Wednesday, January 14, 2015

የቃጠሎው መንስዔ ምንም ይኹን ምን ጣይቱ ሆቴል ወደቀደመ ይዞታው ይመለስ!!!

የቃጠሎው መንስዔ ምንም ይኹን ምን ጣይቱ ሆቴል ወደቀደመ ይዞታው ይመለስ!!!
በ1898 ዓ.ም የጣይቱ ሆቴል ተመሠረተ። ከቤት ውጪ ምግብ በገንዘብ ገዝቶ መመገብ እንደ ትልቅ ነውር በሚቆጠርበት በዚያ ዘመን ሆቴል ለማቋቋም ማሰብ የሩቅ ዓላሚ ሰው ሥራ ነው። ዳግማዊ ምኒልክ ይኼን ሆቴል ከፍተው መኳንንቶችንና ባላባቶችን እየጋበዙ ወደ ዘመናዊነት የሚያሸጋግረውን የቱሪዝምና የሆቴል ሥራ ሀ ብለው የቀደዱት ከዛሬ 109 ዓመት በፊት ነበር . . . በጥንቷ መሀል አራዳ በአሁኗ ፒያሳ እምብርት ላይ። በዓለም ላይ ታላቅ ዝናን ያተረፈው ሂልተን ሆቴል የተመሠረተው ጣይቱ ሆቴል ከተመሠረተ ከ20 ዓመት በሁዋላ እ.ኤ.አ. በ1925 ዓ.ም ነው። ጎበዝና ታታሪ . . . ለአገር የሚቆረቆርና ለቅርስ ግድ የሚለው . . . መንግሥት ቢኖረን ኖሮ በዓለም ላይ ካሉ ጥንታዊ ሆቴሎች አንዱ ባስባልነው ነበር። ያ ሳይኾን ቀርቶ በእሳት ወደመ ለሚል አሳዛኝ ዜና ተዳረገ፤ ተዳረግን።

