግጭት የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ የሆነው ጓደኛውን አንድ የፊቱን ጥርሱን በቦክስ ያወልቀዋል፡፡ የጥርሱን መውለቅ የሰሙ የዚህ ሰው ጓደኞችም ተሰባስበው ይህን ሰው ካልገደልን በማለት ሲጋበዙ ነገሩ በሰላም ያልቅ ዘንድ አንዳንድ የሚያውቋቸው ሰዎች ለሽምግልና ጣልቃ ይገባሉ፡፡
በሽምግልና ድርድር ላይ እያሉም የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ የሆነው ጓደኛውን ጥርስ ያወለቀው ሰው የአያቱ ስም የኦሮሞ ስም ሆኖ ይገኛል፡፡ እነዛም በእንዴት ተደፍረን፣ ይህን ሰው ካልገደልን በማለት ሲዝቱ የነበሩ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችም፣ ይኽ ሰው ለካ ወገናችን ነው በማለት ለበቀል ያነሱትን ሰይፋቸውን ወደ ሰገባው ይመልሳሉ፡፡
ሐሳባቸውን በመቀየር ጉዳዩ በሰላም ተቋጭቶ፣ በሃያ ሺሕ የደቡብ አፍሪካ ራንድ ካሳ ክፍያ እንዲጠናቀቅ ተስማምተው እርቅ ማውረዳቸውንና አያቴ ስም የኦሮሞ ስም በመሆኑ ከጉድ ወጣሁ ሲል በግርምት መንፈስ ሆኖ ገጠመኙን አጫወተኝ፡፡
ይህ ሰው እስከዛች ቀን ድረስ ስለ አያቱ ኦሮሞነትም ሆነ ስለመጣበት ብሔር ወይም ጎሳና ማንነት በቅጡ አስቦ ወይም ትዝ ብሎት እንደማያውቅና ይህ ገጠመኙ ግን ከሚኮራበት ከኢትዮጵያዊነት ማንነቱ ባሻገርም ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ ስለሰኟት ሕዝቦቿ ታሪክ፣ ባህል፣ ማንነትና ቅርስ ለማጥናት የማንቂያ ደወል ሆነኝ ሲል ነግሮኛል፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ሰው በተለያዩ ጊዜያት ወደ ደቡብ አፍሪካ በስደት የገቡና ኖሮአቸውን በዛው ያደረጉ የኦሮሞ ተወላጆች ለደቡብ አፍሪካ መንግሥት የፖለቲካ ጥገኝነት ጥያቄ በሚያቀርቡበት ወቅት የተፈጠረውን እሰጥ አገባም እንዲህ ጨምሮ ተርኮልኛል፡፡
የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ሆኑ ስደተኞች ለፖለቲካ ጥገኝነት ብቁ የሚያደርጋቸውን ቅፅ በሚሞሉበት አጋጣሚ አብዛኛው የኦሮሞ ተወላጆች ዜግነት ወይም አገር በሚለው ክፍት ቦታ ላይ ‹‹ኦሮሚያ›› በማለት በመሙላታቸው የደቡብ አፍሪካ ‹‹ሆም አፌር ቢሮ›› የሥራ ባልደረቦች እኛ ‹‹ኦሮሚያ›› የሚባል አገር አናውቅም በማለታቸው በተነሳ ክርክር፣ እነዚህ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ የሆኑ የፖለቲካ ጥገኝነት ፈላጊዎች፣ ‹‹ኦሮሚያ በቀድሞዋ አቢሲኒያ በአሁኗ ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ስር ምትማቅቅ አገር ናት፡፡›› በማለት በማስረዳት ዜግነት በሚለው ክፍት ቦታ ላይ ‹‹ኦሮሚያ›› የሚለው ማንነታቸው እንዲሞላላቸው ቢጠይቁም ተቀባይነት በማጣታቸው እየጎመዘዛቸው ቢሆንም የማያምኑበትን የኢትዮጵያዊ ዜግነት በክፍት ቦታው ላይ ይሞሉ እንደነበር ይህ ሰው ጨምሮ ነግሮኛል፡፡
