Tuesday, December 10, 2013

የሀረር እስላማዊትነት እንዴት ያለ ነው? (ለጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የተሰጠ ምላሽ)

ላሊበላን አላየሁትም፡፡ ላየው ግን እፈልጋለሁ፡፡ ፍጹም በሆነ የቀረጻ ጥበብ ከድንጋይ ተፈልፍለው የወጡትን አስራ አንዱንም አብያተ ክርስቲያናት ለመጎብኘት እጓጓለሁ፡፡ ዕድሉን ካገኘሁ እዚያ ያየሁትንና የተሰማኝን ስሜት ለመጻፍ እመኛለሁ፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ የግዴታ ክርስቲያን መሆን አይጠበቅብኝም፡፡ ሰው መሆኔ ብቻ በቂ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ የታሪክና የኢትኖግራፊ ጸሐፊ በመሆኔ ደግሞ ስለ ላሊበላ የማውቀውን የማሳወቅ ግዴታ አለብኝ፡፡
ላሊበላ ክርስቲያናዊ መሬት ነው፡፡ ጠሊቅ የሆነ ክርስቲያናዊ ባህል፣ ታሪክና ትውፊት ይታይበታል፡፡ በዚህ ድንቅ የስልጣኔ ምድር ያሉትን ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት ያሳነጹት የኢትዮጵያ ክርስቲያን ነገሥታት ናቸው፡፡ በአሁኑ ዘመን ግን ላሊበላ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ብሄራዊ ሀብት ሆኗል፡፡ ሁሉም እንደ ራሱ ሀብት ነው የሚያየው፡፡
ሀረር እስላማዊት ከተማ ናት፡፡ ከጥንቱ ዘመን ለዐይነት የተረፈች የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የስልጣኔ መዘክር ናት፡፡ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ባህል፣ ታሪክና ትውፊት የምትዘክር ህያው ሙዚየም ናት፡፡ ፈጣሪ እድሉን ሰጥቶኝ በዚህች ከተማ ለስድስት ዓመታት ያህል ኖሬባታለሁ፡፡ ታሪኳ እና ባህሏ በጣም ስለማረከኝ የምችለውን ያህል ከመረመርኳት በኋላ “ሀረር ጌይ፡ የአስገራሚዋ ከተማ የኢትኖግራፊ ወጎች” የተሰኘ መጽሐፍ ጽፌአለሁ፡፡

