Thursday, January 29, 2015

ትግሬ ብሎ ነገር…

አንዳንዶቻችን ኢህአዴግ ያጠፋውን ጥፋት ለትግሬና ለትግራይ ጠቅልላችሁ ለምን እንደምታስረክቡ አይገባኝም፡፡አንዳንዶቻችሁማ ብሶባችኃል ትንሽ ዕድልና ብዙ ሃይል ብታገኙ መታወቂያ እያያችሁ ይሄን ህዝብ ብትረፈርፉት ደስታችሁ መሆኑን ትሰብካላችሁ፡፡ወንድሞቼ ኢህአዴግ ከመላው ብሄረሰቦች የተውጣጡ እንከፎች የመሰረቱት ማህበር እንጂ ትግሬና ትግሬያዊያን የፈጠሩት ክስተት አይደለም፡፡
የአማራ መሬት ምርጥ ሰዎችን እንደማፍራቱ አዲሱ ለገሰ፣ታምራት ላይኔ፣አለምነው መኮነንን የመሰሉ በሰው ደም ሻወር የሚያምራቸው ሰዎችን አፍርቷል፡፡የኦሮሞ ህዝብ ታሪክን በብርሃን ያደመቁ ጀግኖችን እንደመውለዱ አባዱላ ገመዳ፣ሙክታር ከድር፣ግርማ ብሩን የመሰሉ አስረፍራፊዎችን ለኢህአዴግ አዋጥቷል፡፡ጉራጌ ካሱ ኢላላን፣ሲዳማ ሽፈራው ሽጉጤን፣ወላይታ ሃይለማሪያምን አሳድጓል፡፡ሶማሌ ፣ጋምቤላ ፣ሀረር ውስጥ ለተፈጠሩ እልቂቶች ምላጭ ሳቢዎቹ ፣አሰቃዮቹ ራሳቸው በአከባቢው ተወልደው ያደጉ ሳዲስቶች አልነበሩም?


