Wednesday, April 16, 2014

በተወሰኑ ስኬቶች የተሸፈኑ በርካታ ፈተናዎች

ኢትዮጵያ አገራችን አንገቷን በኩራት ቀና የምታደርግባቸው ስኬቶች እየታዩ መሆናቸውን፣ የአገሩን ዕድገት በጉጉት የሚከታተል ማንኛውም ዜጋ የሚመሰክረው ነው፡፡
በተለይ በኢኮኖሚው መስክ የሚስተዋለው በተከታታይ ዓመታት የተገኘው ውጤት ኢትዮጵያ አገራችን በታሪኳ አይታው የማታውቀው ነው፡፡ ለበርካታ ዓመታት ድህነትና ኋላ ቀርነት በተንሰራፋባት አገር ውስጥ ተስፋ ሰጪ ጅምሮች እየታዩ ናቸው፡፡ እነዚህ ስኬቶች እየተገኙ ያሉት ደግሞ ይህ ትውልድ እየከፈለ ባለው ዋጋ ነው፡፡ 
ስኬቶችን አንስተን ስንወያይ ደግሞ ችግሮችን መሸፋፈን የለብንም፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ታላላቅ የመንገድ አውታሮች፣ ታላላቅ የኃይል ማመንጫዎች፣ የቴሌኮምና የኢንዱስትሪ መሠረተ ልማቶች በከፍተኛ ወጪ እየተገነቡ ናቸው፡፡ እነዚህን ስኬች ከለላ በማድረግ የሚፈጸሙ ሕገወጥ ድርጊቶችም አሉ፡፡ ስኬቶችን የሚያደናቅፉ ፈተናዎች ስላሉ የተወሰኑትን ማየት ይገባናል፡፡

የመጀመሪያው ፈተና ሙስና ነው፡፡ እንደ ሰደድ እሳት አገሪቱን እየለበለበ ያለው ሙስና ከአነስተኛ መንግሥታዊ ተቋም እስከ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ድረስ ተንሰራፍቷል፡፡ መንግሥት ራሱ ጉያው ውስጥ ባሉ ግለሰቦችና ቡድኖች አማካይነት ሙስና የሥርዓቱ ጠንቅ እንደሆነ ነግሮናል፡፡ በአንድ ወቅት ባካሄደው ዘመቻም የተወሰኑ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውሏል፡፡ ሙስናን ለመዋጋትም ቃል ገብቷል፡፡ ነገር ግን አሁንም ሙስና በኔትወርክ በተደራጁ ኃይሎች አማካይነት እየተከናወነ ነው፡፡ 
ለበርካታ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች፣ ክሊኒኮች፣ መኖሪያ ቤቶች፣ የመገበያያ ሥፍራዎች፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች፣ የወጣቶች መዝናኛ ማዕከላት፣ ቤተ መጻሕፍት፣ ወዘተ ግንባታ መዋል የሚገባው ሀብት በውጭ ምንዛሪ ወደ ውጭ እንዲሸሽ ይደረጋል፡፡ ያልተገባ ጥቅም በማግኘት ሕንፃዎችንና የተለያዩ ንብረቶችን የሚያፈሩ ግለሰቦች በብዛት እየተፈጠሩ ናቸው፡፡ ትናንት ምንም የሌላቸው ምስኪኖች ዛሬ የናጠጡ ከበርቴዎች እየሆኑ ናቸው፡፡ ሙስና የአገርን ሀብት ከማውደሙም በላይ ለአዲሱ ትውልድ መጥፎ አርዓያ የሚሆኑ ሰዎችን እያፈራ ነው፡፡ ይህ የአገራችን ትልቁ ፈተና ማሳያ ነው፡፡ 
ኢትዮጵያ አገራችን በሰላማዊና በተረጋጋ ድባብ ውስጥ የምትኖረው ሕዝባችን ሕግ አክባሪ በመሆኑ ነው፡፡ የሕግ የበላይነትን ተማምኖ የሚኖር ሕዝብ ሁሌም ከለላው ሕግ ብቻ ነው፡፡ የሕግ በላይነት አለ በሚባልባት አገራችን ውስጥ ሕገወጦች እየተበራከቱ ናቸው፡፡ የመንግሥት ተቋማትን የሚመሩ ባለሥልጣናትን፣ ሕግ ተርጓሚዎችን፣ የፀጥታ ኃይሎችንና ሲቪል ሰርቪሱን ወደ ሕገወጥነት የሚገፋፉ ቡድኖች አሉ፡፡ ፍትሕን በገንዘብ ማፈን የሚፈልጉ፣ የራሳቸውንና የቡድናቸውን ጥቅም ለማስከበር ሲሉ ብቻ የፍትሕ ሥርዓቱን ከመደርመስ የማይመለሱ ማፍያዎች አሉ፡፡ ፍትሕ እንዲዘገይ ወይም እንዲነፈግ በማድረግ ሕዝብ የሚያስለቅሱ ኃይሎች አሉ፡፡ የሕግ የበላይነትና ልዕልናን በመጋፋት የሰው ንብረት የሚቀሙ፣ የሚያሳድዱ፣ መቆሚያ መቀመጫ የሚያሳጡ ሃይ ባይ ያጡ ግለሰቦችና ቡድኖች ትልቅ ፈተና እየሆኑ ናቸው፡፡
የመቻቻልና የመከባበር ተምሳሌት በሆነች አገር ውስጥ ፀብና ጥላቻ በማስፋፋት፣ ማንነትን ሳይቀር በመጋፋት የዜጎችን ክብር የሚያዋርዱ ሞልተዋል፡፡ ከሥልጡን ውይይትና ክርክር ይልቅ በኃይል ፍላጎታቸውን በሌላው ወገን ላይ ለመጫን ሌት ተቀን የሚደክሙ አሉ፡፡ የመሰላቸውን አመለካከት በነፃነት በማንፀባረቃቸው ምክንያት ብቻ ያልሆነ ስያሜ እየተለጠፈባቸውና እየተፈረጁ የሚገለሉ ዜጎች የእነዚህ ኃይሎች ሰለባ እየሆኑ ናቸው፡፡ የፈለጉትን በመደገፋቸውና የማይፈልጉትን በመቃወማቸው፣ ብሔራቸውና ማንነታቸው እየተነቀሰ ሲወገዙ ይሰማል፡፡ በመቻቻልና በመከባበር ተምሳሌትነቷ በዓለም የምትደነቀዋ ኢትዮጵያ በጥላቻ አዕምሮዋቸው በተጋረደ ቡድኖች ምክንያት ትልቅ ፈተና እየገጠማት ነው፡፡
