Thursday, October 25, 2012

ታጋይን በማሰርና በመግደል ትግሉን ማሰር አይቻልም !!!

 የሚመቸውን ህግ በማውጣት ሰውን በፀረ ሽብርተኛ በመክሰስ በማሰርና በመግደል ከአገር እንዲሰደዱ በማድረግ ለሱ የሚመቹትን እና ለሱ የሚሰግዱትን በማገልገል ሌላውን ሕዝብ ከሌላ አገር የመጣ ይመስል እያሰቃየው በሚገኝበት ወቅት ላይ መሆኑን መዘንጋት ያለብን አይመስለኝም ! ‹‹ ታጋይ ይሞታል እንጂ ትግል አይሞትም›› የሚል ፅኑ መፈክር በማሰማት በበርካታ ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት ወደስልጣን የወጣው የኢህአዴግ መንግስት መፈክሩን በመዘንጋት“ታሪክ ራሱን ይደግማል” እንደሚባለው ያለፉትን ገዥዎች ታሪክ እየደገመ ይገኛል፡፡ደርግ ራሳቸውን ‹‹ገንጣይ፣ አስገንጣይ፣ ወንበዴ፣ ሽፍታ…››የመሳሰሉ ስሞችን እየሸለመ ለማጥላላት እንደሞከረው ሁሉ ኢህአዴግም ከጣለው አምባገነን መንግስት ምንም ሳይማር ‹‹ህገ-መንግስቱን በኃይል ለመናድ›› እና አሁን ደግሞ ‹‹ሽብርተኛ››በማለት ዘላለማዊ ሆኖ በመቆየት በመሻት የሰላማዊ ትግሉን ፈርለ ማስለቀቅ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር የሆኑትንና ጋዜጠኞችን  በማሰርና የፈለገውን ፍርድ በመስጠት እፎይታ ለማግኘት ሲሞክር እያስተዋልን ነው ፡፡የኢህአዴግን አገዛዝ ከደርግ የሚለየው ደርግ በአደባባይ ገድሎ ሲፎክር ኢህአዴግ ደግሞ ህግ አውጥቶና ህግ ጠቅሶ ሞት ይበይናል።
               በአደባባይ መግደልና በሚስጥር መግደል ሁለቱም የወንጀል ልዩነት የላቸውም፡፡ የዜጎችን ነፃነት ቀምቶ፣ ሃሳባቸውን በነፃነት እንዳይገልፁ እያሸማቀቁ ፤ ተቃዋሚዎችንም የተለያየ ስም እየለጠፉና 

                 ዛሬ ላይ ሆነን ስንመለከት የገዥው መንንግስት ለራሱእያሰሩ መኖር ጊዜውን ጠብቆ በወንጀለኝነት እንደሚያስጠይቅ ካለፉት ታሪኮቻችን አይተናል ፡፡ አሁን የምንለው ኢህአዴግ ካለፉት የታሪክ ኪሳራዎች በመማር ታጋይን በማሰር ትግሉን ማቆም እንደማይቻል ተገንዝቦ የፖለቲካ እስረኞችን በአስቸኳይ በመፍታት ሰላም ማውረድ አለበት፡፡ኢትዮጵያ የፀረ-ሽብርተኝነት ህግ እንደሚስፈልጋት እሙን ነው፡፡ ይሄ ደግም የአገሪቱን ሉአላዊነት የሚዳፈሩና ህዝቦቿን ለአደጋ የሚያጋልጡ የውጭ ጠላቶችን ለመከላከልና ለመቅጣት ያገለግላል፡፡ በሃገራችን እሆነ ያለው ግን ሌላ ገፅታ ያለው ነው ፡፡ የፀረ- ሽብር ህጉና የደህንነት መስሪያ ቤቱ በመተባበር በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞችን ያጠቁበታል ፡፡ የገዥውን ፓርቲ የስልጣን ጥቅም ይነካሉ ተብለው የሚታሰቡ ኢትዮጵያውያን ገለል እንዲሉ ይደረግበታል፡፡ በሃገራችን ይሄው ህግ እየተጠቀሰባቸው እንደ ቀልድ ‹‹በሽብርተኝነት ተጠርጥረው›› እየተባለ ወደ እስር ቤት የሚወረወሩት በርካታ ናቸው፡፡ ስለዚህ መንግስት ህጉን ለተቀናቀኞቹ እንደ ማጥቂያ መሳርያ እየተጠቀመበት ነው ብለን እናምናለን ፡፡ ዓርብ ሐምሌ 6 ቀን 2004ዓ.ም በወጣቱ ፖለቲከኛ አንዱዓለምአራጌ  የክስ መዝገብ በሽብርተኝነት ስም የተከሰሱ ኢትዮጵያውያንናበታዋቂው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ላይ የተበየነው ከስምንትዓመት እስከ እድሜ ልክ የሚደርስ ፅኑ እስራት የሚያመላክተን ገዥው ፓርቲ እየተከተለው ያለው አቅጣጫ አደገኛና ሃገሪቱን ወደ መጥፎ ሁኔታ የሚከት ተግባር እንደሆነ ነው፡፡ ስለዚህ‹‹የፀረ-ሽብር ህጉ›› እና ‹‹ሽብርተኛ›› የሚለውን ጨዋታ በማቆም እንዲሁም ከተቃዋሚዎች ጋር በመወያየት አፋጣኝ እርምጃዎች መውሰድ ይገባዋል፡፡ በተጨማሪም ገዥዎች ህግ ጠቅሰው ሲፈርዱ ህዝቡ ምን እንደሚላቸው ጆሮ ሰጥተው በመስማት እውነቱን ለማየት መሞከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ መንግስት ህዝብን ማዳመጥ ውዴታው ሳይሆን ግዴታው ነው ፡፡ እንደ እኛ እምነት ታጋይን በማሰር ትግሉን ማቆም ፈፅሞ አይቻልም፡፡ ትውልድ እስከቀጠለ ድረስ ትግሉ ይቀጥላል፡፡ብዙ ሺ አንዷለዓሞች ብዙ ሺ እስክንድሮችም ይፈጠራሉ፡፡ ለዚህነው ማሰርና ማሳደድ ፈፅሞ መፍትሄ አይደለም የምንለው፡፡
          ይልቁንም ስልጡን የሆነውንና ሌላውም ዓለም የሚጠቀምበትን የመነጋገር መንገድ መከተል ይገባል ፡፡ ዛሬም ነገም ወደፊትም ችግር የሚፈታው ህዝብን በማዳመጥና በመነጋገር ብቻ ነው ፡፡ኢህአዴግም አሮጌውን የማሳደድና ስም የመለጠፍ መንገድ እርግፍ አድርጎ በመተው፤ ትእቢትና ከንቱነትን ወደ ትህትና በመለወጥ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር የሚያስማማውን መንገድ ቢከተል ከውርደት ይድናል ብለን እንገምታለን ፡፡ መጨረሻው ወጡ ያላማረላት ሴት መሆናቸው የት ይቀርና !
    ታጋይን በማሰር ትግሉን ማሰር አይቻልም!!
                                                        ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለለም ትኑር !!!

No comments:

Post a Comment