Friday, March 7, 2014

ሰጪው ሕዝብ ሆይ፣ ተቀበል!!

Agegnehu Asegid
ሕዝብ ሆይ! እስከዛሬ “ሕዝብ አይወቀስም” የሚል የጋራ ስምምነት ውስጥ ተጎሽበህ ከወቀሳዎች ክልል ውጪ ሆነህ አሳልፈሃል። ወቀሳን የአንደበትህ ጌጥ አድርገህ በህዝብ አይከሰስም መርህ ብዙ ተከሳሾች ፈልፍልሃል። እኔ ግን የስምምነቱን አጥር ጥሼ ልወቅስህ መጣሁ።
ሕዝብ ሆይ ተቀበል!!

እኔ የምልህ ሕዝብ አንቀላፍተሃል እንዴ? ብዙ ነቄዎች “ሕዝብን ለማንቃት…” በሚል ሰበብ ተደራጅተው ዓላማቸውን ሲያሳኩ አያለሁ። አልነቃህም ማለት ነው? መች ነው የተኛኸው? ኸረ ለመሆኑ ምንስ ላይ ተኛህ? እንደምታውቀው “አልጋው” ተይዟል። አልጋውን ለመጠበቅ በዓይናቸው እንቅልፍ የማይዞር ሰዎች ተኝተውበታል። እስቲ አሁን በፈጠረህ እንቅልፍ ላይተኙ አልጋን መቆጣጠር ምን ይሉታል? ብዙዎች ይህን አይተው አልጋውን፣ “እንቅልፍ አልባው አልጋ” ሲሉ ይጠሩታል፤ ባለ አልጋውንም “እንቅልፍ የሌለው እንቅልፍ አምጪ” ይሉታል። ….እሺ እነሱንስ ተዋቸው፤ አንተ ግን አልጋው ተይዞብህ ምን ላይ ተኛህ? መደብ ላይ አስተኙህ እንዴ? ነው ዝም ብለህ መሬት ላይ ነው የተኛኸው? ወይስ በቁምህ ነውየተኛኸው? …እንዴት ደክሞሃል ጃል! ግን ምን ሰርተህ ደከመህ? መቼም ሌሎችን ስትወቅስ መሆን አለበት።


