Saturday, May 17, 2014

የኛ ነገር፤ የኛ ፖለቲካ፡ ግንቦት ሰባት ምን ነካው?ተክለሚካኤል አበበ

እንደመግቢያ፡ ግንቦት ሰባት ምን ነካው?
፩-ልረብሽ ነው፡፡ ልክ እንደኢሳት ሁሉ፤ “ግንቦት ሰባትም የኛ ነው” ( “የኔ ነው” የሚለው መፈክር አይመቸኝም)፡፡ የኛ ለሆነ ነገር ደግሞ ፍቅራችንን የምንገልጸው፤ በጭብጨባና በሽብሸባ ብቻ ሳይሆን፤ በተግሳጽና በትችትም ጭምር ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ለድርጅታቸው ካላቸው ጽኑእ ፍቅር የተነሳ፤ ድርጅታቸውም መሪዎቻቸውም ሲሳሳቱ፤ መተቸት የሌለባቸው ብጹአን አድርገው ይወስዱኣቸዋል፡፡ በዚህ አልስማማም፡፡ ስለዚህ፤ ግንቦት ሰባትን/የሊቀመንበሩን ቃለምልልስ ትንሽ ልተች ነው፡፡ ይህንን ነው ረብሻ ያልኩት፡፡
፪-በድጋሜ ግልጽ ለማድረግ ያህል፤ ግንቦት ሰባት በንጽጽር ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች የተሻለና የተሳለ ነው የሚል እምነት ስላለኝ/ስለነበረኝ፤ ከግንቦት ሰባት በኩል የሚመጡ መግለጫዎችን፤ መርሀግብሮችን፤ እርምጃዎችን በንቃትና በጥንቃቄ እከታተላለሁ፡፡ የሊቀመንበሩን ዲባቶ ብርሀኑ ነጋን ቃለምልልስም የተከታተልኩት በዚያ እምነት ነው፡፡ በዚህ በያዝነው ሳምንት፤ ሊቀመንበሩ በወቅታዊ የአገራችን ጉዳይ ላይ፤ ከኢሳቱ ሲሳይ አጌና ጋር ቃለ-ምልልስ አድርገዋል፡፡ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌን አብግን ቃለምልልስ ከሰማን ከወራት በኋላ፤ ከሊቀመንበሩ እንዲህ ያለ ተስፋ አስቆራጭ ቃለምልልስ ቶሎ ይመጣል ብዬ አልጠበቅኩም ነበር፡፡
ቀድሞ ነገር የተሰሩ ስራዎችንና መጪ መርሀግብሮችን ለማስረዳት እንጂ፤ ወቅታዊ ትንተናዎችን ለማድረግ የግንቦት ሰባት አመራር እየተፈራረቁ ሊመጡብን አይገባም ብዬ ከዚህ በፊት ጽፌ ነበር፡፡ የሰማኝ የለም፤ ሊቀመንበሩ ለትንተና ተመልሰውብናል፡፡ ያም ይሁን፤ ቢያንስ ትንተናው ውሀ የሚቋጥር ይሆናል ብዬ ጠብቄ ነበር፡፡ በቃለምልልሱ አዝኜ፤ በመጨረሻ፤ በርግጥም አሁን ባለው የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች አያያዝ፤ ጠላት ከሚወድቅ፤ ትንሽ ይሰንብት የሚሉ ወገኖችን ሀሳብ መረዳት እንድጀምር ሆኛለሁ፡፡
