Friday, January 2, 2015

አላስፈላጊ ልማት ከጥፋት አይተናነስም!

ቅድሚያ ተሰጥቷቸው መከናወን ያላባቸው የልማት ስራዎችን በአስተማማኝ መልኩ ባልተረጋገጡበት ሁኔታ ወቅቱን ያልጠበቀና የብዙሀኑን የልማት ጥያቄ መመለስ የማይችል ልማት ተገቢ ልማት ተደርጎ አይወሰድም። ቅድሚያ መሰጠት የሚገባቸውን አንገብጋቢ የህዝብ ጥያቄዎችን ቅድሚያ መሰጠት ሲገባ የተጀመሩ ሰፋፊ የልማት ስራዎች በጅምር በቀረቡት ሁኔታ ከአቅም በላይ የሚደረግ ዝላይ ለመፈጥፈጥ ካልሆነ በቀር ፋይዳው አይታየኝም። ከፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ውጪ በገጠር ዝናብን ጠብቆ መሬት በመርፌ እየጫረ የሚተዳደር አርሶ አደር ይዞ፣ በከተማ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ስራ አጥ ወጣት እያርመሰመሱ፣ አገሪቱ በአለም የስደተኛ ምንጭ በመሆን ቀዳሚውን ቦታ በያዘችበት በአሁኑ ወቅት ሮኬት የማስወንጨፍ ልማት የሚለው ፉገራ ተቀባይነት የለውም።
በአገሪቱ የሚገኙ ሆስፐታሎች የጤና አገልግሎት የሚሰጡበትን አቅም ሳይገነቡ፣ ተመጣጣኝ የጤና አገልግሎት ሽፋን ማግኘት ያልቻለ ህብረተሰብ ይዞ፣ ወጣቶች እንደፍላጎታቸውና አቅማቸው የሚስተናገዱበት በቂ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሌሉበት ሁኔታ ሮኬት ማስወንጨፍ ወደ ህዝብ ላውንቸር እንደመተኮስ የሚወሰድ ድርጊት ነው። የመብራትና ውሀን የመሳሰሉ ለህዝብ በጣም መሰረታዊ የሆኑ ልማቶች ከህዝብ ፍላጎት ጋር ለመራመድ እንደ ኤሊ በሚጓዙበት፣ በአለም በሚያሳፍር ሁኔታ ከድህነት ወለል በታች የሚገኝ ነጭ ድሀ ዜጎች ህይወት መሻሻል በሚያመጡ የልማት ስራዎችን ቅድሚያ መሰጠት ሲገባ "ሁሉ አማረሽን" እንዲሉ ከህዝብ የልማት ጥያቄ ውጪ መንግስት ያማረውን ሁሉ በአድራጊ ፈጣሪ ስሜት ማከናወን ኃላፊነት ከሚሰማው መንግስት አይጠበቅም።
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገራት የልማት ስራዎች ቅድሚያ የብዙሀኑን የልማት ጥያቄ ባገናዘበ መልኩ መከናወን ሲገባቸው በጀት የማዘዙ ስልጣን ስላለ ብቻ ብዙሀኑ መግባባት ላይ ያልደረሰባቸውን የቅንጦት ስራዎች ላይ ትኩረት መስጠቱ ተገቢ አይደለም። ከቁጥር ግርግር ባለፈ መልኩ የዜጎች ቁሳዊና ቁሳዊ ያልሆኑ የልማት ጥያቄዎች በተጨባጭ አስተማማኝ በሆነ መልኩ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ልኬትን አልፎ ወደላይ ማንጋጠጡ በአገር ላይ ከመቀለድ ተለይቶ አይታይም። የአገሪቱን መሬት ቆፍሮ ለጋራ እድገት የሚጠቅሙ ነዳጅን የመሳሰሉ ሀብቶችን ለልማት የመጠቅምን አማራጭ ወደጎን በመተው ወደ ሰማይ ማንጋጠጡ ስንፍና ነው። በአሁኑ ወቅት የጥቂቶች ፍላጎት ካልሆነ በቀር የብዙሀኑን ፍላጎት የሚያሟላ አገራዊ ጥቅም በሰማይ ላይ የለንም። ልማቱ አስፈላጊ ቢሆንኳ ወቅታዊነት የለውም። ቅድሚያ ተሰጥቷቸው መሰራት ያለባቸው በርካታ አገራዊ የቤት ስራዎች አስቀምጦ የሚደረግ የሰማይ ላይ ሽርሽር ተቀባይነት የለውም። የብዙሀኑን ጥያቄ ሊመልስ የማይችል ልማት ከጥፋት ተለይቶ አይታይም። ትክክለኛ የልማት አቅጣጫን እከተላለሁ የሚል መንግስት በቅድሚያ መሰረታዊ የሆኑ የዜጎች የልማት ጥያቄዎችን በአጥጋቢ መልኩ መመለስ የሚችሉ የልማት ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባዋል እንጂ የብዘሀኑን የልማት ጥያቄ የማይመለከቱ ስራዎችን በጭፍን ማከናወን የብዙሀኑን ጥቅም የሚገፋና የአገር ሀብትን ለማባከን በር የሚከፍት ፀረ ዴሞክራሲያዊነት ተደርጎ የሚወሰድ ድርጊት በመሆኑ በአስቸኳይ መታረም አለበት።

No comments:

Post a Comment