Friday, June 27, 2014

በፍረጃና በጥላቻ የተዋጡ 23 ዓመታት

ጌታቸው አምሳሉ በሶሻል ሚዲያ በተለይ ደግሞ በፌስቡክ ስሙን እየቀያየረ የሚጽፍ ወጣት ነው፡፡
በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚሰጣቸው አስተያየቶች ተመሳሳይ ቢሆኑም በተለያዩ የአማርኛ፣ የኦሮሚኛና የትግርኛ የሚመስሉ የብዕር ስሞች ይጽፋቸዋል፡፡ ስሞቹን ለመናገር ግን ፈቃደኛ አይደለም፡፡ 
ከሦስቱም ብሔሮች ስሞችን ይወስዳል፡፡ ብዙም አበላልጦ አያያቸውም፡፡ በተለያዩ ስሞች ለሚሰጣቸው አስተያየቶች የሚቀርቡለት ትችቶችና ነቀፌታዎች ግን የተጠቀመውንም ስም መሠረት ያደረጉ እንደሆኑ ይናገራል፡፡ በጣም ጥቂቶች ግን በተለያዩ ስሞች እየገባ ለሚሰጣቸው አስተያየቶች የሐሳቡ ቁም ነገር ላይ ብቻ ተመሥርተው አስተያየቶች እንደሚሰጡት ያስረዳል፡፡ ቁጥራቸው እየጨመረ ወይስ እየቀነሰ ስለመምጣቱ ተጠይቆ ነበር፡፡ የፌስቡክ ተጠቃሚ ወጣቶች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የፌስቡክ ጓደኞቹም ቁጥር ከፍ ብሏል፡፡ ሐሳባቸውን በምክንያት አስደግፈው የሚጽፉ በርካታ ሰዎች ቢኖሩም፣ በሚለጥፈው ወይም ፖስት በሚያደርገው ሐሳብ ከፍተኛውን ቦታ የሚይዙትና እንደልባቸው የሚጽፉት ግን ‹‹ፅንፈኞች›› መሆናቸውን፣ ኃላፊነት እንደማይሰማቸውና አብዛኛዎቹም በውጭ አገር እንደሚኖሩ አረጋግጧል፡፡

በኢትዮጵያ የግል ፕሬሱም ያላደገ በመሆኑ ምክንያት ከተለመደው አስተሳሰብ የወጣ ጽሑፍ እምብዛም ይስተናገዳል የሚል እምነት የሌለው ጌታቸው፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ግን ተሰምተው የማያውቁ የተለያዩ ሐሳቦች በመንፀባረቃቸው ደስተኛ ነው፡፡ ሆኖም በግሉ ከታዘባቸው የዘረኝነት፣ የፍረጃና የጥላቻ ፖለቲካ በበለጠ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚቀርበው የባሰ እንደሆነ አስተውሏል፡፡ ኃላፊነት በማይሰማቸው ሰዎች ምክንያት አንዳንድ ጊዜ ጥላቻው መረን የለቀቀ እንደሚሆንበት ይናገራል፡፡ 
ሰለሞን ንጉሠ በበኩሉ ‹‹አሉላ ሰለሞን›› በሚል የፌስቡክ አካውንት የሚጠቀም ወጣት ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያው ዲግሪውን ያገኘው ሰለሞን፣ በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ አንድ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪውን በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ በግልጽ ‹‹የመንግሥት ደጋፊ ነኝ›› ባይልም፣ በአብዛኛው የኢሕአዴግን ሐሳቦች በመደገፍ በምክንያት ይከራከራል፡፡ በምክንያት አስደግፎ በሚያቀርበው ክርክር ኢሕአዴግን አምርረው የማቃወሙም ጭምር ሐሳቡን እንዲሰጥ ይጋብዙታል፣ በሐሳብ ይከራከሩታል፡፡ 
‹‹አብዛኛውን ጊዜ ለውጡ የመጣው እኔ የተገኘሁበት ብሔር በከፈለው መስዋዕትነት ትልቅ ድርሻ በማበርከቱ ብቻ የምደግፍ እየመሰላቸው፣ ብሔሬ ላይ ያነጣጠሩ ዘለፋዎችንና ስድብ አዘል አስተያየቶችን አስተናግዳለሁ፤›› የሚለው ሰለሞን፣ በአፀፋው ጉዳዩን በማስረጃ በማስደገፍ ለማስረዳት እንደሚሞክር ይናገራል፡፡
‹‹መስተካከል የሚገባቸውን ነገሮች ስለሚጠቁመኝ›› በማለት በማኅበራዊ ሚዲያ የሚደረጉ ክርክሮች እጅግ እንደሚጠቅሙት ያስረዳል፡፡ ‹‹በተለይ በጥላቻ ያልታወሩት አስተያየት ሰጪዎች እንደ ቅርብ ጓደኞቼ ሆነው ይሰሙኛል፤›› ብሏል፡፡ 
‹‹በብሔር ጥላቻ የታወሩ›› የሚላቸውን ግን እምብዛም ለማስረዳትም አይሞክርም፡፡ እንደ እርሱ እምነት አብዛኞቹ፣ ‹‹እውነቱን ስለሚያውቁ ያን ያህል መልፋት አያስፈልግም፣ በመሠረቱ የመረጃ እጥረትም የለባቸውም፤›› ይላል፡፡ 
የ‹‹ያ ትውልድ›› ትሩፋት
ለአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ውድቀት ምክንያት የሆነው የየካቲት 1966 ዓ.ም. አመፅ መፈንዳቱን ተከትሎ፣ የመገዳደልና የመሰባበር ፖለቲካ በመንገሡ ምክንያት ተቃራኒ ሐሳብ ያላቸው ሰዎች የሚነጋገሩበት ሜዳ ጠፍቶ ብዙ ሕይወት አልፏል፡፡ የ1960/70ዎቹ የለውጥ ትውልድ እርስ በርሱ ሲጨራረስ እንደነበር በርካታ ጸሐፊዎች መዝግበዋል፡፡  
በተለይ በኢሕአፓና በመኢሶን መካከል የተፈጠረው መጠፋፋት የአገሪቱን ፖለቲካ እስካሁን ድረስ ምን ያህል እንደጎዳው በወቅቱ የነበሩት ጸሐፊዎች ያስታውሳሉ፡፡ በወቅቱ የትግሉ ተሳታፊ ከነበሩትና ማስታወሻቸውን ለሕዝብ ካቀረቡት መካከል ‹‹ታወር ኢን ዘ ስካይ›› የሚባለው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ደራሲ የሆኑት ሕይወት ተፈራ አንዷ ናቸው፡፡ እሳቸው ‹‹Crowd Mentality›› (የቡድንተኝነት አስተሳሰብ) እና መፈራረጅ አገሪቱን እንደገደላት በአንድ የንባብ ክበብ ተገኝተው ያደረጉት ንግግር ይታወሳል፡፡ በካናዳ የሚኖሩት ሕይወት፣ በአሁኑ ወቅት ልዩነትን ለመፍታት ወደ ዱላና የኃይል ዕርምጃ ከመሄድ ይልቅ በርካታ መሻሻሎችን የተመለከቱ ቢሆንም፣ አሁንም በጥላቻና በዘረኝነት ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ መኖሩን ግን አልካዱም፡፡ እሳቸው በውጭ አገር ያሉ ዜጎች በፊት በኢትዮጵያ የነበረው ሁኔታ እንዳለ መሆኑንና አክራሪነቱን እንደሚያበዙት ያምናሉ፡፡ ምክንያታቸውን ሲያስረዱ፣ ‹‹እዚህ አገር ሰዎች ባለፉት 20 ዓመታት መነጋገርና መከራከር ለምደዋል፡፡ እዚያ ግን ሁኔታው በአብዛኛው በነበረበት ላይ ነው፤›› ይላሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ ድርጊት ቁጭት ውስጥ ይከታቸዋል፡፡ 
በካናዳ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን በምሳሌ ወስደው አብዛኛዎቹ በኮሚኒቲ ውስጥ እንደሚኖሩ ገልጸው፣ ‹‹ወደ ትምህርት አይሄዱም፣ ራሳቸውንም አያሳድጉም፣ በካናዳ ያለው የዲሞክራሲ ሒደትም አያገባኝም በማለት አይከታተሉም፤›› ብለዋል ‹‹ዲሞክራሲ ባለበት አገር ውስጥ እየኖሩ እንዴት አይለወጡም?›› በሚል ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፡፡ ‹‹እዚህ ተስፋ ያለው ነገር አለ፡፡ ሰው እርስ በርሱ ይከራከራል፡፡ ይጨቃጨቃል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የከፋም ቢመስልም መነጋገር የሚጠላ አይደለም፡፡ ለዜጋ መታፈን ነው መጥፎው ነገር፤›› ብለዋል፡፡ 
