Monday, January 5, 2015

ተስፋዬ ገብረአብ ‹የቅዳሜ ማስታወሻ› ወደሚባለው የጡመራ ገጹ ተመልሷል፡፡ወደ ቀልቡ ግን አሁንም አልተመለሰም

ተስፋዬ ገብረአብ ‹የቅዳሜ ማስታወሻ› ወደሚባለው የጡመራ ገጹ ተመልሷል፡፡ወደ ቀልቡ ግን አሁንም አልተመለሰም፡፡ዛሬም ያው ነው፡፡ የሆነ የማይድን በሽታ የያዘው ይመስለኛል፡፡‹ከዚህ ጊዜ በኃላ ስለምትሞት የጀመርከው ነገር ካለ በቶሎ ጨረስ ፡፡›› ተብሎ መርዶ የተነገረው አይነት፡፡ ተስፋዬ በቀሩት ቀናት ለኑዛዜ የሚያበቃ መልካም ነገር ሳይሆን በክፋት የሚያስመነድገው ሳዲስታዊ ግብር ለማድረግ የቆረጠ አይነት ሰው ስሜት በጽሁፎቹ ውስጥ ተዘርቶ ይታያል፡፡
ጽሁፎቹ ጥጋቸው ሰውኛ አይደለም፡፡ተስፋዬ ታሪክ ያገነነው እውነት አይዋጥለትም ተከታትሎ በጥላሸት ቦንብ ካላደባየው ደረቱ ላይ የሚያቃጥለው መሆኑን እያረጋገጠ ነው፡፡ ህዝብ ከህዝብ ባለው ግንኙነት ውስጥ ያለው የመቻቻል ብሂል ከመፈራራት እና ካለመንቃት መንፈስ ጋር ያሰናስነዋል፡፡እንደ ጀመሪ የፊልም ታዳሚ ‹መቼ ነው ድብድቡን የሚጀመረው?› ጥያቄው አልተቋረጠም፡፡ተስፋዬ ከዕድሜውና ከሚኖርበት ሃገር አንጻር የሚጠበቅበት የሃሳብ ግዝፈትና ሰብአዊነትን ገና አልተጠጋውም፡፡‹ዕድሜ ይስጥህ› የሚለው ምርቃት ርግማን መሆኑን ማሳያ እንደ ተስፋዬ ያለው ካልሆነ ማን ሊሆን ይችላል?


