Friday, April 4, 2014

ነጻ መብራት፣ ስልክ እና ውሃ በካሳ መልክ ሊሰጥ ነው

ዳዊት ከበደ ወየሳ
በመብራት መቆራረጥ የሚሰቃየው የኢትዮጵያ ህዝብ “እፎይ” የሚልበትን ቀን ሁሉም ይናፍቃል። የአባይ ወንዝ ከተገደበ በኋላ የሚመነጨው የኤሌክትሪክ ሃይል ከኢትዮጵያ አልፎ ለሱዳን እና ለግብጽ እንደሚበቃም ይነገራል። ከዚህ ግድብ በተጨማሪ የግልገል ጊቤ 2 እና 3 ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ የሚኖራት የመብራት ሃይል በአስር እጥፍ እንደሚጨምር የዘርፉ ሙያተኞች ይመሰክራሉ።
በዚህ አጋጣሚም በመብራት መቆራረጥ እና እጦት የሚሰቃየውም ህዝብ የሚካስበት አጋጣሚ ይፈጠራል። መብራት ሃይል ዛሬ ያወጣው መግለጫ እንዳረጋገጠው ከሆነ፤ “እስካሁን መብራት ያጣውን የኢትዮጵያ ህዝብ ነጻ የኤሌክትሪክ ሃይል ወይም ግምቱ ታውቆ በጥሬ ገንዘብ ካሳ ይከፈለዋል።” ተብሏል። የቴሌኮምዩኒኬሽንም በበኩሉ የመብራት ሃይልን ተነሳሽነት አድንቆ በቴሌም በኩል እስካሁን በኔት ዎርክ መቆራረጥ ሲሰቃይ የነበረውን ህዝብ ለመካስ፤ በኢትዮጵያ የሚሰራውን “አባ ዱላ” የሚል ስያሜ የተሰጠውን የስልክ ቀፎ ለደንበኞቹ በነጻ እንደሚሰጥ ወይም ከመቶ እስከ 1ሺህ ብር ዋጋ የሚያወጡ ሲም ካርዶችን የሚያድል መሆኑን አሳውቋል።

የመብራት ሃይል እና የቴሌን ካሳ አከፋፈል ያደነቀው የውሃ ሃብት ልማት በበኩሉ በሸገር ሬድዮ ሰበር ዜና አሰምቷል። ሰበር ዜናውን ያነበበው አለምነህ ዋሴ ሲሆን፤ “አስደሳች ዜና ለውሃ አፍቃሪዎች” በማለት ነበር ዜናውን የጀመረው። በመቀጠልም… የውሃ እና ሃብት ልማት ሚንስቴር ዛሬ እንዳስታወቀው ከሆነ፤ “በቅርቡ ውሃን በፕላስቲክ እየሞላን የመሸጥ ፈቃድ ከፌዴራሉ መንግስት ተቀብለን ስራችንን ለመጀመር በዝግጅት ላይ ነበርን። የገፈርሳ የአባ ሳሙኤል እና የቀበና ውሃዎችን እያጣራን ለህዝቡ ጓዳው ድረስ በቧንቧ አቅርበንለታል። አሁን ግን የመብራት እና የቴሌን ፈለግ በመከተል ህዝቡን ለመካስ ተነስተናል። አባይ ይገደባል፣ ህዝቡም ነጻ ውሃ ያገኛል።” ብለዋል። በዚህም መሰረት የውሃ እና ሃብት ልማት በቅርቡ እያሸገ የሚሸጣቸውን የፕላስቲክ ውሃዎች ለደንበኞቹ በነጻ የሚሰጥ መሆኑን ገልጾ፤ ይህንን የሚያስተባብሩ እና የሚያድሉ ሰራተኞቹ ወደ መንደሮች እና ኮንዶሚኒየሞች ሲመጡ፤ ህብረተሰቡ አንድ ለአምስት በመሆን አስፈላጊው ትብብር እንዲያደርግላቸው የባለልጣኑ መስሪያ ቤት አደራ ብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ “ወንዞች ይገደቡ ይዋሉ ለልማት” በሚለው የድሮ የደርግ ዜማ በመታጀብ ዜናውን ለህዝብ አቅርቦ የነበረው ሰይፉ ፋንታሁን ባልታወቁ ታጣቂዎች መታገቱ የ-ኢትዮፒሊንካ አዘጋጅ የሆነው ብርሃኔ ለዝግጅት ክፍላችን ገልጿል። እንደብርሃኔ አባባል ከሆነ፤ “ሰይፉን ያገቱት… ይህን የመሰለ ዜና… እንዴት በደርግ ዜማ አጅበህ አቀረብክ በማለት ነው። እንደአሰራር የሰይፉን ድርጊት ብንቃወምም የአጋቾቹን ድርጊት ግን አጥብቀን አውቅዘናል። ይህንንም ድርጊት በመቃወም ለጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ ደብዳቤ ጽፈናል።” ብሏል።
እኛም ዜናችንን ከማጠናቀቃችን በፊት “እንኳን ለዛሬው April Fool በሰላም እና ጤና አደረሳቹህ እንላለን።” ከላይ በApril Fool ስም ዜናውን እናቅርብ እንጂ እውነት ይህ ህዝብ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ መካስ እንዳለበት እናምናለን።

No comments:

Post a Comment