Thursday, May 1, 2014

በቁሎን አባትህ ማን ነው ቢሉት፣ አጎቴ ፈረስ ነው አለ አሉ፤ ምንነትና ማንነት፡ የዘመኑ አንገብጋቢ ጥያቄ (ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም)

ምጽዓት የቀረበ ይመስላል፤ ብዙ ሰዎች ሳይጠየቁ በቁሎው የተጠየቀውን ጥያቄ ራሳቸውን ጠይቀው አጎቴ ፈረስ ነው የሚለውን መልስ እየመለሱ ናቸው፤ ስለምንነታቸውና ስለማንነታቸው በውስጣቸው አንድ አስጨናቂ ነገር እንዳለባቸው ግልጽ ነው፤ የጎዶሎነት ስሜት ስለሚሰማቸው የድረሱልኝ ጥሪ በጩኸት እያሰሙ ነው፤ ግንባር ቀዳሚ መለከት ነፊም አለ፤ እውነት ግን አይደፈጠጥም፤ እየዘለለ ያፈጥባቸዋል፤ አጎቴ ፈረስ ነው ባሉ ቁጥር፣ አባትህስ እያለ ያፈጥባቸዋል! በፈረስ አጎትነት የአህያን አባትነት መደምሰስ አይቻልም፤ ነገር አፍጥጦ ከመጣ አፍጥጦ ከመግጠም የተሻለ መልስ አይገኝለትም፤ ተቅለስልሰው ሊያልፉት ሲሞክሩ በኅሊና ውስጥ ተቀርቅሮ ይደበቃል፤ ለራስም ለማኅበረሰብም ክፉና ዘላቂ በሽታ ይሆናል፤ ኢትዮጵያዊነት ማንነቱን የሚክድ ኢትዮጵያዊ ሲያቃዠው ያድራል እንጂ ፍቆ አያጠፋውም፤ አንድ ጊዜ በጀኒቫ በአንድ የአበሻ ምግብ ቤት ስበላ አንድ ዱሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪዬ የነበረ የኤርትራ ተወላጅ ሲገባ ተያየን፤ እየሳቅሁ ደሞ እዚህ ምን ልታደርግ መጣህ ስለው፣ ከዚህ ማምለጥ እኮ አይቻልም፤ አለኝ፤ እንዴት ብሎ!
Prof. Mesfin Woldemariam
ምንነት ከማንነት የተለየ ነው፤ ምንነት ከማንነት ይቀድማል፤ ምንድን ነህ? የሚለው ጥያቄ ከተመለሰ በኋላ ነው ማን ነህ? መልስ የሚያስፈልገው፤ የምንነትን ጥያቄ የማያውቁ የማንነትን ጥያቄ ፍልስፍና አዋቂዎች መስለው የተውሶ ሀረጎችን ጣል ጣል እያደረጉ ተደናግረው ለማደናገር ይሞክራሉ፤ ከንቱ ድካም ነው፤ ማንነት ከምን ተነሥቶ ነው ራሱን ችሎ የሚቆመው? ራስን ሳያውቁ ሌላውን ለማወቅ መሞከር፣ ራስን ሳያሳምኑ ሌላውን ለማሳመን መሞከር፣ ያልሆኑትን ለመሆን ከመሞከር የሚቀልለው ራስን መሆን ነው፡፡
በቁሎው አባትህ ማን ነው ተብሎ ሲጠየቅ የነፍሱ ቁስል ተነክቶበታል (ለነገሩ በቁሎ ነፍስ የለውም)፤ ለዚህ ነው እያወቀ ጥያቄውን የሳተው! አሁን ሌላ ጥያቄ ሊያስፈልግ ነው፤ በቁሎው የካደው አባቱን ብቻ ነው? በአባቱ በኩል አጎቱ አህያ ነው፤ በእናቱ በኩል አጎቱ ፈረስ ነው፤በቅሎ አንግዲሀ አጎቴ ፈረስ ነው ሲል የካደው አባቱን ብቻ አይደለም።
