Monday, January 5, 2015

ኮፍያ ደርበው ፥ ኩሽክ ተከናንበው!! – እንግዳ ታደሰ

አፈር ይቅለላቸውና ! በአንድ ወቅት ልደተ ትውልዳቸው ኤርትራዊ ሆኖ ፣ በነፍጠኝነት ዘመቻ ወላጆቻቸው ሃረር ላይ የወለዷቸው ዶክተር አሰፋ መድህኔ ለሥራ ጉዳይ ኖርዌይ በሚመላለሱበት ወቅት ያወጉን ጨዋታ ፣ ለምን እንደሆነ አላውቅም ዘወትር እየተመላለሰ ያስቀኛል ፡፡ ጨዋታው እንዲህ ነው ፡፡ ዶክተር አሰፋ ወደ ኦስሎ በተደጋጋሚ ብቅ ሲሉ
የድሮ ጓደኛቸውን አቶ ዩሱፍ ያሲንን ወይም በብዕር ስሙ ሃሰን ኡመር አብደላን መጥቻለሁ ብለው ይደውሉለት ነበር ፡፡
ዶክተር አሰፋ ሲመጡ ጨዋታቸው እጅግ መሳጭ ስለሆነ ፣አቶ ዩሱፍ ብቻ ሳይሆን ፣ አቶ ግደይ ዘርአጽዮንን ጨምሮ ፣ ኦስሎ ውስጥ በምትገኘው የኢትዮጵያ ማዕከል ውስጥ ሁልጊዜ የምናገኛቸው ሰዎችም ነበርን ፡፡

