Sunday, August 25, 2013

“ሥልጣን ለመያዝ ጨዋታው ቀላል አይደለም”

“ሥልጣን ለመያዝ  ጨዋታው ቀላል አይደለም”
 
አብዮቱን ወደ መጠፋፋት ፖለቲካ የወሰደው ኢህአፓ ነው
የብቻ ሩጫ የትም እንደማያደርስ ከነመኢሶን ዘመን ጀምሮ አይተናል
በኢህአፓና በመኢሶን እስረኞች መካከል ልዩነቱ እጅግ በጣም የተካረረ ነበረ
ዶ/ር መረራ ጉዲና “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የህይወቴ ትዝታዎች” በሚል ሰሞኑን ለንባብ ባበቁት መጽሐፍ ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ኤልሳቤት እቁባይ ጋር አጭር ቆይታ አድርገዋል፡፡
መጽሐፉን ያዘጋጁበት ዋና አላማ ምንድነው?
የአሁኑ ትውልድ ስለኛ ትውልድ ያልሆኑ ነገሮችን እየሰማ ነው፡፡ በማይሆን መንገድ የሚነገሩና የሚፃፉ ብዙ ነገሮች ስላሉ እነሱን ለማስተካከልና ለማረም ፈልጌ ነው፡፡ የኔ ትውልድ እና የአሁኑ ትውልድ እንዲግባቡ ለማድረግ የተሞከረበት መጽሐፍ ነው፡፡
በመፅሃፍዎ ላይ መኢሶን ለደርግ ያደረገውን ድጋፍ በተመለከተ፤ “ያን ድጋፍ ባያደርግ ኖሮ ደርግ ተጠናክሮ መውጣት አይችልም ነበር” ብለዋል።
በቅርቡ በወጣው የህይወት ተፈራ “ታወር ኢን ዘ ስካይ” መጽሐፍ ደግሞ መኢሶንን በዚህ ድርጊቱ የተነሳ “The bad boy of the Revolution” ብለዋለች፡፡ በዚህ ጉዳይ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?
ሁሉም በየደረጃው ስህተት ሰርቷል፡፡ ጥፋት አጥፍቷል፡፡ በመጽሐፉ ላይ “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቡዳ ማነው” ብያለሁ፡፡ መልሱ እንደመላሹ ይለያያል። እሷ ኢህአፓ ስለነበረች ቡዳው መኢሶን ነው ልትል ትችላለች፡፡ እኛ ደግሞ መኢሶን ስለነበርን ቡዳው ኢህአፓ ነው ልንል እንችላለን፡፡ ነገር ግን የቡዳውን ማንነት ለመመለስ ቀላል አይደለም። መኢሶን የኢህአፓን ጥይት ለመከላከል ይሁን ወይም በሌላ ምክንያት አንድ አመት ከደርግ ጋር በሰራበት ጊዜ በቂ ጥንቃቄ ባለማድረጉ፣ መኢሶንንም ሆነ በአጠቃላይ ትግሉን ጐድቶታል፡፡ ሌላው አብዮት የሚባለውን ነገር ወዳልተፈለገ ፣ ጨርሶ ወደመጠፋፋት ፖለቲካ ይዞ የገባው ከደርግ ቀጥሎ ኢህአፓ ነው፡፡ ለምሳሌ ውይይቱን ወደ ጥይት ለውጦታል፡፡ እስከዛ ድረስ በመኢሶን እና በኢህአፓ መሀል የተወሰኑ ክሮች ነበሩ።
ምን አይነት?
