Tuesday, May 13, 2014

ኢትዮጵያዊነት (ሄኖክ የሺጥላ፣ ክፍል አንድ)

ሄኖክ የሺጥላ
ኢትዮጵያዊነት በተቃርኖ የተሞላ የግሳንግስ ስብስብ አይደለም። ኢትዮጵያዊነት የወጪት ሰባሪዎች ትግል፣ ለኔ በገሌ ነው ባዮች ምክር አይደለም። ኢትዮጵያዊነት በበግ ጸጉር ቡክርናውን እንደቀማው ያዕቆብም (“አታላይ ማለት ነው”) አይነትም አይደለም። በጎሳ አሽክላ ተተብትበን፣ በቂም ቆመን፣ ጭረት አመርቅዘን ቁስል አርገን፣ የዛሬ ውድቀታችንን ፣ የዘመን ምክነት አስመስለን፣ ላለመቻላችን መወጣጫ፣ ላለመቆማችን የምክንያት መቆናጠጫ ብንፈልግ፣ ካለፈ ጥፋትም ሆነ ሕዝብ ካለፈለት እውነት ጀርባ መዶለታችንን እስካልተውን፣ የድርሻችንን ለመወጣት ታጥቀን እስካልተነሳን ድረስ፣ ትግላችን እንደ እስከ ዛሬው “ለአፈ ግም አፍንጫ ድፍን ያዝለታል” ሆኖ ስለመቀጠሉ አዋቂ መሆን አይጠይቅም።henok yeshitla

