ብዙ ጊዜ ለአፍሪካ ወይም ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲ አሜሪካ ምሳሌ መሆን የለባትም የሚሉ ክርክሮች ይሰማሉ፡፡ አሜሪካ የተለያዩ ሕዝቦች፣ ባህሎች፣ ዕምነቶችና አመለካከቶች ያሉባት ትልቅ አገር ስትሆን በበርካታ ምክንያቶች ከአፍሪካ ወይም ደግሞ ከኢትዮጵያ ትለያለች የሚል መከራከሪያ አለ፡፡ አፍሪካ አኅጉራችንን ለጊዜው እንተዋትና ኢትዮጵያ ላይ በማተኮር ይኼንን መከራከሪያ እንሞግት፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ቋንቋዎች፣ ዕምነቶች፣ ባህሎችና ልማዳዊ ድርጊቶች ያሉባት አገር ብትሆንም ለዓለም ምሳሌ መሆን የሚችል መቻቻል ያለባት አገር መሆኗን ማስታወስ የግድ ይለናል፡፡ እንደ አሜሪካ ከተለያዩ አገሮችና አኅጉራት የፈለሱ ሕዝቦች ባይኖሯትም፣ የራሳቸው ማንነት ያላቸው ነገር ግን ለዘመናት በኢትዮጵያዊነታቸው ታውቀው የሚኖሩ የተለያዩ ሕዝቦች አሏት፡፡ እንደ አሜሪካ የተለያዩ አመለካከት፣ ፍላጎት፣ ዕምነትና የመሳሰሉት መለያዎች ያሉዋቸው ብሔር ብሔረሰቦቻችን በሰላምና በመቻቻል መኖርን ለረጅም ዓመታት ካዳበሩ እንደምን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ማራመድ ያቅታቸዋል?
ሁሌም ዲሞክራሲን ተለማማጅ እንደሆንን ይነገራል፡፡ ‹‹አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም›› የሚለው አባባል ተፅዕኖ ካልፈጠረብን በስተቀር ዲሞክራሲን መለማመድ ምን ማለት ነው? በማኅበረሰባችን ውስጥ ዕድር፣ ዕቁብና ሌሎች የመረዳጃ ድርጅቶችን መሥርተው ለዓመታት የዘለቁ ወገኖቻችን ችግሮቻቸውን በመተባበር ሲፈቱ ኖረዋል፡፡ ለሚያቋቁሟቸው መረዳጃዎች ሊቀመንበር፣ ጸሐፊና ገንዘብ ያዥ እየመረጡ ተዳድረዋል፡፡ በእነዚህ ማኅበረሰባዊ ተቋማት ምክንያት የተፈጠሩ ግጭቶች ወይም አላስፈላጊ ድርጊቶች ጎልተው አይሰሙም፡፡ በዝቅተኛ ደረጃ ሆነው በርካታ ገንዘብና የሰው ኃይል መምራት የቻሉ ተቋማትን ማኅበረሰባችን ማስተዳደር ከቻለ በየደረጃው አገርን የሚመሩ ሰዎችን መምረጥ እንዴት ያቅተዋል? ለዘመናት በመተማመን መንፈስ እየሠሩ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡት እነዚህ ተቋማት የረሃብና የድርቅ አደጋ ሲደርስ፣ አገር ስትወረርና በተለያዩ ጉዳዮች የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ እናውቀዋለን፡፡
