Sunday, July 20, 2014

ግልፅ ደብዳቤ ለኢሳት (ESAT) ና ታዳሚዎች!!!አንተነህ ሽፈራው

‘የነገዋ ኢትዮጵያ በዛሬው ቅይት ትለካለች’:-
ወያኔ የየካቲት 1967 ዓ.ም አፈጣጠሩ፣ እድገቱ፣ አሁን እየሠራ ያለው ተግባሩ፣ ቀጣይ ዓላማውና እንዲሁም በ1997 ዓ.ም ምርጫ እርቃኑን የቀረው ዘረኛ የፖለቲካ መሠረቱና ኋላቀርነቱ ኢትዮጵያን መሠረት አድርገው ከተደራጁ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ቡድኖችና ከግለሰቦች ጋር ሳይቀር ለሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ስልጡን የፖለቲካ ሥርዓት ተገዥ ሆኖ ለሥልጣን ለመወዳደር ስለማይፈቅድለት ሕዝባችንን አረመኔ በሆነ ድርጊቱ በጠብ-መንጃ በገፍ ይገላል፣ የአገር ንብረት ይዘርፋል፤ አልፎ አልፎ ብቅ ብቅ ያሉ ጠንካራ ጋዜጠኞችም ከመጠን በላይ ስለሚያስፈሩት ያለአግባብ ለተደጋጋሚ ግዜ በእስር ፍዳቸውን አሳይቶአቸዋል፤ የሚወዷት አገራቸውን፣ ሕዝባቸውንና ቤት ንብረታቸውን ትተው ለስደት ዳርጓቸዋል፤ አሁንም ድረስ እልፍ አህላፍ የሕሊና እስረኞችና ጋዜጠኞች ቀድሞ በነበሩትና ወያኔ በከፈታቸው ተጨማሪ እስር ቤቶች በገፍ እየተንገላቱ ይገኛሉ::

ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም እንደሚባለው ሁሉ ‘ኢሳት/ESAT ይህን ሁሉ የወያኔን የአፈናና ግድያ ሰብሮ ሰባብሮ የወጣ ከነፃ ሚዲያነት ወደፊት ወደ ኢትዮጵያዊ ሁለንተናዊ (የዜናና መረጃ) ማዕከልነት ጭምር ሊያድግ ሊመነደግ እንደሚችል ብሩህ ተስፋ ያለው መሆኑ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ‘ያይበገሬ ምልክትም ሆኖ’ ሊጠቀስ የሚችል ይመስለኛል:: ለዚህም ዋናው ምልክት ደግሞ ኢሳት ከግለሰቦች ጅማሮ ወሳጅነት ወጦ በቅርቡ ኢሳትን ለማጠናከር ተብሎ በተዘረጋው መርሃ-ግብር ላይ ኢትዮጵያውያን እያሳዩ ያሉት ተሳትፎና ጥረት አበረታች ሆኖ መገኘቱን ይጠቅሳሉ – - – በግል አስተያየቴ:: እርግጥ ነው ለኢሳት/ESAT መነሻ እንደ ጥሩ ተምሳሌት/አርያ ሆነው ያገለገሉ የመረጃ ተቋማትን ለአፍታም ቢሆን መርሳት የለብንም:: በዚህ ረገድ አበበ በለው ለረጅም ግዜ እያደረገ ያለው የሬድዮ ሙከራና ኢቶ-ሚዲያ፣ ቋጠሮ፣ በተለይ ደግሞ አሁን አሁን እጅግ በጣም ተወዳጅ እየሆነ የመጣው አቡጊዳና ሌሎችም ድህረ-ገፆች ያለምንም በቂ የፋይናንስ አጋዥ ሙሉ ግዜያቸውን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ቤዛ በማድረግ ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ ሓሳብ እንድንለዋወጥና እንድንማማር ጠንካራ ድርድይ ሆነው እያገለገሉ መሆናቸው ለአፍታም እንኳ ቢሆን የሚዘነጋ አይደለም – - – ምንም እንኳን አንዳንድ ግዜ ጽሑፎቻችን በዚያው ቀልጥው የሚቀሩበት ሁኔታ ያሉ ቢሆንም ቅሉ::
ኢትዮጵያ አገራችን በባይታወር የፖለቲካ ሽኩቻ አደጋ ላይ ወድቃ አምባገነኑ ደርግ/መኢሶንና ኢሕአፓ እርስ በእርስ በመሓል አገር ‘አገር ተረካቢውን ጠንካራ ትውልድ እንደቅጠል ሲቀጥፉት’ ወያኔዎች የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም እራሳቸውን አደራጅተውና በታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላት አገሮች ታግዘው የበለጠ ኃይላቸውን ሲያጠናክሩ በሌላው በኩል ግን ‘በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ’ ይሉ በትጥቅ ትግሉ ውስጥ የነበረው ኢሕአፓ የራሱን የውስጥ ችግር መፍታት አልችል ብሎ በ1973 ዓ.ም ከፍተኛ የሆነ የብተና ድርጊት ሲፈጠምና በሂደት አንጀኝ የሚባሉት የኢሕአፓን አመራራ አካላት ጎዳን ብለውና የጎሣ ፖለቲካ ሰለባም ጭምር ሆነው ራሳቸውን ለወያኔ ለሎሌነት (ኢህዴን በሚል ሽፋን ስጭ ስያሜ) አሳልፈው መስጠታቸው የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግር እጅጉን አደገኛ አደረገው::