ሕይወት በመንግሥትና በግል ፕሬሱ መካከል እንደተመለከቱት ልዩነቶች ጎልተው የሚንፀባረቁበት አይደለም፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚታዩ ክርክሮችና ጭቅጭቆችን በበጎ ጎናቸው አይተዋቸዋል፡፡ ‹‹ላለብን የመፈራረጅና የጥላቻ ፖለቲካ መፍትሔው በግልጽ መነጋገር ነው፡፡ የከፋና ጽንፍ የያዘ ሐሳብ ያለው አክራሪ ሰውም ቢሆን፣ በነፃነት ሲጽፍና ሲናገር ብቻ ነው መፍትሔው የሚገኘው፤›› ይላሉ፡፡
በዘመነ ኢሕአዴግ
ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ከዛሬ 23 ዓመታት ወዲህ የተለያዩ ሐሳቦች በተለያዩ መንገዶች እንዲንፀባረቁ ሳንሱርን በሕግ ያስቀረ ሲሆን፣ መንግሥትን የሚቃወሙ ኃይሎችም እንዲደራጁና የመንቀሳቀስ መብታቸው እንዲረጋገጥላቸው አመቻችቶ ነበር፡፡ ሆኖም የግሉ ፕሬስ በአክራሪ ፖለቲከኞች እጅ መውደቁንና በዘር ላይ የተንጠለጠለ ፖለቲካ ማራመጃ መሆኑን፣ ሰሞኑን የግንቦት 20 በዓልን ምክንያት በማድረግ ‹‹ነፀብራቅ›› በሚለው ዘጋቢ ፊልም መንግሥት አሳይቷል፡፡ 
አብዛኞቹ የግሉ ፕሬስ ውጤቶች እስከ 1997 ዓ.ም. ምርጫ ድረስ እጅግ መረን በለቀቀ ሁኔታ በጦርነት ናፋቂነት፣ በአውዳሚ አካሄድና በጥላቻ ፖለቲካ ተዘፍቀው መንቀሳቀሳቸውን ኢሕአዴግ ሲወቅስ ከርሟል፡፡ በዘርፉ ጥናት ያደረጉ አንዳንድ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንም ይህንን ይናገራሉ፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የድህረ ምረቃ ጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ፕሮግራም አስተባባሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር (ዶ/ር) ነገሪ ሌንጮ፣ ‹‹ሰዎች በነፃነት የመጻፍና የመናገር መብታቸው ሊጠበቅላቸው የሚገባ ቢሆንም፣ ኃላፊነት በጎደለው መንገድ በተለይ ዘር ላይ ተመሥርተው ቅስቀሳ ማድረጋቸው ችላ ሊባል የማይገባ ነው፤›› ይላሉ፡፡ ‹‹በአሉባልታ የተሞላ ጭንቅላት አደገኛ ነው፡፡ ምንም መረጃ ከሌለው ኅብረተሰብም የባሰ ጉዳት ያደርሳል፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡
አክራሪነትና ፅንፈኝነት የአገሪቱ የፖለቲካ ነፀብራቅ መሆኑን የሚናገሩት ዶ/ር ነገሪ፣ በጋዜጠኝነትና በፖለቲካ አቀንቃኝነት መካከል ግልጽ የሆነ ልዩነት ሊኖር እንደሚገባ ያምናሉ፡፡ ልዩነቶችን በንግግር ለማጥበብና ለመፍታት የግሉ ፕሬስ ሚና ተኪ የሌለው መሆኑን በመግለጽ፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ግዴታዎች ያሉበት መሆኑን የሚገልጹት ዶ/ር ነገሪ፣ መንግሥትም ለትችቶች ሆደ ሰፊ መሆን ያለበት ቢሆንም፣ በአንድ ሕዝብ ላይ የሚካሄድ የማጥላላት ዘመቻን ተቀምጦ ማየቱ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር እንደነበር ምርጫ 97ን አስታውሰዋል፡፡ ሁኔታው ሊያስከትለው የነበረው ጣጣ የአገሪቱን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን በመከራከር ጭምር፡፡
