Saturday, January 4, 2014

ኦቦ ተማም ባቲ በጀነራል ከማል ገልቹ የሚመራው ኦነግ ቃል አቀባይ ውይይቱ በተለይ ከአፄ ሚኒሊክ ታሪክ ጋር የተያያዘ

Abe Tokichaw

ኦቦ ተማም ገለቶማ!!!
ኦቦ ተማም ባቲ በጀነራል ከማል ገልቹ የሚመራው ኦነግ ቃል አቀባይ ናቸው፡፡ በአንድ ፓልቶክ ሩም ላይ ቀርበው ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ ተከታትያቸው ነበር፡፡ በጣም አስገራሚ ሰው ሆነው አገኘኋቸው፤ እናም አክብሮቴ ካሉበት ይድረስልኝ… ገለቶማ ብያቸዋለሁ!
ውይይቱ በተለይ ከአፄ ሚኒሊክ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነበር፡፡
አቶ ተማም ያሉት ነገር በአጭር ይጠቃለል ቢባል የሚከተለውን ይመስላል፡፡

ሚኒሊክን ቅዱስ የሚሉ ወገኖች ሃጥያት የላቸውም፡፡ ነገር ግን እነዚህ ወገኖች ሚኒሊክ ለሁሉም ቅዱስ ነበሩ፡፡ ስለሚኒሊክ ክፉ የተናገረ በሙሉ እርኩስ ነው ሲሉ ስህተት ሰሩ ማለት ነው፡፡ ሚኒሊክን ርኩስ ነበር የሚሉ ወገኖችም ነውር የላቸውም፡፡ ስለ ሚኒሊክ ጥሩ የሚናገሩትን በሙሉ ርኩስ ናቸው ብለው ከደመደሙ ግን ችግር አለ ማለት ነው፡፡
(እዝች ላይ በቅንፍ እኔ ጣልቃ እገባለሁ… ሚኒሊክን ቅዱስ ናቸው የሚሉ ወገኖች ሚኒሊክ በገዛ ወገናቸው ላይ ያደረጉትን ጦርነት ቅዱስ አሉ ማለት አይደለም፡፡ እንደዛ ሲሉ የሰማችሁ ካላችሁ ጠቁሙኝ! እዚህ ቅንፍ ውስጥ ስለ ቴዲ አፍሮ ካነሳን ቅንፉ ይረዝምብናል…. ይርዘም ስንቱ ችግር ረዝሞብን የለ እንዴ ከተባለ ግን… ቴዲ የሚኒሊክ ጦርነት “ቅዱስ ጦርነት ነው” አለ የተባለው የእንቁ መጽሄት ስህተት ነው እንጂ እኔ አላልኩም ብሏል፡፡ ይሄንን የእንቁ መፅሄት ሰዎችም አምነዋል፡፡ ቴዲ ይሄንን ንግግር ብሎት እንኳ ቢሆን በግዜ ስህተቱን አርሟል ማለት ነው እና አበጀህ ልንለው ነው የሚገባው እኛ ከስንቱ ስህተት ጋር ተስማምተን እንኖር የለ እንዴ….!)
ከቅንፋችን ስንወጣ…. እንደ አቶ ተማም ባቲ፤ ኢትዮጵያውያን የሚጋሩት ታሪክ እንዳላቸው ሁሉ የማይጋሩትም ታሪክ አላቸው፡፡ ይሄን ልዩነት ይዘው ተከባብረው መኖር የሚችሉባት ሃገር እንድትኖረን መጣር የሁላችንም ድርሻ ነው፡፡ ሚኒሊክን Celebrate ማድረግ የሚፈልግ መብቱ ነው፡፡ ያንን መከልከል አግባብ አይደለም፡፡ ነገር ግን ሚኒሊክ በደል የፈፀሙባቸውን ህዝቦች ወይም የcelebratioኑ አካል መሆን የማይፈልጉ ወገኖችን በግድ Celebrate አድርጓቸው ማለት ስህተት ነው፡፡
የኢህሃዴግ ዋና የስራ ሂደት ባለቤቶች (እርሳቸው እንደውም ህውሃቶችን ነው ያሉት) ዛሬ ሚኒሊክን አብረውን እየወቀሱ እና የሚኒሊክ በደል ላይ ሙጥኝ እንድንል የሚያደርጉት እነርሱ እያደረሱብን ያለውን በደል ሊያዘናጉን ፈልገው እንደሆነ ይጠረጠራል እና ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊነቃባቸው ይገባል ብለዋል፡፡ (ዳንኤል እና አሉላ ሰምታችኋል!!!)
በጥቅሉ ሰውዬው አንጀት ላይ ጠብ የሚል ከሰሙት በኋላ በውሃ አወራርደውት ቢተኙ አሪፍ ራት የሚሆን አጥጋቢ ማብራሪያ ለመላው ኢትዮጵያዊ ሰጥተዋል፡፡
እጅግ ተስፋ በሚያስቆርጡ ዘመኖች ሁላ እንዲህ ተስፋ የሚፈነጥቁ ግለሰቦች እና ድርጅቶች እንዲኖሩ ያደረገ እግዚአብሄር እግዚአብሄር ይስጠው፡፡ እኛም ምስጋና እንሰጠዋለን፡፡
የኦነግ ሊቀመንበር ጀነራል ከማል ገልቹ፤ ጀነራል ሃይሉ ጎንፋ እንዲሁም መላው ተከታዮቻቸው እና ደጋፊዎቻቸው፤ የብዙሃኖችን ቀልብ ስባችኋልና እንኳን ደስ አላችሁ፡፡
እንኳንም ኖራችሁ እላለሁ!
ባዬ ገለቶማ ብዬም እጨምራለሁ!
በመጨረሻም በአቶ ተማም ንግግር ቻው እንባባል፤ (የጠቀስኩት ንግግር በሙሉ ቃል በቃል አለመሆኑን ለመግለፅ እወዳለሁ)
“የአማራ ህዝብ ሚኒሊክን “ኦሮሞን ደብድብልኝ” ብሎ አልወከለውም፡፡ ህውሃትንም የትግራይ ህዝብ “ሂድና ህዝቡን አጎሳቁል” ብሎ አልወከለውም፡፡ ምን ጊዜም ቢሆን መታገል ስርአትን ነው እንጂ ህዝቦችን አይደለም ጭቁን ሀዝቦች በሙሉ የዛሬ በደል አጥፍተን ለሁላችንም የምትሆን ኢትዮጵያ እንድትኖረን እንትጋ!”

No comments:

Post a Comment