Sunday, October 14, 2012

ምን ይበጃል ? ምንስ ይሻላል ?


            የቀዝቃዛው የአለም ጦርነት ካከተመ በኋላ እና አለም ወደ አንድ የርዕዮት ዓለም ካምፕ እየገባች ባለችበት አጋጣሚ የስልጣን አክሊል የደፉት ገዢዎቻችን የነፃውን ፕሬስ ዓለም በዚች ሀገር እውን እንዲሆን ሁኔታዎችን ብናመቻች የሰለጠነው አለም ያከብረናል በማለታቸው በርካታ ጋዜጦችና መጽሄቶች ለህትመት በቅተው እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ሆኖም ግን የነፃው ፕሬስ አርበኞች አደገኛውን የጎሳ ፖለቲካ መርዝ ለማርከስ እና የስርዓቱን ብልሹ አሰራር እንደ እሳት በሚፋጅ ብእራቸው ስለተቹ ጥሩ ነገርም ከተሰራ በማመስገናቸው የተነሳ የአገዛዙ አማካሪዎችም ሆኑ ፊት አውራሪዎች በበጎ አይን አልተመለከቷቸውም፡፡ የተለያዩ ስልቶችንም እየተጠቀሙ የነፃውንፕሬስ አባላት የመበተን እርምጃ ወስደዋል፡፡
    ለማንኛውም ከሁለት አስርተአመት በላይ ወጣትና አንጋፋ ጋዜጠኞች እንዲሁም ጥቂትአሳታሚዎች እንደ ጥጃ እየታሰሩና እየተፈቱ የተለኰሰው የፕሬስ ሻማ ድፍን እንዳይል ከባድ መስዋእትነት ከፍለዋል፡፡ አንጋፋው ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ፣ ክፍሌ ሙላት፣ ከፍያለው ማሞ ወዘተ ወደ ውጪ ሀገር የሄዱት ለሽርሽር አይመስለኝም ? በነፃው ፕሬስ መንደር መኖር ስላልቻሉ እንጂ፡፡አለም አቀፍ እውቅና ያለውጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ፣ ርዕዮት አለሙ ወንጀለኞች አይደሉም፡፡ ጨለማ ቤት ውስጥ የተወረወሩት ለነፃው ፕሬስ ህልውና ሲሉ እጃቸው እስኪዝል በመፃፋቸው ይመስለኛል፡፡ስለሆነም ብዙዎች የተሰደዱለትና የታሰሩለት እንዲሁም አንዳንዶች ውድ ህይወታቸውን ቤዛ ያደረጉለት የነፃው ፕሬስ እስከወዲያኛው እንዳይዘጋ ከተፈለገ ህዝቡ እና አሳታሚዎች መተባበር ይገባቸዋል ባይ ነኝ፡፡የፕሬስ እና ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብቶች ለአንድ ነፃ ህብረተሰብ መሠረት ከመሆናቸው ባሻገር አንድ መንግስት ጠንካራ እንዲሆን ያስችላሉ ተብሎ ስለሚገመት በብዙ ሀገራት እየተተገበሩ ይገኛሉ፡፡ነፃው ፕሬስ ሊያድግ የሚችለው ደግሞ በነፃነትና በውይይት እንጂ በማፈን አይመስለኝም ፤ ኦክሲጂን ለሰው ልጆች አስፈላጊ እንደሆነው ሁሉ ነፃነትም እንዲሁ ለፕሬስ ወሳኝ ነው፡፡ የፕሬስና ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብቶች በአለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሰነድ (UDHR) ( አንቀጽ 19) በአውሮፓ ሰብአዊመብት ኮንቬንሽን (አንቀጽ 10) በአሜሪካ የሰብአዊ መብት ኮንቬንሽን (አንቀጽ 13) በአፍሪካ የሰብአዊመብቶች ቻርተር (አንቀጽ 9) እና በኢትዮጵያው ህገ መንግስት (አንቀጽ29) ላይ ሰፍረዋል፡፡ነፃው ፕሬስ ሰላምን ለማስፈን ማህበረሰቡ ዲሲፕሊን እንዲኖረው ለማድረግ፣ መብታችን እና ነፃነታችን እንዳይደፈር፣ ፍትህና እኩልነት እንዲሰፍኑ ሁነኛ ሚና ስለሚኖረው መንከባከብ ይገባል፡፡ በፖለቲካው ምህዳር ደግሞ ነፃው ፕሬስ ሰዎች ከባርነት ነፃ እንዲወጡ፣ እንዳይጨቆኑ፣ ሥቃይ እንዳይደርስባቸው መፍትሄ ጠቋሚ ነው፡፡
     እንደምንሰማው (እንደምናየው) ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ በቂ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ጥቂቶች አይደሉም፡፡ከእነኚህ ውስጥ ደግሞ ሀገራቸውን የሚወዱና ጥፋቷን የማይመኙ ሞልተዋል፡፡ ታዲያ ለምንድን ነው ነፃውን ፕሬስ የማይታደጉት? ታላላቅ ሆቴሎችን፣ አግሮ ኢንዱስትሪዎችን ማቋቋም ከቻሉ ለምንድን ነው በጋዜጣ እና መጽሄት ህትመት ስራ ላይ ንዋያቸውን የማያፈሱት? አፈናውንና ወከባውን ፈርተው ከሆነ ይገባቸዋል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ለልጆቻቸውና ለልጅ ልጆቻቸው ማውረስ የሚገባቸው ንብረታቸውን ብቻ ሳይሆን እውቀትንም ጭምር መሆን አለበት ባይ ነኝ፡፡የኢትዮጵያ ህዝብ ቢሆን ያለ ነጻ ፕሬስ መኖር አልችልም ማለት ብቻ ሳይሆን ያለበት ጋዜጦችን በማንበብ ስህተት ካለ እርምት እንዲወስዱ በመምከር መመስገን ካለባቸው ደግሞ በመሸለም የራሱን እርምጃ መውሰድ ይገባዋል፡፡ ለማንኛውም የፍትህ ጋዜጣ መታፈን ሕዝቡን አሳምሞታል ፡፡ መንግሥት በአስቸኳይ ህትመቷን እንድትቀጥል ቢያደርግ በራሱም ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ መስተዋቱ ትሆናለችና፡፡                                                                                                                     ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር !!!                                                                                                                         ከዘካሪያስ                                          

No comments:

Post a Comment