Tuesday, August 20, 2013

የመለስ መድፍ

ከፋሲል የኔአለም

ለመለስ ሙት አመት መታሰቢያ ይሆን ዘንድ 21 ጊዜ መድፍ መተኮሱን ሰማሁ፤ በአገራችን ለሞቱ መሪዎች መድፍ የመተኮስ ልማድ መኖሩን አላውቅም፤ የሞቱ መሪዎችን በየአመቱ የመዘከር ልማድም ያለ አይመስለኝም። መድፍ ሲተኮስ የማውቀው ለብሄራዊ ባዕላት አንዳንዴም የታፈሩ መሪዎች አገራችንን በሚጎበኙበት ወቅት ነው። መለስ እውነት ታሪክ ሰርተው 21 ጊዜ መድፍ ቢተኮስላቸው ባልጠላሁ፣ ነገር ግን ስራቸው ለመድፍ ተኩስ ቀርቶ ለአንድ ቀን እንኳን እንዲታወሱ ያደርጋቸዋል ብየ አላስብም።
መለስ እድለኛ መሪ ነበሩ፣ የአለም ፖለቲካ መለወጡ እርዳታ በገፍ እንዲጎርፍላቸው አድርጓል፤ እርዳታውን በአግባቡ ተጠቅመው አገሪቱን በፍጥነት ማሳደግ ይችሉ ነበር፤ አላዳረጉትም። 21 ዓመታት በስልጣን ላይ ቆይተው፣ እድገት አስገኘሁ የሚሉት 8 ዓመታቱ ብቻ ነው፤ ለጠፉት 13 ዓመታት የሚጠይቃቸው አልነበረም፤ የመለስ አገዛዝ 21 ዓመታት የኢኮኖሚ ድምር ውጤት በጦርነት ከደቀቁት ከእነ ሶማሊያ ኮንጎና ሴራሊዮን ይሻል ካልሆነ፣ ከየትኛውም ሰላም ከሰፈነባቸው የአፍሪካ አገራት እንደማይሻል በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፤ መረጃዎችን ፈትሾ ማየት ይቻላል ዛሬም ወደ 13 ሚሊዮን ህዝብ በሴፍትኔት ስም እርዳታ ተመጽዋች ነው።
21 ዓመታት ውስጥ 30 እስከ 40 ቢሊዮን ዶላር የውጭ እርዳታ ያገኙ ሰው፣ ከዚህ ውስጥ 50 በመቶው ተጣርቶ እጃቸው ውስጥ ቢገባ፣ ለመንገዶች፣ ትምህርት ቤቶች እና ጤና ኬላዎች ግንባታ ያወጡት ገንዘብ ድምር፣ ለጋስ ልሁንና፣ 6 ቢሊዮን ዶላር አይበልጥም። ስለቀሪው ገንዘብ ተከድኖ ይብሰል ነው።

የፖለቲካ ሳይንቲስቶች እንደሚሉት የአንድ መንግስት ትንሹ ሃላፊነት የአገሩን አንድነት መጠበቅ ነው። መለስ ይህን ሳይወጡ ያለፉ መሪ ናቸው፣ አለም ግዛቱን ለማስፋፋት በሚኳትንበት ዘመን፣ መለስ ኢትዮጵያን ወደብ አልባ ከማድረጋቸውም በላይ ለሱዳን ሆላንድን የሚያክል መሬት አሳልፈው የሰጡ፣ በታሪክ አምሳያ የሌላቸው ገዢ ነበሩ። 
ለውጭ ባለሀብቶች በነጻ የተሰጠው መሬት፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት፣ የዘር ፖለቲካው እና ሙስናው የደረሰበት ደረጃ መለስን በታሪካችን ካፈርንባቸው መሪዎች ተርታ እንደሚያሰልፋቸው ቅንጣት ታክል ጥርጥር የለኝም።

No comments:

Post a Comment