ይህንና ይህን የመሳሰሉ ብሔርን ማእከል ያደረጉ አሳዛኝ ገጠመኞች በኢትዮጵያም ሆነ በውጭ አገር ተደጋግመው የሚከሰቱ መሆናቸው ደጋግምን ያየነውና የሰማነው እውነታ ነው፡፡ በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ በአውስትራሊያና በደቡብ አፍሪካ ዛሬ ዛሬ በትግሬ፣ በአማራ፣ በኦሮሞ … ወዘተ ስምና ማንነት የራሳቸውን ወሰን ወስነውና አጥር ከልልው የሚኖሩና ይህና ያ ብሔር በእኔና በዚህ ብሔር ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው በደል፣ ግፍና ጭቆና አድርሶብናል በሚል የየራሳቸውን የጭቆና ታሪክና የተጋድሎ ገድል ጽፈውና አጽፈው ያሉ፣ ከዚህም የተነሳ ደግሞ ለበቀል የሚፈላለጉና በጎሪጥ የሚተያዩ ሕዝቦች ኢትዮጵያ በምትባለው ምድር ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው፡፡
ይህን ከላይ በመግቢያችን የገለጽኩትን አሳዛኝ ገጠመኝ ወይም ታሪክ ለዚህ ጹሑፍ መግቢያ ይሆነኝ ዘንድ የመረጥኩት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ስለ ኢትዮጵያዊነትና ኦሮሙማ (ኦሮሞ ናሽናሊዝም) በተመለከተ ‹‹በገዳ ዶት ኮም›› እና በሌሎች በተለያዩ ድረ ገጾች ሰፋ ያለ ውይይትና ክርክር ተደርጎ ነበር፡፡ በዚህ ከስምንት የማያንሱ ማእከላቸውን አውሮፓና አሜሪካ ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና የኦሮሞ ምሁራን ባደረጉት ውይይትና ክርክር ከተሳተፉት ፖለቲከኞችና የኦሮሞ ምሁራን መካከል ዶ/ር በያን አሶቦና ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ይኸው የኢትዮጵያዊነትና የኦሮሙማ ሙግትም የፓል ቶክ ዋና የመወያያ ርዕስ ሆኖ ነበር፡፡ ይህ ውይይትና ክርክር ገና ሳይበርድና ሳይቋጭ ነበር በዛው ሰሞን ወጣቱ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና ተንታኝ ጃዋር ሙሐመድ ከአልጄዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ ለዓመታት በዘለቀው የኦሮሞ ጥያቄ፣ የነፃነት ትግል ታሪክ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ትንታኔ የሰጠው፡፡ ጃዋር I am First Oromo. Ethiopia is imposed on me የሚለው አቋሙን ግልጽ ካደረገ በኋላ የኦሮሞን ታሪክና የኦሮሞን የዓመታት ጥያቄ በተመለከተ የፖለቲካ ተንታኙን የጃዋርን ትንታኔና አቋም በመቃወምም ይሁን በመደገፍ የተለያዩ ሐሳቦች መንሸራሸር ጀመሩ፣ አሁንም ድረስም እየተንሸራሸሩ ነው፡፡
ባለፉት ሰሞናትም በተለያዩ በይነ መረቦችና በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይም የጃዋርን ሐሳብ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች በየበኩላቸው አቋማቸውን ለመግለጽ ሞክረዋል፡፡ አንዳንዶችም ስድብ ቀረሽ በሚመስል ጨዋነትና ቅንነት በጎደለው መንፈስ ጃዋር ባነሳው ሐሳብ ላይ የውይይት መድረኩን የሚያጠለሹና የሚበርዙ እሳቤዎችን ከስድብ፣ ከዛቻና ከማስፈራሪያ ጭምር ሲያዘንቡም ታዝበናል፡፡ ከዚህ ውጪ ደግሞ ሰብአዊ ፍቅር፣ ጨዋነትና ቅንነት በተሞላበት መንፈስ ከኦሮሞም ይሁን ከሌላ ብሔር ተወላጆች ዘንድ፣ ሚዛናዊ የሆነ፣ ከጭፍን ጥላቻና ከበቀል ስሜት በጸዳ መንፈስ ሐሳባቸውንና አቋማቸው የገለጹም ጥቂት ጸሐፊዎችና ተንታኞችም ብቅ ብቅ ብለው ነበር፡፡
እኔም በዚሁ ሰሞነኛ በሆነው የኦሮሞ ሕዝብን ታሪክና ጥያቄ በተመለከተ ለኦሮሞ ሕዝብ ነፃነትና መብት ቆመናል በሚሉ አንዳንድ የኦሮሞ ምሁራንና ፖለቲከኞች ዘንድ በኦሮሙማ (በኦሮሞ ናሽናሊዝም)፣ በኢትዮጵያ ታሪክና በኢትዮጵያዊነት ላይ በሚያነሷቸው አንኳር ሐሳቦችና በሚያራመዱት አቋሞቻቸው ዙሪያ ላይ ጥቂት የመወያያ ሐሳቦችን ለማጫር ወደድኩ፡፡