ወያኔ በመንገድ መሪዎች በነታምራት ላይኔና ከኤርትራ በምርኮኝነት የተረከባቸውን እነ ኩማን (ታዬን) ይዞ መላ አገሪቷን ከመውረሩ በፊት ኢሕአፓ አካባቢ የነበረውን የትጥቅ ትግል ክፍተትና ቸልተኝነት ለመለወጥ ይረዳን ዘንድ ሰራዊቱን (ኢሕአሠን) በሞራልና በተለያዩ ስልቶች ለማጠናከር ሱዳን ካርቱም ላይ በወቅቱ የኢሕአፓ ጽ/ቤት ኃላፊዎች/አመራር የነበረውን አካል ደግመን ደጋግመን ሜዳ ሄደን ሰራዊቱን እንድንቀላቀል መስመር እንዲሰጠን ብንጠይቅም “የኢሕአፓን ሰራዊት ለመቀላቀል መጀመሪያ የኢሕአፓ (የፓሪቲ) አባል መሆንን ይጠይቃል” በሚል ቢሮክራሲ ጥረታችን ሁሉ ከንቱ ሆኖ ቀረ:: ምንም እንኳን በወቅቱ ከ30 የማንበልጥ ሰዎች ሜዳ ገብተን የወያኔን የወረራ ድርጊት መለወጥ እንኳ ባንችልም ቅሉ በወቅቱ ኢሕአፖ የነበረውን የትጥቅ ትግል እርሾና ጥሪት ከወያኔ ዘርፋ አድነን በአዲስ ሞራልና የሽምቅ ውጊያ ስልት ወያኔን በሚገባው ቋንቋ ወዲያው ፈጥኖ ማነጋገር በተቻለ ነበር:: ይህ ባለመሆኑ ግን ወያኔ ጭራሽ የልብ ልብ ተሰምቶት በሰኔው 1983 ዓ.ም የሽግግር መንግሥት ተብዮው ላይ ኢትዮጵያውያን ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ተገለው በወያኔና የጎሣ ፖለቲካ ሰለባ ባደረጋቸው ሽፋን ስጭነት (ኦነግን ጭምሮ) የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪካዊ አሰፋፈርና ካርታ በእብሪት ተሸንሽኖ በአገር ላይ አገር ተፈጥሮ በነባር የከተማ ስሞች ላይ አዲስ ስምች እየወጡ ወያኔ በብቸኝነት በሚቆጣጠረው የሕዝብ የብዙሃን መገናኛ ሚዲያ ተቋማት ለሕዝብ ቀረቡ:: እነዚህ አዳዲስ አከላሎችና ስያሜዎች ወያኔ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚጠቀምበት የወታደራዊ ኃይሉ ቅጥዮች መሆናቸውን በሚገባ መገንዘብ አለብን::
የዚህ ጽሑፍ ዐብይ ዓላማም የወያኔን ማሳደድና አፈና ሰብሮ ሰባብሮ ለመውጣት ከፍተኝ ጥረት እያደረገ ያለውንና የሁላችንንም እገዛ የሚሻውን ኢሳት/ESAT ለመወንጀልና ለማሳጣት ሳይሆን ኢሳትና ታዳሚዎቿ በነዚህ ወያኔ ከፋፎሎ ለመግዛት እንዲያመቸው ብሎ በከለላቸው የከፋፍለህ ግዛ ክልሎችና አዳዲስ የከተማ ስያሜዎች ላይና ከዚሁ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ግልፅ ግንዛቤና አቋም እንዲኖረው በማድረግ ኢሳት/ESAT ዛሬ በተለያዩ ክልሎች ተከፋፍላ በወያኔ መዳፍ ውስጥ ገብታ የምትመዘበረው ኢትዮጵያ ነገ ሁሉም ዜጎች በዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ መንገድ ተቻችለውና ተጋግዘው፣ ቋንቋቸውና ባሃላቸው ተከብሮ በእኩልነት የሚኖሩባት ኢትዮጵያን ለመፍጠር ከተፈለገ ኢሳት/ESAT የወያኔን አዲስ አከላለል፣ የከተሞችና የተቋማት አሰያየሞች ከሚዲያ ማዕከሉ ሙሉ በሙሉ ነቅሎ ማውጣት አለበት:: ጉዳዩን የበለጠ ግልፅ ለማድረግ ያህል ዘንድ በአንድ ኢትዮጵያ ውስጥ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ወዘተ የሚባል አገር የለም:: በሌላ አነጋገር ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ወዘተ የሚባል አገር በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም/አልነበረም ወደፊትም አይኖርም:: የሚኖረው አንድና አንድ አገር ብቻ ነው:: ያም ኢትዮጵያ የሁሉም የበላይ የጋራ አገር ሆና ለስልጣን ክፍፍሉና ለአስተዳደር እንዲያመች ግን ከጥንት ጀምረው የነበሩ የክፍለ ሀገር ሥሞች ከጎሣ ስያሜነት ነፃ የሆኑ በመሆናቸው ወደፊትም ያገለግላሉ – - – ዜጎችም ክፍለ-ሀገር ሳያግዳቸውና ጎሠኝነት ጫና ሳይፈጥርባቸው በሚፈልጉት ቦታ (ክ/ሀገር) ተንቀሳቅሰው የመኖርና ሃብት የማፍራት ሙሉ መታቸው ሊሸራረፍ አይገባምና::
