Monday, February 17, 2014

የህወሓት ሰማዕታት አጭር ማስታወሻ (ናይ ህወሓት ሰማአታት ሐፂር መዘካከሪ)

1
ሰላሳ ዘጠኝ ዓመታት ወደኋላ…
“የአብዮቱ ደወል እየተደወለ ነው
ሕዝቦች ሆይ ተነሱ
ስለመብቶቻችሁም ቁሙ
ጠመንጃችሁን አንሱ
ጨቋኞቻችሁንም ታገሉ”
ይህ የመጀመሪያው የህወሓት መዝሙር ለ16 ዓመታት ያህል በሺ በሚቆጠሩ የትግራይ ወጣቶች አንደበት በሰሜን ኢትዮጵያ ተራራና ሸለቆዎች መካከል ተዘምሯል፡፡ የካቲት 11 ቀን 1967 ዓመተ ምህረትም እፍኝ የማይሞሉ ወጣቶች ማንም ቢሆን ‹ያደርጉታል› ብሎ ያላሰበውን ረዥሙን የትግል ምዕራፍ አንድ ብለው የጀመሩበት ዕለት መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ርግጥ ነው እነዚህ መስራቾች ብዙሃኑን ለትግል ከቀሰቀሱበት አጀንዳ ባሻገር የትግራይ ሕዝብን የማይወክል ድብቅ ፖለቲካዊ ፍላጎት የነበራቸው መንደርተኞች ስለመሆናቸው ‹‹ከትግራይ ሪፐብሊክ›› እስከ ‹‹ቋንቋ ተኮር ፌደራሊዝም›› ድረስ የተሻሻሉ ፕሮግራሞቻቸውን ጨምሮ በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ግና፣ የዚህ አጭር ማስታወሻ ዓላማ የፖለቲካውን ጥምዝምዞሽ መተንተን አይደለም፤ ስለህወሓት ከፋፋይነትና ጎጠኝነትም ማውራት አይደለም፤ በብሔር ውክልና ስም ከየስርቻውና ምርኮኛ ማጎሪያ ሰብስበው የፖለቲካ ድርጅትን ያህል ታላቅ ጉዳይ ወንዝ እና ጅረትን ሳጋና ማገር አድርገው ቀልስውላቸው ሲያበቁ፣ ሥልጣን በመስጠት የሀገር ሀብትን ዝንጀሮ የዋለበት ማሳ ስለማስመሰላቸውም አይደለም፤ ይህንን ታላላቆቻችንም ሆኑ እኛ ደጋግመን ብለነዋልና፡፡ የዚህ ማስታወሻ ዓላማ ቀጣዩ ማክሰኞ ሰላሳ ዘጠነኛው የህወሓት የምስረታ በዓል ከመሆኑ አኳያ፣ ደረቁን ፖለቲካ ለጊዜው አቆይቶ የወደቁትን ሰማዕታት ማወደስ ብቻ ነው፡፡
ወደ በርሃ የተወጣበትን ማህበረ-ፖለቲካዊ ምክንያት፣ ከግንባሩ ጥቂት መስራቾች ዋነኛ የነበረውና፣ በ1978 ዓ.ም በድርጅቱ ውስጥ በተገማሸረው የማሌሊት ማዕበል የተገፈተረው አረጋዊ በርሄ ‹‹A political history of Tigray People Liberation Front: Revolt, Ideology And Mobilization In Ethiopia›› በሚለው መጽሐፉ፡-
“የትግራይ ሕዝብ እየደረሰበት የነበረውን ጭቆና ከሌሎቹ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር ሲያነፃፅሩት የከፋ ሆነው አገኙት፡፡ ቀድሞ ትግራይ ከነበራት ታላቅነት ጋር ሲያነፅሩት ከፍተኛ ቁጭት ውስጥ ከተታቸው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ለወደቀው የትግራዋይነት ማንነት እንነሳ የሚለውን የቁጭት ስሜት መፍጠርም የቻለ ነበር” በማለት አለቅጥ ከመለጠጡም በላይ ጭቆናውን የትግራይ ሕዝብ ብቻ ለማድረግ ቢሞክርም እውነታው እዚሁ ውስጥ መገኘቱ አይካድም፡፡
