Tuesday, January 20, 2015

*** የምርጫ ሥነ-ምግባር ደንብ ፈርሙ ድራማ ምክንያቱ ግለጽ ነው፡፡ ***

ዋናው መመሪያና አቋም ይህና አብዮታዊ ዴሞክራሲ ሆኖ ሳለ ታዲያ ከምን ሥነ-አመክንዮ (logic) ወይም ምክንያት ተነስቶ ነው ወያኔ የምርጫ ሥነ ምግባሩን ፈርሙ የሚለው፡፡ እረ እንዲያውም ምርጫ ማካሄድስ ለምን ያስፈልጋልል? እዚህ ላይ ተረስተው ከሆነ ማስታወስ ያለብን ቁም ነገሮች አሉ፡፡ በ1997 ዓም ምርጫ ወቅት እኮ በኢህአዴግና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የምርጫ ሥነ ምግባር ሰነድ ተፈርሞ ነበር፡፡ ምርጫውን በፍፃሜው ከታየው ቀውስ አላዳነውም እንጂ፡፡ በ2ዐዐ2 ዓም ምርጫ ወቀትም የሥነ ምግባሩን ደንብ ከፈረሙት ፓርቲዎች መካከል ዘግይቶም ቢሆን ደንቡን መፈረሙ ከችግር ስለአላዳነው መኢአድም ከስምምነቱ እራሱን ማግለሉ ይታወቃል፡፡ እንዲያው ለነገሩ ሁለትን አጋጣሚዎች አነሳሁ እንጂ የአገሪቱ ሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ሕገ መንግሥት ላለፉት ሃያሶ ስስት ዓመታት እንደተፈለገው እየተጣሰ አይደለም ወይ? በቅን መንፈስ (in-good-faith) ለአገር፣ ለሕዝብ፣ ለታሪክ ታምነን ካልሰራን በስተቀር በአሁኑ ጊዜ ምንም ዓይነት ሰነዶች ቢፈረሙ ከወያኔ ጥቃት ያድናሉ ማለት ሞኘነት ብቻ ሳይሆን ወያኔንም አለማወቅ ማለት ነው፡፡