ጭካኔን የአንድ ትልቅ ህዝብ የወል ሀብት ማድረግ ታላቅ ስህተት ነው፡፡ጀግንነትን ጠራርጎ ለአንድ ህዝብ ማሸከምም ታላቅ ጅልነት ነው፡፡አንድ ሰው ደደብ ቢሆን አፈጣጠሩ ደደብ ስለሆነ እንጂ ከአንድ ብሄር ስለተፈጠረ አይደለም፡፡እሱን ባየ አይናችሁ ብዙ ዕጹብ መስተሃልይ ያላቸውን በዚያው ቦታ ታገኛላችሁ፡፡
ትግራይን ሲያምሳት የነበረ የደርግ ገዳይ ጓድ አስተባባሪ አፈወርቂ ይባላል (የቢቢሲ ዶክሜንተሪ ላይ አለላችሁ) ፡፡ልጃቸውን ገድሎ እናቶችን ዝፈኑ ይላቸው ነበር፡፡ትግሬ ነበረ -ትግራይን ያስለቀሰ ትግሬ፡፡
የጎንደር እናቶች መካን ቢሆኑ የተመኙት በመላኩ ተፈራ ጊዜ ነው፡፡በመላኩ ያልተነጠቀ ልጅ ያለው ጎንደሬ ትንሽ ነው፡፡መላኩ አማራ ነበር-አማራን ያለቀሰ አማራ፡፡
ቀልቤሳን ታውቁታላችሁ፡፡ባሰቃያቸው ሰዎች ተይዞ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ የተላከው ጨካኝ፡፡ጭካኔው ማህጸን ውስጥ ብረት እስከመክተት የደረሰ ደነዝ ነው፡፡ብዙ ተጠቂዎቹ ኦሮሞች ነበሩ፡፡ቀልቤሳ ኦሮሞ ነበረ-ኦሮሞን ያስለቀሰ ኦሮሞ፡፡
ጭካኔ ከግላዊ ሳይጥናኤላዊነት እንጂ ከአንድ ብሄር ጋር አይገናኝም፡፡ተገናኝቶም አያውቅም፡፡ላይ ላዩን አንድ ብሄር አዛዥ የሆነ መሰላችሁ እንጂ ትዕዛዙን ተቀባብለው የሚፈጽሙት የእያንዳንዳችን የቅርብ ሰዎች ናቸው፡፡
በነገራን ላይ ጨካኝ ገዢዎች በብሄሮች መካከል ያሉ ቅራኔዎችን ስፖንሰር በማድረግ ይታወቃሉ፡፡ሁሉም ተባብሮ ብቻቸውን መቅረት ስለማይፈልጉ በተቻለ መጠን ቅራኔና አምባ ጓሮን ያነሳሳሉ፡፡ወደ አንዱ ብሄር ጠጋ ይሉና ‹‹ አንተ እኮ ምርጥ ነህ…የከሌ ግን ሰው ለመባል ይቸግረዋል›› ይሉሃል፡፡አንተ በንጉስ መሞካሸት አቅልህን ያሳጣህና ደረትህን ትነፋለህ፡፡ሌላኛው ብሄር ውዳቂ እንዲሆን ሳታስበው ትመኛለህ፡፡ብቻህን መብለጥ እንጂ በጋራ መራመድ ክብርህን ሚያወርድብህ ይመስልሃል፡፡እና በቃ ‹‹የከሌን በለው!›› ስትባል የንጉሱን ሰይጣናዊ ዕቅድ እያፈጸምክ ሳይሆን…ምርጥነትህን እያስከበርክ ይመስልሃል፡፡ትተኩሳለህ..ትገላለህ…ታስራለህ…..ሰብአዊነትህን በዘረኝነት ዱላ ትጨፈጭፋለህ፡፡እንዳንተ ያለውን ሰው ሳይ ባለጌ መሆንን እመኛለሁ፡፡የአለም ስድብ በቅርጫት ተሰጥቶኝ ባፈስብህ እመኛለሁ፡፡
እና ሰሞነኛዎቹ የዘረኝነት ተኳሾች ብተተው ደስ ይለኛል፡፡ትግራይ ከሌላው ኢትዮጵያ ክፍል የተለየ እየኖረች አንዳልሆነ ውስጣችሁ ያውቃል፡፡በዘመድና በጥቅም የተሳሰሩ እና ስልጣንን በ‹ትግሬ ስም› ርስት ያደረጉ ሰዎችን ቆጥሯቸው፡፡አስርሺ ይሞላሉ! እና በእነዚህ ሰዎች ሰበብ አምስት ሚሊየን ህዝብን በጠላትነት ስትፈርጁ አታፍሩም፡፡
እኔ ምርጥ ትግሬ ዘመዶች አሉኝ፣የማልረሳቸው ጓደኞች አሉኝ፣ከራሴ የማልነጥላቸው ባለንጀሮች አሉኝ፡፡ትግሬነት ከአንባገነንነት እንደማይዛመድ ከኔ በላይ ምስክር የለም፡፡ጠቤ ከኢህአዴግ እንጂ ከትግሬ አይደለም፡፡መከራ ያስቆጠረኝ ኢህአዴግ የተባለው ከሁሉም ብሄር የመጡ ወናዎች ድምር ማህበር እንጂ አንድ ብሄር አይደለም፡፡
እና ከቻላችሁ የጥላቻ መልዕክታችሁን አስቀድማችሁ ‹ታግአታድርጉኝ›፡፡ እንደዚህ ካለ ሀገር ሸርሻሪ አይረቤነት ጋር የምሰለፍበት ልብ የለኝም፡፡ብዙ ነገር ያጣሁ ብሆንም ይሄ የሰውነቴ ምሶሶ ነውና እንድትነኩት አልፈልግም፡፡ደህና ደሩ-ኢትዮጵያዊያን፡፡

fro, Habtamu seyoum

No comments:

Post a Comment