የሆነው ሆኖ ከዚህ በታች የሚነበበው መልዕክት በሥልጣን ላይ ያሉትንም ሆነ በተጋፊነት እና መሰል ጉዳዮች ከድርጅቱ የወጡትን የሚወክል አይደለም፡፡ የመልዕክቱ ተደራሾች ‹‹ተነሱ! ለፍትህና ዲሞክራሲያዊ ትግል ተሰለፉ!›› የሚለው የግራ-ዘመሞቹን ልሂቃን ቅስቀሳ አምነው፣ ውድ ህይወታቸውን የገበሩት የትግራይ አርሶ አደሮች እና ሕፃናት ልጆቻቸው ብቻ ናቸው፡፡ ምክንያቱም እነርሱ በዱር በገደሉ የዋተቱት በዘውግ ማንነት ላይ የተንጠለጠለ ኢትዮጵያዊነትን ፍለጋ አልነበረምና፡፡ የአፍ መፍቻ ቋንቋንም ቢሆን ከመግባባት በዘለለ፣ የልዩነት መገለጫ ረዥም ግንብ አድርገው መውሰድን እንደማይፈቅዱ የቀደሙ ትርክቶች አስረግጠውሏቸዋል፡፡ በአናቱም ንግሠ-ነገሥት አፄ ዮሀንስ ትግራይን ተሻግረው አፄ ቴዎድሮስ የረገጡትን አንኮበር ሲረግጡ፣ የቋንቋ ችግር ያልገጠማቸው ስለመሆኑ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ይህም ኩነት ነው ዘውግና ቋንቋ የልሂቃኑ ግፊት እንጂ ሰማዕታቱ ዋጋ የከፈሉበት ጥያቄ ሊሆን እንደማይችል የሚያስረዳን፡፡
በዚህ አስራ ስድስት ዓመታት በፈጀው የትጥቅ ትግልም፣ ያለ ዕድሜና ፆታ ግደባ ሁሉም እንዲሳተፍ ተደርጎበታል፡፡ በ1988 ዓ.ም በታተመው የህወሓቱ ‹‹አሰር›› መፅሄት፣ በ1973 ዓ.ም አደይ አለማሽ የተባሉ የ64 ዓመት አዛውንት ትግሉን ተቀላቅለው እንደነበረ ተዘግቧል፡፡ ቀዳማይ ታጋይ የውብማር አስፋውም ‹‹ፊኒክስዋ ሞታም ትነሳለች›› በሚል ርዕስ ባሳተመችው መጽሐፍ ‹‹በትጥቅ ትግሉ መጀመሪያ ላይ የተወለዱ ሕፃናት፣ በትጥቅ ትግሉ መጨረሻ ላይ ለታጋይነት በቅተዋል›› ስትል መስክራለች፡፡ በርግጥ ይህ እውነታ ድርጅቱ ኃላፊነት በጎደለውና ጭካኔ በተሞላበት መልኩ፣ ከአስራ አምስት ዓመት በታች ያሉ ታዳጊዎችንም ሳይቀር በጦርነቱ ለመማገድ አለማመንታቱን ያስታውሰናል (በነገራችን ላይ በየትኛውም ሀገር በህፃናት ደምና አጥንት የወደቀ መንግስት ይኖር ይሆን እንጂ፣ የተገነባ ዲሞክራሲ ስለመኖሩ ሰምቼ አላውቅም) ህፃናቱን ግንባር እስከማሰለፍ የጨከነው ‹‹ነፃ አውጪው›› ህወሓት ግን በትግሉ አማካይ ዕድሜ ላይ ትግራይን የናጠውን ችግር እንኳን መጠቀሚያ ከማድረግ አልሰነፈም፡፡ ከምዕራባውያኑ፣ በድርቅ ቸነፈር ለተመቱት የክልሉ
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
2
ነዋሪዎች የተላከውን እህል ሸጦ ለማሌሊት ማጠናከሪያ ሲያውል፣ እናቶችና ህፃናት ግን ወደ ሱዳን ሲሸሹ ዋትተው በመንገድ እረግፈዋል፡፡
