Thursday, July 10, 2014

እኔ የማይገባኝ እንዴት 23 አመት ሙሉ ዜጎችን እያሰሩ ይቀጥላሉ ?

ግርማ ካሳ
ሃብታሙ አያሌው ፣ ዳንኤል ሺበሺ እና የሺዋስ ከበደ ወደ ማእከላዊ መዉረዳቸዉን የሚገለጽ ዜና ተመለከትኩ። በጣም አዝኛለሁ።
habtamu ayalew
ሃብታሙ አያሌው
ሃብታሙ አያሌው በአንድነት ፓርቲ ዉስጥ ትልቅ ሥራ እየሰራ ያለ፣ በቅርቡ ወዳጅ አባቷን ያጣችው እህታችን ባለቤት እና የአንዲት ቆንጅዬ ልጅ አባት ነው።የአንድነት ፓርቲ እና መኢአድ የቅድመ ዉህደት ስምምነት ፈርመው ፣ ዉህደቱን ለማስፈጸም ያቋቋሙት የጋራ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነው። ያ ብቻ አይደለም የሚሊዮኖች ንቅናቄ ግብረ ኃይል ሰብሳቢ ሆኖ ሰርቷል ፣ አቶ ሃብታሙ።
ዳንኤል ሺበሺ የአንድነት ት ጉዳይ ሃላፊ ም/ሰብሳቢ ነው። የአንድነት ፓርቲ ድርጅታዊ መዋቀሩን በአገሩቷ ሁሉ ለማጠናከር እየሰራው ባለው ስራ፣ ወጣት ዳንኤል ሺበሺ ትልቅ ሚና የነበረው ወጣት አመራር ነው።
የሺዋስ አሰፋ የሰማያዊ ፓርቲ ምክር ቤት ም/ሰብሳቢ ነው። በቅርቡም ሰማያዊ ፓርቲ ለሰፍ ቅስቀሳ በሚያደርግበት ጊዜ ታግቶ ከሳምንት በላይ ውህኒ የተወረወረ ወጣት ነው።

ምርጫው እየተቃረበ ሲመጣ፣ ጠንካራ ፉክክር እንዳይኖር ፣ «ከወዲሁ ተቃዋሚዎችን ማዳከም አለብን» የሚል ዉሳኔ ኢሕአዴግ የወሰደ ይመስለኛል። የአመራር አባላትን የማሰሩ አሳዛኝ ተግባር፣ በተለይም ደግሞ የአንድነት እና መኢአድ ዉህደት እንዳይፈጸም፣ በአገር ቤት ያሉ ሰላማዊ ታጋዮች እንዲፈሩና እንዲሸማቀቁ ለማድረግ ሆን ተብሎ የተደረገ ለመሆኑ ብዙ አርቆ ማሰብ አይጠይቅም። አይሳካላቸዉም እንጂ።
yeshiwas
የሺዋስ ከበደ
ከጥቂት አመታት በፊት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን ኢሕአዴግ አሰረ። እንደ አንዱዋለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን ያሉ ተነሱ። የወ/ት ብርቱካን መታሰር ትግሉን አላቆመዉም። እነ አንዱዋለም አራጌን ደግሞ «ሽብርተኞች» ናችሁ ብሎ አሰረ። ትግሉ አላቆመም። ኢሕአዴግ ማሰሩን ቀጠለ። አቶ አስራት ጣሴ፣ አቶ ዳንኤል ተፈራን ለተወሰነ ጊዜ አስሮ ፈታ። አሁን ደግሞ ይኸው እንደ ሃብታሙ ያሉ ፣ በሰላም አገር ቤት የሚንቀሳቀሱ ኢትዮጵያዉያንን አግቶ የት እንዳደረጋቸው አይታወቅም። በቶርቸር በሚታወቀው ማእከላዊ ነው ይባላል።
እኔ የማይገባኝ፣ እንዴት 23 አመት ሙሉ ዜጎችን እያሰሩ ይቀጥላሉ ? ሰው እንዴት አይሻሻልም ? እስከመቼ ነው የጫካ አስተሳሰብ የሚገዛቸው ? ይቅርታ ይደረግልኝና ይሄስ እርግማን ነው !!!
10494588_750671571658261_8784450188684809422_n
ዳንኤል ሺበሺ
በቅርቡ ሰላማዊ ወጣቶችን በአምቦ፣ በጊምቢ … በጥይት ረፈረፏቸው። ፌስ ቡክ ላይ በመጻፋቸው ዞን ዘጠኞችን አስረው ይኸው እያሸማቀቋቸው ነው። ነገ ደግሞ ምን እንደሚያደርጉ አናውቅም። ይሄንን ሕዝብ ምን አድርግ ነው የሚሉት ? እንዴት ነው ኢሕአዴግ ዉስጥ ልብ ያለው ፣ «ይሄ ነገር ትክክል አይደለም። ለኛም ለአገርም አይጠቅም። መካረርና ጥላቻን ያሳድጋል» ብሎ የሚያከላክል የለም እንዴ ?
ነገሮች በጣም እየከረሩ ነው። ብዙዎች እየተናደዱ ነው። ሁኔታው በጣም አስፈሪ ነው። ኢሕአዴግ ቀይ መስመር ላይ የቆመ ይመስለኛል። የሚያደርጋቸዉን እና የሚወሰናቸው ዉሳኔዎችን አስቦና ተጠንቅቆ እንዲወስድ እመክራለሁ። በአስቸኳይ ማእከላዊ እሥር ቤት ጨምሮ፣ በተለያዩ እሥር ቤቶች በግፍ ያጎራቸውን ሰላማዊ ዜጎች እንዲፈታ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን እንዲያሰፋና ለብሄራዊ እርቅም እንዲዘጋጅ፣ አኩረፈው ነፍጥ ካነሱ ወገኖች ጋር ችግሮችን በሰላም ለመፍታት ዉይይት እንዲጀምር፣ እመክራለሁ። አስጠነቅቃለሁም።
ጆሮ ያለው ይስማ ! ልብ ያለው ይስተዉል !

No comments:

Post a Comment