በመኖሪያ አካባቢዎች፣ በሥራ ቦታዎች፣ በትምህርት ቤቶችና በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ውስጥ አለመግባባቶች ሲኖሩ የሚወገዱበት የሽምግልና ሥርዓቶች በአገራችን ውስጥ በሰፊው ይታያሉ፡፡ ከዕለት ድንገተኛ ጠብ ጀምሮ በእርሻ መሬት፣ በግጦሽ ቦታ፣ በንግድ ተወዳዳሪነት፣ በገንዘብ መካካድና በመሳሰሉት ምክንያቶች የሚፈጠሩ ግጭቶች ፍርድ ቤት ከመሄዳቸው በፊት ‹‹አንተም ተው….›› እየተባለ በሽምግልና ሥርዓት መፈታታቸው በማኅበረሰቡ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ ይሰጠዋል፡፡ የሕግ ባለሙያዎች ሳይቀሩ ይህንን ዓይነቱን ባህላዊ ሥርዓት የበለጠ ማጠናከር ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ ከዚህ በተረፈ ከበድ ያሉ ጉዳዮች በመደበኛ ፍርድ ቤቶች እንዲዳኙ ስለሚደረግ ማኅበረሰባችን ለሕግ የበላይነት ትልቅ አክብሮት አለው፡፡ ‹‹በሕግ አምላክ›› ከተባለ ብዙኅኑ ሕዝብ ለሕግ ልዕልና ትልቅ ክብደት ይሰጣል፡፡ አገሪቱ በሕግ የበላይነት ሥር በመተዳደሯም ሰላሙና ደኅንነቱ አስተማማኝ መሆኑን ይረዳል፡፡ የዲሞክራሲ አንዱ ትልቁ ዋስትናም የሕግ የበላይነት ነው፡፡ ዜጎች በሕግ ፊት እኩል መሆናቸው በተግባር ከተረጋገጠ የሕግ የበላይነት ከቃላት በላይ ተግባሩ የገዘፈ ነው፡፡
ከላይ በመጠኑ ያነሳሁዋቸው ምሳሌዎች በምንም ዓይነት ሁኔታ ለዲሞክራሲያዊ ባህል እንግዳ ወይም ባይተዋር አለመሆናችንን ይጠቁማሉ፡፡ ትልቁ ችግር የሚታየውም በሕዝቡ ውስጥ ሳይሆን በፖለቲከኞቻችን አካባቢ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ መልካም መሪ ካገኘ አገሪቱን ከወራሪ ለመታደግ ሕይወቱን ይገብራል፡፡ ተገዶ ሳይሆን በሙሉ ፈቃደኝነት፡፡ በተለይ በዓድዋ ጦርነትና በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት በአርበኝነት ተሰልፎ ደሙን ያፈሰሰው አገሩን ስለሚወድ ብቻ ነው፡፡ አገሩን የሚወድ ይሞትላታል፡፡ ያበለፅጋታል፡፡ ምንጊዜም ለእርሷ ህልውና ማንኛውንም መስዋዕትነት ይከፍላል፡፡ ባራክ ኦባማም ሆኑ ሚት ሮምኒ እንዳሉት በአገር ጉዳይ ላይ የፖለቲካ ልዩነት ወይም ተቀናቃኝነት ቦታ አይኖረውም፡፡ በተለይ አገር ወሳኝ የሆነ ፈታኝ ወቅት ላይ ስትገኝ ከፖለቲካው በላይ የሚያስተሳስረው የተጋረጠው ችግር ነው፡፡ ልዩነትን ወደ ጎን በማለት ለአገር አንድነትና ዕድገት በመቆም የችግር ጊዜን ማሳለፍ የእያንዳንዱ ዜጋ ግዴታ ነው፡፡
በዳበረ ዲሞክራሲ ውስጥ ያለ ሕዝብ ሀብታም ወይም ደሃ፣ ነጭ ወይም ጥቁር፣ ሒስፓኒክ ወይም እስያዊ ወይም ነባር ሕዝብ፣ ወጣት ወይም አዛውንት፣ አካለ ሙሉ ወይም አካል ጉዳተኛ፣ ዲሞክራት ወይም ሪፐብሊካን፣ ወዘተ በድምፃቸው ልዩነት መፍጠራቸው ነው የተወሳው፡፡ ‹‹እንደ ፖለቲካችን የተከፋፈልን ሳንሆን የጋራ ራዕይ ያለንና የወደፊቱን የምናልም ነን፤›› ነበር ያሉት ኦባማ፡፡ ከግለሰባዊ ፍላጎታችን ይልቅ አሜሪካዊነታችን ይቀድማል በማለት ነው የገለጹት፡፡ ለነገሩ የዲሞክራሲ ትልቁ መገለጫ ልዩነት አይደል? የተለያዩ አመለካከቶች መኖራቸው የተሻለውን ለመምረጥ ስለሚያግዝ ሁሌም ‹‹ልዩነት ለዘለዓለም ይኑር›› የሚለውን የፈረንሳዮች አባባል መቀበል የግድ ነው፡፡