የምርጫ ሥነ-ምግባሩን ፈርሙ ጥያቄን በብዙ መልኩ ማየት ይቻላል፡፡ በአንድ መልኩ ሲታይ ኢህአዴግ/ወያኔ ከ1997 ዓም ምርጫ በኋላ በግልጽና በጉልበት ሲመቸውም በስልት የሚያካሄደው የመድብለ ፓርቲ ዴሞክሪሱ ቅልበሳ አካል ነው፡፡ ለሠላማዊ ሕጋዊ ፖለቲካና ለመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ ግንባታ ያለው ከፍተኛ ጥላቻ አካልም ነው፡፡ በአጠቃላይ የፖለቲካ ድርጅቶችን አስፈላጊ መስሎ ሲያገኘው አባል ፓርቲዎችን ነጥሎ ፀረ-ሠላም፣ ፀረ-ሕዝብ ሽብርተኞች፣ የሻዕቢያ ተላላኪ ወዘተ ብሎ የማጥቂያ ስልቱ አካል ነው፡፡ በመርህ ደረጃ ተቃዋሚ ፓርቲን መፍቀድ በተግባር ግን ለኢህአዴግ/ወያኔ አስጊ የሚባሉ ፓርቲዎች ውጤት አልባ እንዲሆኑ የማኮላሸት አካሄድ አካል ነው፡፡ ወዳጆቻችን ይህንን ስትረዱት ሟቹ ጠ/ሚኒስትሩም ሌላ ምክንያት ማዘጋጀት የግድ ይላቸዋል፡፡
ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ወቅት እንደተናገሩት ‹‹ተቃዋሚዎች እግር እስኪያወጡ እንጠብቃለን እግር ሲያወጡ ግን አንቆርጣለን›› ያሉት አነጋገር አካል ነው፡፡ ሀቀኛ ተቃዋሚዎችን ተቀባይነትና ተደማጭነት የማሳጣትና ከሕዝብ የመነጠል ድርጊት አካል ነው፡፡
በሌላ በኩልም ሁኔታው ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ መርህ አንፃርም ይታያል፡፡ በምርጫ ላይ የተመሠረተ አምባገነናዊ ሥርዓት (Electoral Authoritarian) የመፈጠር መርህ አካል ነው፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የይስሙላ ደሞክራሲ ነው፡፡ ለመኖር የሚፈቀድላቸው ፓርቲዎች የአጋርነት ሚና ወይም የማስመሰል ሚና የሚጫወቱ የምርጫ ጨዋታዎችን የሚያሳምሩ ሕልውና የሌላቸው አሻንጉሊቶች ብቻ ናቸው፡፡ የአውራ ፓርቲ አገልጋይ መሆን አለባቸው፡፡ ጠንካራነትና ተቀናቃኝነትን አይፈቅድም፡፡ ድርጊቱ በተግባር የአንድ ፓርቲ ሥርዐት የመፍጠር እንቅስቃሴ አካል ነው፡፡ እስከአሁን ካልተፈጠረ ማለት ነው፡፡ የኢህአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የዴሞክራሲ አዋላጅ ዋና መሣሪያ የሆነውን ነፃና ፍትሓዊ ምርጫን አይቀበልም፡፡ በአፍሪካ ተሞክሮ ላይ ጥናት ያካሄዱ ዲያመራድ የተባሉ ምሁር ፍሪደም ሀውስ (Freedom House) በተባለው ተቋም ጥናት ላይ በመመርኮዝ የአፍሪካን መንግሥታት አራት ቦታ ላይ ይመድቧቸዋል፡፡ እኚሁ ምሁር ኢትዮጵያን የመደቡት በይስሙላ ዴሞክራሲ (Pseudo-Democracy) ምድብ ውስጥ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃን ያልጠበቁ የመድብለ ፓርቲ ምርጫዎችን ለይስሙላ የሚያካሂዱ ማለት ነው፡፡ ዋና ዓላማውም አንድን አምባገነን ፓርቲን ለረጅም ጊዜ ሥልጣን ላይ እንዲቆዩ ለማድረግ ሲሆን በሌላ በኩልም ፈላጭ ቆራጭ አገዛዞች በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ፊት ተቀባይነት እንዲያኙና የተሻለም ገጽታ እንዲኖርራቸው ለማድረግ ነው፡፡ ‘’Index Politics ’’ በ2ዐ1ዐ ባወጣው የዴሞክሪሱ ደረጃ Democracy index-The Economist Intelligence unit 60 መመዘኛዎችን ተጠቅሞ ኢትዮጵያን በአምባገነንነት ሥርዓት ውስጥ ያለች አገር ብሎ መድቧታል፡፡
በሌላ በኩል ሲታይም ኢህአዴግ /ወያኔ አንዳንዴ በግልጽ ሌላ ጊዜ በተዘዋዋሪ ልማትንና የዴሞክራሲን ትስስርና ቁርኝት ለማደብዘዝ እንዲያውም ለመለያየት የሚያደርገው እንቅስቃሴ አካልም ነው፡፡ እራሱን ልማታዊ መንግሥት ብሎ በመሰየም ዋናው የአገራችን ችግር የልማት፣ የዳቦ ጥያቄ ነው የሚለው አካሄድ አካል ነው፡፡ ይህም ዴሞክራሲን ለማኮላሽት የሚቀጠምበት ስልቱ አካል ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ዓመታት የፈጁ ስለ ዴሞክራሲ የተደረጉ በርካታ ጥናቶች የሚያሳዩት እውነታዎች አሉ፡፡ በዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓትና የኢኮኖሚ እድገትና ልማት መካከል ቀጥታ ግንኙነት አለ፡፡ እንደያውም ሁለቱ አይለያዩም ማለት ይቀላል፡፡ ዴሞክራሲ ልማትን ያሳድጋል ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ መሆን አለበት፡፡ ዴሞክራሲ ለኢኮኖሚ እድገትና ለልማት የሚያስፈልጉ የፖለቲካ ተቋማት በጥሩ ሁኔታ እንዲሰሩ ያደርጋል ማለት ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ይከበራል፣ የግለሰቦች ሰብዓዊና የሲቪል መብቶችና ነፃነቶች ይከበራሉ፣ መልካም አስተዳደርን ያሰፍናል፡፡ የነፃ ገበያ ሥርዓትን ያረጋግጣል፣ ሙስናን ይከላከላል ማለት ነው፡፡ የሕግ የበላይነት መከበር ለእድገትና ልማት ወሳኝና ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት መሠረቱ ደግሞ የዴሞክራሲያዊ ተቋማት መኖር ነው፡፡ ይህም መድበለ ፓርቲ ሥርዓትን፣ ነፃና ፍትሓዊ ምርጫን፣ ነፃ የብዙሃን መገናኛዎችን መኖርና በብቃት መስራትን ያካትታል፡፡