ዶክተር አሰፋ ፣ የአቶ ግደይን ተክለ ሰውነት ወይም ቁመና ገርመም አደረጉና ፣ ግደይ አሉት ፡፡ የቁመትህን ርዝማኔ ሳየው ወደ ሜትር ከሰማንያ አካባቢ ይመስለኛል ፡፡ ህወሃትን የመሰረታችሁት ሰዎች አብዛኞቻችሁ ቁመታችሁ ከሜትር ከሰማንያ በላይ ነው ፡፡አረጋዊ በርሄን ውሰድ በትንሹ ሜትር ከዘጠና ውስጥ ይሆናል ፡፡ አስፋሀን ውሰድ ሁለት ሜትር
ያህል ይሆናል ፡፡ ሁላችሁም ረጃጅሞቹ ከጨዋታ ውጭ ሆናችሁ ፡፡ የተከረከመች የመሰለችው አጭሯ መለስ ግን ገለባበጠቻችሁ አሉት ፡፡ ጨዋታቸውን በማስረጃ ሲያስደግፉ ይህ ህወሃት ላይ ብቻ አልሰራም ፡፡ አጼ ምንይልክን ውሰዳቸው አጭር ናቸው ፡፡ አጼ ኃይለስላሴን፥ ኮለኔል መንግሥቱን ብትወስድ አጫጭሮች ናቸው ፡፡ ስለዚህ ረጃጅሞች
ስልጣን ላይ ለመድረስ ድንክየዎች ስለሆናችሁ ፣ ድንክየዎቹ ናቸው ስልጣን ላይ የሚደርሱት ያሉት አባባል ፣ የአቶ ገብሩ አስራትን መጽሃፍ ሳነብ ዶክተር አሰፋ ትዝ አሉኝ ፡፡ ረጅም ነህና ሞኝነት አታጣም በማለት አስናቀች ወርቁስ አዚማ የለ ?
በዚህ በያዝነው የኢትዮጵያውያን ዓመት ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ ያሳለፍነውን ጭጋጋዊ የፖለቲካ አክሄዶቻችንን የሚዳስሱ እና የሚፈትሹ ፣የፖለቲካ መጽሃፍቶች የወጡበት ወቅት ነው ፡፡ ከብላቴናው ደራሲ ኤርምያስ ለገሰ ጀምሮ የጎምቱዎቹን ፣ ዶክተር ነገደ ጎበዜ ፥ የኣይተ ገብሩ አስራትን እና የአቶ ዩሱፍ ያሲንን ጨምሮ ፡፡ መጽሃፍ ጽፍው በዚህ አመት ባያስነብቡንም የኖርዌይ ብርድ አስመርሯቸው የቀድሞ የኦነግ አክሄድን ኮንነው አዲስ መንገድ ካለተከተልን መድረሻችን የንቧይ ካብ ነው ያሉትን አቶ ሌንጮ ለታን አክሎ የሄድንበትን ትውልድ አኮላሽ ጉዞ እንደገና እንድናስብበት ለትውልዱ የተነገረበት ወቅትም ነው ፡፡ በአሰባሳቢ ማንነት በአንድ አገር ልጅነት የአቶ ዩሱፍ ያሲን መጽሃፍ ላይ መግቢያ የሆኑትም አባ ባህርይ አቶ አሰፋ ጫቦን ከገቡበት ሱባኤ አውጥተው ወደ ኋላ ሄደው ያሳለፍነውን ፖለቲካ እንድናይና እንድንወያይበት ምልከታ እየሰጡን ያዳመጥንበት ዓመትም ነው ፡፡
የዛሬው ጽሁፌ ታሪካዊውን የአቶ ገብሩ አስራት መጽሃፍን ለመቃኘት አይደለም ፡፡ ታሪካዊ ስል ብዙዎችን ቃሌ እንደሚያበሳጫቸው ይገባኛል ፡፡ መጽሃፉን ሳያነቡ ግን እንዲሁ በጥላቻ ጥላቻን በመግለጽ ከመሳደብ ይልቅ የመጽሃፉን ጠንካራና ደካማ ጎን አይቶ ነቀፋም ሆነ ድጋፍ መስጠት ይቻላል የሚል የግሌ አቋም ስለ- አለኝ ነው ፡፡ ነቀፋው ላይ
አይጋም ስላላንቀላፋ ፣ባይሆን ይህ መጽሃፍ እንደሚሰማው በስፋት ኢትዮጵያ ውስጥ እ አይጋም የተነበበ ነው ስለሚባል፣ ጭፍን የህወሃት ደጋፊ ወያኔዎችን የት ጋ ያቆማቸው ይሆን የሚለውን ወደፊት እንድናይ ያደርገናል ፡፡
በዚህ መጽሃፍ ውስጥ ከነ- ክርብቴ እስከ ውሃ ገብቴ ያሉትን የህወሃት መሪዎች እንዴት ከነገብሩ አስራት ቡድን ሸርተት ብለው ከማኪቬልያዊው መሪ መለስ ስር እንደተሸጎጡ መጽሃፉ ግልጽ አድርጎ ሲያስነብበን ፣ እኔም የአቶ ገብሩ አስራትንና የአፈንጋጮቹን የቁመት ርዝመት ስንት ይሆን ብየ እንደ ዶክተር አሰፋ እንድጠይቅ አደረገኝ ፡፡ |የመለስን
ተገለባባጭ ጸባይ ከሽሉ ጀምረው የሚያውቁት እነ ኣይተ ገብሩ በመዘናጋታቸው ፣ የነበራቸውን ከፍተኛ ድጋፍና ድምጽ በልዩ ሴራው ጊዜ እየገዛ ውስጥ ውስጡን የአዜብ መስፍንን የኩሽና ሙያ እያንዳንዱን አፈንጋጭና የጦር መሪዎች ጭምር እንዲበሉ ጋብዞ ጉድ እንዳደረጋቸው መጽሃፉ በዝርዝር ይገልጻል ፡፡
መለስ የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ በወቅቱ በድምጽ ብልጫ ድባቅ እንደመታው ሲያውቅ ፣ አጋር ፍለጋ የሄደው ወደ ብአዴን ነበር ፡፡ብአዴኖችን፣ አፈንጋጮቹ ጠባብ የትግራይ ብሄረተኛ ሆነው አስቸግረውኛል ፡፡ ሁሉም ነገር ለትግራይ በሚል ጠባብነት ተነሳስተው ትግራይ ብቻ ትልማ በሚል የያዝኩትን አገር በእኩልነት የማስተዳደር ትልሜን ሊያመክኑት
