Friday, January 2, 2015

መለስ ሰርቶ ያልጨረሰው አሻንጉሊት

ቹቸቤ
ለኃይለማርያም ደሳለኝ የተጻፈ ሽሙጥ
ይህን ለሕዝብ ጆሮ ብሎ መጻፉ በራሱ ሰቅጣጭ ቢሆንም አንዳንዴ ስቆ ለማለፍም መጋራት ይበጃል እናም ለሳቸው እንዲህ ብዬ ብነግራቸው ጥሩ ነበር ያልኩትን ለናንተም አካፍላለሁ።Hailemariam Desalegn, Meles Zenawi's unfinished toy
አቶ ሐይለማርያም ሆይ ስለ እርስዎ ማፈራችን እስከመቼ ይቀጥላል? ገና መናገር ሲጀምሩ ስቅቅ ይለኛል። ተናግረው ሲያበቁ ሙሉ ሰው መሆንዎንም ማመን ያቅተኛል። እንዲያውም አሁን አሁንማ መለስ ጀምሮ በወጉ ያልጨረሰው አሻንጉሊት ይመስሉኛል። መለስ ኮርጀን ገልብጠን ቢል ያምርበታል መገልበጥም መኮረጅም ማስመሰልም ማድበስበስም የክብር የዶክትሬት ዲግሪ የሚያሰጠው ብልጥ ሰው ነው በቃ ሞላጫ አራዳ የሚሉት አይነት ነው።