የእኛ ፖለቲከኞች ልዩነትን እንዴት ያስተናግዳሉ? በተለይ ባለፉት 40 ዓመታት ውስጥ የምናውቃቸው ፖለቲከኞቻችን ለልዩነት ያላቸው አመለካከት እንዴት ነው? በልዩነት ውስጥ አንድነትን ለማስተናገድ ያላቸው ፈቃደኝነትስ እንዴት ይገለጻል? እነዚህ ቀለል ያሉ ጥያቄዎች ሲነሱ ደስ የማይላቸው ወገኖች አሉ፡፡ ከኢሕአዴግ ጀምሮ እስከ ዳያስፖራው ድረስ ያሉ ፖለቲከኞቻችን ስለ ዲሞክራሲ ሲደሰኩሩ እንሰማለን፡፡ በመካከላቸው የተሰነቀረውን ልዩነት ለመፍታትና ለመነጋገር ያላቸው ዝግጁነት ግን የሚያሳዝን ነው፡፡ የፖለቲካ ተቀናቃኝነት ከአባት ገዳይ በላይ ጠላትነት የሚታይበት ነው፡፡ በአገር ጉዳይ ላይ ተቀራርቦ ለመመካከር አይደለም በሩቅ እንኳን ተሁኖ ሐሳብ ለመለዋወጥ ሲሞከር አይታይም፡፡ ሁሌም አፍራሽ ቃላትን በመጠቀም፣ ‹‹ጎጠኛ፣ ጠባብ፣ ትምክህተኛ፣ ገንጣይ አስገንጣይ፣ ኪራይ ሰብሳቢ፣ ሽብርተኛ፣ ወዘተ›› በመባባል ለአገር ሊውል የሚችለው ወርቃማ ጊዜና ዕድል ይበላሻል፡፡ አገሪቱ አራት ጊዜ ምርጫ ብታካሂድም ውጤቱን ሁላችንም እንዳየነው ነው፡፡ ከአሜሪካ ጋር አይደለም ከቢጤዎቻችን ጋር እንኳ ሊወዳደር አልቻለም፡፡ በዲሞክራሲ ስም እየተማለ የአምባገነንነት አባዜ ነው የሚታየው፡፡ ገዥው ፓርቲ ተቀናቃኞቹን በሙሉ ለሕዝብ የማይበጁ ብሎ ሲፈርጅ ተቃዋሚዎቹ የአገር ጠላት ነው ይሉታል፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ ጽንፈኛ አቋም ምክንያት ዲሞክራሲን ማሰብ ቅንጦት ሆኗል፡ት፡
የዳያስፖራው ፖለቲካ መሪዎችን በሩቅ ርቀት መንግስት በመቆጣጠር የአገር ቤቱን ፖለቲካዊ ሒደትመንግስት እየበጠበጡ ናቸው፡፡ መንግስት ያልተረዳውን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በቅጡ ሳያስተዳድር ህዝብን፣ ወገኖቻችን የጥላቻ መርዝ እየረጩ ወገንን ከወገን እያራኮቱ ናቸው፡፡ የተለየ አስተሳሰብ ያለውን ወገናቸውን በጠላትነት እየመረዙ ያሸማቅቃሉ፡፡ የእነሱን አመለካከት የሚቃወም ወይም ማራመድ የማይፈልግ ዜጋን ማንነቱን ጭምር እያራከሱ ሰብዕናውን ይነካሉ፡፡ እነሱ የማይውሉበትን የጦር ሜዳ መሥርተው ኢትዮጵያውያንን ለማጨፋጨፍ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ መንግስት ትናንት ስለ ሰላማዊ ትግል ሲሰብኩ የነበሩት ሳይቀሩ የሽብርተኛ ስራ አስፈፃሚ እያሉ እየፈረጁ ነው በጣም ያሳፍራል፡፡ ዳያስፖራው የሚኖሩባት አሜሪካ ወይንም አውሮፓ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ልዩነትን የሚያስተናግድ፣ ከፀብና ከዱላ ይልቅ ውይይትን የሚያስቀድም፣ ለሰብዓዊ መብት ክብር የሚጨነቅ ስለወነ ለህዝባቸው ለወገኖች በመጨነቅ እየሰሩ ያሉትንም ዳያስፖራው መንግስት በሽብርተኛ መፈረጅ ልማዱ ሆኗል፡፡ ዳያስፖራው ዕውቀት፣ ሀብትና ቴክኖሎጂን ከዲሞክራሲ ጋር ማስተላለፍ ሲፈልግ መንግስት ደግሞ የዘረኝነት አረንቋ ውስጥ ገብቶ ይዳክራል፡፡
ደግሞ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ የሚመራውን መንግሥት ሙሉ አቅም በመጠቀም ሕዝቡን በሙሉ የራሱ ደጋፊ ለማድረግ ዘመቻ ይዟል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎችን እያሸማቀቀና በተለያዩ ሕጎች እያስፈራራ ዜጎች በነፃነት እንዳይቀርቡዋቸው እያደረገ ነው፡፡ በተለይ የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ከወጣ ወዲህ እየታየ ያለው ሁኔታ ይኼንን በሚገባ ይገልጸዋል፡፡ ሥራ ለማግኘት፣ ሹመት ለማግኘት፣ የትምህርት ዕድል ለማግኘት እየተባለ ሲቪል ሰርቪሱ ለኢሕአዴግ እንዲሰግድ እየተደረገ ነው፡፡ ከገበሬ ማኅበራት እስከ ወጣት ማኅበራት ድረስ ኢሕአዴግን ካልተለጠፉ መንቀሳቀስ አዋጪ አይደለም፡፡ ሲቪል ማኅበረሰቡ ሽባ በመደረጉ ዲሞክራሲያዊ ውይይቶችን ማካሄድ አልተቻለም፡፡ በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሆቴል አዳራሽ ተከራይተው ስብሰባ ማካሄድ ያልቻሉበት ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ ነጋዴዎች ሳይቀሩ በፎረም ተደራጅተው ኢሕአዴግን በገንዘብ ይደግፋሉ፡፡ ሌሎቹ ፓርቲዎች ይኼንን ለማድረግ ቢሞክሩ በፍራቻ የሚጠጋቸው የለም፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ የተወጠረ ድባብ ውስጥ ዲሞክራሲ አለ ተብሎ ይለፈፋል፡፡ የፓርላማው መቀመጫ በኢሕአዴግና በአጋሮቹ ተሞልቶ መድበለ ፓርቲ ሥርዓት ስለመኖሩ ይደሰኮራል፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድ ስንመጣ ችግሩ የዚያኑ ያህል ነው፡፡ ብዙዎቹ ፓርቲዎች ምን ያህል አባላትና ደጋፊዎች እንዳሉዋቸው አይታወቅም፡፡ የረባ ቢሮ የላቸውም፡፡ ጊዜውን የጠበቀ ጉባዔ አያካሂዱም፡፡ የገንዘብ አቅማቸው ያሳዝናል፡፡ ብዙዎቹ የሚመሩት ዕድሜያቸው በገፋ አዛውንቶች ነው፡፡ እንደ ኢሕአዴግ እነዚህም የተለየ አመለካከትና አስተያየት መስማት አይወዱም፡፡ የትግል