Wednesday, November 26, 2014

በጋምቤላ ክልል ያለው የኤች አይቪ ስርጭት በሀገር አቀፍ ደረጃ ካለው ስርጭት በላይ መሆኑ ተገለፀ

በ2 ሰዓታት 2ሺ ሰዎችን ለመመርመር ታቅዷል
በሀገራችን ለ26ኛ ጊዜ የፊታችን ህዳር 22ቀን 2007 ዓ.ም የሚከበረውን የአለም የኤድስ ቀን አስመልክቶ ትናንት በካፒታል ሆቴል እና ስፓ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተገለፀው በአሁኑ ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለው የኤች አይ ቪ ስርጭት 1ነጥብ 5 በመቶ ሲሆን፤ በጋምቤላ ክልል ያለው ስርጭት ግን 5 ነጥብ 9 በመቶ ሆኖ ተገኝቷል። በክልሉ ያለው የኤች አይ ቪ ስርጭት ከፍተኛ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፣ በተለይ በሴት ወጣቶች ላይ ያለው ስርጭት አሳሳቢ ነው ተብሏል። በክልሉ በከፍተኛ ሁኔታ ለኤች አይቪ ተጋላጭ ናቸው በተባሉት ሴቶች ዘንድ ያለው ስርጭት 8 በመቶ ሲሆን፣ በወንዶች ላይ ደግሞ 5 በመቶ መሆኑ ተገልጿል። በክልሉ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ብቻ 380 አዲስ የኤች አይቪ ተጠቂዎች መመዝገባቸውንም ይፋ ሆኗል።
news
በክልሉ ያለው የኤች አይቪ ስርጭት ከፍተኛ እንዲሆን ያደረገው በህብረተሰቡ ዘንድ ስለኤች አይ ቪ በሽታ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑ ነው ያሉት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዲዱሞ አደር፣ ከዚሁ በተጨማሪም ክልሉ ከተለያዩ አምስት ብሔረሰቦች የተዋቀረ እንደመሆኑ የየብሔረሰቡ ባህል በዚህ ስርጭት ከፍተኛ መሆን የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልፀዋል። በክልሉ በተለይ የውርስ ጋብቻ የተለመደ መሆኑን የገለፁት አቶ ዲዱሞ፤ በዚህም አንድ ወንድ ሲሞት የሞተበትን ምክንያት ሳያጣራ ልጅ ወይም ወንድም የዚያን ወንድ ሚስት ስለሚወርስ ይህም የበሽታውን ስርጭት ከፍ ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንዱ ሆኗል። ከሌሎች አካባቢዎች ለየት ባለመልኩ ወንዶች እና ሴቶች በነፃነት የሚገናኙበት “ፍሪ ዴይ” የሚባለው ባህልም ሌላኛው የዚህ ምክንያት እንደሆነ ኃላፊው ገልጸዋል።

በጋምቤላ ክልል ያለውን የኤች አይ ቪ ስርጭት ለመግታት ያግዝ ዘንድም የዘንድሮው የዓለም የኤድስ ቀን በጋምቤላ ክልል “አንድም ሰው በኤድስ እንዳይያዝ፣ እንዳይገለል እና እንዳይሞት ኃላፊነታችንን እንወጣ” በሚል ቃል ይከበራል። በዚህ በዓል ላይ ከፍተኛ የሆነ የምክር አገልግሎት እና ምርመራ የሚካሄድ ሲሆን፤ ይህንንም በአለም አቀፍ የድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ለማስመዝገብ ታስቧል። ከበዓሉ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ህዳር 21 ቀን 2007 ዓ.ም በጋምቤላ ስታዲየም በሚካሄደው የምክርና ምርመራ አገልግሎት በ8 ሰዓታት ውስጥ 2ሺህ ሰዎችን ለመመርመር ታስቧል። ይህን በማድረግም ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት አሜሪካ እና አርጀንቲና በ8 ሰዓታት ውስጥ 1ሺ 380 ሰዎችን በመመርመር ይዘውት የነበረውን ሪከርድ ለማሻሻል ታስቧል።
ሰዎች በእለቱ ተገኝተው ምርመራ እንዲያደርጉ በመቀስቀስ እና ወደ ምዝገባም በመግባት ላይ መሆናቸውን የገለፁት አቶ ዲዱሞ፣ በተያዘው እቅድ መሠረት እያንዳንዱ ቀበሌ እንዲሁም ሁለት ቤተክርስቲያናት እያንዳንዳቸው ከሁለት መቶ በላይ ሰዎችን እንዲያስመረምሩ ይደረጋል። ይህ የምክር እና ምርመራ አገልግሎት በክልሉ ለአንድ ሳምንት የሚቀጥል ሲሆን፤ በአጠቃላይ ከ5ሺህ በላይ ሰዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።
የኤች አይ ቪ ወረርሽኝ በአለማችን ከተቀሰቀሰ ከ30 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን፤ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ 78 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው 35 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ 800ሺህ ኢትዮጵያውያን ለቫይረሱ የተጋለጡ ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ኢትዮጵያውያን መካከልም 200ሺዎች ህጻናት ናቸው። በአለፈው የፈረንጆች 2013 ዓ.ም ብቻ በአለማችን ላይ 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን አዲስ የቫይረሱ ተጠቃሚዎች መመዝገባቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

No comments:

Post a Comment