ይህ ሁሉ የመከራ ውጣ-ውረድ ኖሮም የትግራይ እናቶች ልጆቻቸውን ‹‹ጥይት ግንባራችሁን እንጂ፣ ጀርባችሁን እንዳይመታችሁ›› እያሉ መርቀው ወደ በረሃ መሸኘታቸውን የሚነግሩን የትግሉ ድርሳን ጸሐፊዎች ሳይቀሩ፣ ‹ዓላማችን ተቀልብሷል› እያሉ እንደኛው ማለቃቀስ ከጀምሩ ዓመታት መቆጠሩ እውነት ነው፡፡ መቼም ስለተቀለበሰ ትግል መፃፍ አጥንትን ይሰረስራል፤ ይህችን ሀገር በሁለንተናዋ የተሻለች ለማድረግ ከእናቶቻቸው ጉያ ወጥተው በርሃ የበላቸውን ልጆች፣ በትግሉ ሽንፈት ሃያ ሶስተኛ ዓመት ላይ ማሰብ የንቅናቄውን መሪዎች የሰብዓዊነት መንጠፍ ይነግራል፡፡ በዚህ አብዮት ክሽፈት ስር የፈራረሱ ቤተሰቦች የሚያቃትት ድምፅ፣ እስክርቢቶ በመያዣቸው ወቅት ብረት ነክሰው ያለቁ ህፃናት ደም ይጮሃል፡፡ በሞታቸው የሚያነቡ እናቶችን ሀዘን አለቅጥ የሚያበዛው ደግሞ፣ አምነው ልጆቻቸውን የሰጧቸው ታጋዮች ትግራይን እንኳን በጭካኔ መዳፍና በወታደር ጫማ ሲረግጧት ማየታቸው ነው፡፡ ትላንት የአብራክ ክፋዮቻቸውን እያነቀ በዘግናኞቹ እስር ቤቶች ሲያጉር በሀዘንና ፍርሃት ተውጠው ይመለከቱት የነበረው ደርግ በብዙ ደም ቢወድቅም፣ ‹የእኛ ነው› ያሉት ሕወሓት ከኦሮሚያ እስከ ኡጋዴን እነርሱ ያሳለፉትን መከራ ሲደግም መመልከት ምንኛ ነፍስን ይንጣል?!
መቼም የትጥቅ ትግል መስዋዕትነት፣ እስራት፣ ስቅየት፣ ረሃብ፣ ጥማት፣ ጉስቁልና፣ ሽንፈት፣ ድል… ቅፅበታዊ በሆነ ፍጥነት የሚፈራረቁበት መድረክ ነው፡፡ የድርጅቱን ተልዕኮ ስትወጣ፣ የዘንዶ ራት ከሆነችው ማርታ ተስፋይ ጀምሮም፣ ወታደራዊው መንግስት በሚያስተዳድረው ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርቦ በድፍረት ‹‹እዛ ያለው የተቆጣ ሕዝብ ነው›› ሲል የተናገረው አሞራው እና የ16 አመቷ ብላቴና ቀሺ ገብሩ ድረስ የሚቆጠሩ ሰማዕታት ዋጋ የከፈሉት ሀገሪቱን በብሔር ሸንሽኖ የማዳከምን አጀንዳ ለማንበር አለመሆኑም ይታወሳል፡፡ ይህ አይነቱ እውነታም ነው እልፍ አእላፍት ትግሪኛ ቋንቋ ተናጋሪ ጎበዛዝቶች፣ ወታደራዊው መንግስት ያሰለፋቸውን የጦር ጄቶች፣ ቢ.ኤሞች፣ ታንኮች… ፊት ለፊት ገጥመው የተፋለሙት ስለምን ነበር? ብለን እንድንጠይቅ የሚያስገድደን፡፡
የዘንድሮው የህወሓት ሰላሳ ዘጠነኛ ዓመት የምስረታ በዓል የትግሉን አቅጣጫ በቀለበሱት (አወናብደው በመሩት) እና ዛሬም በስልጣን ላይ በሚምነሸነሹት ‹‹ታጋዮች›› የክብር እንግድነት መዘከሩ ሰማዕታቱን ማቃለል ነውና በተቃውሞ ማስቆሙ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ስለምን? ቢሉ ያ ሁሉ ሕዝብ የተሰዋው፣ የትግራይ ተወላጆች ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኖቻቸው ተነጥለው ባይተዋር እንዲሆኑ፣ በስማቸው ጭቆና እንዲበረክት፣ አድሎአዊ አሰራር እንዲሰፍን፣ ፍትህ እንደጉሊት ቲማቲም በገንዘብ ተተምና እንድትቸረቸር፣ ዲሞክራሲ እንድትሴስን፣ ሥልጣን የሀብት ምንጭ እንዲሆን… አይደለምና ይሆናል መልሱ፡፡