የምርጫ 97ን ቀውስ ተከትሎ የወጣው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅም የዘገየና ቀደም ብሎ መውጣት እንደነበረበት ይናገራሉ፡፡ በርካታ የሚዲያ ሰዎች የአዋጁን አፋኝነት በማጉላት በመልካም ዓይን አይመለከቱትም፡፡ አሁን በስደት ላይ የሚገኘው የቀድሞው የአዲስ ነገር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሸ፣ ቀደም ሲል ይኼና የፀረ ሽብር አዋጁ የግሉ ፕሬስ ‹‹ታምሞ አልጋ ላይ ተኝቶ እንዲገኝ አድርገውታል›› የሚል አስተያየት ለጀርመን ድምፅ ሬዲዮ የሰጠ ሲሆን፣ ‹‹ፕሬስ ሕክምና አይደለም፡፡ በሕግ አይገደብም፡፡ የተለየ ባህሪ ያለው ኢንዱስትሪ ነው፤›› ብሏል፡፡ ‹‹ቀደም ሲል ጋዜጣ ማሳተም ማስቲካ እንደ መሸጥ ቀላል ነበር፡፡ እጅግ ኃላፊነት የጎደላቸው ጋዜጦች እንደነበሩ አውቃለሁ፤›› በማለት አክሏል፡፡ የመስፍን አቋም ጥላቻ የሚያራምዱ ፖለቲከኞችም ሆኑ አክቲቪስቶች ፖለቲካው ራሱ ከገበያ ውጪ እስኪያደርጋቸው ድረስ በትዕግሥት ሊታለፉ ይገባል የሚል ነው፡፡ የመስፍን ሐሳብ፣ ‹‹ምንም ሆነ ምንም መጥፎ አስተሳሰብ መታፈን የለበትም፤›› የሚል ነው፡፡ 
‹‹ጨቋኝና ተጨቋኝ ብሔር የለም››
የአንድነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው በበኩላቸው፣ ‹‹በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ማንኛውም ወገን ሐሳቡ መታፈን የለበትም፤›› ይላሉ፡፡ ሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ አዋጪ ነው ብሎ እስካመነ ድረስ፡፡ 
1983 ዓ.ም. የሐሳብ ነፃነት መክፈቻ ምዕራፍ አድርገው የተመለከቱት አቶ ሀብታሙ፣ በጉልበት ላይ የተመሠረተው የደርግ ሥርዓት በኢሕአዴግ አሸናፊነት በመጠናቀቁ ብዙ ተስፋዎች ተጥለውበት ነበር ይላሉ፡፡ ብዙ ቁርጠኝነት የሚጠይቁ የነፃነት መርሆዎች ሕጋዊ ዕውቅና ቢያገኙም፣ ተግባራዊነታቸው ፈተናውን ማለፍ አልቻለም በማለት ያስረዳሉ፡፡ 
አንድነትና ሰማያዊ ፓርቲዎች በቅርቡ ባካሄዱዋቸው ሰላማዊ ሠልፎች በዘር ጥላቻ ላይ የተመሠረቱ መፈክሮች መሰማታቸውን አንዳንድ ጋዜጠኞች ይገልጻሉ፡፡ አቶ ሀብታሙ ግን የአተረጓጎም ልዩነት መኖሩን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ስለታሰሩና ስለተጨቆኑ ሰዎች ስናወራ በምሬት ይሆናል፤›› በማለት፡፡ መንግሥት የሰከነ ፖለቲካ መከተል አለበት የሚልም አቋም አላቸው፡፡ ጥያቄዎች እስካልተመለሱ ድረስ መቃወምን እንደማያቆሙ በመግለጽ፡፡