እርግጥ ነው ኢጣሊያን አገራችንን በወረረ ግዜ የኢትዮጵያን ሕዝብ በጎሣና በሃይማኖት ከፋፍሎ ለመግዛት ይመቸው ዘንድ ቀድሞ የነበሩ ክ/ሀገሮችን በጎሣ አካሎ አማራ፣ ኦሮሞ-ሲዳሞ፣ ሱማሌ፣ እስላምና ክርስቲያን በማለት ይጠቀም የነበረ መሆኑ በሚገባ ቢታወቅም የኋላ-ኋላ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ የኢጣሊያን የመከፋፈል አሽክላ ሰብሮ የመጣውን የውጭ ጠላት አብሮና ተባብሮ አሳፋሪ በሆነ መንገድ ወደ መጣበት መልሶታል:: ዛሬ በወያኔ እስር ቤት በግፍ እየተንገላታ ያለው አበበ ደብተራው “የሞሶሎኒ ጦር” ብሎ የሚጠራው ወያኔ ግን ያ የበፊት አለቆቹ የወጠኑትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ሲል የጎሣና የሃይማኖት ክፍፍሉን በአዲስ መልክ ጭራሽ አባብሶ መልሶ ስላመጣው ኢሳትና ታዳሚዎች ግልፅ አቋም ይዘው ሊመክቱት ይገባል እንጅ ወያኔና እነ ስዬ አብርሃ፣ ገብሩ አሥራትና ነጋሶ ጊዳዳ እንደዚሁም ቢጤዎቻቸው እርቃኑን የቀረውን ወያኔን ኢህአዴግ፣ ናዝሬትን አዳማ፣ ወልቃይት-ጠገዴንና ሴቲቱ-ሁመራን ትግራይ ክልል፣ አዲስ አበባን ፍንፍኔ፣ የተለያዩ ክ/ሀገሮችንና ቋንቋውን እንኳ መስማትና መናገር የማችሉትን እጅግ በጣም ብዙ የሕብረተሰብ ክፍሎችን አንድ ላይ ጨፍልቆ ኦሮሚያና አማራ ወዘተ እያሉ የሚጠሩትን ተቀብለን የምናስተጋባበትና ታሪክ የምናዛባበት ሁኔት ጭራሽ መኖር የለበትም:: ኢሳቶች ወያኔን ኢህአዴግ- ናዝረትን አዳማ – የተለያዩ ክ/ሀገሮችንና ማኅበረሰቦችን አንድ ላይ ጨፍልቀው ኦሮሚያ፣ አማራ፣ . . . ወዘተ የሚሉ ስያሜዎችን በምሰማ ግዜ የወያኔ የዜና ማዕከል አልያም የእነ ስዬ አብርሃና ገብሩ አሥራትን አንደበት የማዳምጥ ይመስለኛል::
በተለይ ደግሞ ይህን ጽሑፍ ግልፅ ደብዳቤ ለኢሳት በሚል እንዳቀርብ ያስገደደኝ ዐብይ ምክንያት የኢሳት ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም ከአባ ኒቆዲሞስ ጋር ያደረገውን ቃለ መጠይቅ በጽሞና በተከታተልኩ ግዜ በአንድ ቃለ-መጠይቅ ውስጥ የተለያዩ ገፀ-ባሕሪዎችን አዳብሎ ያያዘ መሆኑን መገንዘብ በመቻሌ ነው:: በመጀመሪያ ነገር ኢሳት ይህን የወያኔን፣ የኦነግን፣ የኦህዴድንና የነታምራት ላይኔን የአማራንና ኢትዮጵያን የሚወዱ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘር እየተፈራረቁና በጋር ርብርብ በማጥፋት ተግባር ላይ እንደተሰማሩ በሚገባ የሚይሳይ ምስክርነት አፈላልጎ ማቅረቡ የሚያስመሰግነው ቢሆንም ቅሉ ፋሲል የኔዓልም ግን የተከበሩ አባ ኒቆዲሞስ ኦነግ የሰራውን ዘር በማጥፋት ድርጊት ለዘብ አድርገው ወደ ወያኔ ብቻ እንዲያተኩሩ ለማድረግ ያደረገው እጅግ በጣም ከፍተኛ ጥረት ልክ አንድ ፍርድ ቤት የቀረበ መስካሪ ይህን ብለህ መስክር የሚባል ዓይነት ሕገ-ወጥ አቀራረብ ከማድረጉ በተጨማሪ “ምናልባት ነግ ኦነግ በተመሳሳይ ሁኔታ ኦሮሚያን ቢያስተዳድር ሌላ ቋንቋ ተናጋሪ በሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይ ችግር አያመጣም” ወደ ሚል መደምደሚያ እንዲሄዱለት ለማድረግ መሞከሩ ለመሆኑ ከወያኔ መውደቅ በኋላ ኢሳት በራሱ መነፀር የሚመለከታት ኢትዮጵያ ያለ ታሪካዊ መሰረትና አግባብ ወያኔና ኦነግ ኦሮሚያ ብለው የፈጠሩትን አዲስ አገር ለኦነግ አሳልፎ የመስጠት ዕራይም ይኖር ይሆን? የሚል እይታ አህምሮዬ ላይ ተሰክቶ በመቅረቱ ከወዲሁ እንደዚህ ካለው አካሄድ ኢሳት ራሱን አጥድቶ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ እንዲመጣ ለማመላከት ነው::
እዚህ ላይ አንድ ግልፅ መሆን ያለበት ጉዳይ ወያኔ ከመጀመሪያውም ጀምሮ ትግል ሲጀምርና (ከዚያም በፊት ቢሆን) የአማራን ዘርና ኢትዮጵያን የሚወደውን የሕብረተሰብ ክፍል ጭምር አብሮ ደርቦ አስቀድሞ በማጥፋት ኢትዮጵያን በማዳከምና በሂደትም በመበታተን ታላቋን ትግራይ ለመመስረት የተመሠረተ ዘረኛና ኋላ-ቀር ድርጅት መሆኑ በሚገባ የሚታወቅ ሆኖ ሳለ የኦነግን ተመሳሳይ ዘር የማጥፋት ድርጊት ለመሸፋፈን መሞከር ግን ‘ወያኔን በኦነግ የትግራይ ተስፋፊነትን በታሪክ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ አዲስ ኦሮሚያ አገር’ የመተካት ያህል ከመሆኑ ባሻገር ደማቸው ባለድረቀ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይም መሳለቅ ይሆናል:: ለዚህም ነው ኢሳት ነገ ሊያያት የሚፍልጋት ኢትዮጵያ በዛሬው የኢሳት ቅይት ውስጥ ትታያለች በሚል ርዕስ የተነሳሁ::