፫–በቃለምልልሱ ውስጥ፤ እኔ አሁን የምጸጸትባቸውንና የዛሬ አስር አስራአምስት አመት የማምንባቸውን ሀሳቦች ከሊቀመንበሩ ስሰማ ግራ ገብቶኛል፡፡ በቃለምልልሱ ውስጥ በአመታት ሂደት ያልተለወጡና ያልተሸሻሉ፤ የኢትዮጵያን ችግር በቅጡ ያልተረዱ ወይንም ለኢትዮጵያ ፈጽሞ መፍትሄ የማይሆኑ ሀሳቦችን ብሰማም፤ በጣም ያበሳጨኝ ጥያቄና መልስ ግን የሚከተለው ነው፡፡ ሲሳይ ይጠይቃል፤ ከሞላ ጎደል እንዲህ ብሎ፤ “አሁን ወያኔዎቹ የአዲስ አበባን መሬትና ሀብት በሙሉ ተቆጣጠርዋል፡፡ ወደኦሮሞ ምድርም እየተሸጋገሩ ነው፡፡ ይሄን አይነቱን ገበሬውንና አገሬውን አፈናቅሎ ራስን የማሸጋሸግ እርምጃ፤ ኢህአዴግ ከስልጣን ቢወርድ እንኳን፤ ወደፊት እንዴት ነው፤ አሁን እየተደረገ ያለውን ኢፍትሀዊ አካሄድ የምናስተካክለው የሚል ነው”፡፡ ሊቀመንበሩ፤ ጥያቄውን አልመለሱትም፡፡ “ይሄንን ሁሉ በደል እየፈጸመ ያለው ወያኔ ስለሆነ፤ ባጠቃላይ ወያኔን መጣል ላይ ነው መስራት ያለብን” የሚል ነው መልሳቸው፡፡ ሊቀመንበሩ፤ ወያኔን መጣል የችግራችን ሁሉ መፍትሄ ነው ብለው አስቀምጠውታል፡፡ ይሄ የድርጅታቸውም አቋም ይመስለኛል፡፡
፬-ይሄ መልስ ቀላል፤ ያልረቀቀ፤ ነው፤ የዛሬ አስር አስራአምስት አመት በልጅነትና በጅልነት ዘመን የምቀበለው ቀላል መልስ ነበር፡፡ ማደግና መማር ግን ቀላል የልጅነት ድምዳሜዎችን በረቀቁና ጥልቀት ባላቸው ትንታኔዎች መተካት ከሆነ፤ የሊቀመንበሩ መልስ ጥልቀትም ብልሀትም እድገትም ይጎድለዋል፡፡ አንደኛ ነገር፤ የኢትዮጵያን ችግር ኢህአዴግ የፈጠረው ብቻ አድርጎ የማስቀመጥ ሀሳብ ስህተት ነው፡፡ በመፈክር ደረጃ ትክክል ነው፡፡ በውይይትና በምርምር ደረጃ ግን የአገራችን ችግር ከዚያም የሰፋ ነው፡፡ ኢህአዴግ ለወቅታዊ ችግራችን የአንበሳውን ድርሻ ቢወስድም፤ ችግራችን የዘመናት፤ የባህል፤ የታሪክ፤ የአካባቢና የአያሌ ነገሮች ጥርቅም ነው፡፡ በራሳቸው በሊቀመንበሩ ንግግር ውስጥ ይሄንን ሀሳብ የሚደግፉ ማስረጃዎችን እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ፤ አንዱ ችግራችን ዘመን እንደሚሻገር ማሳያ ጥሩ ምሳሌ፤ ሊቀመንበሩ ራሳቸው የተናገሩት፤ አንዳንድ ኢትዮጵያዊያን/ኦሮሞዎች የኢትዮጵያን ችግር ምኒሊክ ጋር ወስደው ያላክኩታል የሚለው ሀሳብ ነው፡፡ ሁለተኛ ያበሳጨኝ ነገር፤ ግንቦት ሰባትም ይሁን ብዙዎቹ ፖለቲካ ድርጅቶች፤ የኢትዮጵያ ችግሮች ከኢህአዴግ መውደቅ በኋላ በቀላሉ የሚፈቱ አድርገው የሚያስቀምጡት ነገር ነው፡፡ ይሄ ምሁራዊ ድህነትና ፖለቲካዊ ስንፍና ይመስለኛል፡፡ ኢህአዴግ፤ ደርግን መጣል ብቻ ኢትዮጵያን እንደማያድን ወይም አላማውን እንደማያሳካ አውቆ፤ ከደርግ መውደቅ በኋላ ምን አይነት ኢትዮጵያ መመስረት እንዳለባትም አስቦ፤ የሽግግር ወቅቱን ሳይጨምር፤ ላለፉት 19 አመታት አገሪቷን የሚመራበትን ብሄርን/ቋንቋን መሰረት ያደረገ ፌደራሊዘምም ሰንቆ ነው ስልጣን ላይ የወጣው፡፡ የተማሩ የተመራመሩ አባላት የታጨቁበት ግንቦት ሰባት እንዴት ይሄንን ማሰብ እንደተሳነው ተደናግሮኛል፡፡ እኔ ደግሞ ስንቱ ቦታ ልሁን፡፡
