ከበፍቃዱ ዘ ኃይሉ
“ለ7 ዓመታት በተከታታይ 11·6 በመቶ አድጓል” የተባለው የመለስ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፥ የዓለም ባንክ እና አይኤምኤፍም ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሚገኘው መረጃ ላይ ቢመሠረቱም “የለም፤ ከ6 እስከ 8 በመቶ ነው ያደገው፣ ቢሆንም ቀሽት ነው” ይላሉ።
“ኢኮኖሚው ሲመነደግ” የሕዝቦች ኑሮ ደረጃስ እንዴት ነው?
ኢትዮጵያ በየአረብ አገራቱ የቤት ሠራተኛ አቅራቢነት ከፍተኛ ደረጃ የደረሰችው በመለስ ዘመን ነው። (ለምሳሌ አሁን ኢትዮጵያውያንን አልቀበልም ያለችውን ሳውዲ አረቢያ የቤት ሠራተኛ ፍላጎት 10 በመቶ ኢትዮጵያ ትሸፍን ነበር።) በየአረብ አገራቱ የኢትዮጵያውያን ስም ከሌብነት እና ሴተኛ አዳሪነትጋ የተያያዘ ነው።
ከኢትዮጵያ ውጪ መውጣት ለሁሉም ዜጋ ቢፈቀድ ዐሥር ሚሊዮን ሰው እንኳን ይቀራል ብዬ መገመት ይከብደኛል። ከተሜውም ገጠሬውም ወደቻለው ቦታ ይፈልሳል። የተማረውም፣ ያልተማረውም ኢኮኖሚያዊ ስደትን የመምረጡ እውነት የኢኮኖሚያዊ ዕድገቱን እውነተኝነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይከተዋል።
የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በተለይ የመንገድ ሥራዎች ሲነቃቁ የግሉ ዘርፍ (ከኢሕአዴግ “የኢንዶውመንት” ቢዝነሶች በቀር) ተዳክሟል። ያሉትም የግል ቢዝነሶች ቢሆኑ በፖለቲካ ጥቅም የሚለመልሙ በመሆናቸው በከተሞች መሐል የሚበቅሉ ብልጭልጭ ሕንፃዎች የሙስና ሲሳይ ናቸው። ከሕንፃዎቹ ጀርባ ያሉት ያው የድሮዎቹ ቆሼ ሰፈሮች ናቸው። እንደ HDI ያሉ የUN የሰብኣዊ ልማት መለኪያዎችም የሚያሳዩን ኢትዮጵያውያን ዛሬም በድህነት እየማቀቁ መሆኑን ነው።
“ስኳር የተወደደው ድሃው ስኳር መብላት ጀምሮ ነው” ያሉት መለስ ስኳሩን የሚልሱት እነማን እንደሆኑ እንኳ ሳይረዱ ያለፉ ይመስለኛል።
አቶ መለስ ምንጩንና መጠኑን ማንም ያልገመተው፣ የባለብዙ ሀብት ባለቤት፣ የትዳር አጋራቸውን ጨምሮ ሌሎች ጥቂት ሀብታሞች ያሉበት የጥቅመኞች ክበብ እየዳጎሰ ብዙኃኑ የሚቀጭጩበትን የቢዝነስ ስርዓት በመፍጠር በቁጥር ጫወታ አድጋችኋል ይሉናል። ድሃ ተኮር ፖሊሲ ቀርጫለሁ፣ ለልማቱ ብዬ ነው ዴሞክራሲን የበደልኩት ብለው ያተረፉልን ነገር ቢኖር አገርክን ጥለህ ብረር፣ ብረር የሚያሰኘው ምስኪን፣ ድሀ ትውልድ ብቻ ነው።
No comments:
Post a Comment