ስትራቴጂያቸውና አማራጫቸውን ሕዝቡ አያውቀውም፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚያማክሩዋቸው የኢኮኖሚ፣ የፋይናንስ፣ የግብርና፣ የማዕድን፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ ወዘተ ባለሙያዎች የሉዋቸውም፡፡ ብዙዎቹ እርስ በርስ በተቀናቃኝነት ይተያያሉ፡፡ በርዕዮተ ዓለምና በመስመር ተመሳሳይ አቋም ኖሮአቸው በግለሰቦች መካከል በተፈጠረ ልዩነት ምክንያት በጠላትነት ይተያያሉ፡፡ በቃላት ጦርነት ይተጋተጋሉ፡፡ ኢሕአዴግ ከሚያደርስባቸው ጫና ባልተናነሰ በራሳቸው አቅም ውሱንነትና ተቀናቃኝነት ይዳከማሉ፡፡ ትግሉ ለሚጠይቀው መስዋዕትነት በሚገባ ባለመዘጋጀታቸው በትንሽ በትልቁ ሲያለቅሱ ይታያሉ፡፡ ፖለቲካ ማንኛውም መስዋዕትነት የሚከፈልበት መሆኑን ዘንግተው የትርፍ ሰዓት ሥራ ያደረጉትና የሚጦሩበትም አሉ፡፡ ከሁሉ በላይ የሚያሳስበው ደግሞ እነዚህም ከልዩነት በላይ ስላለው አገራዊ አጀንዳ ራዕይ አልባ መሆናቸው ነው፡፡
ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚ የሚባለው ስብስብ የሚነታረኩበትን ተራ ጉዳይ ለሚረዳ ዜጋ ራዕይ አልባነት አገሪቱን ምን ያህል እየጎዳት እንዳለ ያንገበግባል፡፡ ሁለቱ ወገኖች አገሪቱን ዲሞክራሲያዊትና የበለፀገች ለማድረግ እንፈልጋለን ይሉና በዓይን ለመተያየት ፈቃደኞች አይደሉም፡፡ ውጥረት ውስጥ ያለው ፖለቲካ ረግቦ ዲሞክራሲያዊ ሒደትን ለማስቀጠል የሁለቱ ወገኖች ውይይትና ድርድር የግድ ነው፡፡ አንዱ የምርጫውን ሥነ ምግባር ደንብ ካልፈረምክ የራስህ ጉዳይ ሲል፣ ሌላኛው ደግሞ በርካታ የሚወራረዱ ጉዳዮች ስላሉ አልፈርምም ይላል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ አስፈራሚውም ፈራሚውም የሚጨቃጨቁት ሕግ በሆነ ጉዳይ ላይ ነው፡፡ ሕግ ከሆነ በኋላ ቢፈረምም ባይፈረምም ማንም ይገዛበታል፡፡ ስለዚህ ማስገደድን ምን አመጣው? በሌላ በኩል ደግሞ ሕግ ሆኖ ከወጣ በኋላ አልፈርምም ከማለት ይልቅ ፈርሞ ወደ ድርድር ቢገባ ምን ይጎዳል? ሁለት ግትሮች በፈጠሩት የአልሸነፍም ባይነት ጀብደኝነት ምክንያት ፖለቲካው ተወጥሮ ዜጎች ይሸማቀቃሉ፡፡ እንዲህ እንደተወጣጠሩ ምርጫ ይመጣና የተለመደው ‹‹ጠብ ያለሽ በዳቦ›› ይጀመራል፡፡ ለአገራችን ስንል ሸብረክ ብንል ክብር ያስገኛል እንጂ አይጎዳንም ነበር፡፡ በሴራ የተጠላለፈው ፖለቲካችን ግን እንደ ጠላት እያስተያየን እስከ መቼ እንደምንዘልቅ ግራ ያጋባል፡፡