፭-ሊቀመንበሩ በጎን ያለፉትን ጥያቄ ብንወስድ፤ ኢህአዴግ አሁን እየደረሰ ያለውን አሉታዊ ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ለውጥ፤ ለምሳሌ የተቀማውን መሬት፤ የተዘረፈውን ሀብት፤ ኢህአዴግ ከስልጣን ከተወገደ በኋላ፤ እንቀለብሰዋለን ወይ? ይሄንን ለማድረገስ ግንቦት ሰባት ምን አይነት ሕገመንግስታዊ ወይንም፤ ፖለቲካዊ ብልሀት አለው የሚል ነው፡፡ ሊቀመንበሩ ጥያቄውን ፊትለፊትም ከጀርባም አልነኩትም፡፡ “የለም እሱ አያስቸግርም፤ ይልቅስ ማተኮር ያለብን ኳሷ ላይ፤ ኳሱም ወያኔን መጣል ነው” የሚል መልስ ነው የሰጡት፡፡ ይሄን መልስ እንደዋዛ ፓልቶክ ውስጥ ብሰማው ወይም ፌስቡክ ላይ ባነበው፤ ወይም ከኔ ቢጤ ግለሰብ ቢሰማ አይገርመኝም፡፡ ኢህአዴግን ጥሎ ኢትዮጵያን ወደተሻለ ስርአት ለመቀየር ከሚታገል ድርጅት ሲሰማ ትንሽ ያስደነግጣል፡፡ ወዳጄ ሲሳይ አጌናም ጥያቄው እንዳልተመለሰ እያወቀ፤ ሌሎች ላይ እንደሚያደርገው ሊቀመንበሩን ወጥሮ አልያዘም፡፡ በነገራችን ላይ፤ አንደኛ፤ ይሄ የግንቦት ሰባት ሰዎች ኢሳት ላይ በቀረቡ ቁጥር አልጋ ባልጋ የሆነ ቃል ምልልስ አድርገው የሚመለሱት ነገር አልተመቸኝም፡፡ ሁለተኛ በዚህ ጉዳይ ላይ፤ አዳዲስና ለየት ያለ ከዚህ በፊት በቅጡ ያልተደመጣውን ወገን ሀሳብ የሚወክሉ ሰዎችን እንጂ፤ ለአመታት የሰማናቸውን የወዳጆቼን ብርሀኑንና ታማኝን ትንታኔ ደጋግሞ የማቅረቡን ብልሀት አልተረዳሁትም፡፡ ወይ ከተቃራኒ እይታዎች ጋር በክርክር መልኩ ቢቀርቡ ይሻል ነበር፡፡ በዚህ ረገድ ኢሳትም ሰነፍ ነው፡፡ ወጣ፤ ራቅ ብሎ ሄዶ የተለየ ሀሳብ ያላቸውን ሰዎች ከማቅረብ ይልቅ፤ እጓሮው ያሉትን ብቻ ጎትቶ የማቅረብ የስንፍና ስራ ከአራት አመት በኋላም መቀጠል የለበትም፡፡ የሆነ ሆኖ፤ ከሊቀመንበሩ መልስ የተረዳሁት ነገር ቢኖር፤ የግንቦት ሰባት ፖለቲካ ላለፉት ስድስት አመታት ምንም አይነት መሻሻልም እድገትም እንዳላሳየ ነው፡፡ እንዲያውም ካሮት ሆነ ልብል? ቁልቁል፡፡
ሀተታ፤ ችግራችንም መከራችንም ከኢህአዴግ ይሰፋል
፮-ከኢህአዴግ መምጣት በፊት የተጠራቀሙ የኢትዮጵያ ችግሮች እንደተጠበቁ ሆነው፤ ኢህአዴግ በዚህ 23 አመት ብቻ የፈጠራቸው፤ ኢህአዴግ እስኪወድቅም (መቼ እንደሆነ እንጃ) የሚፈጥራቸው ፖለቲካዊ ምስቅልቅሎች፤ ሊቀመንበሩ እንዳሉት፤ ወያኔን በመገርሰስ ብቻ ወይም ከተገረሰሱ በኋላ በቀላሉ የሚፈቱ አይደሉም፡፡ እንደዚያ ማመን ፖለቲካዊ የዋህነት ነው፡፡ ግንቦት ሰባትን በፖለቲካዊ የዋህነት መጠርጠር ደግሞ ጅልነት ይሆንብኛል፡፡ ስለዚህ ይሄንን አብይ ስህተት ከየዋህነት ይልቅ በፖለቲካዊና ምሁራዊ ስንፍና መፈረጁን ፈቀድኩ፡፡ የኢህአዴግ ዋንኛ የፖለቲካ ምሰሶ፤ የብሄር ፖለቲካ ይመስለኛል፡፡ ዲባቶ ብርሀኑ እንደሚሉት ዋና ዋናዎቹን