Sunday, July 20, 2014

የለውጥ እንቅስቃሴ ጥሪ!

ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ድርጅቶች፣ የሃይማኖትና የሲቪክ ተቋማት በሙሉ!

በአሁኑ ጊዜ በሰሜን አፍሪካና በሌሎች አገራት የሚካሄደውን ለውጥ እየተመለከትን እኛም ለአገራችን የማናስብበትና የህውሃት/ወያኔን የሚመስሉ ጨቋኝ አምባገነኖች ከሌሎች አገሮች እየተወገዱ እኛ ዝም ብለን የምንመለከትበት ምንም ምክንያት ሊኖር አይገባም፡፡ በእነዚህ የሰሜን አፍሪካ አገራት የኑሮ ውድነት፣ የነጻነት ዕጦት፣ ጭቆና፣ ግድያ፣ ሕገወጥነት ወዘተ ያንገፈገፈው ሕዝብ የደረሰበትን የምሬት ደረጃ የኢትዮጵያ ሕዝብ አልደረሰበትም ማለት ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ምናልባትም ግፉ ከዚህ የበለጠ ሊሆን ይችላል፡፡

 ግብጽን ለ30 ዓመታት በአምባገነንነት የመሩትን ሆስኒ ሙባረክ ሥልጣን እንዲለቁ የተደረጉት በቱኒሲያ የቤን አሊ የ23 ዓመት ጨቋኝ አገዛዝ ከተገረሰሰ በኋላ እንደመሆኑ ከእነዚህ አምባገነን መንግሥታት በላቀ መልኩ ኢትዮጵያውያንን አፍኖ ያለው የህውሃት/ወያኔን አገዛዝ በሕዝባዊ ለውጥ ከሥልጣን መነሳት የሌለበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ሕዝባችንም ለዘመናት የተጠማውን ነጻነትና ፍትሕ እንደሌሎቹ የሰሜን አፍሪካ አገራት ተግባራዊ እስኪያደርግ ትግሉን እንደማያቆም እሙን ነው፡፡ ለ ኢትዮጵያ  ንቅናቄም ሁከት አልባ በሆነ መንገድ በኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ለውጥ እንዲመጣ ሲያደርግ የነበረውን ትግል ከመቼውም ይልቅ በማጠናከር በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ይህንን መርህ የተከተለ ለውጥ እንዲከሰት በማድረግ በኩል እየተካሄደ ላለው እንቅስቃሴ ያለውን ድጋፍ ይገልጻል፡፡
እንዲህ ያለው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ምናልባት ለግብጽና ለቱኒሲያ ሕዝቦች አዲስ ሊሆን ይችላል እንጂ ለኢትዮጵያ ፈጽሞ ያልተለመደ ተግባር አይደለም፡፡ በ1997 ዓም በተደረገው የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ቅንጅትን በመደገፍ በጸጥታና በሰላም ድጋፉን በመግለጽ የተመመው በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ አሁንም ተመሳሳይ መልኩ ሁከት አልባ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ለውጥ ማምጣት የማይችልበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ይህ ሲሆን ግን የህውሃት/ወያኔን አገዛዝ እንደያኔው ሁሉ አሁን የሚካሄደውን የሕዝብ እንቅስቃሴ በኃይል በማፈንና የግድያ ተግባር በመፈጸም ሊገታ የሚችልበት ሁኔታ በጣም አናሳ ነው፡፡ምክንያቱም የአሁኑ የለውጥ እንቅስቃሴ አህጉራዊ እየሆነ መምጣቱ አንዱ ሲሆን ሌላው ደግሞ ‹‹ወዳጅ›› አድርጎ ለዘመናት ያቆያቸው ምዕራባውያን ለነሙባረክ ፊታቸውን ማዞራቸው ነው፡፡ በተለይም በአሁኑ ጊዜ በግብጽ እየተፈጸመ ያለውን የኢንተርኔት ሽበባ በቶሎ ካልተገታ የኦባማ አስተዳደር ለዘመናት ለግብጽ የሚሰጠውን የእርዳታ እንደሚያግድ መግለጹ ለአብነት የሚጠቀስ ነው፡፡
ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ የብዙዎች ጥያቄ ምን እናድርግ በመሆኑ የሚከተሉትን የድርጊት እርምጃዎች ለመጠቆም እንወዳለን፡፡
አንደኛ፡- ይህንን ሕዝባዊ ለውጥ ካጠናከሩት ነገሮች መካከል በዋንኛነት የሚጠቀሰው በኢንተርኔት የማኅበራዊ ድረገጾች ሚና እንደመሆኑ ኢትዮጵያውያን በፌስቡክና መሰል የመገናኛ መንገዶች ከመቼውም ይልቅ እንዲጠቀሙና እስካሁን ያልተጠቀሙ ደግሞ አሁኑኑ እንዲጀምሩ ልናሳስብ እንወዳለን፡፡ እንዲህ ዓይነቱ መረብ እርስበርስ እንድንገናኝ እንዲሁም ከንቅናቄያችንም ሆነ ከሌሎች የዴሞክራሲ ወዳዶች የሚቀርበውን ወቅታዊ መልዕክት በፍጥነት ለማድረስ የሚቻልበት ዓይነተኛ መንገድ በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ በአገርቤትም ሆነ በውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያን እንደ ፌስቡክ፣ ትዊተርና ዩትዩብ የመሳሰሉትን የመገናኛ መንገዶች በቅርብ የመጠቀም ልምዳቸውን በማጎልበት በየጊዜው የሚያገኙትን መረጃ ላልሰሙ በሙሉ ማስተላለፍ አለባቸው፡፡ የመረጃ በፍጥነት መተላለፍ ለሕዝባዊ ለውጥ መጠናከር ብሎም ውጤታማነት ዓቢይ ሚና የሚጫወት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ለዚህ ሥራ ይረዳ ዘንድ ፍትሕ፣ ነጻነት፣ እኩልነት፣ ዕርቅና መቻቻል በአገራችን ሊያሰፍኑ የሚችሉና ሕዝባዊ ለውጡን የሚደግፉ ወቅታዊ ጽሁፎችን ማውጣት ከእኛ በኩል በዋንኛነት የያዝነው ተግባር መሆኑን እናሳውቃለን፡፡
ሁለተኛ፡- ህወሃት/ኢህአዴግ እንዳቀደልን ሳይሆን ልዩነታችንን እንደ ሃብት በመቁጠርና የአንድነታችን መሠረት መሆኑን በመገንዘብ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አስተሳሰብ፣ ወዘተ የተደራጀን በሙሉ ወደ ኅብረት እና ትብብር መምጣት ይገባናል፡፡ ለእንደዚህ ዓይነቱ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ የመተባበርና አብሮ የመሥራት ፍላጎታችን ከምንግዜውም ይልቅ የጠነከረ መሆን አለበት፡፡ በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ አይቻልም ወይም አስቸጋሪ ነው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ለዚህም ምክንያታቸው በራሳችን እንዲሁም ህወሃት/ኢህአዴግ በተከለብን የመከፋፈል አባዜ እስካሁን በአንድነት መስራት አለመቻላችን እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ቢነሳ ሁኔታውን ለመምራት የተዘጋጀ የፖለቲካ ፓርቲ የለም፤ ቢኖርም የተወሰኑ ሰዎች ምርጫ ነው እንጂ የሚሆነው የብዙሃኑ ድጋፍ ያለው አይሆንም በማት ያላቸውን ፍርሃት ይናገራሉ፡፡
ሆኖም ግን ጊዜው ይህንን የሚፈቅድበት ወቅት ላይ አይደለም ያለነው፡፡ ‹‹ከዘር ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ የሚሰጥባትን››  ኢትዮጵያ ለመመሥረት የምንፈልግ ከሆነ እስካሁን የከፋፈሉንና የለያዩንን አጥሮች በማፍረስ ወደ ትብብር መምጣት አለብን፡፡ በግብጽ እንቅስቃሴው በተጀመረበት ወቅት ከዚህ በፊት ሲናቆሩ የኖሩ የፖለቲካ ድርጅቶች የተፈጠረውን አጋጣሚ ለመጠቀም ከዚህ በፊት የነበራቸውን መከፋፈል በመተው ወደትብብር በመምጣት ሕዝባዊውን እንቅስቃሴ ሲቀላቀሉ ያየነው ጉዳይ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ሁኔታ የሥልጣንን ጥማት ለማርኪያ የምንጠቀምበት ሳይሆን ከፈጣሪ የተሰጡንን መብቶች በማስከበር በአገራችን ላይ ዘላቂ የሰላም፣ የፍትሕ፣ የእኩልነት፣ ወዘተ መብቶች የሚከበሩበትን መሠረት የምንጥልበት ነው፡፡ ስለዚህ እንደዚህ ዓይነቱን መሠረት በአገራችን ላይ ለመጣልና ወደፊት ሕዝባዊው እንቅስቃሴ መሥመር እየያዘ ሲመጣ ሊከሰት የሚችለውን የአመራር ክፍተት ለመሙላት የሚችሉ ብቃት ያላቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ በልበሙሉነት ለማሳወቅ እወዳለሁ፡፡
ሦስተኛ፡- ማንኛውም ዓይነት ሕዝባዊ እንቅስቃሴ እንደከዚህ በፊቱ ሁሉ የኃይል እርምጃ የሌለበትና ሁከት አልባ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ ይህ እንቅስቃሴ ብጥብጥ ለመፍጠር፣ ሁከት ለማስነሳት እንዲሁም የግል ጥላቻን ለመወጣትና ለብቀላ የምናደርገው ሳይሆን ከዚህ ሁሉ የተገታ መሆን አለበት፡፡ ወቅቱ ይህንን የሚፈቅድበት መሆን በፍጹም የለበትም፡፡ ፍትህን ከመንገድ ላይ በጥላቻና በብቀላ ተሞልተን ሳይሆን ለማግኘት መፈለግ ያለብን ወደፊት በምንገነባት አዲስ ኢትዮጵያ በምናስቀምጣቸው መርሆዎች እና ተቋማት ብቻ ነው መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ በተለይ ሕዝባዊው እንቅስቃሴ መስመሩን እንዳይለቅና የሁከትና ብጥብጥ መነሻ እንዳይሆን ሕዝባችን ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደር ላሳስብ እወዳለሁ፡፡ አለበለዚያ ሕልማችን ቅዠት፤ ተስፋችንም የማይጨበጥ ሆኖ ነው የሚቀረው፡፡
ማጠቃለያ፡- ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ደካማ በሆነበት አገር በሙሉ ምዕራባውያን ለአምባገነን መሪዎች ድጋፍ መስጠታቸው ስንታዘበው የቆየ ተግባራቸው ነው፡፡ ሆኖም ግን ሕዝብ ሲያብርና ኃይሉን ሲያሳይ ለለውጥም ያለውን ቁርጠኝነት ሲመለከቱ ከሕዝብ ጋር ማበራቸው አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ ሕዝባችን እነዚህን ሁሉ እውነታዎች እንዲረዳና ለለውጥ ያለውን ቁርጠኝነት በማያወላውል መልኩ እንዲያሳይ ይጠበቅበታል፡፡ ፍትሕን፣ ሰላምን፣ እኩልነትን ወዘተ የሚሰጡን ምዕራባዊያን አይደሉም፤ ራሳችን ነን የራሳችን የምናደርጋቸው፡፡ በቱኒሲያና በግብጽ የለውጥ ማዕበል እንዲነሳ ያደረገው ሕዝብ ነው፡፡
ንቅናቄያችን ይህንን ለሕዝባችን በማድረስ በኩል የሚገባውን ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት በድጋሚ ማሳየት ይኖርበታል፡፡  በኢትዮጵያችን እየደረሰ ያለው ረሃብ፣ የዋጋ ግሽበት፣ የኑሮ ውድነት፣ ሙስና፣ ፍትሕአልባነት፣ አፈና፣ ግድያ ወዘተ የተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍልን ብቻ ሳይሆን ከሲቪሉ ጀምሮ ጦር ሠራዊቱን፣ ደኅንነቱ፣ ተማሪውን፣ ገበሬውን፣ የመንግሥት ሠራተኛውን፣ ወዘተ ቤት ያንኳኳ በመሆኑ ከእንግዲህ ጸጥ ተብሎ የሚቆይበት ሁኔታ እየተመናመነ የመጣበት ነው፡፡ ስለዚህ ለለውጥ እንመካከር! እንዘጋጅ! እንተባበር!

ፈጣሪ ማስተዋልን እንዲሰጠንና በግላዊ ስሜታችን የምንነዳ ሳይሆን በእርሱ የምንመራ እንድንሆን ይርዳን፡፡ በየእምነታችንም ይህንን በማሰብ ‹‹የኢትዮጵያን እጆች ወደላይ እንዘርጋ››!!

No comments:

Post a Comment