ለምሳሌ እነሀይሌ ፊዳ ከእነ ተስፋዬ ደበሳይ ጋር ይገናኙ ነበር፡፡ ኢህአፓ ፍቅሬ መርዕድን ሲገድል ጨዋታው ፈረሰ፡፡ ሁሉም ነገር እዛ ላይ ቀረ፡፡ ስለዚህ መኢሶን ከደርግ ጋር አብረው እንዲህ አደረጉን የሚለው እንዳለ ሆኖ፣ ኢህአፓ የከተማ ትጥቅ ትግል ብሎ በአብዮቱ ዙሪያ የነበሩ ብዙ ጥያቄዎችን ከቃላት ውይይት ይልቅ ወደ ጥይት ውይይት መውሰዱ ለራሱም ሆነ ለሌላው ቀላል ያልሆነ ጥፋት ነበር፡፡
ሁሉንም ነገር ያበላሸው የጥይት ጉዳይ ነው። ሌሎቹ ስህተቶች የሚታረሙ ነበሩ፡፡ ሰው እንዳይነጋገር፣ እንዳይገናኝ፣ እንዳይመካከር ተደርጐ የመጠፋፋት ጨዋታ ውስጥ ነው የተገባው፡፡ ሌሎች ነገሮች የስትራቴጂ ጉዳዮች ናቸው፡፡ አንዱ ወደ ደርግ ተጠግቷል፤ ሌላው ወደ ኤርትራ ግንባሮች ተጠግቷል የሚሉ ብዙ ክሶች ነበሩ፡፡ በተለይ ግን ምንም በማያውቀው ወጣት ላይ ጦርነት እና ጥይት መከፈቱ በጣም ጐድቶናል፡፡ መጽሐፉ ላይ እንዳየሽው፤ እኛ የሁለተኛ አመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሆነን፣ ራሳችንን በቂ እውቀት እንደሌለን ነበር የምንቆጥረው፡፡ ምክንያቱም የኢህአፓ እና የመኢሶንን ልዩነት አውቆ የገባ ወጣት በጣም የተወሰነ ነው፡፡ እኔ የነበርኩበት ቡድን የሚያነበው አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ስለሆነ፣ ያን ለይቶ አቋም መውሰድ ስለተቸገርን ነው ከዘመቻ እስከምንመለስ ድርጅት ውስጥ አንገባም ብለን ወስነን የነበረው። ከዘመቻ ስንመጣ ኢህአፓ ውይይቱን ወደ ጥይት ወስዶት ነበር፡፡ የውስጡንም ቅራኔ በጉልበት ወደ መፍታት ነው የሄደው፡፡ ለዚህ ደግሞ የነጌታቸው ማሩን፣ የእነ ብርሃነ መስቀል ረዳን፣ የነጌታሁን ሲሳይንና የነይርጋ ተሰማን ዕጣ ማየት ነው፡፡
በትግሉ ወቅት የመኢሶን መለያ ምን ነበር?
መኢሶን እኮ ታላቅ ነው፡፡ መንገደኛ አልነበረም። መኢሶንን የፈጠሩ ሰዎች እኮ የትግሉ አንጋፋዎች ናቸው፡፡ ዶ/ር ወርቁ ፈረደ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ኮሚኒስት ይባል የነበረ ሰው ነው። ከመኢሶን መስራቾች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በህክምና ወይም በሌላ ዘርፍ ዶክትሬት የነበራቸው ናቸው፡፡ በማንበቡም ሆነ በትምህርት ከነበሩት ሁሉ የተሻሉ ናቸው፡፡ መኢሶኖች ሊከሰሱ የሚችሉት በእድሜ የገፉ፤ መለዘብ ወይም እርጋታ የጀመሩ ናቸው በሚል ነው፡፡ መንገደኞች ግን አልነበሩም፡፡
ቀኝ መንገደኞች የሚባለው ነገርስ?
እሱ ጨዋታ ነው፤ ደርግ ወደኋላ ላይ የለጠፈብን ስም ነው፡፡
የመኢሶንና የኢህአፓ የመጨረሻ ውይይት እንዴት ነበር የተቋጨው?