*****
“ሀረር እስላማዊት ከተማ ናት” የሚለውን አባባል ለመጀመሪያ ጊዜ በጽሑፍ ያሰፈረው ማን እንደሆነ አላውቅም፡፡ ነገር ግን ከሀያኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ጀምሮ በጽሑፍም ሆነ በንግግር የሚዘወተር ዐረፍተ ነገር ነው፡፡ ስለከተማዋ የጻፉት ኤንሪኮ ቼሩሊ፣ ኢዋልድ ዋግነር፣ ኡልሪች ብራውኬምፐር፣ ካሚላ ጊብ፣ ኤልሳቤት ሄክትና ሌሎች በርካታ አውሮጳዊያን አባባሉን ይደጋግሙታል፡፡ የጽሑፋቸው ርዕስ አድርገው የተጠቀሙበትም በጣም ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ፈረንጆች “Islamic city in Ethiopia, The Muslim City in Ethiopia, The City of Saints, the Fourth Holy City of Islam ከመሳሰሉት አንዱን መጠቀማቸው የተለመደ ነገር ነው፡፡ ከሀገራችን ጸሐፍትም ከአንጋፋው ደራሲ ስብሐት ገብረ እግዚአብሄር ጀምሮ ሌሎችም ጸሐፍት “ሀረር እስላማዊት ከተማ” ወይንም “ሀረር የቅዱሳን ከተማ” እያሉ መጻፋቸው በስፋት ይታወቃል፡፡ እኔም በሀረር ጌይ መጽሐፌ አባባሉን ተጠቅሜበታለሁ፡፡
ግን…ግን… “ሀረር እስላማዊት ከተማ ናት” ሲባል ምን ማለት ነው? በሸሪዓ ህግ መተዳደር አለባት ማለት ነው? ክርስቲያኖች ከከተማዋ መውጣት አለባቸው ማለት ነው? ከኢትዮጵያ ተገንጥላ በራሷ አሚሮች መተዳደር አለባት ማለት ነው? በጭራሽ! እንዲህ ብሎ የጻፈ ደራሲ የለም፡፡ እንደዚህ የሚል ጸሐፊ ያለም አይመስለኝም፡፡ “ሀረር እስላማዊት ናት” ሲባል ሁለት ነገርን ነው የሚወክለው፡፡ አንደኛ ሀረር በጥንት ዘመኗ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የአስተዳደር፣ የትምህርትና የሀይማኖት ማዕከል ነበረች ማለት ነው፡፡ ሁለተኛ በዛሬው ዘመን እስላማዊ የስልጣኔ ታሪክ፣ ባህልና ትውፊት ይታይባታል ማለት ነው፡፡ በከተማነቷ፣ በቅርስነቷና በብሄራዊ ሀብትነቷ ግን የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ናት፡፡
*****
በትናንትናው ዕለት (ህዳር 28/2006) በወጣው “ፋክት” መጽሔት ላይ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ “የምስራቅ ኢትዮጵያ ፖለቲካ” በሚል ርዕስ አንድ መጣጥፍ አቅርቧል፡፡ የመጣጥፉ አርዕስተ ነገር የአካባቢውን ፖለቲካ መተቸት ይመስላል፡፡ እንደ ማጠንከሪያ የተጠቀመባቸው ማስረጃዎች ግን ከጭብጡ ጋር የሚሄዱ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ በገጽ 32 ላይ “አፈንዲ ሙተቂ የተባሉ ጸሐፊ “ሀረር ጌይ” በተሰኘ መጽሐፋቸው “ሀረር እስላማዊት ከተማ ናት” ብለዋል” ይልና እንዲህ ዓይነት አባባል ያለበት መጽሐፍ መዘጋጀቱን በመጥፎነት ያነሳዋል፡፡ ይህንን አባባል የያዘ መጽሐፍ በመንግሥታዊው የሀረሪ ህዝብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ መታተሙንም በህገ-ወጥነት ሊፈርጅ ይሞክራል፡፡
ተመስገን የኔን መጽሐፍ አለቦታው ማንሳቱ አስገርሞኛል፡፡ በርሱ ቤት ካድሬ ሆኜ የፕሮፓጋንዳ ስራ የምሰራ መስሎት ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁንና መጽሐፉ ለሶስት ዓመታት በተደረገ የኢትኖግራፊ ጥናት የተዘጋጀ እንጂ በጨበጣ የተጻፈ የካድሬ ድርሳን አይደለም፡፡ እኔ ደራሲው በህይወቴ የምኮራበት ብቸኛው ስራዬ እርሱ ነው፡፡ ሌሎች ድርሰቶች ቢኖሩኝም የርሱን ያህል አልሳሳላቸውም፡፡
“ሀረር ጌይ”ን የጻፍኩት በራሴ መንገድ ተመርቼ ነው፡፡ ማንም ሰው አልኮረኮረኝም፡፡ በመጽሐፉ የተጻፈው ሁሉ የራሴን እምነት ነው የሚያንጸባርቀው፡፡ በመጽሐፉ የምመታው ሀይማኖታዊም ሆነ ፖለቲካዊ ግብ የለም፡፡ ዓላማዬ ታሪክን፣ ባህልንና የህዝቦቻችንን ውብ የቋንቋና የኑሮ መስተጋብር ማሳወቅ ብቻ ነው፡፡ ላሊበላንና አክሱምንም ብጎበኝ ኖሮ ተመሳሳይ መንገድ ነበር የምከተለው፡፡
መጽሐፉን የጻፍኩት ብቻዬን ሆኜ ነው፡፡ አንዳንድ ምሁራን በምክር ቢያግዙኝም ሁሉንም የተወጣሁት በራሴ ነው፡፡ በመጽሐፉ ያለውን መረጃ የሰበሰብኩት፣ የመረመርኩት፣ ያመሳከርኩት፣ በጽሑፍ ያሰፈርኩት፣ ለህትመት እንዲሆን አድርጌ ያዘጋጀሁት እኔው ነኝ፡፡ የሀረሪ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ህትመቱን ስፖንሰር ያደረገው ሌሎች አሳታሚዎች ለህትመቱ የሚያስፈልገውን ወጪ ለማውጣት ስላልደፈሩ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ በኔና በቢሮው መካከል የተለየ ግንኙነት የለም (ቢኖር እንኳ የሙያ ጉዳይ እስከሆነ ድረስ ወንጀል አይደለም)፡፡ በነገራችን ላይ ቢሮው መጽሐፉን እኔ እንዳቀረብኩለት ነው ያሳተመው፡፡ በመጽሐፉ አስኳል ላይ የተቀነሰም ሆነ የተጨመረ ነገር የለም፡፡ አንድ የተደረገ ነገር ቢኖር ቢሮው “መልዕክታችን” የሚል ሁለት ገጽ ማስታወሻ ከመጽሐፉ ጋር እንዲታተምለት በጠየቀው መሰረት በመግቢያው ላይ መካተቱ ብቻ ነው (እርሱንም የጻፍኩት እኔ ነኝ)፡፡ ቢሮው ነጻነቴን ጠብቆ “ሀረር ጌይ”ን እኔ እንደጻፍኩት ለማሳተም በመስማማቱ አደንቀዋለሁ፤ አመሰግነዋለሁ፡፡ ይህም በሌሎች የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ዘንድ የሌለ ባህል በመሆኑ በጣም ተገርሜበታለሁ፡፡
“ቢሮው እስላማዊት ከተማ የሚል አባባል ያለበት መጽሐፍ ለምን አሳተመ” የሚል ጥያቄ ከተነሳ ደግሞ መልሱን መመለስ ያለበት እርሱ ራሱ ይመስለኛል፡፡ ለመረጃ ያህል ግን ቢሮው እንዲህ ዓይነት ድርሰቶችን ሲያሳትም የመጀመሪያ ጊዜው አለመሆኑን ለመግለጽ እሻለሁ፡፡ ቢሮው “እስላማዊት ከተማ” የሚለውን አባባል የሚረዳው ሌሎች ጸሐፍት ከሚረዱበት በተለየ መንገድ አይመስለኝም፡፡
ተመስገን “ሀረር እስላማዊት ከተማ ናት” የሚለው አባባል አደናግሮት ይሆን? በዚህ ተደናግሮ መጽሐፉን አለቦታው እንዳላነሳው እገምታለሁ፡፡ ይህንን አባባል ከዚህ በፊት ካልሰማ (ካላነበበ) ግን ሌሎች መጽሐፍትን እንዲመረምር እጠይቀዋለሁ፡፡ በተረፈ ነገሮችን በጥልቀት ሳንረዳ ሰዎችን በተሳሳተ አቅጣጫ ለመፈረጅ ባንቸኩል ጥሩ ነው፡፡
አፈንዲ ሙተቂ
ህዳር 29/2006

No comments:

Post a Comment