የወያኔ የፖለቲካ ምሰሶዎች፤ (ምን ምን እንደሆኑ አልጠቀሱም፤ አንዱ ግን የብሄር ፖለቲካ ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ)፤ እናጥፋ ካልን ጸባችን ከኢህአዴግ ጋር ብቻ ሳይሆን፤ ኢህአዴግን ከሚታገሉ የብሄር ፖለቲካ ድርጅቶችም ጋር ሊሆን ይችላል፡፡ ኢህአዴግን ወይንም አስተዳደሩን እየተቃወሙ፤ የኢህአዴግ ዋንኛ የፖለቲካ አስተሳሰቦችን፤ ለምሳሌ በብሄርና በቋንቋ መደራጀትን ግን አሳምረው የሚቀበሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ከአገርቤትም ከውጭም አሉ፡፡ ምሳሌ ኢትዮጵያዊው ኦፌኮ፡፡ ኦነግን ለጊዜው እንተወው፡፡ ስለዚህ፤ ወያኔን ከጣልንና የወያኔን ዋና ዋና ፖለቲካዊ ምሰሶዎች ከነቀልን፤ የተቀረው የኢትዮጵያ ችግር እዳው ገብስ ነው የሚለው የሊቀመንበሩ ወይም የድርጅቱ አመለካከት በእውኑ ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ችግር የሚመጥን ሀሳብ አይደለም፡፡
፯-አላስተዋሉት እንደሆን እንጂ፤ መራራ ጉዲናና ብርሀኑ ነጋ ለኢትዮጵያ ያላቸው ፖለቲካዊ ራእይ የተለያየ ነው፡፡ ቡልቻ ደመቅሳና መስፍን ወልደማርያም የእድሜ አቻዎች ቢሆኑም፤ ስለኢትዮጵያ ችግር እንዲሁም ለኢትዮጵያ ያላቸው ራእይ ፈጽሞ የተለያየ ነው፡፡ ለምሳሌ፤ ለቡልቻ ደመቅሳ፤ ምኒሊክ ቅኝ የገዛ ነው፡፡ ለነዳውድ ኢብሳ ምኒሊክ ጡት ቆራጭም ነው፡፡ ለመስፍን ወልደማርያም ግን ምኒሊክ የነጻነት አርበኛ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህልውና ላይ ምንም ጥያቄ ባይኖራቸውም፤ ለመራራ ጉዲናና ለቡልቻ ደመቅሳ፤ የድሮዋ ከኢህአዴግ መምጣት በፊት የነበረችው ኢትዮጵያ መመለስ ዘበት ነው፡፡ የብርሀኑን እንጃ፤ ለመስፍን ወልደማርያም ግን፤ የአሁኗ ኢህአዴግ የፈጠራት ኢትዮጵያ፤ በተለምዶ የአንድነት ሀይል እየተባለ የሚጠራው ቡድን፤ የሚመኛት ኢትዮጵያ ተቃራኒ ነች፡፡ በእውኑ በዚህ አይነት ምስቅልቅል ውስጥ፤ የሊቀመንበሩ “ኢህአዴግ ይወገድ እንጂ ሌላው ሁሉ ቀላል ነው” ሀሳብ በዚህ ዘመን ኢትዮጵያን የሚዋጅ ሀሳብ ነውን? በዚህ አምስት አስር አመት የኖርኩት ኑሮ እንደሚያሳየው ከሆነ አይመስለኝም፡፡ በርግጥም የግንቦት ሰባት ሊቀመንበር በቃለምልልሳቸው ላይ ሰሞኑን የጎረቤት ከተሞችን ወደአዲስ አበባ የሚጠቀልለውን ፕላን ተከትሎ የተነሳውን ተቃውሞ የተነተኑበትን ሁኔታ ስንመለከት፤ ግንቦት ሰባት የኢትዮጵያ ችግር ገብቶታል? የመፍትሄውንስ ብልት አግኝቶታል? የሚለው ያጠራጥራል፡፡