መኢሶን እና ኢህአፓ የአጭር ጉዞ፣ የረጅም ጉዞ በሚል ሲጨቃጨቁ ከቆዩ በኋላ፣ አፄ ሀይለስላሴ ሊወርዱ ቀናት ሲቀሩ የመጨረሻው ስብሰባ በርሊን ላይ ተደረገ፡፡ ስብሰባው ላይ አልተስማሙም፡፡ አብዮቱ መጥቶ ንጉሱ ሊወርዱ ሲሉም መስማማት አልተቻለም፡፡ ሲለያዩ የኢህአፓው ቡድን፣ የኔን አቋም ትክክለኛነት የካርል ማርክስ እና የሌኒን ሀውልቶች ምስክር ይሆናሉ አለ፡፡ መኢሶን ደግሞ ታሪክ እና የኢትዮጵያ ህዝብ ምስክሬ ነው አለ፡፡ በዚህ ላለመስማማት ተስማምተው ተለያዩ፡፡
በልዩነታቸው በጣም የተበሳጨው ፕሮፌሰር ማሞ ሙጨ፤ እሪ በይ አገሬ ብሎ አለቀሰ፡፡ ሳገኘው እሱን እያነሳሁ እቀልድበታለሁ፡፡ በወቅቱ ቃለ ጉባኤ ፀሐፊው ሀይሌ ፊዳ ነበር፡፡ “የኢህአፓ መሪዎች እንዲህ አሉ -የመኢሶን መሪዎች እንዲህ አሉ … ላለመስማማት ተስማሙ… የሁለቱ መለያየት ያበሳጨው፣ ማሞ ሙጨ ደግሞ በእንባ ለተሰብሳቢው ንግግር አደረገ” ብሎ ጽፏል፡፡ ኢህአፓ ሀውልቱን፣ መኢሶን ታሪክን በምስክርነት ጠርተው ነበር፡፡
ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲን በተማሪነት ያውቁታል። አሁን ደግሞ በመምህርነት ይመላለሱበታል፡፡ እዚህ ግቢ ውስጥ ካሉ ቦታዎች በትዝታ ወደ ኋላ የሚወስድዎት ምንድነው?
ሁለት ቦታዎች አሉ፡፡ መልሰው መላልሰው ወደዛ ዘመን የሚወስዱኝ፡፡ አንደኛው ልደት አዳራሽ ነው። ብዙ ጊዜ ስብሰባ እናደርግበት ነበር፡፡ በነገራችን ላይ እስካሁን ድረስ ብዙ ውጣ ውረዶችን ያየ አዳራሽ ነው። ኢህአዴግ ሲመጣም ለመጀመሪያ ጊዜ የሰበሰበን እዛ ነው፡፡ ከአፄው ጀምሮ አዳራሹ ታሪካዊ ስለሆነ ወደኋላ ይመልሰኛል፡፡ ሌላው ኪሲንግ ፑሉ ነው፡፡ ከቀልድ ጋር እና ከጥናት እንዲሁም ቆነጃጅቶቻችንንም ከማየት ጋር ተያይዞ ትዝታው ውስጤ አለ፡፡ አሁን ስያሜው ወደ በግ ተራ ተቀይሯል፡፡ አርት ፋካልቲም አንዳንድ ግዜ ስብሰባ እናደርግ ነበር፡፡ ህግ ፋካልቲ ደግሞ የተለየ ዶርም ነበረው፤ እዛ እንሰበሰብ ነበር፡፡ ሁለቱ ግን ዋነኞች ናቸው፡፡ በአፄው ጊዜ መሰብሰቢያ ነበር፤ ደርግም ተጠቅሞበታል፤ ኢህአዴግም በመጀመሪያ ስብሰባውን ያደረገው እዛ ነው፡፡ ኢህአፓና መኢሶን ግጭት ካደረጉባቸው ቦታዎች አንዱ ልደት አዳራሽ ነው፡፡
ብዙ የግድያ ሙከራዎችን አምልጠዋል፡፡ እድል ነው ወይስ …