እርስዎ እግዜር ሲፈጥርዎ የሞኛ ሞኝ ገጽታ የየዋህ ሰው ቆዳ ይዘው የመገለባበጥ ችሎታው ሳይኖርዎት እንደልብ የሚዘግኑት የቃላት ቀረጢት ሳይዙ ጋዜጠኛ ፊት ቀርበው በማትረባ ጥያቄ ላብ ላብ ሲሎት ማየት እንዴት አሳዛኝ እንደሆነ ቢያውቁ ደግ ነበር።
በሚናገሯቸው ቃላት የእውቀትዎ ልክ ብቻ ሳይሆን የማስተዋል ብቃትዎ የብልጠትዎ መጠን ፍንትው ብሎ ይታያል እናም ያሳፍራል። እውነቴን ነው የምሎት በጣም ያሳፍራሉ። እኚህ ሰው እንኳን የተማሩ በትምህርት ቤት በኩል ያለፉ አይመስልም እያሉ ሰዎች ቢያወሩስ እንዴት ይፈረዳል? አረ ጥሩ አይደለም ለመሆኑ መልሰው ቃለመጠይቅዎን ሲመለከቱ ምን ይሰማዎታል? ምናልባት እኮ የቢቢሲን ጋዜጠኛ ልክ ልኩን ነገርኩት ይሉ ይሆናል ቂ ቂ ቂ … የቂል ነገር።
እውነቴን ነው የምሎት እርስዎ ድንገተኛ መገጣጠም ካልሆነ በቀር ፖለቲካ በደረሰበት ሊደርሱ አይገባም ነበር። “አህያም ቢሆን በኔ ያመነ ኢሕአድግ ይሆናል” እንዳለው ጌታመለስ እርስዎም እንደዚያ ሆነው ጠቅላይ ሆኑና የውርደት ቀንዎ መሽቶ በነጋ ቁጥር መሳቀቃችን በዛ። ታድያ ከመለስ መማር ሲገባዎ የብልጦቹ ብልጥ የመሰሪዎች መሰሪ ከሆነ ሰው ልኮርጅ ብለው እማይሆን ገደል ላይ ተንጠለጠሉብንና ተሳቅቀን አለቅን… አረ ለ እርስዎ በጣም አፈርን። “ብልጥ የእለቱን ብልህ የአመቱን” የሚል አባባል ባስኮርጅዎ አስበው መናገር ይጀምሩ ነበር … ወይ አለመተዋወቃችን!
አንዳርጋቸው በኤርትራ መሬት ሊገደል ‘አንገረብና ቄሱ’ ሲዶልቱ የርስዎን ይሁንታ የጠየቀ የለም። ተይዞ አዲስ አበባ ሲመጣ እርስዎ የሚያውቁት ነገር አልነበረም። የአንድ ጊቢ የጥበቃ ሰራተኛ ወጪና ገቢውን የማየት እድል አለው የቤት ሰራተኛ ደግሞ ጓዳ ጎድጓዳውን የማወቅ እድል አላት እርስዎ ከነዚህ ከአንዳቸው እንኳ ያነሱ ሰው መሆንዎን ለመገንዘብ ያለመቻልዎ ለምን? ለነገሩ ስሜትዎን ገድለው ሰብዕናዎን ሽጠው መዳን በመለስ ነው ብለው የሚያድሩ ስለሆነ ግድ የሎትም። እኔ ግን ስለ እርስዎ ግድ ይለኛል። መዋረድ ይብቃዎ! መጫወቻስ መሆን ምን በወጣዎት ለየትኛው ዓለም? ከንግዲህ ይህ አለም ፍጹም ቤቴ አይደለም ብለው የዘመሩ ሰው አይደሉም እንዴ? ማን ያውቃል እሱም ከፈረንጆች የተኮረጀ መዝሙር ስለሆነ ይሆናል የዘመሩት። እውነት እውነት እሎታለሁ በኢየሱስ ስጋና ደም እንጂ በድሃ ደም ታጥበው ዘለዓለማዊ ህይወት አያገኙም።
እኔ እንደሰማሁት በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ሕንድ ድረስ ዘልቀው ተምረዋል ኮሌጅ ውስጥም ሰርተዋልና ኩረጃ የሚያፍሩበት እንጂ የሚመጻደቁበት ነገር አይደለም። አሁንማ ሳስበው እነ ካራቱሪን ከሕንድ ያመጡትና ባለመሬት ያደረጉት የኮረጁበትን ውለታ ለመክፍል ይሆን እንዴ? ማለት ጀምሬአለሁ። ቃል በቃል ገልብጠን ወሰድን ብሎ መለስ ሲናገር ቦታ ይመርጣል። እነዚያ እሱ ፈገግ ሲል በሳቅ የሚፈርሱ ሲቆጣ የሚያለቅሱ የፓርላማ አባላት ፊት ስለተናገረው ትክክል የሆነ ይመስል ሲመጻደቁበት ፈረንጆቹ ራሳቸው “This guy must be dumb” እንደሚሉ እርግጠኛ ነኝ። የቢቢሲን ጋዜጠኛ አንተንም ቢሆን ዋጋህን እሰጥሃለሁ ብለው ሲናገሩ ከፊትዎ የሚያዩት ጋዜጠኛ ያ የሚፈሩት ኦባንግ ነው ብለው የጠረጠሩ ይመስላል። ሀኪሙም ከህክምና ስራው ውጪ ፖለቲካ ከነካ አልቀውም ሲሉ እርስዎ ማህበራዊ ሳይንስ (አስተዳደር፣ ፖለቲካል ሳይንስ ወይም ሕግ) ተምረው ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑ ይመስላል። ከደናቁርት ጋር ውለው ደነቆሩ እንዳልል ከዚህ የተለየ ሰው መሆንዎን አስረጂ አላገኘሁም።
እንደ ማነጻጸርያ የፀረ ሽብር አዋጅ ሃሳቡን ከእንግሊዝ ተውሰን ከሀገራችን ሀኔታ ጋር አገናዝበን ይህንን አደረግን ቢሉ ትንሽ አለ አይደለም ግርማ ሞገስ የሚባል ነገር እሱን ጨመር ያደርግሎት ነበር። ፈረንጆቹን ስለፈራን እነሱ ያሉትን ብቻ ተጠቀምን ሲሉ ዝቅ ያደርጎታል። እንዴት ሆኖ ነው የእንግሊዙን ስለገለበጡ ትክክል ነን ሊሉ የሚችሉት? የእንግሊዝ ስለገለበጡ አፈፃጸሙ አተረጓጎሙ አተገባበሩ ሁሉ ትክክል ይሆናል ያለውስ ማን ነው? ይህ አባባልዎ እርስዎን ያለውድድር ከቂልነት ወደ ጅልነት የሚወስድ የአገላለጽ ስልት ነው። መለስ ይህን ሰምቶ ሊተርቦት ቢፈልግ ሊል የሚችለውን ሳስብ ሳቄ ይመጣል። ከአማርኛ ተረት ኮርጆ “ሲሉ ሰምታ ዶሮ በገመድ ታንቃ ሞተች” ይሎት ነበር መድረክ ላይ። የሌላውንማ እንዴት ብዬ እፅፈዋለሁ። እኔ ግን በኩረጃ ስለማላምን አዲስ ተረትና ምሳሌ ፈጥሬ “እንደ መለስ በሞከረ ምላሱ ተሳሰረ” እላለሁ።
ሕገመንግስቱ ከካናዳ ተኮርጆ፣ የፀረ ሽብር አዋጁ ከእንግሊዝ ቃል በቃል ተገልብጦ እርስዎ ራስዎ ከመለስ ተኮርጀው እንዴት ይዘልቁታል? ለምን የተደላደለ ኑሮን ደግሞ ከአንዱ የበለጸገ ሀገር የማትኮርጁልን ቂ ቂ ቂ በእርስዎ የቂል መልስ የፈጣሪዎን የመለስን አጭበርባሪነት እያጋለጡ ነውና የወያኔ ሰይፍ እንዳይከትፍዎ በጣም እፈራለሁ። ጌታ (የርስዎን ጌታ ባላውቅም) ብቻ ጌታ ይጠብቅዎ። ብዬ ምክሬን እጨርስ ነበር።

No comments:

Post a Comment