ብሔርን በተለከተ በእምነት ደረጃ የፓርቲያቸውን የፀና አቋም ሲገልጹ፣ ‹‹የእኛ እምነት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ጨቋኝና ተጨቋኝ፣ የበለጠ ተጠቃሚ ብሔር የለም፡፡ እየጨቆነን ያለው ሥርዓቱ ነው፡፡ ሥርዓቱ ደግሞ የአንድ ብሔር ስብስብ አይደለም፡፡ ይህንን መለየት ያቃታቸው ፖለቲከኞች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ትልቅ በሽታም ድንቁርናም ነው፤›› ሲሉም ይወቅሳሉ፡፡ ‹‹ግልጽ ላድርግልህ›› ብለው፣ ‹‹በትግራይ ሕዝብ ላይ እየተንፀባረቀ ያለው መረን የለቀቀ ጥላቻ ሊቆም ይገባል፡፡ ይኼ ሕዝብ ለዚህ አገር ክብርና ነፃነት ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለ የመጣ ነው፡፡ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከሌላው ሕዝብ  በበለጠም እየተጨቆነ እንደሆነ እናውቃለን፤›› ብለዋል፡፡ ነገር ግን ብሔር የማይገድበው ተጠቃሚ ገዥ ቡድን እየተፈጠረ እንደሆነ ግን ተናግረዋል፡፡ 
የኤዴፓ ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፣ ተቃዋሚዎች መንግሥትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመጣል ሲሉ በሚያሰራጩዋቸው ሐሳቦች ስህተት ሊሠሩ ቢችሉም፣ በትዕግሥት መታለፍ አለባቸው ይላሉ፡፡ መንግሥትም ተቃዋሚዎችን በሙሉ በጠላትነት ከመፈረጅ እንዲታቀብ ያሳስባሉ፡፡ ‹‹በመጀመርያዎቹ የኢሕአዴግ ዘመናት መነጋገርና መወያየት የተሻለ ነበር፡፡ አሁን ግን መቻቻል እንደ ነውር እየሆነ መጥቷል፤›› ብለዋል፡፡ ኢሕአዴግ በሥልጣን መደላደሉን ተከትሎ ብዙ ደጋፊ አለኝ በሚል መኩራራት የመጣ አቅጣጫ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡ ተቃዋሚዎችንና ጋዜጠኞችን ሁለት ነገሮች መክረዋል፡፡ አንደኛው በተለይ በዘር ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ ከማራመድ እንዲቆጠቡ፣ ሁለተኛ መንግሥትም ቢሆን እንደ መንግሥት ለሠራቸው ሥራዎች ዕውቅና ሰጥቶ ያልሠራቸውን መተቸትና አማራጭ ሐሳብ ማቅረብን በመፍትሔነት ጠቁመዋል፡፡
ሰለሞን ንጉሠም፣ ‹‹የከፋና አሉታዊ ትችት በአዳጊ ዲሞክራሲ ያለና የተለመደ ነገር ነው፡፡ የጥላቻ ፖለቲካ ግን ኋላቀርነት ነው፡፡ የዲሞክራሲ አቅጣጫን አያመላክትም፡፡ የተሻለ ዲሞክራሲ ለማምጣት ከጥላቻና ከስድብ ወጥቶ ሥልጡንና ገንቢ ትችት በማቅረብ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፤›› ሲል ሐሳቡን ይቋጫል፡፡    

1 comment:

  1. Attractive section of content. I just stumbled upon your site and in accession capital to assert that I get in fact enjoyed account your blog posts. Anyway I will be subscribing to your feeds and even I achievement you access consistently quickly.





    harga ranjang pasien

    ReplyDelete