አንድ ምዕተ ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረው ጣይቱ ሆቴል ተቃጠለ የሚል ዜና መስማት በራሱ ከመርዶዎች ሁሉ ከፍ ያለ መርዶ ነው። መርዶው ከፍ ያለ የኾነብኝ ዳግማዊ ምኒልክ ስላሠሩትና በንግሥት ጣይቱ ስም ስለተቋቋመ ብቻ አይደለም። ማንም ቢሠራውና ቢያሠራው ችግር የለውም። ትልቁ ቁም ነገር ታሪካዊ ቅርስነቱ ነው። ቅርስ ሲወድምና ሲጠፋ . . . ታሪክ ሲበላሽና ሲያከትም የማይናደድና የማይበግን ሰው ካለ ጤናማ አእምሮ የሌለው ብቻ በመኾን አለበት። በአንድ አገር ወይም ከተማ . . . አሊያም መንደር ውስጥ የተሠራ . . . በጎም ኾነ መጥፎ ታሪክ መጥፋት የለበትም የሚል ጽኑ እምነት አለኝ። በመጥፎም ኾነ በጥሩ የሚነገረው ታሪክ ስላለፈው ሕብረተሰብ ዕድገት/ ሁዋላ ቀርነት . . . ወይም በጊዜው ስለነበረው አስተሳሰብና አመለካከት የሚነግረን አንዳች እውነት ስላለው . . . ለመጪው ትውልድ መማርያ ኾኖ ባለበት እንዲቆይ መደረግ ይኖርበታል።
የጣይቱ ሆቴል እንዴት ሊቃጠል ቻለ ለሚለው ጥያቄ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ መልስ ማግኘት እንደማይቻል እሙን ነው። ብዙዎች የራሳቸውን መላ ምት እያስቀመጡም ነው። ከሁሉ ያስገረመኝ ግን የኢቲቪ አዘጋገብ ነው። የጣይቱ ሆቴል ታሪካዊነት . . . ጥንታዊነት . . . አርክቴክቸራል ውበት . . . እና የመሳሰሉት ከሆቴሉ ጋራ የተያያዙ ወሳኝ መሠረታዊ ነገሮች ለኢቲቪና ለኢቲቪያውያን አላስፈላጊ ነገሮች ናቸው። ከዚያ ይልቅ በሆቴሉ ውስጥ የተከራየ የአንድ ባንክ ጉዳይ ግብግብ ያደረገው ይመስላል። ይህ ዐይነቱ ሐላፊነት የጎደለው ለታሪክና ለቅርስ መጥፋት ግድ የማይሰጠው አዘጋገብ ከቃጠሎው በስተጀርባ ምን ይኖር ይኾን የሚል ጥያቄ ማንሳት ለሚሹ ወገኖች በቂ ምክንያት ሊሰጣቸው ይችላል።
በመላምት ላይ ተንተርሶ የቃጠሎው ምክንያት እንዲህና እንዲያ ሊኾን ይችላል ለማለት የሚገፋፋንም ይህ መሰሉ ጉዳይ ነው። እጅግ አሳዛኙና አስገራሚው ነገር ከጣይቱ ሆቴል አፍንጫ ስር ያለው የእሳትና አደጋ መከላለከያ ጣቢያ እሳቱን ለማጥፋት ፈጥኖ መድረስ አለመቻሉ ነው። ለአንድ እግረኛ ዐሥር ደቂቃ የማይፈጀው ርቀት ለእሳት አደጋዎች እንዴት ሰዓታት ፈጀባቸው? በምን ሂሳብስ ነው ከግማሽ በላይ የወደመን ሆቴል እሳት ያጠፋ ቡድን ምስጋና የሚዥጎደጎድለት? እውነተኛ የመልካም አስተዳደር ቢኖርማ የጊዮርጊስ እሳት አደጋ ጣቢያ በዚያ ቅርብ ርቀት ላይ ኾኖ ሆቴሉ በዚህ ደረጃ እስኪወድም ድረስ በመዘግየቱ ብቻ በሐላፊነት ሊጠየቅ በተገባው ነበር።
ጣይቱ ሆቴል አዲስ አበባ ላይ ካሉ ሆቴሎች በተለየ በዚህ ዘመን ትኩረት መሳብ የሚያስችሉ ብዙ ነገሮችን እያከናወነ ያለ ሆቴል ነው። መንግሥት የሥነ ጥበብ ሥራዎች “በልማታዊ ሥነ ጥበብ ፖሊሲ” ታጥረው . . . በነጻ ሐሳብ ላይ ቆመው ያለገደብ ለእውነትና ለእውነት እንዳይቆሙ ካደረጋቸው ሰንብቷል። ቴአትር ቤቶች ሙሉ በሙሉ “በልማታዊ አርቲስቶች” ተውጠው ለዘመናት የዳበረ ልምድ ያላቸውን ባለሞያዎች በግምገማ ቁም ስቅላቸውን ያሳዩዋቸዋል። ይኹንና ሥነ ጥበብ ያብብበታል . . . ተብሎ የሚጠበቅበት ይህ ቦታ በልማታውያኑ ተጠርንፎ መላወሻ ባጣበት በዚህ ወቅት ብዙ ገጣምያንና የስነ ጥበብ ሰዎች በነጻነት ሥራቸውን የሚያቀርቡበት አንድ ስፍራ ጣይቱ ሆቴል ነበር። ለዚህ እንደ ማስረጃ ከሚጠቀሱት አንዱ ጃዝ አምባ ነው። ምናልባት እንደ አንዳንድ ሰዎች መላምት ከጣይቱ ሆቴል የእሳት አደጋ ጀርባ ብዙ መጠየቅ ያለባቸው ጥያቄዎች ሳይኖሩ አይቀሩም የሚለውን ሐሳብ የሚያጠናክረውም ሆቴሉ የነጻ ሐሳብና ገደብ የሌለበት የጥበብ መፍለቂያ ቦታ መኾኑም ጭምር ይመስለኛል።
የእሳትና አደጋዎች መከላከያ በምን ያህል ደረጃ የእሳት አደጋ መንስዔዎች እንደተከሰቱ የሚያጣራበት የፎረንሲክ ቴክኖሎጂ ላይ እንደደረሰ መረጃው ባይኖረኝም ሆቴሉ እንዴት ሊቃጠል እንደቻለ እውነተኛና በቂ የኾነ ማስረጃ ሰብስቦ ለሕዝብ እውነቱን የመናገር ሐላፊነቱን እንደሚወጣ ተስፋ ማድረጉ የሚበጅ ይኾናል። ከጀርባው ሌላ ፖለቲካዊ የማቃጠል ተልእኮ ከሌለው በስተቀር ይህ ጉዳይ ከባድ ሥራ አይደለም ከሚል የዋህነት በመነሳት ጭምርም ነው ይህን ማለቴ።
ከዚህ በተረፈ ሌላው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነገር ሆቴሉ በፈለገው ደረጃ የመቃጠል አደጋ ቢደርስበትም . . . መንግሥት ሐላፊነቱን ወስዶ ቀድሞ ወደነበረበት ይዞታ እንዲመለስ በከፍተኛ ሐላፊነት መሥራት አለበት። የጣይቱ ሆቴል አሁን በሕይወት ያለነው ሰዎች ከመታሰባችንም ከመታለማችንም በፊት ቀድመውን በዚያች ምድር ይኖሩ የነበሩ አያት ቅድመ አያቶቻችን ያስረከቡንና የሰጡን ታሪካዊ ቅርሳችን ነው። የአንድ መንግሥት ሐላፊነት (ምንም ዐይነት ፖለቲካዊ ርዕዮት ይከተል) የአገሪቱን ቅርሶችና ታሪኮች ለቀጣዩ ትውልድ ሳይሸራረፉ ማስረከብ ነው። ይህ ሳይኾን ቀርቶ (በተቃጠለ ስም እንደተለመደው) የልማታዊ ግብ ማስፈጸሚያ ሊያደርገው ካሰበ በድጋሚ የአገሪቱን ታሪኮች ለማጥፋትና ለመቅበር ቆርጦ የተነሳ መንግሥት ለሚለው ክስ ባንድም ኾነ በሌላ መልኩ ማረጋገጫ አስቀመጠልን ማለት ነው።
እኔ በበኩሌ የጣይቱ ሆቴልን መቃጠል በተመለከተ አንድ ዘመቻ መጀመር አለበት ባይ ነኝ። የቃጠሎው መንስዔ ምንም ይኹን ምን ሆቴሉ ቀድሞ ወደነበረበት መልክ ይመለስ የሚል ዘመቻ ያስፈልገናል። ምናልባትም መንግሥት ይህን ጉዳይ በቸልተኝነት ለማለፍ ቢሞክር ሰላማዊ ሰልፍ እስከማድረግ የሚያስኬድ ዘመቻ ማቀናጀት ተገቢ ነው።
የቃጠሎው መንስዔ ምንም ይኹን ምን ጣይቱ ሆቴል ወደቀደመ ይዞታው ይመለስ!!!

No comments:

Post a Comment