በእርግጥ ይህ ለውይይት ማጫሪያ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ አጭር ጽሑፍ የኦሮሞ ተወላጅ ምሁራንና ፖለቲከኞችን፣ አሊያም ደግሞ በኦሮሞ ሕዝብ ስም ተቋቋመው እየተንቀሳቀሱ ያሉ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ታሪክና በኢትዮጵያዊነት ላይ ያላቸውን አቋማቸውንና ለኦሮሞ ሕዝብ አለን ስለሚሉት የትግል አቅጣጫዎቻቸውን ለመተንተን፣ ለመተቸትና ለመገምገም አይደለም አነሳሱ፡፡ ይህን ለማድረግ እንሞክር ቢባል እንኳን በእነዚህ ጥቂት ገጾች ለመሞከር የሚታሰብ አይሆንም፡፡
ለዚህም እንደ ዋና ሆነው ከሚነሱት ዐበይት ምክንያቶች መካከል ደግሞ በኦሮሞ ሕዝብ ስም እየተንቀሳቀሱ ያሉ በዓላማም በአቋምም የተለያዩ ፓርቲዎች መኖራቸው፡፡ እንዲሁም እነዚሁ ፓርቲዎችም የኦሮሞን ሕዝብን ታሪክና ጥያቄ በተመለከተ የሚያራምዷቸው አቋሞችና ጥያቄዎች ‹‹ከባርነት ወይም ነፃነት›› ወይም ደግሞ ‹‹ከአቢሲኒያ/ከዛሬዋ ኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ነፃ የመውጣት ጥያቄ ነው፡፡›› ከሚለው ፖለቲካዊ አቋም አንስቶ በተለያዩ የኦሮሞ ተወላጅ ምሁራንና ፖለቲከኞች ዘንድ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች ባሉ የኦሮሞ ሕዝብ ታሪክ፣ ባህል፣ እምነትና ቅርስ አኳያ ያሉት አመለካከቶችና ትንታኔዎች መንገዳቸው የየቅል መሆኑን ነገርዬውን ቀላል አያደርገውም ብዬ ስለምገምት ነው፡፡
ለአብነትም ያህል የኦሮሞን ብሔርተኝነት በእጅጉ ያራምዱና ‹‹የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ የነጻነት ጥያቄ ነው፡፡›› ሲሉ የነበሩ አንዳንድ የኦሮሞ ምሁራንና ፖለቲከኞች በጊዜ ሂደት ኦሮሞ በኢትዮጵያ በቆዳ ስፋት ትልቁና የሕዝቡም ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ውስጥ ግዙፍ ሆነ ቦታ ሊሰጠው ይገባል፣ የኦሮሚፋም በኢትዮጵያ የፌዴራል መንግሥት ፖለቲካ አሥተዳደር ውስጥ የፌዴራል መንግሥቱ ቋንቋ መሆን የሚችልበት መንገድ ሊታሰብብት ይገባዋል፣ የሚሉ የተለሳለሱ አቋሞችን የሚያራምዱ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ፖለቲከኞችም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብቅ ብቅ ማለታቸውንም ታዝበናል፡፡
ስለሆነም በዚህ ጽሑፍ የኦሮሞን ታሪክ፣ ባህል፣ ማንነት፣ የኦሮሞን የመብት ጥያቄና ትግል ተመለከተ በፊትም ሆነ በተለይም ደግሞ ከሰሞኑን የፖለቲካ ተንታኙ ጃዋር ሙሐመድ ባነሳው የኢትዮጵያዊነትና የኦሮሙማ አንኳር እሳቤዎች ላይ ተመርኩዤ ጥቂት ነገሮችን ለማለት ወደድኩ፡፡