አጋጣሚዎች ናቸው፡፡ በቀጥታ እኔ ላይ ሊተኮሱ የታሰቡ ጥይቶችን አይደለም የማመልጠው፡፡ ለምሳሌ ኢህአፓና መኢሶን ልደት አዳራሽ የተጋጩ ዕለት ከመኢሶን ውስጥ ሙሉ ስሙን ያልፃፍኩት አጤ፤ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ካለነው የመኢሶን አመራሮች ውስጥ ኢህአፓ አስርጐ ያስገባው ነበር። እሱ የኛን ዝግጅቱ ሙሉ በሙሉ ለኢህአፓ ይንገር አይንገር እግዚአብሔር ይወቀው፡፡ ያ ዝግጅት የከሸፈው አጤ ተነጥሎ ኢህአፓ መሃል ሲገባ ነው። እርምጃ ውሰድ ተብሎ ትዕዛዝ ያልተሰጠው ኢህአፓ፣ “ይሄ ባንዳ መሀላችን ምን ያደርጋል” ብሎ በራሱ ሽጉጥ ጭንቅላቱን መታው፡፡ አንድ አመት ተኩል አካባቢ ሆስፒታል ተኝቷል፡፡ ለምሳሌ ያ ልጅ ባይመታ ኖሮ፣ ኢህአፓ ሊወስድ የተዘጋጀውን እርምጃ አናውቅም። በኋላ ላይ የጠረጠርነው ምንድን ነው … እዚህ ጊቢ ያሉትን ባንዳ የሚባሉትን ሠቅሎ ለመሄድ እንዳሰበ ነው፡፡ ከዛ ከተማ ውስጥ ትንሽ ግርግር ፈጥሮ፣ እነ ኮሎኔል አለማየሁ ሀይሌ ደግሞ ደርግ ውስጥ ያለውን ስራ እንዲሰሩ ነው፡፡ ኢህአፓ ሁሉም ቦታ ከሸፈበት። ገሠሠ በላይ፤ “እዚህ ምንም አንሰራም ራሳችንን እንጠብቅ፤ ከዩኒቨርሲቲ እንውጣ” ብሎኝ ነበር፡፡ እሱን ኢህአፓ ገደለው፡፡ ከሱ ጋር እሺ ብዬ ብሄድ ኖሮ አልተርፍም ነበር፡፡ አምቦ ላይም አማረ ተግባሩ በጠራው ስብሰባ፣ ታላቅ ወንድሜና እነ ዶ/ር ተረፈ ሲገደሉ እኔ በአጋጣሚ ተርፌያለሁ፡፡
ያ ትውልድ ለመስዋዕትነት ዝግጁ የመሆኑን ያህል የመካካድ ባህሉም ስር የሰደደ እንደነበር ወቅቱን ተንተርሰው የሚወጡ ጽሑፎች ያመለክታሉ
መካካዱ እንደዛሬው አይበዛም፡፡ በቁጥር የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የትግል እምነቱ የጠነከረ ነበር። መካካድ በኢትዮጵያ ታሪክ ስር ሰዶ የቆየ ነው፡፡ ለአላማዬ እሞታለሁ፤ ለአላማም እገድላለሁ የሚለው በወቅቱ ያስቸገረን ጉዳይ ነበር፡፡
በመጽሐፍዎ “ደርግ፤ የመኢሶንን የማሌሪድን፣ የኢህአፓን ልጆች ወረሳቸው” ብለዋል፡፡ ሰው መውረስ ምንድን ነው?
ደርግ ከሁሉም ድርጅቶች ልብሳችሁን ቀይራችሁ ግቡ ብሎ ነበር፡፡ እሱን ነው ውርስ ያልኩት፡፡ ከሱ የተሻለ አማርኛ ስላላገኘሁ ነው፡፡ ቀደም ሲል የሌሎች ድርጅት አባል የነበሩ በኋላ ላይ የደርግ የሆኑትን ለማመልከት ነው፡፡
እስር ቤትም አንድም ቀን አልተገረፉም፡፡ ይሄስ እድል ነው?
እሱን እኮ ተናግሬያለሁ፡፡ ተይዤ ልክ ደርግ ጽ/ቤት በራፍ ላይ ስደርስ አምቦ የማውቀው አወቀ የሚባል ልጅ አገኘሁ፡፡ ምን ያህል እንደረዳኝ ባላውቅም መረራን ረዳሁት ብሎ ለአምቦ ልጆች አውርቷል፡፡
አምቦ ላይ ሲያዙ ገበሬው መንግስቱ ሃይለማርያምን እያሞገሰ በመዝፈኑ ተበሳጭተው እንደነበር ጽፈዋል፡፡ ያው ህዝብ በ97 ምርጫ ላይ በነቂስ ወጥቶ መርጥዎታል፡፡ ነገሩን እንዴት አዩት?
ነገሩ አርሶ አደሮቻችን በነበራቸው ንቃት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ገጠር ውስጥ በደርግ ስር አርሶ አደሩን ማደራጀት ፋሺዝም ነው በማለት፣ ኢህአፓ የመኢሶንን የማንቃት ስራ ይቃወም ነበር፡፡ እኛ ደግሞ ሰፊውን ህዝብ ማደራጀት ፋሺዝም አይደለም እንል ነበር፡፡ በሩቅም ቢሆን እኔን እያወቁ ለሞት አሳልፈው መስጠታቸው የእኔንም እምነት ቀላል ባልሆነ መንገድ እንዲናጋ አድርጓል፡፡ ምን ያህል ሁኔታውን አገናዝበው ነበር የሚለው ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ በ1997 ምርጫ ላይ ያኔ ለደርግ አሳልፎ የሰጠኝ የቀበሌ ገበሬ ማህበር ሊቀመንበር ልጅ ነበር የፓርቲያችን ዋነኛ ካድሬ፡፡ እዚህ ላይ ግን ከአርሶ አደር በላይ የኛው የነበሩ የተማሩ ሰዎችም አሳልፈው ሰጥተውናል፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ችግር በዋናነት መመለስ ያለባቸው ጥያቄዎች ምንድን ናቸው?
የትግራይ ልሂቃን ስልጣን የሙጥኝ ማለት፣ የአማራ ልሂቃን የኢትዮጵያዊነት ሠርተፊኬት ሰጪ ነኝ ባይነት እና የኦሮሞ ልሂቃን ኦሮሚያን የሚያህል ሰፊ ህዝብ ይዞ የመገንጠልን ሃሳብ ማቀንቀን ናቸው። የትግራይ ልሂቃን ስልጣን ወይም ሞት ማለት፣ ጨዋታው ውሎ አድሮ እነሱንም አይጠቅምም። የአማራ ልሂቃን የኢትዮጵያዊነት ሠርተፊኬት ወይም የበላይነት እኔ ጋ ነው የሚለው ጨዋታም አያዋጣም፡፡ ከሌሎች ጋር ተደራድሮ መሀል መንገድ ላይ ካልተገናኘ የትም መድረስ አይቻልም፡፡ የኦሮሞ ልሂቃን የመገንጠል ጨዋታም የትም አያደርስም። እነዚህ ሶስቱ ነገሮች አቅጣጫ ይዘው በትክክል ካልተፈቱ በስተቀር የኢትዮጵያ ፖለቲካ በኛ ትውልድ የትም ላይደርስ ይችላል፡፡
የሌሎቹ ብሔሮች ቦታስ የት ነው?
መጽሐፉ ላይ አስቀምጫለሁ፡፡ ከዲሞክራሲ ፀጋ ጋር ጠብ የሌላቸውን በተመለከተ ብዙ ዝርዝር ውስጥ አልገባሁም፡፡
ጆሊ ጃኪዝም ለማን የተሰጠ መጠሪያ ነበር?