የፕለቲካ ድርጅቶች መግለጫና ትርጉም
የ-ወያኔው ስርዓት እንደ ወየነ 40 ዓመት ሞላው። እኛም የዚህ ስርዓት አድማቂዎች መሆን ከጀመርን እንዲሁ። የተለያዩ ያልተቀናጁ፣ በማይረባ የትግል ቅርጽ የተጠረቡ ድርጅቶችም ይሄንን ስርዓት እሱን በሚመቸው መልኩ እየታገሉት (በጩኸት እያጫፈሩት) ተጉዘዋል፣ ብዙዎቹ መሰረት አልባ፣ የማይጨበጥ፣ የማይያዝ ትግል አድርገዋል። ባንጻሩ ደሞ ጥቂቶች ደማቸውን አፍስሰዋል፣ ጥቂቶች ራሳቸውን ባደባባይ ገብረዋል፣ ጥቂቶች ተሰውተዋል። እና በዚህ በማይረባ የትግል መስመር ውስጥ ባሉትና በቆራጥ አቁዋም ራሳቸውን በሰዉት መሃከል ግን በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ይህ ነው የማይባል በደል (እስር፣ እንግልት፣ ግድያ፣ አፈና፣ ስደት እና ወዘተ) ደርሶበታል እየደረሰበትም ነው፣ ገና ወደፊትም ይደርስበታል።
ታጋዮቻችን ለአመታት ከማሳሰቢያ ያለፈ ነገር ሲያደርጉ አይስተዋሉም” የወያኔ መንግስ በንጹሃን ኢትዮጵያውያኖች ላይ እያደረሰ ያለውን ነገር ባስቸኩዋይ እንዲያቆም አከሌ የተባለው ድርጅት አበክሮ አሳሰበ”። እኔ እምለው እንዲህ አይነት ማስጠንቀቂያ ስትጽፉ ነው የኖራችሁት፣ በማስጠንቀቂያ ቢሆን ኖሮ ወያኔ አዲስ አበባም አይገባ ነበር። እስኪ ማስጠንቀቂያችሁን አልሰማ ሲል አጸፋ መመለስ የምትችሉ እስክትሆኑ ድረስ እባካችሁ ማስጠንቀቁን ተዉት። ይሄ ጭፍን እና መሰረት አልባ ጀብደንነት ነው አርባ ዓመት አጫፋሪ ያደረገን። እስኪ አሁን ማን ይሙት ዛሬም (በ 2006) ማስጠንቀቂያ የምንጽፍ ሰዎች መሆን ነበርን? “ብልህነት እንጂ ብልጠት ባከተመለት ዘመን ተፈጥረን” ማንን ለማሞኘት ነው። ወይስ አንድን ድርጅት ድርጅት የሚያስብለው እንዲህ ነገሮች ሲጦዙ እመር እያለ በማስጠንቀቂያ ቀለም መጨረሱ ነው። አይግባኝም። እዚህ በምኖርበት ሀገር አማሪካ አንድ ሰው የቤት ኪራዩን ወይም የስልክ አገልግሎት ክፍያውን በአግባቡ መፈጸም ካልቻለ ማስጠንቀቂያ ወረቀት ይደርሰዋል፣ ሰውየው/ሰትይቱ በተባለው ግዜ ክፍያውን ካልፈጸመ/መች አገልግሎት ሰጪው ድርጅት የአገልግሎት ተጠቃሚነቱዋን ይሰርዛል። ማስጠንቀቂያ ማለት እንዲህ ነው። እኛ ግን ወያኔ አርባ ዓመት ሲረብሽ፣ አርባ ዓመት ማስጠንቀቂያ የምንጽፍ ተራ ጀብደኞች ነን። በምክንያት የታጠርን፣ የማናታግል፣ የማንታገል፣ ስለ አንድነት የምንሰብክ ግለኞች፣ በጠባብ ተሰፍረን ስለ ሆደ ሰፊነት የምናወራ። አረ እንደውም ይሄ ሆደ ሰፊነት ስለሚባለው ነገር እናውራ። በአዲስ መስመር ይጀመር።
ሆደ ሰፊነት ማለት ምን ማለት ነው? ጭቆናን መቀበል? በኢትዮጵያዊነት ጉዳዮች ላይ የጋራ ዝንባሌም ብቻ ሳይሆን ፍጹም ተቃራኒ በሆነ መልኩ ከሚሄዱት ጋ ፣ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር የለችም ከሚሉትጋም እስከ መተባበር ድረስ ነው? ሆደ ሰፊነት እና ሆደ ቡቡነት እኮ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። እንደውም ታጋዮቻችንን የምጠይቀው ነገር አለኝ። በእውነት መታገል ትፈልጋላችሁ? በእውነት ለውጥ ማምጣት ትፈልጋላችሁ? በእውነት እየሆነ ያለው ነገር ይገባችሁዋል? ቢሆን ኖሮ ዘንድሮም ወረቀት በተንን ብላችሁ ባላወራችሁ፣ ቢሆን ኖሮ እንደ ትልቅ ነገር በየድህረ ገጾቻችሁ የማስጠንቀቂያ ሐተታ ባላወጣችሁ። የምታደርጉት ነገር ልክ አይደልም እያልኩ አይደለም፣ ግን ከዚያ አንድ ጋት ፈቀቅ ማለት አልቻላችሁም፣ ግብራችሁ ከአንደበታችሁ (ከምታወሩልን ነገር ጋ) ይጣረሳል። ከስብሰባና ዓመት እየጠበቁ የምስረታ በአላችሁን ከማክበር ያለፈ አንድም ነገር ስታረጉ አላየናችሁም። አለን ትላላችሁ እንጂ የላችሁም። መነሳት አልቻላችሁም፣ ወጣቶች እንዲነሱ መንገድ ማሳየት አትፈልጉም፣ ከስር ሆኖ ጉልበት የሚስም እንጂ የናንተን ጉልበት ይዞ የሚነሳ ልጅ አልወላዳቹም፣ ሲመቻችሁ ትውልዱን ጫታም፣ ሴሰኛ፣ ራስ ወዳድ ፣ ምናምን ብላችሁ ትረግሙታላችሁ። ትውልዱ በማን ይውጣ፣ ማንን ይከተል፣ ምን አስተማራችሁት። ከናንተ የተማራው እምቢ ማለትን ሳይሆን፣ ከእሳት መሸሽን ነው። መስእዋትነትን የምታውቁት ከናንተ ጋ ቆመው በተሰዉት ሰዎች እንጂ በራሳችሁ አይደልም። በሰው ደም ለመንገስ፣ በሰው ደም ለመኮፈስ፣ በሰው ደም አናት ለመሆን ከመዳዳት ውጪ፣ ጉልበታችሁም ወኔያችሁም፣ እምቢታችሁም በራሳችሁ ገድል ላይ የተመሰረተ አይደለም።
መጋደልንም ሆነ መሞትን ማወቅ አትፈልጉም፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያሳስባችሁ ይሆናል ግን እንቅልፍ አይነሳችሁም፣ ነገሮች መስመር ሲለቁና የህዝቡ እሪታ ሰማይ ሲደርስ፣ ባፋጣኝ ድርጅት ትመሰርታላችሁ፣ የሚገርመው ከሚያልቀው ሰው ይልቅ አብልጣችሁ የምትጨነቁት ስለድርጅታችሁ ስም እና አባላት ነው። እያንዳንዱ የኢትዮጵያ መከራ ለናንተ የገንዘብ መሰብሰቢያን ዕድል ይፈጥራል፣ ይህንንም ያለ ሀፍረት ባደባባይ ታደርጉታላችሁ። ባጭሩ ትግል ምን እንደሆነ አታውቁም። እናንተን የሚያታግላችሁ በየጊዜው የሚፈነዳው የህዝብ ብሶት እንጂ አላማችሁ አይደለም። አጀንዳም፣ የትግል መዋቅርም፣ ሕልምም የላችሁም። በተገኘው አጋጣሚ ትግሉ እንዲፋፋም ትፈልጋላችሁ፣ ስለዚህ አልተሳካላችሁም፣ ምክንያቱም እያንዳንዱ አጋጣሚ የራሱ የሆኑ ውድቀቶች አሉትና።
ሙህርነታችሁን ፋና ወጊ ከመሆን ይልቅ መመጻደቂያ ስታደርጉት ነው ያየነው። በሁለት ሃሳቦች መሃከል ያለውን ልዩነት ለመፍታት የምታደርጉት ውይይት የምሁርነታችሁን ልክ ሳይሆን የጥላቻችሁን ቁመት ነው የሚያሳየን። ባልነበርንበት፣ በማናውቀው፣ ፍጹም ልክ የሚባል መረጃ በሌለበት ሆኔታ እንኩዋ ፍጹም ልክ የሆነ ተበዳይ እንሆናለን።
እስኪ ትንሽ ምሳሌዎች ላንሳ
ዶር መራራ ጉድና ከኢሳት ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌናጋ ባደረገው ቃለ ምልልስ። “አያቴም በሚኒልክ መሬታቸው ተወርሶዋል ይህም የሆነው አድዋ አልዘምትም በማለታቸው ነው” ይላል። እንዴ ጋሼ መራራ ለካ የእርሶም አያት አድዋ አልዘምትም ብለው ነበር። እኔ ይሄ የሰሜን ባንዳዎች ታሪክ ብቻ ይመስለኝ ነበር። እንግዲህ እግዚአብሔር ይግለጥላችሁ ምንሊክ ምክንያታቸው አደዋ ዝመት ነው። አይ አድዋ አልዘምትም! እንግዲያውስ አንተ ኢትዮጵያዊ አይደለክም ስለዚህ የኢትዮጵያውያኖች መብት ሁሉ ያንተ መብት አይደለም ይመስለኛል የምንሊክ ሃሳብ። ይሄን ውሳኔ የሚቃረኑ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ ግን እስኪ ደሞ ዘንድሮ እየተደረገ ያለውን እንመልከት። መሬትትህን ሽጥ ወይም ልቀቅ? ለምን የህንድ ገበሬ እንዲያርስበት። አዩ ያባቶት አለመዝመት ያመጣብዎ ጣጣ?
ይቀጥላል

No comments:

Post a Comment