በቁሎ አጎቴ ፈረስ ነው አለ የተባለውን ሳስብ የአባቴ ሸክሊት የምትባለዋ በቁሎ ትዝ አለችኝ፤ ማይጨው ዘምታለች! እሷ ትዝ ስትለኝ የማላውቃቸውን ወላጆችዋንም አሰብሁ፤ አንድ ወንድ አህያና አንዲት ባዝራ (ሴት ፈረስ)፤ ለመሆኑ አጎቴ ፈረስ ነው ያለው አህያ አገሩ የት ይሆን? ለመሆኑስ አጎቴ ፈረስ ነው ሲል ምን ማለቱ ነው? የሸክሊትን ዘር በአጭሩ ብናየው እንደሚከተለው ይሆናል፤–
አንደኛበቁሎው በአባቱ በኩል አንድ ወንድና አንዲት ሴት አያት አህዮች አሉት፤
ሁለተኛበቁሎውበእናቱበኩልአንድወንድናአንዲትሴትፈረስአያቶችአሉት
ሦስተኛ አባቱ፣ አህያው፣
አራተኛ እናቱ ፈረስዋ (ባዝራዋ)፣
አምስተኛ አህያ አጎትና አህያ አክስት፣
ስድስተኛ ፈረስ አጎትና ፈረስ አክስት፣
ከአንድ በቁሎ ተነሥተን ወደአንድ አህያና ወደአንድ ፈረስ ተሸጋግረን ስንት አህያና ስንት ፈረስ አዛመድን!
ስለኢትዮጵያ ሕዝብ ጎንደሬው የሲዳሞ ሰው፣ መሀንዲሱ፣ የሕግ ባለሙያው ደመቀ መታፈሪያ ያደገበትንና ያየውን በልብ-ወለድም በታሪክም እያቀነባበረ ከአርባ ዓመታት በፊት ጀምሮ ደጋግሞ ጽፎበታል፤ ብዙዎቻችን አልተማርንበትም፤ አላሰብንበትም፤ አልተወያየንበትም።
በማእከላዊ እስር ቤት፣ ከዚያም በቃሊቲ ከአንድ የወላይታ ወጣት ጋር (በአለበት ይቅናውና) ወዳጅነት ጀምረን ነበር፤ ስለወላይታ ለመማር ፈልጌ ገና ጥያቄዎችን መጠየቅ ስጀምር ወላይታ ውስጥ ብዙ ጎሣዎች መኖራቸውን ነገረኝ፤ ብዙ ነገር ለመማር ተዘጋጅቼ ሳለሁ መቼም ሁሌም በባርነት ውስጥ ስላለን እንደፈቀድን ለመሆንና እንደፈቀድን ለማድረግ አይፈቀድልንምና ለያዩን (ይለያያቸውና)፤ ያሰብሁትን ሳልፈጽም ቀረሁ፤ ቢሆንም ወላይታ ብዙ ከሌሎች የኢትዮጵያ ጎሣዎች ጋር ዝምድና ያላቸው ጎሣዎች መኖራቸውን ለመገንዘብ ችያለሁ፤ የደመቀ መታፈሪያን ሀሳብ በትንሽዋ ወላይታ ውስጥ ለማየትና ሀሳቡን ለማረጋገጥ አስችሎኛል፤ መማር ለፈለገ ቃሊቲም ትምህርት ቤት ነው።
ከብዙ ዓመታት በፊት አንድ የተምቤን ሰው ከጻፈው እንደተገነዘብሁት፣ በአንድ ዘመቻ ጊዜ ከሸዋ ከዘመተ ሰው መወለዱን በዳዊት መጽሐፍ ላይ ተጽፎለት ያገኝና የቅኔ ትምህርቱን ሲጨርስ አባቱን ፍለጋ ወደሸዋ ይመጣል፤ ቡልጋ ይደርሳል፤ እየጠየቀ የአባቱን ዘመዶች ያገኛል፤ የአባቱ ልጅ (ወንድሙ) አዲስ አበባ መሆኑ ይነገረውና አዲስ አበባ ይመጣል፤ በእንግሊዝ አገር ተምሮ የተመለሰውን ወንድሙን ያገኛል፤ ሥራ ያስገባዋል፤ የፈረንጁን ትምህርት ይማራል፤ ራሱን ችሎ ይኖራል፤ ወንድሙን ከነልጁ ደርግ ይገድለዋል፤ የተምቤኑ ተወላጅ ለሸዋው ወንድሙ ለቅሶ ይቀመጣል።
