Thursday, May 22, 2014

ኢትዮጵያዊነት – ክፍል አንድና ሁለት (ሄኖክ የሺጥላ)

flag ethio

ኢትዮጵያዊነት በተቃርኖ የተሞላ የግሳንግስ ስብስብ አይደለም። ኢትዮጵያዊነት የወጪት ሰባሪዎች ትግል፣ ለኔ በገሌ ነው ባዮች ምክር አይደለም። ኢትዮጵያዊነት በበግ ጸጉር ቡክርናውን እንደቀውማው ያዕቆብም ( “አታላይ ማለት ነው”) አይነትም አይደለም። በጎሳ አሽክላ ተተብትበን፣ በቂም ቆመን፣ ጭረት አመርቅዘን ቁስል አርገን ፣ የዛሬ ውድቀታችንን ፣ የዘምን ምክነት አስመስለን፣ ላለመቻላችን መወጣጫ፣ ላለመቆማችን የ ምክንያት መቆናጠጫ ብንፈልግ ፣ ካለፈ ጥፋትም ሆነ ሕዝብ ካለፈለት እውነት ጀርባ መዶለታችንን እስካልተውን ፣ የድርሻችንን ለመወጣት ታጥቀን እስካልተነሳን ድረስ ፣ ትግላችን እንደ እስከ ዛሬው “ለ አፈ ግም አፍንጫ ድፍን ያዝለታል” ሆኖ ስለመቀጠሉ አዋቂ መሆን አይጠይቅም።

የፕለቲካ ድርጅቶች መግለጫና ትርጉም
የ-ወያኔው ስርዓት እንደ ወየነ 40 ዓመት ሞላው። እኛም የዚህ ስርዓት አድማቂዎች መሆን ከጀመርን እንዲሁ። የተላዩ ያልተቀናጁ፣ በማይረባ የትግል ቅርጽ የተጠረቡ ድርጅቶችም ይሄንን ስርዓት እሱን በሚመቸው መልኩ እየታገሉት (በጩኸት እያጫፈሩት) ተጉዘዋል፣ ብዙዎቹ መሰረት አልባ፣ የማይጨበጥ፣ የማይያዝ ትግል አድርገዋል። ባንጻሩ ደሞ ጥቂቶች ደማቸውን አፍስሰዋል፣ ጥቂቶች ራሳቸውን ባደባባይ ገብረዋል፣ ጥቂቶች ተሰውተዋል። እና በዚህ በማይረባ የትግል መስመር ውስጥ ባሉትና በቆራት አቁዋም ራሳቸውን በሰዉት መሃከል ግን በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ይህ ነው የማይባል በደል ( እስር ፣እንግልት፣ ግድያ፣ አፈና ፣ስደት እና ወዘተ ) ደርሶበታል እየደረሰበትም ነው፣ ገና ወደፊትም ይደርስበታል። ታጋዮቻችን ለአመታት ከማሳሰቢያ ያለፈ ነገር ሲያደርጉ አይስተዋሉም ” የ ወያኔ መንግስ በንጹሃን ኢትዮጵያውያኖች ላይ እያደረሰ ያለውን ነገር ባስቸኩዋይ እንዲያቆም አከሌ የተባለው ድርጅት አበክሮ አሳሰበ ” ።
እኔ እምለው እንዲህ አይነት ማስጠንቀቂያ ስትጽፉ ነው የኖራችሁት፣ በማስጠንቀቂያ ቢሆን ኖሮ ወያኔ አዲስ አበባም አይገባ ነበር። እስኪ ማስጠንቀቂያችሁ አልሰማ ሲል አጸፋ መመለስ የምትችሉ እስክትሆኑ ድረስ እባካችሁ ማስጠንቀቁን ተዉት። ይሄ ጭፍን እና መሰረት አልባ ጀብደንነት ነው አርባ ዓመት አጫፋሪ ያደረገን። እስኪ አሁን ማን ይሙት ዛሬም ( በ 2006) ማስጠንቀቂያ የምንጽፍ ሰዎች መሆን ነበርን ? “ብልህነት እንጂ ብልጠት ባከተመለት ዘመን ተፈጥረን ” ማንን ለማሞኘት ነው። ወይስ አንድን ድርጅት ድርጅት የሚያስብለው እንዲህ ነገሮች ሲጦዙ እመር እያለ በማስጠንቀቂያ ቀለም መጨረሱ ነው። አይግባኝም። እዚህ በምኖርበት ሀገር አማሪካ አንድ ሰው የቤት ክራዩን ወይም የስልክ አገልግሎት ክፍያውን በአግባቡ መፈጸም ካልቻለ ማስጠንቀቂያ ወረቀት ይደርሰዋል፣ ሰውየው/ሰትይቱ በተባለው ግዜ ክፍያውን ካልፈጸመ/መች አገልግሎት ሰጪው ድርጅት የአገልግሎት ተጠቃሚነቱዋን ይሰርዛል። ማስጠንቀቂያ ማለት እንዲህ ነው። እኛ ግን ወያኔ አርባ ዓመት ሲረብሽ፣ አርባ ዓመት ማስጠንቀቂያ የምንጽፍ ተራ ጀብደኞች ነን። በምክንያት የታጠርን፣ የማናታግል፣ የማንታገል፣ ስለ አንድነት የምንሰብክ ግለኞች ፣ በጠባብ ተሰፍረን ስለ ሆደ ሰፊነት የምናወራ። አረ እንደውም ይሄ ሆዴ ሰፊነት ስለሚባለው ነገር እናውራ። በአዲስ መስመር ይጀመር።
ሆዴ ሰፊነት ማለት ምን ማለት ነው? ጭቆናን መቀበል? በኢትዮጵያዊነት ጉዳዮች ላይ የጋራ ዝንባሌም ብቻ ሳይሆን ፍጹም ተቃራኒ በሆነ መልኩ ከሚሄዱት ጋ ፣ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር የለችም ከሚሉት ጋም’ እስከ መተባበር ድረስ ነው? ሆዴ ሰፊነት እና ሆደ ቡቡነት እኮ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። እንደውም ታጋዮቻችንን የምጠይቀው ነገር አለኝ። በእውነት መታገል ትፈልጋላችሁ ? በእውነት ለውጥ ማምጣት ትፈልጋላችሁ ? በእውነት እየሆነ ያለው ነገር ይገባችሁዋል ? ቢሆን ኖሮ ዘንድሮም ወረቀት በተንን ብላችሁ ባላወራችሁ፣ ቢሆን ኖሮ እንደ ትልቅ ነገር በየ ድህረ ገጾቻችሁ የማስጠንቀቂያ ሐተታ ባላወጣችሁ። የምታደርጉት ነገር ልክ አይደልም እያልኩ አይደለም፣ ግን ከዚያ አንድ ጋት ፈቀቅ ማለት አልቻላችሁም፣ ግብራችሁ ከአንደበታችሁ ( ከምታወሩልን ነገር ጋ) ይጣረሳል። ከስብሰባና ዓመት እየጠበቁ የምስረታ በአላችሁን ከማክበር ያለፈ አንድም ነገር ስታረጉ አላየናቹም። አለን ትላላችሁ እንጂ የላችሁም። መነሳት አልቻላችሁም፣ ወጣቶች እንዲነሱ መንገድ ማሳየት አትፈልጉም፣ ከስር ሆኖ ጉልበት የሚስም እንጂ የናንተን ጉልበት ይዞ የሚነሳ ልጅ አልወላዳቹም፣ ስመቻችሁ ትውልዱን ጫታም፣ ሴሰኛ፣ ራስ ወዳድ ፣ ምናምን ብላችሁ ጥረግሙታላችሁ። ትውልዱ በማን ይውጣ፣ ማንን ይከተል፣ ምን አስተማራችሁት። ከናንተ የተማራው እምብ ማለትን ሳይሆን፣ ከእሳት መሸሽን ነው።
መስእዋትነትን የምታውቁት ከናንተ ጋ ቆመው በተሰዉት ሰዎች እንጂ በራሳችሁ አይደልም። በሰው ደም ለመንገስ ፣ በሰው ደም ለመኮፈስ፣ በሰው ደም አናት ለመሆን ከመዳዳት ውጪ ፣ ጉልበታቹም ውኔያችሁም፣ እምቢታቹም በራሳችሁ ገድል ላይ የተመሰረተ አይደለም። መጋደልንም ሆነ መሞትን ማወቅ አትፈልጉም፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያሳስባችሁ ይሆናል ግን እንቅልፍ አይነሳችሁም፣ ነገሮች መስመር ሲለቁና የህዝቡ እሪታ ሰማይ ሲደርስ፣ ባፋጣኝ ድርጅት ትመሰርታላችሁ፣ የሚገርመው ከሚያልቀው ሰው ይልቅ አብልጣችሁ የምትጨነቁት ስለድርጅታችሁ ስም እና አባላት ነው። እያንዳንዱ የኢትዮጵያ መከራ ለናንተ የገንዘብ መሰብሰቢያን ዕድል ይፈጥራል፣ ይህንንም ያለ ሀፍረት ባደባባይ ታደርጉታላችሁ። ባጭሩ ትግል ምን እንደሆነ አታውቁም። እናንተን የሚያታግላችሁ በየጊዜው የሚፈነዳው የህዝብ ብሶት እንጂ አላማችሁ አይደለም። አጀንዳም፣ የትግል መዋቅርም፣ ሕልምም የላችሁም። በተገኘው አጋጣሚ ትግሉ እንዲፋፋም ትፈልጋላችሁ፣ ስለዚህ አልተሳካላችሁም፣ ምክንያቱም እያንዳንዱ አጋጣሚ የራሱ የሆኑ ውድቀቶች አሉትና።
ምሁርነታችሁ ፋና ወጊ ከመሆን ይልቅ መመጻደቂያ ስታደርጉት ነው ያየነው። በሁለት ሃሳቦች መሃከል ያለውን ልዩነት ለመፍታት የምታደርጉት ውይይት የምሁርነታችን ልክ ሳይሆን የጥላቻችሁን ቁመት ነው የሚያሳየን። ባልነበርንበት፣ በማናውቀው፣ ፍጹም ልክ የሚባል መረጃ በሌለበት ሆኔታ እንኩዋ ፍጹም ልክ የሆነ ተበዳይ እንሆናለን።
እስኪ ትንሽ ምሳሌዎች ላንሳ
ዶ/ር መራራ ጉድና ከኢሳት ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ጋ ባደረገው ቃለ ምልልስ። ” አያቴም በሚኒልክ መሬታቸው ተወርሶዋል ይህም የሆነው አድዋ አልዘምትም በማለታቸው ነው ” ይላል። እንዴ ጋሼ መራራ ለካ የእርሶም አያት አድዋ አልዘምትም ብለው ነበር። እኔ ይሄ የሰሜን ባንዳዎች ታሪክ ብቻ ይመስለኝ ነበር። እንግዲህ እግዚአብሔር ይግለጥላችሁ ምንሊክ ምክንያታቸው አደዋ ዝመት ነው። አይ አድዋ አልዘምትም ! እንግዲያውስ አንተ ኢትዮጵያዊ አይደለክም ስለዚህ የኢትዮጵያውያኖች መብት ሁሉ ያንተ መብት አይደለም ይመስለኛል የምንሊክ ሃሳብ። ይሄን ውሳኔ የሚቃረኑ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ ግን እስኪ ደሞ ዘንድሮ እየተደረገ ያለውን እንመልከት። መሬትትህን ሽጥ ወይም ልቀቅ ? ገበሬ ” ወይ መራራ ራሳቸው ” ለምን የህንድ ገበሬ እንዲያርስበት። አዩ ያባቶት አለመዝመት ያመጣብዎ ጣጣ ?