እንደሚታወቀው ባለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት ውስጥ የእከሌ ብሔር ወይም ጎሳ በዚህኛው ብሔር ወይም ጎሳ ላይ ለፈጸመው በደልና ጭቆና በሚል ያልተወራረዱና ጊዜ እየጠበቁ ቦግ እልም የሚሉ ምሬቶችን፣ ቁጣዎችንና የበቀል ሰይፎችን በተለያዩ የአገራችን ክልሎች መከሰታቸውን ታዝበናል፡፡ ይህን እኩይ የሆነ የበቀል ሒሳብ በማወራረድ የተጠመዱ አንዳንድ ፓርቲዎች፣ ፖለቲከኞችና ግለሰቦችም ሆን ብለውና ያልተገባ ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግበስበስ ሲባል እውነታን በማጣመም በሚጻፏቸውና በሚያጽፏቸው የተዛቡ የታሪክ ድርሳናትና ገድሎቻቸው፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ትናንትና ያልነበረ ዛሬም የሌለ ቅዠት ወይም ሕልም ነው እስኪባል ድረስ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በርካታ ትንታኔዎቻቸውን ሰምተናል፣ የዳጎሱ ጥናታዊ ጽሑፎቻቸውንም አስነብበውናል፡፡
በዚህ እነዚሁ የብሔር ፖለቲካ ጽንፈኞች፣ በቀልን ሰባኪዎች፣ የብሔራዊ መግባባትና እርቅ ተቀዋሚዎች በተጻፉ የተዛቡ ታሪኮችና ያልተወራረዱ የበቀል ሒሳቦች ክፉ ስብከት የተነሣም ለዘመናት ተዋደውና ተከባብረው፣ በጋብቻና በአምቻ ተሳስረው፣ እኔ ትብስ አንተ ትብስ ብለው የኖሩ ሕዝቦች የተሳሰሩበትን የአንድነት ድርና ማግ ለመበጠስ ሲባል የተደረጉ አያሌ ዘመቻዎችንም በዘመናችን በሐዘንና በግርምት ሆነን አስተውለናል፡፡
ዛሬም ድረስ ለኦሮሞ ሕዝብ መፍትሔው የእኔ የፖለቲካ አቅጣጫ ነው የሚሉ በርካታ የኦሮሞ ምሁራን፣ ፖለቲከኞችና ፓርቲዎች በአገር ውስጥና በውጭ አገር ሆነው ለኦሮሞ ሕዝብ ይጠቅማል በሚሉት መንገድ የራሳቸውን አቋም በማራመድ ይጻፋሉ፣ ይወያያሉ፣ ይከራከራሉ፣ ይሟገታሉም፡፡
ይሁን እንጂ እስካሁኗ ቅጽበት ለኦሮሞ ሕዝብ ነፃነት፣ መብትና ጥቅም ቆመናል በሚሉት በበርካታ የኦሮሞ ፖለቲከኞች፣ ምሁራንንም ሆነ ፓርቲዎች ዘንድ ቢያንስ ባለፉት ሁለት ዐሥርተ ዓመታት የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክና ጥያቄ በማስተጋባትና በመፍትሔ አቅጣጫዎችም ዙሪያ በሚያራምዱት አቋማቸው እርስ በርሳቸው የተለያዩና የተከፋፈሉ መሆናቸውን በተለያዩ አጋጣሚዎች ዐይተናል፡፡ በዋነኝነት የኦሮሞ ሕዝብን ጥያቄ ለመፍታት ከእኔ ወዲያ ለአሳር በማለት ሲምል ሲገዘት የነበረው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በዕድሜ የሚያክለውና የሚስተካከለው ባይኖርም ዛሬም ድረስ በተለያዩ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ውስብስብ ችግሮች ተተብትቦ እየዳከረ ያለ ፓርቲ መሆኑን የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
በተጨማሪም ባለፉት ዓመታት በፓርቲው አመራሮቹ መካከል በተፈጠረ ልዩነትና ውዝግብ የፓርቲው ህልውና አበቃለት እስኪባል ድረስ የነበረውና አሁንም በያዝ ለቀቅ በፓርቲው ውስጥ የሚነሱት ወጀብና ዐውሎ ንፋሶች ዛሬም ድረስ ገና መፍትሔና መቋጫ ያገኙ አይመስሉም፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው፣ ነፃነትን የማወጅ፣ ሉዓላዊነትን የማስከበር፣ የማንነት፣ የታሪክና ፖለቲካ ጥያቄ ነው፣ በማለት ጽንፈኛ አቋሙን በሚያራምደው ኦነግና ደጋፊዎቹ ዘንድ ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በሸዋው ንጉሥ በምኒልክ ሰይፍ ተቀጥቅጦ በአማራ ታሪክና ማንነት ላይ የተገነባ ነው የሚለው መከራከሪያቸው አሁንም ድረስ በአቋም ደረጃ በግልጽ የሚንጸባረቅ ነው፡፡