በዚሁ ቃለመጠይቅ የፋሲል የኔዓልም አቀራረብ ኦነግን በመሸፋፈን ላይ እጅግ በጣም እርቆ የሄደ በመሆኑ የቀድሞው የኦነግ መሪ የነበሩት ዶ/ር ዲማ ነጎ እንኳን በአንድ ወቅት በጉዳዩ ላይ በኢሳት ቴሌቭዥን ቀርበው “በአማራ ሕዝብ ላይ ደረሰ የሚባለው ጥቃት በነፃ አጣሪ አካል ይጣራ ብለን በይፋ ብንጠይቅም ወያኔ ፈቃደኛ አልነበረም” የሚለውን አቋማቸውን እንኳ የሚጋፋ በመሆኑ እጅግ በጣም አዘንኩ:: እርግጥ ነው የፋሲል አካሄድ ምንግዜም ቢሆን ዋናው የአገርና የሕዝብ ጠላት ወያኔ በመሆኑ ሁሉም ኃይል በወያኔ ላይ መረባረብ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ከሚል አግባብ ተነስቶ ሊሆን እንደሚችል በሚገባ ብገነዘብም ቅሉ በሕዝባችንና በጋራ አገራችን ላይ ደባና ወንጀል የፈፀሙ ሁሉ ያለምንም ሽፍንፍን በሕግ ፊት መቅረብ ይኖርባቸዋል::
ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ “አዲስ አበባ ላይ የፈሰሰ ደም አለ” እያለ ተከታዮቹን ብዙ ብዙ ይሰብክ ነበር:: ለመሆኑ ማን የማንን ደም አፈሰሰና ነው ያልሆነ ታሪክ ለተከታዮቻቸው የሚሰብኩ? ዶ/ር ነጋሶ ሐረር ጨለንቆ ላይም በንጉሰ ነግሥቱ ዐፄ ዮሐንስ ትዕዛዝ መሰረት ዐፄ ምኒሊክ በግብፆች ተሹሞ ከነበረው ከአሚር አብዱላሂ ጋር የተደረገውንም የታኅሣሥ 29 ቀን 1879 ዓ.ም ኢትዮጵያን ከግብፆች የተቀነባበረ ጦርነት መከላከልንም የኦሮሞን ሕዝብ እንደመውረር ተቆጥሮ ብዙ ብዙ ቀስቅሰውበታል፤ ንፁሃንን ዜጎቻችን አስገድለውበታል:: እውነቱ ግን ዐፄ ምኒሊክ ጦርነት ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ለዕርቅ አስበው “ግባ እኔ ላንት ነው እንጂ የመጣሁት አገር ለማጥፋት አልመጣሁም:: ተገባህ ተተገዛህ አገር አልነሣህም ኋላ ይጠጥትሃል” (ተ.ጻ.መ በ1982 ዓ.ም ገጽ 291-2) ብለው መላዕክተኛ ወደ አሚር አብዱላሂ ላኩ:: አሚር አብዱላሂ ግን ዐፄ ምኒሊክና ሠራዊታቻው የፈሩ መስሎት መላዕክተኞችን አስሮ በማስቀረት ከግብፅ ያገኘውን መጠነ ሰፊ ትጥቅና ሰራዊት አሰልፎ አድፍጦ በዓለ ገና (ልደት) ቀን ምኒልክና ሠራዊታቸው በበዓለ ገና ቀን ጦርነት ውስጥ አይገቡም ብሎ ጅሃድ አውጆና ተዘጋጅቶ ለጦርነት ከሩቅ ሲመጣ ዐፄ ምኒሊክ በጦር መነጥራቸውን ከዙፋናቸው ፊት አቁመው በአጋጣሚ ስለተመለከቱት ሠራዊታቸው ያልተጠበቀውን ጥቃት በስልት ገብቶ እንዲገጥመው ወዲያው ትዕዛዝ ሰጡና ከከፍተኛ ጦርነት በኋላ የአሚር አብዱላሂ መድፎችና ወታደራዊ ትጥቆች ሊማረኩ በመቻላቸው የዐፄ ምኒሊክ ሠራዊት የኢሚር አብዱላሂን ጦር ድል ነሳው:: ነጋሶ ጊዳዳ ግን ይህን ጦርነት የኦሮሞን ሕዝብ እንደመጨፍጨ አድርጎ በመስበክ በደቡብና ሐረር አካባቢ በነበሩ የአማራ ተወላጆች ላይ እጅግ በጣም ከፍተኛ ወንጅል እንዲፈጠም ለወያኔ ተባባሪ ሆነ:: ለመሆኑ የሐረር ግንብ ተብሎ ዛሬም ድረስ የሚታወቀው መቸና ለምን እንደተገነባ ኦነጎችና ነጋሶ ትክክለኛ ታሪኩን ያውቁት ይሆን?
“Although Nur was unable to dislodge the Galla from the parts of the Chercher-Harar plateau which they had overrun and settled, his tireless campaigning and the wall which, according to tradition, he had built around the town, temporarily curbed the advance of the Baraytuma and saved Harar.” [Abir, p. 137, 1980].
“. . . the Baraytuma swept the area and destroyed many hamlets and villages as fas as the hirterland of Zayla. The town of Harar itself was besieged for a time and had it not been for the timely arrival of reinforcements from the coast it might also have fallen to the Galla. . . .” [Abir, p. 139, 1980].