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በሰማያዊ ፓርቲ አዘጋጅነት ፣ ” መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” የሚለው መጽሐፋቸው ላይ በሚደር ውይይት ካንድ ተሳታፊ ለቀረበላቸው ትያቄ ሲመልሱ፣
“አንዳን የሚያሳዝኑ ነገሮች ተነስተዋል እዚህ አካባቢ ነው መሰል ትግሬ ነኝ ያለ ልጅ አለ ፣ ትግሬ ነኝ ብለሃል፣ እኔም ትግሬ ነኝ፣ ነገር ግን ልዩነታችን ትግሬ ሆነህ በማንበብህና ኢትዮጵያዊ ሆነህ በማንበብህ ላይ ነው። እውነት ነው፣ ትግሬነትን እያሰቡ እንደ ኢትዮጵያዊ መኖር አይቻልም ፣ ኦሮሞነት ኢትዮጵያዊ ለመሆን ባሰበ ቁጥር የተበዳይነት እና የተገፊነት ስሜት የሚጭር ከሆነ በምንም መልኩ ኢትዮጵያዊ መሆን አይቻልም። ፋሲለደስን ስንመለከት አማራ አደረሰብን የምንለው በደል ከሆነ ትዝ የሚለን ኢትዮጵያዊ መሆን አይቻልም ፣ አክሱምን ስንመለከት የትግሬዎች ክፋት ከሆነ ትዝ የሚለን ኢትዮጵያዊ መሆን አይቻልም፣ ሰንደቅ አላማችንን ስንመለከት አሁንም ሰንደቁ ከተሸከመው ምልክታዊ ትርጉም ውጪ የአማራነት መለኪያአንድን ጎሳ የጥፋት ብብሃር ታሪክ ካደረግነው አሁንም ኢትዮጵያዊ መሆን አይቻልም። ስለ ብራና እና መሰንቆ ስናወራ ወደ አእምሮዋችን ቀድሞ የሚመጣው ቁሶቹ የኢትዮጵያውያኖች እሴት ስለ-መሆናቸው ካልሆነ ኢትዮጵያዊ መሆን ይከብዳል።
ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ ማርያም በዚሁ ከላይ በጠቀስኩት መጽሐፋቸው ላይ “ድሃነት የጥቃት መከታ መሆኑ የልማቱ መንገድ ፍጽሞ መክሸፉን የሚያረጋግጥ መንገድ ነው ” ይላሉ።
አዋ! የተጠቂነት ስሜትን አዝሎ የተጠያቂነት ባለቤት ነው ከምንለው አካል ጋ የፖለቲካ ውህደት ሲደረግ ጥምረቱ ሳይመሰረት ይፈርሳል ። ሁለት በፍጹም የተለያየ አላማ ያላቸው አካላት ፣ በጋራ ጠላትነት የሚፈርጁት አንድ የጋራ ጠላት ስላላቸው ብቻ ውህደታቸው መፍትሄ ያመጣል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው። አንበሳም ጅብም ሚዳቆን አድነው ይበሉ ይሆናል፣ የሚዳቁ’ዐ ምግብነት ግን አንበሳ እና ጅብን ዘመድ አያደርጋቸውም ፣ ምክንያቱም በአመጋገብ ስርዓታቸውም ይሁን ፣ በተፈጥሮ ባህሪያቸው የተለያዩ ፍጥረቶች ናቸውና።
የተበዳይነትን ስሜት የትግል አላማው አድርጎ የተነሳ ድርጅት የተሸነፈው ሲመሰረት ነው። የተፈጠረበትን ምድር፣ መልካም ምድራዊ አቀማመጥ፣ የህዝቡን ባህል፣ ስነልቦናና ታሪክ ወደ ጎን ጥሎ ፣ መሆን አለበት ብሎ ስለሚያስበው ነገር ብቻ እያሰበ በርሃ የወረደ ታጋይ ቢያሸንፍም እንኩዋ ተሸንፎዋል ፣ ለዚህ ከወያኔ የተሻል ጥሩ ምሳሌ ማግኘት አንችልም። ግን ማሸነፍ ብለን የምንለው፣ መንበሩን መቆናጠጥ፣ ወዲህ ሂድ፣ ወዲህ ተመለስ የሚል ት’ዛዝን መስጠት ከሆነ እሱ ሌላ ነገር ነው። እንደምሳሌ ብዙ ግዜ የምሰማው እና የሚገርመኝ ነገር አለ። አብዛኛዎቹ የትግል አቀንቃኞች ” ወያኔን አሸንፈን መስቀል አደባባይ ተሰብስበን እንዲህ እናደርጋለን ፣ እንዘፍናለን፣ አንተም ሄኖክ ግጥም ታነብልናለህ ወዘተ ወዘተ ሲሉ መስማት አሁን አሁን የተለመደ ነገር ሆኖዋል ። ቁም ነገሩ እኮ መስቀል አደባባይ ላይ መደነስ አይመስለኝም ፣ዳንሱ የድሉ ማድመቂያ እንጂ የድሉ የመጨረሻ ግብ መሆን አለበትም ብዬ አላስብም። ሕልማችን ከድል አጥቢያ ጭፈራ ልቆ መሄድ ያለበት ይመስለኛል። ፍጹም ተገዢዎች ሆነን ሳለ ከድል ማግስት ስለምንረግጠው ጮቤ ከሆነ የምናስበው፣ ገና ስንነሳ ነው የወደቅነው። የትግል አላማ ከዚህ ሁሉ ፍሬ ከርስኪ ሃሳቦች ይልቃል የሚባለው ለዚያ ነው። ታግለው አሸንፈው ለውጥ ማምጣት በቻሉትና ምንም ባልተሳካላቸው ( እንደውም ወደ ባሰ መቀመቅ በመሩን) መሪዎቻችን መሃከልም ያለው ልዩነት ይሄው ነው ። የትግላቸው መነሻ እራሳቸውን ደርሶብናል ብለው ያሳመኑት በደል ሲሆን፣ መድረሻው ደሞ በቀል ነው።
ጆን ዶኔ (ትርጉም በቀብጽ እና በግርድፉ ) ብቻህን ተነጥለህ የምትኖር አንተ ማነ ነህ? ደንመና ውቂያኖሱን ቢጠርገው አውሮጳ ታንሳለች፣ የማንም ሰው ሞት እኔን ያጎለኛል ምክንያቱም ሰው ነኝና ምናምን ይላል ) በሱ ቁዋንቁዋ
No man is an island,
Entire of itself,
Every man is a piece of the continent, A part of the main.
If a clod be washed away by the sea, Europe is the less.
As well as if a promontory were.
As well as if a manor of thy friend’s
Or of thine own were:
Any man’s death diminishes me,
Because I am involved in mankind,
And therefore never send to know for whom the bell tolls; It tolls for thee.
እኔም ከሱ የተለየ ስሜትም እምነትም የለኝም፣ ግን ሞትህ የሚያሳዝነኝ ቢያንስ ቢያንስ አንተ በኔ ሞት ባታዝን እንኩዋ ደስተኛ እስካልሆንክ ነው። አንተ ለኔ መቆም ባፀራ እንኩዋ ለጥፋቴ እስካልታተርክ ድረስ ነው። አዎ ሞትህ ያሳዝነኛል፣ በደልህ ያመኛል፣ ስቃይህ ይቆጨኛል፣ ግን ቢያንስ ቢያንስ የሃዘኔን ያህል ባይሆንም እንኩዋ የሰው ልጆች የመሆናችንን ያህል አንተም ለኔ ፍቅር ይኑርህ። እኛ ግን እንደዚያ አይነት አይደለንም እኛ
“No man can Judge his agony against an objective scale, his toothache is more than a 1000 death in another part of continent “
እንዳለው አይነቶች ሆንን። ላይቤርያ ውስጥ አንድ ሺ ሰው አለቀ ሲሉን ” የራሳቸው ጉዳይ እኔ ጥርሴን አሞኛል ” የምንል ሆነን። የበደል ትንሽ የለውም፣ የሞት ግማሽ የለውም።
አንተ አንቦ ላይ ስትገደል ለምን አላዘንክም አትበለኘን ይልቅ እኔ ሌሎች ሲበደሉ ተሙዋግቼላቸዋለሁ ወይ ብለህ ራስህን ጠይቅ፣ እምነት ቢኖርም ባይኖርም በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርም፣ ተሰፋፋሪ ሆኖ ከመኖር ግን የሚሻለው ተፋቅሮ መኖር ነው። ፍቅርን መሰረት ያላደረገ ትግል ፣ እሱም ላይ ሌላ ትግል እንዲነሳ ያደርጋል እንጂ የለውጥ ምሰሶ አይሆንም። በእርግጥ እወድሃለሁ፣ በእርግጥ ግማሽ ማንነቴ አንተ ነህ፣ ግን ፍቅሬን መሰረት አልባ አታድርገው፣ ካንተም፣ ከራሴም ፣ ከማውው ጥሩ ነገር ሁሉ ሃገሬን አስቀድማለሁ፣ ምክንያቱ ደሞ አማራ ወይ ኦሮሞ ስለሆንኩ አይደልም፣ ምክንያቱ እኔና አንተ አላፊና ጠፍ መሆናችንን ስለማውቅ ነው። ስለዚህ አስብ ይሄ የምለውን ነገር ትግሬ ሆነህ አታንብበው ይልቁንስ ኢትዮጵያዊ ሆነህ አንብበው።

No comments:

Post a Comment