በርግጥም ዓላማው መጠለፉን ለመረዳት የህወሓት መስራች የነበሩት እና የትግሉ ጀማሪዎች ደደቢት በርሃ በደረሱ ዕለት ጠብ-መንጃ መፍታት፣ መግጠም፣ መተኮስን ጨምሮ ወታደራዊ ሥልጠና የሰጡትን የአስገደ ገ/ስላሴ ልብ የሚነካ ታሪክ ማድመጡ ነው፡፡ አስገደ ወደ በርሃ የወጡት ከስድስት ወንድሞቻቸው ጋር ቢሆንም፣ 1983 ዓ.ም ግንቦት ሃያ ለመድረስ ዕድለኛ የሆኑት ግን እርሳቸው ብቻ ነበሩ፤ ወንድሞቻቸው በሙሉ ተሰውተው ነበር፡፡ ይሁንና የአስገደ መከራ ዛሬም አላበቃም፤ ልዩነቱ ያንጊዜ ብረት አንስተው በታገሉት የደርግ ስርዓት ሲሆን፣ ይህኛው ደግሞ በወታደራዊ ስልጠና አጠናክረው ለድል ባበቁት ህወሓት መሆኑ ብቻ ነው፡፡ ከጥቂት ወራት በፊትም ከእርሳቸው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ፣ ሶስት ልጆቻቸው ለአሰቃቂ እስር ተዳርገው ነበር፤ በዚህ የጭካኔ ስራም የሁሉም ታናሽ የሆነው ልጅ ለአእምሮ መታወክ በመዳረጉ፣ አዲስ አበባ ለህክምና ይዘውት በመጡ ጊዜ ሁኔታውን በሀዘን አጫውተውኛል፡፡ መቼም ህወሓት እና ሰማዕታቱ፣ ቃየልና አቤል ለመሆናቸው ከዚህ በላይ አስረጅ የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡
የሆነው ሆኖ አንዳንድ ቤተሰቦች የአስገደን ከወንድሞቻቸው መካከል በህይወት መትረፍ እንደዕድለኝነት ይቆጥሩታል፤ ምክንያቱ ደግሞ ሁሉም ልጆቹ አልቀውበት፣ ቀን ከሌሊት የወጡበትን በር በሰቀቀንና በሀዘን እየተመለከተ የሚቆዝመው ወላጅ ጥቂት ባለመሆኑ ነው፡፡ ሁለት፣ አንድ ልጅ ያጣውንማ በርህ ይቁጠረው ከማለት ባለፈ ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም፡፡ በዚህ ዕልቂትም በርካታ አረጋውያን ጧሪ አልባ ሆነው፣ ድህነትና ማጣት አዋርዶ ለልመና ዳርጓቸው ቁራሽ ፍለጋ ተንከራታች ከሆኑ ሁለት አስርተ ዓመታት አልፈዋል፡፡ በግልባጩ የሰማዕታቱን አስክሬን ተራምደው፣ የፈሰሰ ደም ረግጠው፣ ትግሉን እንደ ቁማር ‹ብናሸንፍ እንነግሳለን፤ ብንሸነፍ የአርሶ አደሩ ልጅ ነው የሚያልቀው› በሚል ተወራርደውበት ለስልጣን የበቁ ጉምቱ የአመራር አባላት፣ የትግራይ ሕዝብ ‹‹የአፓርታይድ መንደር›› በሚል ተቀፅላ በሚያውቀው እና በመቀሌ ከተማ በሚገኘው ገረቡቡ መንደር ባስገነቡት የተቀናጣ ቪላ ተንደላቅቀው፣ በሽንጠ ረዥም ዘመናዊ መኪና ተንፈላሰው፣ በብላኤ ስብዕ ድላቸው ተምነሽንሸው ስናስተውል ለዚህ ያደረሳቸውን የድርጅታቸውን ሰላሳ ዘጠነኛ የምስረታ በዓል በፌሽታና ደስታ ማሳለፋቸው የሚያስደንቅ አይሆንም፡፡ በነገራችን ላይ ግብዣው ምንም እንኳ የተትረፈረፈ ቢሆንም የሰማዕታቱ የተራቡ እናቶች ለመቀላወጥ እንኳ እንደማይፈቀድላቸው ሰምቻለሁ፡፡ ሌላው በእጅጉ የሚገርመው ደግሞ ዛሬም ድረስ የክልሉ ሕዝብ መዝሙር በትግሉ ዘመን የህወሓት መቀስቀሻ የነበረው የፋኖ ዜማ መሆኑ ነው፡፡
የቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንትና የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር ገብሩ አስራት ‹‹ደርግን ከመጣል ውጪ ያሳካነው ግብ የለም!›› እንዲል፤ ሰሞኑን ኢቲቪ የሚያሳየን ትዝታ ዘ-ህወሓትም ታንኮች ረዣዥም ተራሮችን ሲደበድቡ፣ ቀጫጭኖቹ ታጋዮች ጋራ ሸንተረሩን እየቧጠጡ ወደፊት ሲገሰግሱ፣ ኃየሎም አርአያ በርካታ ጓዶቹ የተጫኑበትን ግልፅ መኪና በፈገግታ ተሞልቶ ሲያሽከረክር፣ ድሉ የመለስ ዜናው ጠበብትነት ስለመሆኑ፣ ደርግ ስለመደምሰሱ… ከመሆን አይዘልም፡፡
3
እርግጥ ነው በመግቢያዬ ላይ በጠቀስኩት በዚህ ግፉአንን ወደ ከፍታ እንዲወጡ በሚጣራው የህወሓት የመጀመሪያ መዝሙር ውስጥ ስሁት ነገር የለም፡፡ በጥልቅ መገፋት የሚዳክር ሕዝብ፣ ጨቋኞቹን ለመጣል ብረት ማንሳቱ ትላንትም ትክክል እንደሆነው ሁሉ ነገም የሚቀር አይሆንም፡፡ መሰረታዊው ጥያቄ ግን ‹በእነዚህ ስንኞች ሙቀት መንገድ የጀመሩት የያንጊዜ ብላቴናዎች፣ የዛሬ ጨቋኞች ይህንን መዝሙር ከፍ አድርገው በሚያሰሙ የዚህ ዘመን ወጣቶች ብርቱ ክንድ ለመውደቅ ምን ያህል ቀናት፣ ወራት… ቀርቷቸው ይሆን?› የሚለው ነው፡፡
በመጨረሻም በምንም አይነት ቃላት ልንገልፀው የማይቻለንን አምባገነኑ ደርግ መቃብር ላይ ‹ዲሞክራሲን በማስፈን› ግብ ተቀስቅሰው፣ በህወሓት ስር ተሰልፈው በበርሃ የወደቁ ኢትዮጵያውያንን፣ ስሙ ተለይቶ የልተመዘገበ አንድ የ60ዎቹ አብዮተኛ ገጣሚ፣ በቋጠራቸው ስንኞች ሰማዕትነታቸውን ማሰብ ወደድኩ፡፡
‹‹የወደቁትን አመስግኑ፣ አልፈዋልና!
ህልውናችን እንዲቀጥል ስለሞቱልን
እነርሱ ትላንት ሆነው እኛን ወደነገ ስላሻገሩን
የወደቁትን አመስግኑ!!››
(Salute the dead because they died
Salute the dead for they made living Possible,
Salute the ones who have given life to future by becoming the past)
ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com
February 16, 2014

No comments:

Post a Comment