አሁን የአራዳ ልጆች የምትሏቸው አይነቶች ናቸው፡፡ አውሮፓ እና አሜሪካ ተምረው የመጡ፣ የወቅቱን ፋሽን ይከተሉ የነበሩ ባለ አፍሮ ፀጉሮችና የፖለቲካው ጉዳይ ምንም የማይመስላቸው ነበሩ፡፡
መኢሶን ህቡዕ ሲገባ ስላልነገርዎት ተከፍተው እንደነበርና ከዛም “ፈሪ ለናቱ” የሚል አቋም እንደያዙ መጽሐፉ ውስጥ ጠቅሰዋል፡፡ እስቲ ስለለውጡ ይንገሩኝ—
መኢሶን ህቡዕ ሲገባ ወይም ሲሸፍት ስላልተካተትኩ ተንቄ የቀረሁ መስሎኝ እኔም መሸፈት አለብኝ ብዬ አጥብቄ ተከራክሬ ነበር፡፡ ብሄድ ኖሮ ያው የነሱ ዕጣ ይደርሰኝ ነበር፡፡ ህቡዕ ከገባው ቡድን ውስጥ ለወሬ ነጋሪም የተረፈ የለም፡፡ ሞትን ያመለጥኩበት ሌላው አጋጣሚ ያኔ ነው፡፡ ከዛ በኋላ የመሸፈት ጉጉት ወጣልኝ ማለት ነው፡፡
በየፖለቲካ ፓርቲው የነበረው ልዩነት እስርቤት ድረስ ይዘልቅ ነበር፡፡ እስቲ የእስር ቤቱን ሁኔታ ይንገሩኝ–
ከርቸሌ እየተዋወቅሽ አትነጋገሪም፡፡ በኢህአፓ እና በመኢሶን እስረኞች መካከል ልዩነቱ እጅግ በጣም የተካረረ ነበረ፡፡ በኢህአፓ እና በመኢሶን መሃል ግድግዳ ነበር፡፡
ለኡዝዋ የፀሐፊነት ቦታ የተደረገውን ውድድር በተመለከተ ስለመለስ ዜናዊ ያነሱት ነገር አለ፡፡ እስቲ ስለዚህ ይንገሩኝ…
ኦቦማ የንግግር ችሎታው፣ የቋንቋ ብቃቱ ከፍተኛ ነበር፡፡ በወቅቱ ከነበሩ የኦሮሞ ተማሪዎች የላቀ እውቀት ነበረው፡፡ ለፀሐፊነት የሚወዳደሩት መለስ ዜናዊ እና እሱ ነበሩ፡፡ መለስ ኦባማን እንደማያሸንፍ ስለገባው ከውድድሩ ራሱን አገለለና ኦቦማ አሸነፈ፡፡ ኦቦማ በኋላ ኦነግን ተቀላቅሎ ነበር፤ አሁን በህይወት የለም፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ የሚገርመኝ፣ የሽግግር መንግስት ጊዜ ሌንጮ ለታ ከመለስ ጋር ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር ከገባ በኋላ ራሱን ከዕጩነት አገለለ፡፡ ይህ የኦሮሞ ህዝብ ትግል ምን አይነት አመራር እንደያዘ ያሳያል፡፡
ወደ አሁኑ ፖለቲካ ስንመጣ…ሰማያዊ ፓርቲ ከሌሎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር እንደማይሰራ አቋሙን ገልጿል፡፡ ስለፓርቲው አቋም እርስዎ ምን ይላሉ?
እነሱ ወጣቶች ናቸው፡፡ ሮጠው ስላልጠገቡ፣ ሩጫ ገና ስለጀመሩ ነው፡፡ ውለው አድርው ወደ መሀል የሚመጡ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም የብቻ ሩጫ የትም እንደማያደርስ ከነመኢሶን ዘመን ጀምሮ አይተናል፡፡ ሁለት ችግሮች አሉ፤ ስልጣን ለመያዝ ጨዋታው ቀላል አይደለም፡፡ ከተያዘ በኋላም በኢትዮጵያ ሁኔታ አገር ማስተዳደር ቀላል አይደለም፡፡ ለምሳሌ ቱኒዚያና ግብጽን ማየት ይቻላል፡፡ ተቃዋሚዎች ስልጣን ከያዙ በኋላ አገር ማስተዳደሩ ያሰቡትን ያህል ቀላል አልሆነላቸውም፡፡ ግብጽ “ሙባረክ ማረን” እስኪሉ ድረስ እልቂቱ እንደቀጠለ ነው፡፡ ስለዚህ በኛ ትውልድ አንድ ቡድን ይሁንታ አግኝቶ ኢትዮጵያን ይገዛል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ኢህአዴግም እዛ ጣጣ ውስጥ ገብቶ ነው መውጣት ያቃተው፡፡ ከኢህአዴግ በላይ ሀይል እና አቅም አግኝቶ የሚንቀሳቀስ ቡድን አላየሁም፤ ነገር ግን ጨዋታው ለኢህአዴግም ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ የሰከነ ስራ መስራት እና መተባበር ወሳኝ ነው፡፡ አለበለዚያ
በህልም እና በቅዠት መሞኘት ነው፡፡ ኢህአፓ እና መኢሶን እኮ ቀላል ድርጅቶች አልነበሩም፡፡

አዲስ አድማስ

No comments:

Post a Comment