ባራክ ኦባማ አሜሪካ ‹‹ከማንኛውም አገር በላይ ሀብት ያላት አገር ናት፡፡ ነገር ግን ይህ ሀብት አይደለም እኛን ሀብታም ያደረገን፡፡ አሜሪካ በዓለም ላይ ትልቁ ወታደራዊ ኃይል አላት፡፡ ነገር ግን ይህ አይደለም ጠንካራ ያደረገን፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቻችን፣ ባህሎቻችን ዓለምን ይማርካሉ፡፡ ነገር ግን ዓለም ወደ እኛ እንዲጎርፍ ያደረጉት እነዚህ አይደሉም፡፡ አሜሪካን በዓለም ላይ ልዩ የሚያደርጋት በከፍተኛ ሁኔታ በሕዝቦቿ ስብጥርነት የተያያዘች በመሆኗ ብቻ ሳይሆን የእኛን ዕምነትና ዕጣ ፈንታ ሌሎችም የሚጋሩት በመሆኑ ነው፤›› አሉ፡፡ የአሜሪካ ፍቅር፣ ለጋሽነት፣ አርበኝነትና ኃላፊነት አሜሪካን ታላቅ ያደርጋታል ብለው፣ እኛ ለአሜሪካ የምናበረክተው እንጂ ከአሜሪካ የምንፈልገው አይደለም የሚያሳስበን በማለት የጆን ኦፍ ኬኔዲን ታሪካዊ ንግግር አሜሪካውያን እንዲያስታውሱ አድርገዋል፡፡ የእኛ ፖለቲከኞች ሌላው ቀርቶ በጠላትነት ከመተያየትና ጠልፎ ከመጣል አባዜ በመውጣት ልባቸውን ለስለስ ቢያደርጉ የማይለወጥ ነገር ይኖር ይሆን? ካላስፈላጊ ፍረጃ ተላቀው አገርንና ሕዝብን ማዕከል ማድረግ ከቻሉ ሌላው ዕዳው ገብስ ይመስለኛል፡፡
ፖለቲከኞቻችን ሕዝብን በማስቀደም በሕዝቡ ማዕከልነት አገርን ቢያስቡ ኖሮ ቅጽል እየተለጣጠፉ ባልተራኮቱና መሳቂያ ባልሆኑ ነበር፡፡ ለፖለቲካ ሥልጣን በሚያደርጉት ሽኩቻ ናላቸው ዞሮ የወረደ ተግባር ውስጥ ባይገቡ ኖሮ የሚያሳስባቸው የአገር ጉዳይ በሆነ ነበር፡፡ ራስ ወዳድነት፣ ትዕቢት፣ ክፋት፣ ጥላቻና ሰፋ አድርጎ አለማሰብ የፖለቲካችን መገለጫ ሆኗል፡፡ ሁሌም አንዱ ሌላውን ጠልፎ ለመጣል እንጂ በአገር አንገብጋቢ አጀንዳዎች ለመነጋገር ያለው ፍላጎት የከሰመ ነው፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ ድባብ ውስጥ ሆነን መልካም አስተዳደር፣ የሕግ የበላይነት፣ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ችግር ውስጥ ሲገቡ እንዴት መነጋገር ይቻላል? አገሪቱን ከድኅነት ለማውጣትና የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ በሁሉም መስክ የተሰማሩ ዜጎች ተሳትፎ ካላደረጉ ምን ዓይነት ተዓምር እንዲፈጠር እንፈልጋለን? ለሕዝብ ድምፅ የሚገዙት ልዩነቶቻቸውን ወደጎን አድርገው አሜሪካን ከፈተና ለመታደግ ሲስማሙ እኛ እስከ መቼ እየተናጀስን እንኖራለን? የጀመርነው ጉዞ አያዋጣምና ሰከን ብለን ራሳችንን እንመርምር፡፡
መንግስት የህዝባችን ድምፅ ሊያከብር ግድ ይለዋል ! ህዝባችን ነው ሊዳኝ የሚችለው ! መንግስት አስመራጭ እራሱ ደግሞ መራጭ ሆኖ መቀጠል የለበትም ። ፍትህና ዲሞክራሲ መልካም አስተዳደር ለኢትዮጵያ ህዝብ !!
ኢትዮጵያ በከብር ለዘላለም ትኑር !!!
ከዘካሪያስ
No comments:
Post a Comment