፰-ሊቀመንበሩ፤ ሰሞኑን በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች/ትምህርትቤቶች ውስጥ ስለተነሱት ተቃውሞዎች ያብራሩበት መንገድ ሆን ብለው ለፖለቲካዊ ስልት ለግመው ካልሆነ በስተቀር፤ ጥለቅትም ብስለትም ሀቅም ይጎድለዋል፡፡ በርግጥም ይሄንን የአዲስ አበባን ከአጎራባች ከተሞች ጋር የመቀየጥ እቅድ፤ የወያኔ የተንኮል ስራ ውጤት ብቻ አድርጎ መመልከትና፤ ሌሎች ኦሮሞ ያልሆኑ ኢትዮጵያዊያን ተቃውሞውን ያልተቀላቀሉት ጥያቄው የሚመለከተው የተወሰነ ብሄርን ብቻ ስለሆነ ነው የሚለው ትንታኔ ጎዶሎ ነው፡፡ ኢህአዴግ የወሰደውን የግድያ እርምጃ ማውገዝ ወይንም የጠያቂዎቹን ጥያቄ የመደገፍ ያለመደገፍ ሁኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ መሰረታዊ ጥያቄው ኢትዮጵያን ከሞላ ጎደል በሁለት ጎራ የከፈለ ወይም ሊከፍል የሚችል ጉዳይ እንደሆነ አድርጎ አለመመልከት፤ ራስን ማታለል ነው፡፡ ሊቀመንበሩ ከክልል ሶስት ምክትል ሊቀመንበር አለምነው ማንትሴ አማራውን መሳደብ ጋር ያመሳሰሉበት መንገድ ደግሞ የበለጠ ያናድዳል፡፡ በርግጥም በኦሮሞ ተማሪዎች ተቃውሞ የተቀረው ኢትዮጵያዊ ያልተሳተፈው ስለማይመለከተው ነው የሚለው ትንታኔ ጥልቀት ይጎድለዋል፡፡ ስለማይመለከተው ብቻ ሳይሆን፤ አንደኛው ወገን ሌላኛውን ወገን በጥርጣሬና በፍርሀት ስለሚመለከት ጭምርም ነው፡፡
፱-በኔ አስተያየት፤ አንደኛው ወገን፤ ከአዲስ አበባ ጋር የቆመ ነው፡፡ አንዱ ከፊንፊኔ፡፡ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሕገመንግስት፤ አዲስ አበባ በኦሮምያ ውስጥ እንደምትገኝና የኦሮሚያ መንግስትም በአዲስ አበባ ውስጥ ያለው ልዩ ጥቅም እንደሚጠበቅ ቢደነግግም፤ ባለፉት መቶ ምናምን አመታት በተካሄዱ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ለውጦች የተነሳ፤ የአዲስ አበባ ኦሮሟዊ መልክ ተቀይሮ፤ አዲስ አበባ፤ አዲስ አበቤ በተሰኘ ብሄር ተወራለች፡፡ አዲስ አበባ አምሀራይዝድ ሆናለች፡፡ ላለፉት 23 አመታት፤ የኛና የናንት የናንተና የነሱ፤ የዚህና የዚያ ብሄር ክልል በሚል አስተሳሰብና ርእዮተአገር የተገዛ ህዝብ፤ የአዲስ አበባ ጎረቤት ከተሞች ከኦሮሚያ ወጥተው ወደአዲስ አበባ ከተቀላቀሉ፤ ልክ እንደፊንፊኔ ቡራዩንም፤ እንቶኔንም ልናጣ ነው የሚለው ስጋት የለትም ማለት አይቻልም፡፡ ኦሮሚያም ይሁን ጋምቤላ፤ አፋርም ይሁን ሶማሌ ክልሎች የኢትዮጵያ ናቸው፤ ስለዚህ የትም መኖር፤ መከበር መብቴ ነው የሚለው የአንድነቱ ሀይል፤ ይሄንን ኦሮምያን ለኦሮሞዎች ከሚል አስተሳሰብ የተወለደ አዲስ አበባ ልትውጠን ነው የሚል ከኢትዮጵያዊነት ያፈነገጠ ተቃውሞ በስጋት አይመለከተውም ማለትም ስህተት ነው፡፡ አማራ ይውጣ፤ ትግሬም እንደዛው የሚለውን ሀሳብም ጠላት እንደበተነው ብቻ አድርጎ መናገር በበታች ካድሬዎች ደረጃ ቢነገር ያምር እንደሆን እንጂ፤ በግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ደረጃ፤ ጉዳዩ ከዚህ ከፍ ያለ ትንታኔ ያስፈልገዋል፡፡ ስለዚህ፤ የሊቀመንበሩ ትንታኔ ከስንፍና ወይም ከግዴለሽነት የተወለደ ለመንግስትነት የማይመጥን ትንታኔ ነው፡፡