ተዘጋጅተዋል የሚል ቅስቀሳ በማድረግ ፣የብአዴኑን ጄኔራል ኃይሌ ጥላሁንን በጸረ ትግራዋይነት ከጎኑ ሲያሰልፍ ፣ ከኦህዴድም ጄኔራል ባጫ ደበሌንና ጄኔራል አለም እሸት ደግፌን ጭምር ፣ በጸረ ትግራይነት እንዲሰለፉ አድርጓቸው ነበር ፡፡
በአንድ ወቅት መለስ ከጫናቸው ጄኔራሎች አንዱ የነበረው ባጫ ደበሌ፣አፈንጋጮች የትግራይን ህዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለየ ተጠቃሚ አድርገዋል ብሎ ሲመሰክር « እኔ እስከማውቀው ድረስ ቀድሞ የትግራይ ገበሬ ለእግሩ መጫሚያ አልነበረውም ፣ በቅርቡ ግን ትግራይ ውስጥ ተንቀሳቅሼ እንዳየሁት እያንዳንዱ ገበሬ ጫማ አድርጓል፡፡ ይህም ክልሉ ልዩ ተጠቃሚ መሆኑን ያመለክታል ብሎ ባጫ እንዲናገር በማድረጉ መለስ ከብአዴን እንዲሁም ከኦህዴድ ድጋፍ እንዲያገኝ አድርጎት ባሸናፊነት እንዲወጣ አድርጎታል ብለው በመጽሃፋቸው ገብሩ ያወጉናል ፡፡ መለስ ከጭንቅ ቀን ያዳኑትን ወላዋይ የብአዴንና የኦህዴድን ሰዎች አለምሸትንና ኃይሌ ጥላሁንን ጨምሮ ጊዜ በመጠብቅ ወርውሯቸዋል ፡፡ አለምሸትን ማዕረጉን ገፎ እንደ ሸንኮራ ጭማቂ ወርውሮታል ፡፡ ሌሎችንም እንደዛው፡፡ሰሞኑን ደግሞ የህወሃትን የአርባኛ ዓመት የውልደት ቀን አስመልክቶ በደደቢት በተደረገው የሟሟሻ ቅድመ ማሟሟቂያ ዝክረ በዓል ከአዲስ አበባ በጋቢናና -ፖርቶመጋሌ ላይ ጭነው በወሰዷቸው ታዋቂ የኪነጥበብ ሰዎች ፣ እንዲነገር የተደረገው አዲስ ትርክት ፣መለስ በዚያን ጊዜ አፈንጋጮችን ለማሳጣት እንደተጠቀመበት አይደለም ፡፡ የትግራይን ህዝብ ወዘና ስናየው ዱቄት የተነፋበት ነው የሚመስለው ፡፡ ይህ ህዝብ ልጆቹን ገብሮ ነጻ ቢያወጣንም ገጽታው ግን የተለወጣ አይደለም የሚል የሃዘን መግለጫ በከያኒዎቹ ጉሮሮ እንዲንቆረቆር ተደርጓል ፡፡
ይህ ንግግር አባይ ወልዱን ያስደስታል ተብሎ ባይታመንም ፣ የትግራይ ህዝብ ተጠቃሚ ሆኗል ተብሎ በስፋት የሚዘገበውን ንግግር ግን ያረክስልናል የሚል የህወሃት ብልጣ ብልጦች አካሄድ ነው ፡፡ እነኝህ የታወቁ የተባሉ የኪነጥበብ ሰዎች በደደቢት ዋሻ ውስጥ ኩሽክ” የተባለውን ተጋዳላዮች አንገታቸው ላይ የሚጠመጥሙትን ሻርፕ አንገታቸው ላይ ጠምጥመው ፥ በኮፍያ ላይ የህወሃትን ኮፍያ ደርበው በተለይ ረጃጅሞቹ ሠራዊት ፍቅሬና አበበ ባልቻን ስመለከታቸው ዶክተር አሰፋ መድህኔ ትዝ አሉኝ ፡፡ ረጃጅሞች የፖለቲካ ጨዋታውን አያውቁበትም ያሉትን ዓይነት ፡፡
በኮፍያ ላይ ኮፍያ መደራረብን እስከመቼ እንደሚቀጥሉ ባናውቅም ፣በደርግ ስርአት የብሄራዊ ውትድርና የሰራዊት አባል የነበረው ሠራዊት ፍቅሬ ፣ ህውሃት በማረከው ታንክ ላይ ወጥቶ በወገን ሠራዊት ደም ላይ ተሳልቆ ሰላምታ ሲሰጥ ማየትና በቴዎድሮስ ቲያትር ላይ ግርማ ሞገስ ተላብሶ ጀግናውን ገብርየን ሆኖ የተወነው አበበ ባልቻ የህወሃትን ኮፍያ
አድርጎ ባለቀው የወገን ሰራዊት ላይ እንደጠላት ሲሳለቅ ማየት ህሊናና ሆድ እንዴት እንደተራራቁ ያሳያል ፡፡
በስተመጨረሻም እነኝህን የኪነጥበብ ሰዎች ሳስብ አንድ የስታሊን ቀልድ ትውስ አለኝ ፡፡እንዲህ ነበር ትርክቱ ፡፡ስታሊን በአንድ ወቅት አንድ አስቂኝ ኮሜዲ ፕሬሚየር ፊልም እንዲመርቅ ይጋበዛል ፡፡ፊልሙን መመልከት እንደጀመረ በሳቅ ይሞታል ፡፡ እጅግ በማሽካካት ይስቃል ፡፡ ፊልሙ እንዳለቀም ስለፊልሙ አስተያየቱን እንዲሰጥ ይጠየቃል፡፡ስታሊን
ኮራ ብሎ ድንቅ ፊልም ነው ፡፡ በተለይ ዋናውን ተዋንያን እንደኔ ከላይ ጺሙን አሳድጎ የተወነውን አደንቀዋለሁ ግን ረሸኑት ብሎ ትዕዛዝ ይሰጣል ፡፡ ሁሉም ተዋናይ በቆመበት ይደርቃል ፡፡ ከዚያም የፊልሙ ዋና አዘጋጅ ጓድ ስታሊን ጺሙን ላጭተን ብንተወውስ ብሎ ቢያማክረው…..መልካም ላጩትና ረሽኑት እንዳለው ፣ እነኝህ ተዋንያን የተባሉት
አርቲስቶች ለቀዳዳ መሙያ እንደተፈለጉ አለማወቃቸው ነው የሚያሳዝነው ፡፡ በህወሃት እጅ ካርዶቻቸው ተይዟል፡፡
አንድ ቀን የማይወጡት ሥራ ይሰጣቸዋል፡፡ ወይ ንብረታቸውን ወይ ደግሞ ጺማቸውን… ምርጫው የነርሱ ነው ፡፡

No comments:

Post a Comment