“. . . Harar, however, gradually declined because its economy was adversely affected by the occupation of most of its lands by the Galla . . . “the fortunes of Zayla were always closely connected to those of Harar. It was, therefore, badly affected by Harar‟s decline and the deterioration of law and order in the whole region”” [Abir, p. 140, 1980].
“By 1570, exploiting the topography of Amhara and the character of its government and population, the Baraytuma began to raid westwards into Ethiopia‟s heartlands, as far as Gojjam and Dembiya. In the 1570s and 1580s, using Angot and Amhara (where the Wollo group began to settle) as their main bases they (mainly the Karayu-Azebu) pillaged Tigre, Begemder, northern Showa and parts of Gojjam. The Borana renewed their westward advance immediately after the departure of Serse Dingil in 1572. No longer hampered by the network of Chewa and the presence of royal army, they submerged the southern provinces and by 1576/7 penetrated Showa. In the coming years the numerous clans of the Mecha group moved west of Showa and began to raid Damot and nearby territories. Concurrently, their Tulama brothers began to settle in western and norhwestern Showa and to raid Gojjam across the Abbay. During the 1580s, while the Abitchu penetrated southern Showa, the Mecha and related groups occupied Bizamo and overran a large part of Damot. From there or from Showa their Sadetcha clans continued to expand towards the Omo-Gibe basin while, at the same time, their Afra-Gudru clans reached the Abbay from the south and increased their pressure northwards on Gojjam and westward on Damot”. [Abir, p.164, 1980].
ወያኔና እነ ነጋሶ ጊዳዳ በሕገወጥ መንገድ ለሸነሸኑት ክልል ከፍተኛ እውቅና በመስጠት ኦሮሚያ አዲስ አበባ ላይ ያላት መብት (legislation that would materialize the Oromia Regional State’s right over the capital Addis Ababa) በሕግ ተሎ ካልወጣልን እያለ አጥብቆ እየጠየቀ እንደሆን ለሕዝብ ለንባብ የቀረቡ እነ ካፒታል ዝርዝሩን አቅርበውት ነበር::
ወያኔስ እኛን እርስ በእርስ ካላጋጨንና ካላጋደለን የሥልጣን መሰረት እንደሌለው እየታወቀ ከቶ ለመሆኑ እነ ነጋሶ ጊዳዳና ኦነጎች ለምን ያልሆነ ታሪክ በመፍጠር በኢትዮጵያዊነቱ ኮርቶ የሚኖረውንና ለዛሬዋ ኢትዮጵያ እልውና ከሌሎች ወንዶሞቹ ጋር በመሆንና በመሰለፍ ከፍተኛ አስተዋህፆ ያደረገውን ኦሮምኛ ተናጋውን ወገናችንን ከአማራው ሕብረተሰብ ጋር በማጋጨት የማደርቅ ደም ማፍሰስ እንደፈለጉ አይገባኝም?
ከሁለት ዓመታት በፊት ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በኦሮሞ ወጣቶች ስብሰባ ላይ እንዲገኝ በተደረገ ግዜ የገዳ ሥርዓትን እንደ አንድ የአፍሪካ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግኝት አድርጎ በማቅረቡ እጅግ በጣም መደንገጥ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ፖለቲከኛ ነን የሚሉት ከራሳቸው አገር (ከኢትዮጵያ) ታርክ ጋር ጭራሽ የማይተዋወቁ መሆናቸው ይችን አገር የቱን ያህል እንደጎዳት ይጠልጥ ተገነዘብኩ:: ዶ/ር ብርሃኑ የገዳን ሥርዓት አፍሪካዊ በቀል የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው ብሎ የምስክርነት ቃሉን የሰጠበትን ምክንያት እውነትነት የሌለው መሆኑን የራሴን የግል ግንዛቤ ለማስጨበጥ አስቤ እጅግ በጣም ሰፊ ጽሁፍ የዶ/ር ብርሃኑ ሰነድ ለሕዝብ ለንባብ በቀረበበት ድህረ-ገጽ በኩል ብልክም ጽሑፌ እቀባ ተደርጎበት ሊወጣ አልቻለም:: ለነገሩ ዶ/ር ብርሃኑ በማያውቀው ታሪክ ውስጥ ገብቶ የምስክርነት ቃሉን ለመስጠት የሄደበት አካሄድ አሳዝኖኝ በወቅቱ ግዜዬን ላጠፋ ተገደድሁ እንጅ በዛሬ ላይ ቆመን (አገራችንና ሕዝባችን በታሪክ ታይቶ ተሰምቶ በማይታወቅ የወያኔ አደጋ ላይ ሁነው) ስለ ገዳ ሥርዓት የምንነጋገርበት ወቅት አልነበረም:: እናም በወቅቱ እንዲወጣ የላክሁት ጽሑፍ ለንባብ ባይበቅም የቀረብኝ ነገር የለም::
“As Amartya Sen said there is “nothing exclusively “Western” about valuing liberty or defending public reasoning . . . there is, in fact, a long tradition of participatory governance in Africa as well ” This certainly is not a debatable point for the Oromo community as the Gaada is the perfect example of this tradition in our own region.” [Identify politics and the struggle for liberty and democracy in Ethiopia, posted on Ethiomedia.com on Aug 2010. Dr Birhanu Nega, page 19].