በሌላ አንፃር ሲታየ ደግሞ አምባገነናዊ ሥርዓት ለንብረት ባለቤትነት አደገኘነት አለው፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት (በኢህአዴግ ትንታኔ) የተጠናወተው ነው፡፡ የሕግ የበላይነትን አያሰፍንም፡፡ አምባገነኖች በታሪክም ሆነ ዛሬ የሚታወቁት የመንግሥት ሥልጣን ጠቅልሎ በመያዝና ከዚህም የሚመነጨውን ጥቅማ ጥቅሞች ለራሳቸውና ደጋፊዎቻቸው በተለይም በሥልጣን ላይ እንዲቆዩ የሚረዱዋቸውን በማበልፀግ ነው፡፡ ሙስና የተንሰራፈበት ሥርዓት ነው፡፡ የነፃ ገበያን ያዛባሉ በመሆኑም ለልማትና ለእድገት አመቺ አይደለሙ ብቻ ሳይሆን ፀር ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ታዲያ በልማታዊ መንግሥት ስም እየተፈፀመ ያለው ፀረ-ልማትና እድገት ሥራዎች ናቸው፡፡ ልማትና እድገት ያመጣ መንግሥት ወይም ገዢ ፓርቲ ምርጫን ለማሸነፍ ሕዝብን ማስፈራራት፣ ሕዝብን በአንድ ለአምስት መጠርነፍ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችንና አባሎቻቸውን ማሰር ማዋከብ፣ ሕዝባዊ ስብሰባዎች በስልትና በዘዴ መከልከል፣ የምርጫን ሥርዓት ሚሰጥራዊነት ለማሳጣትና የቡድን ሥራ ማድረግ አያስፈልገውም ነበር፡፡
በአጠቃላይ የምርጫ ሥነ-ምግባር ደንብ ፈርሙ ድራማ ምክንያቱ ግለጽ ነው፡፡ ኢህአዴግ/ወያኔ ሥልጣን ላይ ለመቆየት (ስንት ዓመት እንደሆነም የሚታወቅ አይመስልም)
ኢ-ዴሞክራሲያዊና ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ አሠራር የመጠቀም ስልቱ አካል ነው፡፡ ጽሑፌን በቀድሞ የአሜሪካን ፕሬዚደንት ጆን.ኤፍ.ኬኔዲ አነጋገር አጠቃልላለሁ፡፡ ‘’Those who make peaceful revolution impossible will make violent revolution inevitable’’ ከሞላ ጎደል ሲተረጎም ሠላማዊ ለውጥን የማይቻል የሚያደርጉ ሰዎች የአመጽ ለውጥን የማይቀር ያደርጉታል ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሁኔታ ሲታይ ደግሞ የሚያስፈልጋት ሠላማዊና ሕጋዊ ለውጥ ነው፡፡ አገራችን ደግሞ በብዙ ችግሮች የተተበተበች ናት፡፡ ስለዚህ መፍትሔው የምርጫ ሥነ-ምግባር ፈረሙ አይደለም፡፡ ጉዳዩ ከምርጫ በላይ ነው፡፡ ጉዳዩ ከሥልጣን በላይ ነው፡፡ ጉዳዩ የአገርና የሕዝብ ጉዳይ ነው፡፡ ጉዳዩ የታሪክም የሕግም ተጠያቂነት የሚያስከትል ነው፡፡ ስለሆነም ዛሬም ከረፈደም ቢሆን ኢህአዴግና እሱ የሚመራው መንግሥት በሰከነ አዕምሮና ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ ተቃዋሚ(ተፎካካሪ) ፓርቲዎችና ሌሎች ባለድረሻ አካላት ጋር ቅድመ ሁኔታ የሌለው ድርድርና ውይይት ማድረግ አለበት እላለሁ፡፡ ወይም ከሥነ ምግባር ደንቡ የተለየ በቂ ምከነያት መፈለግ ይኖርበታል፡፡ የሚያገናኘን፣ የሚያወያየን የጋራ አጀንዳ የለንም ማለት ጠቃሚም ተገቢም አይደለም፡፡ የጋራ አገር አለን፣ የሕግ የበላይነትና የመልካም አስተዳደር ከፍተኛ ችግር አለብን፣ አብዛኛው ሕዝብ በድህነት እየማቀቀ ጥቂቶች የሚበለጽጉባት፣ የሚንደላቀቁባት አገር ውስጥ ነን ያለነው፣ የሰብዓዊና የዴሞክራሲ መብቶች ጥሰት ተንሰራፍቷል፣ የብዙሃን መገናኛ አውታሮች የአንድ ፓርቲ መገልገያዎች ሆኗል፡፡ ነፃ ፕሬስ በሞት አፋፍ ላይ ብቻ ሳይሆን አክትሞለታል፣ ቅድመ ሳንሱር በጓሮ በር እየመጣ ነው፣ ሬዲዮኖች እየታፈኑ ነው፡፡ የቡድኖች የመጨቆን ስሜት የመከፋት ስሜት እየጨመረ ነው፣ ሙስና ተንሠራፍቷል፡፡ ወ.ዘ.ተ እነዚህ ጉዳዮች እንድንወያይ፣ እንድንነጋገር ካነሱ ሊያወያዩን የሚችሉ ጉዳዩች ምን ሊሆኑ ይችላሉ? አገራዊ መግባባትና እርቀ ሠላም መፈጠር ወያኔም ወደደም ጠላም ስልጣኑን ለህዝብ ማስረከብ አለበት፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ኢህአዴግ/ወያኔ በለመደው የግትርነት አቋሙ ቀጥሎ እንደ ሁልጊዜው ሁሉ ‹‹ ሁለም ነገር የሚከለሰው፣ የሚለወጠው፣ በመቃብሬ ላይ ነው›› የሚል ከሆነ ይህው ይፈፀም ዘንድ የግድ ይሆናል፡፡
ከሰብኣዊ

No comments:

Post a Comment