ለኢትዮጵያ አገራችን ዕድገትና ብልፅግና ሰለቸኝ ደከመኝ ሳይሉ ሌት ተቀን የሚማስኑ ያሉትን ያህል፣ በአሁኑ ጊዜ በተጨባጭ እየታዩ ያሉ ስኬቶችን በዜሮ የሚያባዙ ወገኖች በየቦታው ሞልተዋል፡፡ በአስቸጋሪ የመሬት ገጽና የአየር ጠባይ ውስጥ ታላቁን የህዳሴ ግድብ፣ ሌሎች የኃይል ማመንጫዎች፣ የመንገድና የባቡር ፕሮጀክቶች፣ ወዘተ እየገነቡ ያሉ ዜጎች ባሉበት አገር ውስጥ ተቃራኒውን በማከናወን ሕዝብን የሚያስለቅሱ አሉ፡፡ የተሰጣቸውን የሕዝብ አገልጋይነት ኃላፊነት ወደጎን በመግፋት ሥራቸውን እየወዘፉ፣ ‹‹… ራዕይ እናሳካለን›› በሚል መፈክር ውስጥ የተሸጎጡ ብዙ ናቸው፡፡ ከአገራዊ ራዕይ ይልቅ የራሳቸውንና የመሰሎቻቸውን ጥቅም እያስቀደሙ ሕዝቡን የሚያስለቅሱ አሉ፡፡ በስብሰባና በግምገማ ሰበብ ከቢሮአቸው እየጠፉ ሰደልሉ የሚውሉ አሉ፡፡ ሕዝቡ መብቱን ሲጠይቅ ያሸማቅቃሉ፣ ያስፈራራሉ፡፡ እንደነዚህ ዓይነቶችን ተሸክሞ መጓዝ ለአገሪቱ ትልቅ ፈተና ሆኗል፡፡ 
በአሁኑ ወቅት በበርካታ ጉዳዮች ዙሪያ በርካታ ፈተናዎች እየታዩ ናቸው፡፡ ብዙዎችን በዝርዝር ማንሳት ቦታ ስለማይበቃን እንጂ የአገሪቱን ስኬቶች የሚያደበዝዙ ፈተናዎች የየዕለት ገጠመኝ እየሆኑ ናቸው፡፡ አንድ ቀላል ምሳሌ እናንሳ፡፡ ከተወሰኑ ወራት ወዲህ የግል ጋዜጦችን በቀናቸው ወጥተው ማየት ብርቅ ሆኗል፡፡ ማተሚያ ድርጅቱ ብሔራዊ ፈተና ስለሚያትም በማሽን እጥረት ችግር እንደገጠመው ይናገራል፡፡ ጋዜጦቹ ይህንን ችግር በመገንዘብ ማተሚያ ቤት የሚገቡበትን ጊዜ ወደኋላ በመሳብ ጥረት ቢያደርጉም፣ በተለይ ከተወሰኑ ሳምንታት ወዲህ በ48 እና በ72 ሰዓታት እየዘገዩ እየወጡ ናቸው፡፡ ጋዜጦቹ የችግሩን መጠን በመገንዘብ የበኩላቸውን ጥረት ቢያደርጉም ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰባቸው ነው፡፡ የማወቅ መብት ያላቸው አንባቢያን ጋዜጦችን በጊዜ ማግኘት አልቻሉም፡፡ በተለይ በዕረፍት ቀናት ዘና ብለው መረጃ ማግኘት የሚገባቸው ዜጎች በጋዜጣ እጦት ተቸግረዋል፡፡ አዲስ አበባ ከተማ በጠላት የተወረረ እስኪመስል ድረስ በዕረፍት ቀናት ጭር ብሎ ሲውል ለምን ብሎ የሚጠይቅ የመንግሥት አካል አለመኖሩ እያነጋገረ ነው፡፡ በማተሚያ ቤቱ ብቃት ማነስ ምክንያት ይህ ሁሉ አበሳ ሲታይ መንግሥት ዝም ማለቱ ከማሳዘኑም በላይ ወዴት እየተጓዝን ነው ያስብላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ አንደኛው የአገራችን ትልቅ ፈተና ሆኗል፡፡ የፕሬስ ነፃነትን ወይም ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት የሚጋፋ ፈተና፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ በኢኮኖሚውና በማኅበራዊው መስክ እያሳየችው ያለው ስኬት ጥሩ ነው ቢባልም፣ በሌላ በኩል የምንመለከታቸው ችግሮች ያስከፋሉ፡፡ ግማሽ ጎፈሬ ግማሽ ልጩ የሆነው የአገራችን ሁኔታ ሊቀየር ይገባል፡፡ አንዱ ላቡን ጠብ አድርጎ እየሠራ ሌላው የሚያላግጥበት ድባብ መለወጥ አለበት፡፡ አንዱ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ይገንባ ሲል ሌላው ኢ ዲሞክራሲያዊ ሲሆን፣ አንዱ የሰው ልጆች መብት ይከበር ሲል ሌላው አፈናን ሲያበረታታ፣ አንዱ በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተች አገር ትኑረን ሲል ሌላው በእኔ የበላይነት ሥር ካልሆነ ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ ካለ፣ አንዱ ፍቅር የሰፈነበት ማኅበረሰብ እንገንባ ሲል ሌላው ጥላቻና ክፋት ካልነገሡ ካለ፣ አንዱ የሕግ የበላይነት ይኑር ሲል ሌላው ሕገወጥነትን ለማንገስ ከተሯሯጠ፣ አንዱ ሙስና የትውልድ ገዳይ ነው ሲል፣ ሌላው የሕይወቴ እስትንፋስ ነው ብሎ ከፎከረ የምትጎዳው አገራችን ናት፡፡ የሚጎዳው ወገናችን ነው፡፡ ስለዚህ ከስኬቶች ጀርባ የተደበቁ በርካታ ፈተናዎች ይፈተሹ፡፡ ለአገር አይጠቅሙምና!   
ከሪፖርተር

No comments:

Post a Comment