ወጣቱ የፖለቲካ ምሁርና ተንታኝ ጃዋር ሙሐመድም ይህንኑ ሐሳብ በመድገም እንዲህ ብሎአል፡- ‹‹ … ኢትዮጵያን የመሠረታት የሦስትዮሽ ጦርነት ግብግብ ነው፡፡ በአማራው፣ በኦሮሞው፣ በትግሬው ግብግብ ውስጥ ወደ መጨረሻ ላይ በአመራር ስር የበላይነቱን የያዘው አማራው ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ አሁን የምናያት ኢትዮጵያ ማንነቷ በአማራ ባሕላዊ ሥርጭትና በአማራ ፖለቲካ የተገነባች ነች፡፡ … የኢትዮጵያ አገራዊ ማንነት የምንለውም የአማራ ባህላዊ ማንነት ነው፡፡›› ሲል ከኢትዮጵያ ታላቅ ሥልጣኔ፣ ታሪክና ከኢትዮጵያዊነት መንፈስ ወይም ማንነት ጋር የሚጣረስ ድምዳሜን ሰጥቶአል፡፡
ይህ ዓይነቱ ትንታኔ የኢትዮጵያን ታሪክ በአግባቡ ያለመረዳት ቀውስ ወይም ደግሞ ሆን ብሎ የታሪክ እውነታን የማዛባት ዘመቻ ነው የሚመስለው፡፡ ኢትዮጵያ የምትባለው ምድርና ሕዝቦቿ ትናንትና ከመቶ ዓመት በፊት ምኒልክና ተከታዮቹ በኃይልና በሰይፍ በሚፈልጓት ቅርፅና ይዘት ቀጥቅጠው የፈጠሯት እንጂ የሚለው መከራከሪያ ሐሳብ በምንም መንገድ ውኃ ሊያነሳ የሚችል ሐሳብ አይመስለኝም፡፡ ይህ ዓይነቱ አመለካከት ከሺሕ ዓመታት በፊት ጀምሮ በገናና ሥልጣኔዋና ታሪኳ በዓለም መድረክ ስሟ ገኖ የወጣውን፣ ከአፍሪካ አልፎ በሰሜን አሜሪካና በካረቢያን በባርነትና በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ተይዘው ሲማቅቁ ለነበሩ ሕዝቦች የነፃነት ምድር፣ የጥቁር ሕዝቦች ተስፋ ‹‹የጥቁር ሕዝቦች የከነዓን ምድር›› በሚል በሰቀቀንና በናፍቆት ሲያስቧትና ሲዘክሯት የኖረችውን ኢትዮጵያን ህልውና የመካድ ያህል የሚቆጠር ይመስለኛል፡፡
ኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት መንፈስ የነፃነት ተምሳሌት፣ የአንድነትና የፍቅር ኪዳን ሆኖ በብዙዎች ልብ ውስጥ ሲንቀለቀልና ለዘመናት ሲያበራ የኖረ እውነት መሆኑን መካድ አንችልም፡፡ ከአፍሪካ አስከ አሜሪካ፣ ካረቢያና ጃማይካ ይህ ኢትዮጵያዊነት መንፈስ በእውቁ የነፃነት ታጋይ በእነ ማርከስ ጋርቬይ፣ በሬጌው ንጉሥ በእነ ቦብ ማርሌይ፣ በእነ ፒተር ቶሽ፣ በአፍሪካውያኑ የነፃነት አባቶች፣ በእነ ጆሞ ኬንያታ፣ በንኩርማ፣ በማንዴላና በበርካታ የነፃነት ታጋዮች ዘንድ የሞራልና ወኔ ስንቅ ሆኖ ያገለገለ፣ ክቡር ታሪክ፣ ሕያው አሻራና ቅርስ መሆኑን መዘንጋት ከታሪክ ሐቅ ጋር መጣላት ነው የሚሆነው፡፡
በተጨማሪም ለዚህችው በሺሕ ዘመናት ገናና ሥልጣኔዋ፣ ነፃነቷ፣ ታሪኳና ሉዓላዊነቷ ሲሉ በዐድዋ ጦር ግንባር ከወራሪው የአውሮጳ ኃይል ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ለሕዝቦቿም ነፃነት ዋጋ የከፈሉትን የኦሮሞ ተወላጆቹን የእነ ባልቻ አባ ነፍሶን፣ የእነ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪን፣ የእነ ራስ አበበ አረጋይን፣ አውሮጳ ምድር ድረስ ዘልቆ በሮማ አደባባይ የኢትዮጵያውያንን አይበገሬነትና ለነፃነታቸው ቀናኢ ሕዝብ መሆናቸውን ያሳየውን የአብዲሳ አጋንና የበርካታ እልፍ የሚሆኑ የኦሮሞ ልጆችን ለሰው ልጆች ነፃነት የፈሰሰ ደምና መሥዋዕትነት ማራከስ ነው የሚሆነው፡፡
