በዘሪሁን ሙሉጌታ
የአንድነት ለዴሞክራሲ ለፍትህና ፓርቲ (አንድነት) ለሦስት ወራት የጀመረውን የሕዝብ ንቅናቄ በመቀጠል በቀጣዩ ሳምንት በኦሮምያ ከተሞች ውስጥ ዘመቻውን እንደሚቀጥል አስታወቀ።
የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ምክትል ኃላፊና የብሔራዊ ም/ቤት አባል አቶ ሐብታሙ አያሌው ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ፓርቲው በኦሮምያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን፣ በባሌ ዞን ባሌ ከተማና በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳማ ከተማ ሰላማዊ ሰልፎች እንደሚያደርግ አስታውቀዋል። በሦስቱም ከተሞች በተመሳሳይ ቀን ነሐሴ 19 ቀን 2005 ዓ.ም ሰልፉ ይካሄዳል።
ፓርቲው በመንግስት የአስተዳደር አካላት እየደረሰበት ያለውን ተፅዕኖ ተሸክሞ ንቅናቄውን ከማቆም መቀጠል መርጧል ያሉት አቶ ሐብታሙ፤ መንግስት በፓርቲው ላይ የተቀነባበረ ወንጀል እየፈፀመ ነው ብለዋል። እንደምሳሌ ፓርቲው ያስፈረመው የፀረ-ሽብር ሕግን የመቃወሚያ ሰነድ ፖሊስ ከሚያስፈርሙ አባላቱ ነጥቋል አባላቱም በእስር እየተጉላሉ ነው ብለዋል።
ፓርቲው ንቅናቄውን ከጀመረ በኋላ እየደረሱበት ያሉትን ተፅዕኖዎች የሚያመለክት ዝርዝር መረጃ ለብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ማቅረቡን፣ ለአዲስ አበባ ከንቲባ ጽ/ቤት፣ ለሀገሪቱ ጠ/ሚ ጭምር ደብዳቤ ለመፃፍ መገደዱን ገልፀዋል። በክልልም ለየክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና ለፀጥታው ዘርፍ ኃላፊዎች ለማስረዳት መሞከሩንና ችግሩ ግን ፓርቲው እንቅስቃሴ በሚያደርግበት ወቅት የማደናቀፍ ተግባሩ እየተፈፀመ ነው ብለዋል።
ፓርቲው የጀመረው የሦስት ወራት ሕዝባዊ ንቅናቄ በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ አዲስ አበባ ውስጥ በሚካሄድ ትልቅ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚጠናቀቅ መግለፁ ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment