Saturday, November 24, 2012

ኢትዮጵያ በዲሞክራሲ እንዳትኖር ማን አደረጋት ??


«…ሀገራዊ ታሪካችንንም ሆነ ፖለቲካዊ እውነታዎችን በግልፅ ፍርጥርጥ አድርገን የመናገር ችግር አለብን፡፡ አንድ የፖለቲካ ሁኔታ ወደኋላ መለስ ብለን አንስተን ስንወያይ እውነታውን ለመቀበል ምን ያህል ዝግጁ ነን የሚለው መታየት ያለበት ይመስለናል፡፡ እኔ መሰረታዊ ችግር ነው የምለው ይህንን ነው…» በምድረ ኢትዮጵያ ስለዲሞክራሲ ሲነገር ሲደሶከር ሲዘመርና ሲተነተን ከአራት አስርት አመታት በላይ መቆጠሩ እውነትነው፡፡ ነገር ግን የተነገረውንና የታወቀውን ያህል የዲሞክራሲ ዘር ተዘርቶ ፍሬ ሲያፈራ አልታየም፡፡ ወይም ሊታይ አልቻለም፡፡
የዲሞክራሲ መርህ የተቀበሉ አብዛኛው የአለም ሐገራት ወደላቀ እድገት ብልጽግና እና የተሟላ ሰላም ተሸጋግረው ብሔራዊ እና ሀገራዊ ልእልናቸውን ለተምሳሌትነት ባበቁበት ዘመን እኛ ኢትዮጵያውያን ለዲሞክራሲ ባይተዋር ሆነን መገኘታችን የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ስለዲሞክራሲ እያነበብን የምንብከነከንበት እየተብከነከንን የምንተክስለ መሆን ተገደናል፡፡ በአጭሩ የዲሞክራሲ ፅንሰ ሀሳብ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ የምንጠላለፍበት ተጠላልፈንም የምንወድቅበት ሆኗል ብንል ስህተት አይሆንም፡፡
…ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በትክክል የማይተረጉም ወይም የማይገልፅና የአለምን ነባራዊ ሁኔታ ከማንነቱ አንፃር ማየት የማይችል ህዝብ ለራሱ የሚጠቅመውን ገንቢ የሆነ ተግባራትን ሊፈፅም አይችልም፡፡ የሥነ ልቦና ባርነት ያድርበታልና…

በ1960ዎቹ መጀመሪያ በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት የታገለው ትውልድ ቆራጥ ትውልድ ነበር፡፡… ነገር ግን መብትን ማስከበር ነፃነትን መጎናፀፍ ብልፅግና ማስፈን ወዘተ የሚል መርሆዎችን ይዞ ይነሳ እንጂ የተመኛቸውን እነዚህን ለውጦች ለማምጣት የሚያስችል የእውቀት የባህልና የስብእና ብቃት አለኝ ብሎ በጥሞና ራሱን አለመመርመሩ ነበር ችግሩ፡፡ በዚያ ዘመን ለውጥን አመጣለሁ ብሎ ለትግል የተነሳው ኢትዮጵያዊ ምሁር የነፃ አውጪነት ሚና ሲጫወት ለዚህ የሚመጥን ብቃት እንዳለው በሚገባ አላሰበበትም...
በዲሞክራሲ ሰበብ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ከአርባ አመታት በላይ በተዘፈቅንበት ችግር ለቁጥር የሚታክቱ በርካታ ምክንያቶችን መዘርዘር እንችላለን፡፡ ከነዚህ በርካታ ችግሮች መሀል ዋናው የዲሞክራሲ ፅንሰ ሃሳብ በቀደምትነት እያቀነቀነለ ለውጥ የተነሳው ትውልድ (1960ዎቹ) ህይወት ተቀጥፏል ሰበቡ ባመጣው ጦስ ምትክ የማይገኝላቸው ወጣቶች አገራቸውን ለቀው ለመሰደድ ተገደዋል፡፡ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖችም ለሞት እና ለእስር ተዳርገዋል አካላቸው መንፈሳቸውም እንዲኮላሽ ሆኗል፡፡ ቤተሰብ ተበትኗል…ወዘተ አሁንም እንደዛው ለውጥ የለም በባሰ ሁናቴ ቀጥሏል !!
በዚህም የተነሳ አጠቃላይ በሚባል መልኩ በኢትዮጵያ ህዝብ ህሊና ውስጥ የማይሽር ቁስል እንደማህተም ተቀርጾ ሊኖር ግድ ሆኗል፡፡ ትውልድ በዲሞክራሲ ስም የደረሰበት ግፍና በደል ሁሉ አንገት ደፊ ሆኖ ለመኖር እስከመወሰን ደርሶ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡
እንዲህም ይሁን እንዲ የዲሞክራሲን ስርዓት ለዚች ሀገር ለማስፈን የታገሉና የሚታገሉ አልጠፉም ፡፡ ግን ምን ያደርጋል በየዘመናቱ ለሀገራዊ ራዕይ የተዋጣለት ስኬት ያስገኛል የተባለው ዲሞክራሲ ከተራ ቃልነት በዘለለ ይህ ነው የሚባል ውጤት ሳያስገኝ ይኸው እንዳለን አለን፡፡ ለምን?
እኛ ኢትዮጵያውን የዲሞክራሲ ፅንሰ ሃሳብ ስላልገባን? ወይስ ሊገባን የማይችል ስለሆነ? ወይም የዲሞክራሲን መሰረታዊ ሃቆች በቃል ብቻ የምናነበንበው ሌሎች ያሉትን እንደበቀቀን ደግመን የመናገር ልማድ ስለተፀናወተን? ወይስ ሌላ ያላየነውና ያልለየነው ምክንያት ይኖር ይሆን?... ወዘተ ብለን መጠየቅና ራሳችንን መመርመር ግድ የሚለን
ይመስለኛል፡፡
…ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በትክክል የማይተረጉም ወይም የማይገልፅና የአለምን ነባራዊ ሁኔታ ከማንነቱ አንፃር ማየት የማይችል ህዝብ ለራሱ የሚጠቅመውን ገንቢ የሆነ ተግባራትን ሊፈፅም አይችልም፡፡ የሥነ ልቦና ባርነት ያድርበታልና…

ከዚህ በላይ በዝርዝር እና በጥልቀት ጥያቄውን ማስፋት ይቻላል በኢትዮጵያ ምድር ዲሞክራሲ በእውነተኛ መልኩ ላለመስራት ተጠያቂው ምሁሩ ነው? ወይስ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና አባሎች ወይስ አጠቀላይ ህዝቡ? አለያስ ለተጠያቂነቱ ሁሉም የየራሱ ድርሻ አለው ይሆን? …..ወዘተ
አሁን ባለንበት ሁኔታ እነዚህንና መሰል ጥያቄዎችን መጠየቅና ምላሹን መፈለግ" ፈልጎ መፍትሄውን ማካበት በዲሞክራሲ ይገኛል የተባለውን ዘላቂ ሀገራዊ ራዕይ ገቢራዊ ለማድረግ አይነተኛ መሳሪያ ሊሆን ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡ይህ እምነት የእኔ የአንድ ግለሰብ ብቻ አይመስለኝም፡፡ አይደለምም የሁሉም ኢትዮጵያዊ እንጂ ከአርባ አመት በላይ እነዚህ የዲሞክራሲ እሴቶች ለአንድ ጊዜ እንኳን በትክክል ያለመተግበራቸው ሚስጥር መደማመጥ ያለመቻላችን" አንዳችን የገነባነውን ሌላኛው ለማፍረስ ወጥመድ ማዘጋጀታችን …..ወዘተ እነዚህን እና መሰልችግሮችየዲሞክራሲእሴቶችንእንድናጣጥም አልታደልንም፡፡
ይህንን እንድል ያደረገኝ እና ብዕሬን እንዳነሳ ያስገደደኝ ምክንያት አለ ከምክንያቶቼ አንዱና ዋነኛው የዲሞክራሲ ፅንሰ ኃሳብ ምንነትና በኢትዮጵያ ያስከተለው ውጤት ነው፡፡ በአርባ አመት በፊት የአፅውን ፊውዳላዊ ስርዓት ገርስሶ ለውጥ ላለማምጣት የታገለውና ዛሬ «ያ ትውልድ» ለመባል የበቃው ሀይል የተነሳው «ዲሞክራሲን» ብሎ ነው

የዚህን ትውልድ መነሻ አበላሽቶ ለ17 አመታት ስልጣን የተቆናጠጠው የደርግ መንግስት ለራስ አገዛዝ አድሃሪ የሚል ስያሜ ሸልሞ ዲሞክራሲን ማላገጫ አድርጎ እንደነበረ አስታዋሽ የሚያስፈልገን አይደለም፡፡ የደርግ ስርዓትን ገርስሶ መንበሩን ከጨበጠ 22 አመታትን ያስቆጠረው የኢህአዲግ መንግስት ከደርግ በተሻለ መልኩ አንዳንድ የዲሞክራሲ ስርኣት መገለጫዎችን ከብዙ ጥቂቶቹን እንኳን ያሳያል ወይም ይከውናል ተብሎ ሲጠበቅ ዋና ዋና የሚባሉ የዲሞክራሲ እሴቶችን ወደኋላ እየገፋ መሆኑ እየታየ በበርካታ ወገኖች ከውስጥም ከውጪም እየተነቀፈ መምጣቱ እውነት ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ የሲቪክ መህበራት በስፋት እና በጥልቀት እንዲደራጁ አለመፍቀድ" የአመለካከት እና ሀሳብን በነፃነት የመያዝና የመግለፅ መብትን መንፈግ" የፕሬስ ነፃነትን መንፈግ" የመሰብሰብ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትን መከልከል" በነፃ የመደራጀት
መብትን እና የመሳሰሉትን … ወዘተ ማድርግ በፍጹም የማይቻልና የማይታሰቡ ከሆኑ ውለው አድረዋል፡፡

ይህ ከሆነ ዘንዳ እኛ ኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲ ያልቀናን ወይም ለዲሞክራሲ ቀና ያልሆንበት ምክንያት ምንድን ነው?ብለን መጠየቅና መፍትሔ መፈለግ ግድ ነው፡፡ ምነው ቢሉ የዲሞክራሲ ጽንሰ ሃሳብ በዚች ሀገር መቀንቀን ከተጀመ ጊዜ አንስቶ እስካለንበት እስከዚህ ዘመን ድረስ የሆነውና እየሆነ ያለው ነገር ሁሉ እኛ ኢትዮጵያውያን የዲሞክራሲ አዙሪት በሽታ ውስጥ እየሰከርን የሌሎችን እያዩ በመጎብጀት ብቻ ዘመናችንን እንድንጨርስ ሆኗል ብል የተሳሳትኩ  አይመስለኝም፡፡ ወይም ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን የዲሞክራሲና የዲሞክራሲ እሴቶችን እንዳንኖር ፍሬውንም በልተን  እንዳናጣጥም የረገመን አለወይ የሚል ጥያቄን አጫረብኝ እናንተስ?

በዚህ ዘመን ያለን ሰዎች እራሳችን ነን ለዲሞክራሲ መታገል ያለብን !!!
                       ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር !!!



                                           






No comments:

Post a Comment