ተስፋዬ በሚያቀርበው የክፋት ግብር ልክ ሃይል የሚታደል የቤተ-ሰይጣን አስተባባሪ እየሆነ ነው፡፡ደራሲነትን የሰፋ አለም ከመፍጠሪያነት ይልቅ በጠባብነት ጎሬ ውስጥ መቆያ ያደርገዋል፡፡ተስፋዬ ብርሃን ያስፈራዋል፡፡ፈገግታ ይጨንቀዋል፡፡መዋደድ ይከብደዋል፡፡ይቅርታ ያመዋል፡፡አብሮ መኖር ያስጮኸዋል፡፡
ተስፋዬ ‹ለዞምቢ ፊልም የሚጠጋ እልቂት › እየተመኘ ነው፡፡እኛ ታናናሾቹን በዘር ረድፍ አሰልፎ በመካካላችን ተበግሮና መዳፉን ዘርግቶ ‹መዳፌን መቶ ቀድሞ የሚመታ› ይለናል፡፡‹አትችለውም…አሳምነው…የዛሬ አመት እኮ እንዲህ ብሎ ነበር› እያለ ገስግስና በለውን ይዘምራል፡፡
አንተ ሰውዬ በብዙ ነገር ትበልጠኛለህ፡፡ይሄን እውነት ግን በፍጹም አትነጥቀኝም፡፡ኢትዮጵያ ውስጥ አንደኛው ዘር ከአንደኛው ጋር የሚኖረው ለሌላኛው ዘር ስኬት አይደለም፡፡ለራሱ ሲል ነው፡፡በአመታት ውስጥ አንደኛን ከአንደኛው የሚያተሳሳረው ስውር መረብ ሰፋና አንድ ቦታ ስትበጥሰው መላ ማንነትን የሚያናጋ ሆነ፡፡ ይሄ በመሆኑና ያሰብከው ባለመሳካቱ አዝናለሁ፡፡ግን እውነታው ይሄ ነው እኛ ኢህኣዴግ የተባለ ወንበዴ‹ መንግስታችሁ› ነኝ ይለናል፡፡የምናስተዳድረው ግን ራሳችንን ነው፡፡ ህገመንግስት የተባለ ህግ አላችሁ ይለናል- የራሳችን ህገ- ልቦና ብቻ ያስተዳድረናል፡፡‹ተከባብራችሁ የኖራችሁት እኔ ስላለሁ ነው › ብሎ ያላዝንብናል፤ ተከባብሮ መኖር የመፍቀድ እንጂ የመገደድ ስሜት ውጤት እንደማይሆን ስለምናውቅ ግን እንስቅበታለን፡፡አንድ ላይ የምንኖረው ተገደን ወይም ሳይገበን ቀርቶ አይደለም፡፡አብሮ የሚያከርመን የህላዊ ትስስር ሰናስበው ስለ ገነነብን ነው፡፡ምን እናድርግህ?
ተስፋዬ አንድ ጥያቄ መልስልኝ….አንተና እኔ እንኳ ብሄርን መሰረት አድርገን ልንጣላ ሰበቡ የለንም፡፡እስቲ አንተ የትኛውን ብሄር ወክለህ ትገጥመኛለህ? ኤርትራዊ ደምህን ትመዛለህ ወይስ ያደክበትን ኦሮሞነት ትወክላለህ ? ወይስ ኦሮሞዎች አሳደጉት ያልከውን አማርኛ የሚናገረውን አማራነትን ታስቀድማለህ?
እኔስ የተወለድኩበትን ጎጃም ላስቀደም ወይስ፣ወይስ የአባቴን የደቡብ ሰውነት ወይስ የአራት የባለውለታዎቼን ትግሬነት፡፡
ለፍልሚያ የሚሆን ክፍፍል ለማድረግ እንኳ የከበደን ህዝቦች ነን፡፡ መታወቂያ ለማውጣት ብዙ ጊዜ የሚፈጀው ምስክር ማምጣቱ መሰለህ? ‹ ብሄር?› የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ መክበዱ ነው፡፡በደማችን እንዳንሄድ ብዙ ነን፡፡በተወለድንበት እንዳንመዘገብ ያደግንበት ይከሰትብናል፡፡ ያደግንበት ሲመጣ ባለውለታዎቻችን ያሉበት ቡድን ይታየንና እሱን መቀላቀል ይነሽጠናል፡፡ ኢትዮጵያዊ ነኝ ከሚለው ጥዑም ቃል ወዲያ የትኛው ቃል የበዛ ምንነታችንን አቅፎ ይይዝልናል?
ይሄን የምንለው ደግሞ አንድን ብሄር ‹አትፋለመኝ› ብሎ ለማባበል አይደለም፡፡አባይና አዋሽን በደም ለማቅለም ገና ደህነኛ ሰበብ እንዳልተገኘ እያስረዳውህ ነው እንጂ ቀን ሲካፋ ትልቁ ትንሽ ትንሹ ትልቅ የሚሆንበትን ሃይል ካልታሰበ ታዛ ስር እንደሚጎናጸፍ እየካድኩልህ አይደለም ፡፡ተለማኝ ብሄር እና ተለማማጭ ህዝብ ያለ አታስመስለው….
በነጻነት ወርቅነህ ቅላጼ እንዲህ ልበልህ ፤
ተስፋዬ እውነቴን ነው አሞሃል፡፡እስቲ ታየው ግዴለህም፡፡ለኤርሚያ ለገሰ ቀልብን፤ለጁነዲን ጸጸትን፣ለሬድዋን ውርደትን ህይወት አዝዛላቸዋለች፡፡ እስቲ አንተም ታየው ላንተ የሚሆን ነገር አታጣልህም፡፡
እስቲ እሺ በለን ታየው ፡፡ወጪውን እኛ እንቻል፡፡የቃጭማው ጊዮርጊስ ላንተ ሚያንስ ሆኖ ነው? ግዴለህም እስቲ ጸበሉን በተን በተን ያድርጉብህ ፡፡ዓለም አንድ እየሆነ አንተ አንደ ሃገርን አርባ አንድ ለማድርግ መጣርህ፣ የጤና ነው ብለህ ነው? ግዴለህም ታየው፡፡
የኔ ዘመን ከባድ ነው፡፡ የእኔ ትውልድ ህመም እንደ ኢህአዴግ ባለ ማህበረ- ብላሽ መመራቱ ብቻ አይደለም እንዳንተ ካለው የክፋት ባለ ወንጭፍ ጋር ዘመኑን መጋራቱ ጭምር እንጂ፡፡
ጻፍ- ተንኮልህም ይብዛ -ጠንክረህ ልትነጣጥለን ሞክር….እንዲህ እያደረክ ነውና ያለመለያየታችንን እውነታ ምታሳየን፡፡
ይቅናህ፡፡

No comments:

Post a Comment