ቢያንስ ቢያንስ የገዳ ሥርዓት ባሉት ስድስት የዕድገት እርከኖች ውስጥ ከመጀመሪያው ወደ ሚቀጥልው የሥልጣን ደርጃ ለመሽጋገር በስምንት ዓመታት አዳዲስ አካባቢዎችን በመውረርና ኗሪውን ሕዝብ በመግደል አልያም ቤት ንብረቱን ዘርፎ በማባረር በራስ ቁጥጥር ውስጥ እያስገቡ ወደፊት የመገስገስ ሥርዓት መሆኑን አለማወቅ ግን እጅግ በጣም የሚያሳዝን ከመሆኑ በተጨማሪ የገዳ ሥርዓት ነበር በሚባልበት ዘምን ላይ ኦሮሞ የሚባል ማኅበረሰብ ሳይሆን የነበረው የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪና የጎሣ (example: Baraytuma Galla, the Ittu, Humbana and Karayu tribes, they were many different tribes) ዝርያዎችና እምነት ተከታዮች የነበሩ መሆናቸውን አለማወቁ ጭምር ነው::
አንድ ግለሰብ የገዳ ስድስተኛው እርከን ላይ ሲደረስ ግን በአንድ ወቅት አፍለኛ ወራሪ፣ ጦረኛና የጦር የጎበዝ አለቃ (አባ ዱላ የሚባለው) እድሜው ስለሚገፋ በኋላ ደጀንነት ከነባሩ ሕዝብ የተዘረፉና ወደፊት በአፍለኛ ጦረኞች የሚዘረፍ ንብረትን፣ ከብቶችንና እፃናት ልጆችን እንዲጠብቅ ይደረጋል:: ይህን መሰሉን ሥርዓት ለኢትዮጵያ ሕዝብ መመኘት ግዜው ያለፈበትና ኢትዮጵያን ሕጅጉን ወደ ኋላ ያስቀረ ብቻም ሳይሆን ቀጣዩ ኑሮአችን አንዱ ሌላውን እንዲያሳድደው ከማበረታታት ያነሰ አይሆንም፤ አልያም የግዜአዊ የፖለቲካ ጥቅም ለማግኘት ተብሎ የሚደረግ አካሄድ ለሁላችንም የማይበጅ መሆኑን አለመገንዘብ ይሆናል:: . . . as Gada was set to achieve only a specific objective, i.e., to kill and raid on others society’s areas it was not convenient to model centralized administration structure that enables to govern by bringing these different clans at a specific given space in which this don’t allow it to have what Birhanu claimed it participatory governance!!
ዶ/ር ብርሃኑ በቅንጅት ግዜ በስለት አንደበቱ ያደረገው እጅግ በጣም ከፍተኛ እንቅስቃሴ ወያኔን እርቃኑን ያስቀረ ብቻ ሳይሆን አሁንም ዘረኛውን ወያኔ በሚያምንበት የትግል መንገድ አንለቀውም ማለቱን አደንቃለሁ – - – የትግሉ ጅማሮና አቅጣጫ ምን እንድሆን ማወቅ ባልችልም ቅሉ:: ሆኖም ግን አሁንም ቢሆን የዴሞክራሲያዊ አንድነት ኃይሉ ይበልጥ መተማመን ያለበት ‘ጥርት ባለ ኢትዮጵያዊ መሰረቱ፣ የእምነት ጽናቱና ታግሎ ሊያታግል በሚችል ተጨባጭ ተግባሩ’ መሆኑ በሚገባ መታወቅ አለበት:: በአንድ አጋጣሚ አንድ የቅርብ የትግል ባልደረባዬ የነበር ኢትዮጵያዊ አንጋፋ የኢሕአፓ ሰው የነበረው አቶ ሣሙኤል ዓለማየሁ ከዚህ ዓለም በሞት በመለየቱ ምክንያት በአሜሪካ በተደረገው የቀብር ሥነስርዓት ላይ ተገኝቶ ስለ ሟቹ የሚያውቀውን ሲናገር የሚከተለውን ብሎ ነበር:: “. . . አቶ ሣሙኤል ጥሩ ጓደኛችን የነበር መሆኑ ብቻ ሳይሆን ጥሩ ምሁርም ነበር፤ እኔ ምሁር የምለው በከፍተኛ የትምህርት ተቋም ውስጥ ገብቶ መማርን ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ፍቅሩና መከራና የተለያዩ ፈተናዎች የማይለውጡት ጽኑ እምነት ያለውን ዜጋ ነው . . .” ብሎ መናገሩ ዛሬም ድረስ ትዝ ይለኛል:: ይሁን እንጅ አሁን አሁን ምሁር የሚባለው ግን ይህን መሰሉ ጠንካራ ትውልድ ሳይሆን የአገሩን ታሪክ እንኳን በአግባቡ የማያውቅ ግን ደግሞ በዘመናዊ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ገብቶ ተማርኩ፣ ዶክተርና ፕሮፌሰር ሆንኩ የሚለውን (ብቻ) መሆኑ እጅግ በጣም ያሳዝናል:: ለመሆኑ ስንቱ ምሁር ነው ወያኔ በአ/አበባ ዩንቭርስቲ ውስጥ ለረጅም ግዜ ያገለግሉ የነበሩ አንጋፋ ፕሮፌሰሮች ተባረው የነሱን ቦታ በአዲስ ተመልማዮች እንዲሸፈን ሲደረግ የወያኔን አገርና ትውልድ የማምከንን ድርጊት በመቃወም በዩንቭርስቲው ውስጥ አላስተምርም ያለ? አልያም ራሱን ለወያኔ ምልምልነት አሳልፎ ላለመስጠት የወሰነ? These are key moral and ethical issues in which Ethiopia and Ethiopians Needed Most!!