ከአንድ ሳምንት በፊት አንዲት ሴት አራት ልጆች ይዛ በአጠገቤ ስታልፍ ሳቅ ብላ አንገትዋን ሰበር አድርጋ ሰላምታ አሳየችኝ፤ አወቅኋት፤ ከአምስት ስድስት ዓመታት በፊት በዚያው በእኔ ሰፈር አካባቢ ትለምን የነበረች የመቀሌ ሴት ናት፤ በዚያን ጊዜ አርግዛ ሳያት የመጣሽው ከነባልሽ ነው ወይ ብዬ ስጠይቃት ወንድ ልጅዋ አባቱ እንዳልመጣ ነገረኝ፤ እርግዝናዋ ድንገተኛ አደጋ መሆኑን ነገረችኝ፤ በጣም ትልቅ ሆና ስለነበረ ወደሀኪም ቤት እንድትሄድ ገንዘብ ሰጠኋት፤ ከወለደች በኋላም አንድ ጓደኛዬ መሣፈሪያ ሰጣትና ወደመቀሌ ተመለሰች፤ አሁን እንደገና መጣች፤ ስጠይቃት ሁሉም ነገር ተባብሷል፤ የማዳበሪያ እያሉ ያስጨንቁናል፤ አለች፤ በይ አሁን ደግሞ ተጠንቀቂ ብዬ ተሳስቀን ተለያየን፤ ችግርም ያዛምዳል።
እንደመደምደሚያ አድርጌ ቢትወደድ አስፍሐን ላንሣ፤ ቢትወደድ አስፍሐ ለኢጣልያ ያደሩ ባንዳ ነበሩ፤ በመጨረሻም በጎንደር ላይ ኢጣልያ ድል ሲሆን ከጌታቸው ጋር ነበሩ፤ ኢጣልያኑ ጌታቸው ወደአገሩ ሲሸሽ ቢትወደድ አስፍሐን ይዞ ለመሄድ ፈልጎ ነበር፤ ቢትወደድ አስፍሐ ግን ለሁለተኛ ጊዜ አልከዳም ብለው በአገራቸው ቀሩ፤ የዱሮዎቹ ሰዎች ያላቸው ሰብአዊነትና አብሮ የመኖር ጥበብ ቢትወደድ አስፍሐን ከራስ አበበ አረጋይ ጋር አገናኛቸው፤ ታላቁ ባንዳ የትግራይ ገዢ ለነበሩት ለታላቁ አርበኛ ረዳት ሆኑ፤ ራስ አበበ ስለቢትወደድ አስፍሐ ያላቸውን አስተያየት ለማወቅ ዕድሉ አልገጠመኝም፤ ቢትወደድ አስፍሐ ስለራስ አበበ ያላቸውን አስተያየት ግን በመጠኑም ቢሆን ለማወቅ ችዬአለሁ፤ ቢትወደድ አስፍሐ ራስ አበበን በጣም ያከብሩአቸዋል፤ በጣም ያደንቁአቸዋል፤ የቢትወደድ አስፍሐ አማርኛና የኢትዮጵያ ታሪክ እውቀት ሳይተላለፍልን በመቅረቱ በጣም አዝናለሁ፤ ስለኤርትራ ‹ናጽነት› ድምጽ እንዲሰጥ ወያኔ በሚገፋፋበት ጊዜ ቢትወደድ አስፍሐ በሙሉ መንፈሳዊ ወኔ የወያኔንና የሻቢያን ጫና ተቋቁመው ኢትዮጵያዊነታቸውን አልክድም ብለው በኩራት ቆሙ፤ ባንዳው አርበኛ ሆኑ! ንስሐ ያጸዳል! ንስሐ ነጻነትን ያጎናጽፋል፤ የደበቁት ኃጢአት ግን በቀን ያቃዣል!
ባንዳና የባንዳ ልጅ ሁሉ የአርበኛ ስም ሲጠራ ያቃዠዋል! አጎቴ ፈረስ ነው! ይላል።

No comments:

Post a Comment