ልደምድመው፤
፲-በየግዜው ከግንቦት ሰባትና አመራሩ የምሰማቸው ፖለቲካዊ ትንታኔዎች ሊገቡኝ፤ ሊረዱኝ አልቻሉም፡፡ እንደመፍትሄ የተጠቆሙት ሀሳቦች፤ እንኩዋንስ ሳይንስን፤ ታሪክንና የፖለቲካ ባህላችንን፤ ወቅታዊ ፖለቲካችንንም በቅጡ የመረመሩና ያጤኑ ሆነው አላገኘኋቸውም፡፡ ከ23 አመት በኋላም፤ በንጽጽር ከሌሎች የተሻለና የተሳለ ነው ያልነው የፖለቲካ ድርጅት፤ ግንቦት ሰባት፤ የኢትዮጵያ ችግር ወይም የችግሯ መፍትሄ የገባው አይመስልም፡፡ በርግጥ ይሄ መጀመሪያ ኢህአዴግን እንጣለው፤ የተቀረው ከዚያ በኋላ ይደረስበታል የሚለው ደካማ አስተሳሰብ በግንቦት ሰባት ዘንድ ብቻ ሳይሆን፤ አገር ቤት ባሉትም የፖለቲካ ድርጅቶች ዘንድ ይሰተዋላል፡፡ በርግጥም በዚህ ኢህአዴግን ጥለን ስለምንተካው ስርአት ባልተዘጋጀንበት ወይም ህዝቡን ባላዘጋጀንበት ሁኔታ፤ የኢህአዴግን መውደቅ መመኘት ወይም በኢህአዴግ መወድቅ ላይ ብቻ መሰማራት ስህተት ሊሆንም ይችላል፡፡ በተለይ በተለይ፤ ኢህአዴግን እንጣል፤ የተቀረው ይደርሳል የሚለው አስተሳሰብ ከምሁራንና ከመሪዎች ሲፈልቅ፤ አንድም ስንፍና ነው፤ አልያም ግዴለሽነትና ሀላፊነት የጎደለው አካሄድ ነው፡፡ በዚህ የተነሳም፤ ይሄ ኢህአዴግ ይውደቅ፤ ይደምሰስ የሚለው ሀሳብ አደገኛም ነው የሚሉት ኢህአዴግን የሚጠሉ ምክንያታዊ ሰዎች ሀሳብ ራሱም ስሜት እየሰጠኝ መጥቷል፡፡ ይሄንን መጀመሪያ ወያኔን እንደምስስ የሚል ሀሳብ የሚያራምዱ ሰዎች፤ አድማጮቻቸው በሙሉ ልብ የሚያምኗቸው ቲፎዞዎቻቸው ብቻ ሳይሆኑ፤ የሚናገሩትን የምንመረምር ሰዎች ስለሆንም፤ እንዲህ ካለው ጥልቀት ከጎደለው ሰንካላ ትንተና መታቀብ አለባቸው፡፡ ኢህአዴግ እስኪወድቅ፤ ከወደቀ በኋላም ነገሮች ሁሉ ቆመው አይጠብቁንም፡፡ ኢህአዴግን የመጣልም ኢህአዴግን የመተካትም ስራዎች ተያያዙና ተወራራሽ ናቸው፡፡
እንደማስታወሻ፤ ወዳጄ መሳይ መኮንንና እህትዓለም መታሰቢያ ቀጸላ ዛሬ ቅዳሜ ግንቦት 9፤ ሜይ 17፤ ኦታዋ፤ ነገ፤ እሁድ ሜይ 18 ቀን ደግሞ ሊቀካህናት ምሳሌ እንግዳንና አቶ መሀመድ ሰይድን ጨምረው፤ ለኢሳት አራተኛ አመት ክብረበዓል ቶሮንቶ ከተማ ይመጣሉ፡፡ በአካባቢው ያለን ብቅ እንበል፡፡ ባለፈው ቃል የገባሁበት የኢሳት ጽሁፍ አልደረሰልኝም፡፡
ልጅ ተክላይ፤ ቶሮንቶ፤ ካናዳ፤ ግንቦት 2006/2014

No comments:

Post a Comment