ከሰሞኑን የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩና አንጋፋው ፖለቲከኛ ፕ/ር መረራ ጉዲና፡- ‹‹የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የሕይወቴ ትዝታዎች፡- ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ እስከ ኢህአዴግ›› በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፋቸውም በዓድዋው ጦርነት ከየትኛውም ሕዝብ ይልቅ የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ ጦር አዝማቾችና ጀግኖች ታላቅ መሥዋዕትነት መክፈላቸውን በመግለጽ የዓድዋ ድል የምኒልክን ቅኝ ግዛት ዘመቻ ያጠናከረ ዓውደ ግንባር ነው የሚለውን ሐሳብ አጣጥለው በመከራከር ጽፈዋል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ታላቅነትና አይበገሬነት በኦሎምፒክ መድረክ ከፍ ያደረጉ አበበ በቂላ፣ ዋሚ ቢራቱ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ብርሃኔ አደሬ፣ ጌጤ ዋሚ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ፋጡማ ሮባ፣ ደራርቱ ቱሉ … እነዚህ ሁሉ በሮጡበት መድረክ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ብሔርና ሃይማኖት ሳይለዩ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ አብረው ሮጠዋል፣ ስለ ኢትዮጵያ ክብርና ድልም አብረው አምጠዋል፣ ተጨንቀዋል፡፡ በባርሴሎና ኦሎምፒክ መድረክ አበባችን ደራርቱ ቱሉ በአሥር ሺሕ ሜትር የመጀመሪያቱ አፍሪካዊት ሴት ወርቅ ሜዳሊስት በሆነችበት ድሏ የአገሯ ብሔራዊ መዝሙርና ሰንደቅ ዓላማ በስፔን ሰማይ ላይ ሲናኝና ከፍ ብሎ ሲታይ በጉንጯ ላይ ኮለል ብሎ የፈሰሰውን ዕንባዋን የታዘብን ሁሉ፣ በኢትዮጵያዊነት ኩራትና አይበገሬነት መንፈስ አብረናት በደስታ ሲቃ አንብተናል፣ መሬት ስመናል፡፡
ይህን ታሪክ በወርቅ ቀለም የጻፈውን የበርካታ ኦሮሞ ጀግኖችን ገድልና ለኢትዮጵያዊነት የተከፈለ መሥዋዕትነትን ማቃለልና ታሪክን ማዛባት ጤነኛ አካሄድ አይደለም፡፡ በዘመናችን ኦሮሙማን/የኦሮሞን ብሔርተኝነት በእጅጉ የሚሰብኩና የሚያራግቡ ሰዎች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ኦሮሙማን ወይም የኦሮሞ ብሔርተኝነነትን ለመገንባት ሲሉ የኢትዮጵያን የሺሕ ዘመናት ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ ቅርስና የኢትዮጵያዊነትን መንፈስ ማጣጣልና መንኳሰስ ጤነኛ አካሄድ አይመስለኝም፡፡
ኢትዮጵያዊነት እንደ ኮሶ ተበጥብጦ በግድ እያነገፈገፈን የተጋትነው፣ እየቀፈፈንና እየኮሰኮሰን የተደረበብን ማንነት ብለው ለሚከራከሩ ሰዎች በእርግጥም በግድ ሳይወዱ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ተቀበሉ ብሎ ማስገደድ እንደማይቻል አሳምሬ አውቃለሁ፡፡ ኢትዮጵያዊ ለመሆን ያለመፈለግ መብታቸውንም በግሌ አከብራለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ታሪክን በማዛባት ጥቁር ሕዝቦች፣ መላው አፍሪካና በአጠቃላይ ነፃነትን አፍቃሪ የሆኑ ሕዝቦች ልብ ውስጥ ትልቅ ዋጋና ክብር ያለውን የኢትዮጵያዊነትን መንፈስ ማራከስ፣ በኢትዮጵያና በሕዝቦቿን ታሪክ፣ ቅርስና ማንነት ላይ መዘባበት ጤነኛ አካሄድ እንዳልሆነ አሁንም በድጋሚ አስረግጬ ለመናገር እወዳለሁ፡፡
No comments:
Post a Comment