እርግጥ ነው ከወያኔና ቢጤዎቹ ጋር የሚደረገው አገርና ሕዝብን የመታደግ ትግል ጽኑ ኢትዮጵያዊ ፍቅሩ፣ መከራና የተለያዩ ፈተናዎች የማይለውጡት እምነት ያለው ዜጋ መሆንን የግድ ይላል እንበል እንጅ በዘመናዊ የትምህርት ተቋማት ገብተው እውቀት የገበዩ ዜጎች ቀጥተኛ ተሳትፎና አመራር ሳይኖርበት የአገርና የሕዝብ እድገት ሊኖር እንደማችል ደግሞ በትግራይ ካድሬዎች የተሞላው የወያኔው መንግሥት ዐብይ ምስክር ነው::
ለዚህም ነው ኢሳት/ESAT ከግለሰቦች ጅማሮ ወሳጅነት አልፎ የወያኔን አሰልች የውሽት ቋት ሙሉ በሙሉ በመናድና በማምከን የኢትዮጵያውያን ዐብይ የዜናና የመረጃ ምንጭ እንዲሆን ወያኔና የወያኔ የጎሣ ፖለቲካ ሰለባ የሆኑ ድርጅቶ፣ ቡድኖችና ግለሰቦች ከሚጠቀሙባቸው አዳዲስ ስያሜዎች ራሱን ሙሉ በሙሉ አጽድቶ ጥርት ያለ ጽኑ ኢትዮጵያዊ አቋም መያዝ የሚኖርበት:: ይህም ማለት በኢትዮጵያ ውስጥ በምንም መንገድ ይሁን ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሱማሌ፣ ወዘተ የሚባል አገር ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች ተቻችለውና ተጋግዘው በሰላምና በእኩልነት ሊኖሩባት በሚችሉባት (በነገዋ) ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ውስጥ ሊኖር ስለማይችል የበፊት የክ/ሀገር፣ ከተሞችና ተቋማት ስሞች እንደ በፊቱ መጠቀም የወያኔን አዲስ የጎሣ ክፍፍል/ክልል አለመቀበል ብቻም ሳይሆን ወያኔና የጎሣ ፖለቲካ ሰለቦቹ በብቸኝነት የቀረጹት ሕገ-መንግሥትም ሕገ-ወጥ በመሆኑ ትግላችን ፍፁም ሥር ነቀል መሆኑን ጭምር አስረግጠን ማሳየት የሚኖርብን:
በእኔ የግል እምነት መሰረት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ከወያኔያዊ አቋማቸው መጀመሪያ ራሳቸውን አጥድተው ወጣቱ ትውልድ አሳፋሪ ለሆነ ጥቅም ሲል በወያኔ የጎሣ ፖለቲካ ሰለባ እንዳይሆን በአንድነት ፓርቲ ውስጥ “ምክር ስጭ አባት ሆነው” እንዲያገለግሉ ራሳቸውን ከሥልጣን እርካቡ ገድበው ቢሆን ኖሮ እጅግ በጣም በተከበሩ ነበር:: ይሁን እንጅ ‘ድመት መልኩሳ አመሏን አትረሳ’ ሆነና የአንድነት ፕሬዜዳን ሆነ ተመረጠ በተባለ ግዜ “ኢህአዴግ የአራት ድርጅቶች ግንባር ሆኖ እያለ ሥራ የሚሰራው ግን አራቱም ድርጅቶች አንድ ላይ ሆነው ነው” ብሎ ኢህአዴግ የአራት ድርጅቶች ግንባር እንደሆነ አድርጎ ግንዛቤ ለማስጨብጥ ይጥር ነበር:: ለመሆኑ የአገሪቷን ወታደራዊ ጠቋም፣ የመንግሥት የሥልጣን መዋቅሮች፣ የደኅንነቱን፣ የፖሊስ ተቋማትንና ልዩ ጥበቃ ኃይልን፣ ኤኮኖሚውን (ንግዱንና እርሻውን)፣ የአገሪቷ በጀት እየተባለ በይፋ የሚነገረውን ግን ደግሞ ወያኔ ብቻ እንደፈለገ የሚጠቀምበትን፣ የተለያዩ ሃይማኖት ተቋሟትንና የውጭ ኤምባሲዎችን፣ . . . ወዘተ ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠረው ወያኔ ብቻ መሆኑ እየታወቀ ለምንስ ነው ወያኔን ኢህአዴግ ብለን የምንጠራበት ምክንያትና አግባብ?