ያልነቃኸው ሕዝብ ሆይ! ተቀበል!!
“በሀገሩቱ አንድም ጠንካራ ፓርቲ የለም!” ስትል ትደመጣለህ ደግሞ። አየህ ሌሎች መጥተው ነፃ እንዲያወጡህ ነው የምትፈልገው። ሁሌም የምላስህ ጥቁምታ ወደሌሎች ነው። ለምን እራስህን ነፃ አታወጣም፤ እውነቱ እሱ ነው! “እውነት ደግሞ ነፃ ያወጣሃል”
ተቀበል አንተ ነፃ ያልወጣህ ሕዝብ!!
ታውቃለህ አይደል ደግሞ አንባገነን እንደሆንክ? አዎ አንባገነን ነህ! አንተ ግን መንግስትን አንባገነን ነው ስትል ትወቅሳለህ። ቢገባህ መንግስት ሁሉ የሕዝብ ፍቃድ ነው። ኸረ እንደውም መንግስት ሕዝብ ነው ይባልልሃል። ካላመንክ ሂድ የታች ክፍል ሲቪክስ መፅሐፍ አገላብጥ። ታዲያ መንግስት አንተ ከሆንክ፣ መንግስት አንተን ከሆነ… መንግስትም አንባገነን ነው ካልክ፣ አንባገነን አይደለሁም ብለህ ልትክድ ነው? ከአምባገናዊ ስርዓት ጋር ተስማምተህ መኖርህስ በውስጥህ ያለውን አንባገነናዊ አስተሳሰብ አያሳይም? እስቲ እውነቱን ተናገር አትዋሽ። ውሸት በሕዝብ አያምርም!
ተቀበል አንተ አንባገነን ሕዝብ!
እየሰማህ ነው አይደል ሕዝብ? አንዴ ዙሪያህን ተመልከትማ። በየአካባቢው ፀዳት የለም። የሕዝብ የተባሉ ንብረቶችህንም እይ! ተቋማትህን እይ! አውቶብሶችህን እይ! “ወራጅ” ብለህ ሹፌሩ ባይሰማህ እየደበደብክ የምታወላልቃቸውን። አመፅ ቢነሳ በድንጋይ ቡን የምታደርጋቸውን። ግን በስምህ ይጠራሉ። የምትገለገልባቸውም አንተው ብቻ ነህ! …አንተው ነህ በየጎዳናው ቆሻሻ የምትጥል! ከዛ “የሚመለከተው አካል…” የሚል የተለመደው ፉጨትህን ታፏጫለህ። አንተን አይመለከትህም ወይ? አንተ ምን እየተመለከትክ ነው የሚመለከተው አካል የምትጮኸው?
ተቀበል ለራስህ ጉዳይ ተመልካች የምትሻው ሕዝብ!
ራስህን ንቀሃል። ከራስ ቀድመህ የነጭ ሕዝብን ማክበር ይቀልሃል። እንግዳ አክባሪ ነኝ ትላለህ እንጂ፣ ለእንግዳ ተንበርካኪ ነህ። ቅድሚያ ለሌሎች የሚል ሞኝ መንፈስ ልብህን ተቆጣጥሮታል። በጠራራ ፀሐይ በተሰለፍክበት ከኋላ መሰለፍ የነበረበትን ነጭ ስታስቀድም አላየሁም። “ኢትዮጵያ ከመኖር…” እያልክ እያማረርክ እራስህ የፈጠርከውን ሀገር በምድር በሰማይ ጥለህ አልተሰደድክም? የቀረው አካልህስ ቢሆን ውስጥ ነው የሚባል ነው? እየተንፏቀቀም ቢሆን ሀገሩን ጥሎ መውጣት እንደሚፈልግ ልትክድ ነው? ኸረ ተው ሕዝብ ውሸት ባንተ አያምርም!
የአካልህ ፍንቃጭ የሆኑ ግለሰቦች በጉልበተኞች ሲመዘበሩ ዝም አላልክም? ሲደበደቡ ፊትህ አላዞርክም? ሲጮሁ ጆሮህን አልዘጋህም? የግለሰቦቹስ ሌላ ነው ብለን ብንተወው፣ እራስህ ስትመዘበር፣ ስትደበደብ ችለህ ዝም አላልክም? ዝም ብለህ ወቀሳህን ሌሎች ላይ አልሰነዘርክም? ማንም ካንተ የበለጠ ሃይል እንደሌለው እያወክ ድረሱልኝ ብለህ አልጮህክም? …ወድቆ መነሳት ሲችል፣ አንሳኝ በሚል አባቱን ሽቅብ የሚያይ ልጅ እኮ ነው የመሰልከው።
ተቀበል ሃይልህን የማታውቀው ሕዝብ!!
በአባቶችህ እና ምዕራባውያን ባራገፉብህ ባህል መሃል ከመንከራተት ውጪ ምን የራስህን በሃል ፈጠርክ? የፈጠርከው የለም። መቀላቀል ብቻ። አየህ ሕዝብ ቆየህ ከቀላቀልክ! እስቲ የራስህን ነገር ፈጥረህ አሳይ። የሚስማማህን ምረጥ እንጂ ያገኘኸውን አታንሳ። እየሰማህ ነው ህዝብ? እስቲ ጆሮህን ኮርኮር አድርገው?
ተቀብሎ የሚሸከም እንጂ አስቦ የሚፈጥር አዕምሮህን የዘነጋኸው ሕዝብ ሆይ! እስቲ ተቀበል። በርግጥ መቀበል ትፈራለህ። ሁሉን መስጠት ነው የምትወደው። ልብህን ሰጥተሃል። ተስፋህን ሰጥተሃል። ንቃትህን ሰጥተሃል። ደንዳና ትከሻህን ሰጥተሃል!! ቢሆንም ተቀበል እልሃለው!!
ተቀበል!!!!

No comments:

Post a Comment