ከዚያም አልፎ ተርፎ ነጋሶ “የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል ድረስ ያለን መብት መቀበል ዴሞክራሲያዊ ጉዳይ እንጅ ልንቃወው አይገባም” እያለ ትንታኔ ይሰጥ ነበር:: እነዚህ የነጋሶ ጊዳዳ ትንታኔዎችና ግንዛቤዎች በቀጥታ የሚያሳዩን ምንም እንኳን ነጋሶ የአንድነት ፖርቲ ፕሬዜዳንት ሆኖ ይመረጥ እንጅ በፊት ከነበረው የወያኔ የጎሣ ፖለቲካ ሰለባነቱ ቅንጣት ታክል እንኳ ፈቅቅ አለማለቱን ነው:: እናም እኔን ያሳዘነኝ ነጋሶ በድፍረት ያን ማለቱ ሳይሆን በየትኛውም አህጉር ያለው ገራገሩ ሕዝባችን ወዳጅና የትግል አጋር ያገኘ እየመሰለው ወያኔ አላምጦ ለተፋው ሁሉ አጨብጫቢና አስተናጋጅ መሆኑ ነው:: እውን አቶ ገብረመድህን አርያን የመሰለ ቆራጥና ጽኑ ኢትዮጵያዊ ወገናችን እያለ አቶ ስዬ አብርሃ በኢትዮጵያውያን መድረክ ላይ በትርፍ ግዜው ተገኝቶ መለስ ገንዘብ እያሸሸ እንደሆን እንዲነግረን መጋበዝ ነበረበት – - – ሕዝባችን እሱ ባሰለጠነው በአጋዚ ልዩ ኃይል እየተጨፈጨፈ ባለበት እጅግ በጣም አሽቸጋሪ ወቅት??? አቶ ስዬ አብርሃ እኮ አገር እያጠፋ ያለውን የወያኔን ዘረኛ ሠራዊት መናድ ከፈለገ ብዙ ብዙ ስራ መስራት በቻለ ነበር:: እሱ ግን የወያኔ ጦር እንዲነካ አይፈልግም:: እንዲያውም ይህን ለማድረግ የሚፍጨረጨሩ ቢኖሩ ተገቢ እንዳልሆን ብዙ ብዙ ብዥታ ለመፍጥር ይሞክራል:: ዳሩ ምን ይደረግ እንደ ሌሊት ወፍ ሁለት ክንዱን ግራ ቀኝ እየዘረጋ (የስዬንና የነጋሶን ክንዶች ወደላይ በማንጠልጠል) አንድነትን ያፈረሰው ኢ/ር ግዛቸው ሰለሆነ ወጣቶች ነጋሶንና ስዬን ቢያሽቃብጡ አይፈረድባቸውም::
ሌላው ግን ምንም እንኳን ወያኔ በአገር ቤት በሕዝባችን ላይ እየፈፀመ ያለው ግፍ በደሉ ከሚፈፀምበት ሕዝባችን የተደበቀ ባይሆንም ቅሉ በደርግ ግዜ አገር ቤት ውስጥ የነበረውን ሁኔታ በስፋት በመዘገብ ረገድና ከዚያም አልፎ በመሄድ በወቅቱ ከደርግ ጋር ጦርነት ያደርጉ ለነበሩት ለሻዐቢያና ለወያኔ እንደ ቃል አቀባይ ይቆጠር የነበረው የአሜሪካ ራዲዎ ድምፅ VOA የአማርኛው ክፍል ዛሬ ዛሬ ጭራሽ ከጥቅም ውጭ እየሆነ በመጣበት ወቅት – - – እንደ-አብነት ያህል አልፎ አልፎ የሚደረጉ ቃለመጠይቆች እንኳን ሳይቆራረጡ ለአድማጭ እንዳይደርሱ በማሰብ የ5 ደቂቃ ቃለመጥይቅ ጭራሽ ትርጉሙን አጦ ስንት ግዜ እንደሚቀርብ አሉላ ቃለመጠይቅ ብሎ ጀምሮ ሰዎችን አስተዋውቆን ቀሪውን በሚቀጥለው ሳምንት ይዘን እንቀርባለን ብሎ በስልት ሸውዶን የሚያልፈውን፣ የዋልድባ ታሪካዊና ጽንታዊ ገዳማት በስኳር ልማስት ስም በወያኔ አደጋ ላይ ወደቁብን ብለው የገዳሙ አባቶች ለVOA ቃለመጠይቅ በሚሰጡበት ግዜ እጅግ በጣም ኃላፊነት በጎደለው መልኩ “ታዲያ መንግሥት አካባቢውን ለልማት የሚፈልገው ከሆነ ለናንተ ሌላ ምትክ የሚሆን ቦታ አልተሰጣችሁም እንዴ?” ብሎ አዲሱ አበበ ወያኔ ለቀደደው አፍራሽ ድርጊት ተባባሪ መሆኑንና ሄኖግ ሰማ-ሕ/ብሔር የሚባል VOA ዘጋቢ በG-8 የመሪዎች May 18, 2012 ሰብሰባ ላይ ተገኝቶ ያደረገው ቃለመጠይቅና ያቀረበው ዘገባ ሚሚ ስብሀቱ በነ ሞሶሎኒና ናዚ ዲቃላዎች ማካከል ተገኝታ በቆራጡ ጋዜጠኛና ወጣት ሙሁር አበበ ገላው ላይ ከሰጠችው ታሪክና ትውልድ የማይረሳው አሳፋሪ ድርጊት ጋር የማይተናነስ መሆኑን መስማት እጅግ በጣም አስነዋሪ ብቻም ሳይሆን አሁን በተቋሙ ((VOA) ላይ ያሉ ሁሉ (በራሳቸው ፍላጎትም ይሁን አልያም በሚደረግባቸው ጫና ምክንያት) ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትክክለኛ ዜና እያቀረቡ ስላልሆነ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በቀጥታ ከመጣላታቸው በፊት በምልካም ፈቃደኝነት ስራውን ጭራሽ እንዲተውት ወደምንጠይቅበት ሁኔታ እየተገፋን ባላበት ወቅት – - – ኢሳት/ESAT አስተማማኝ በሆነ መንገድ ለኢትዮጵያውያን ጠንካራ የዜናና የመረጃ ምንጭ ሆኖ እንዲቀጥል የፋይናስ ሃቅሙ ከቀጥታ ሙያተኛ የሰው ኃይሉ ጋር ተጣጥመው የሚሄዱበትን ስልት የኢሳት ማኔጅመንት በየግዜው ማገናዘብ ተገቢ ከመሆኑ በተጨማሪ በመልካም ፈቃደኝነት ላይ በተመሰረተ መልኩ በነፃ ግልጋሎት ሊሰጡት የሚችሉትን ተሳታፊዎችና የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያውቁ አማካሪዎች (የሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ተዋዕፆ ያለበት) ቢኖሩት እጅግ በጣም ይጠቅማል የሚል የግል አስተያየት አለኝ::
ምን እንኳን የኢሳት ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም ከአባ ኒቆዲሞስ ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ “ምናልባት ነግ ኦነግ በተመሳሳይ ሁኔታ ኦሮሚያን ቢያስተዳድር ሌላ ቋንቋ ተናጋሪ በሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይ ችግር አያመጣም” ወደ ሚል መደምደሚያ እንዲሄዱለት ለማድረግ መሞከሩ አሳዝኖኝ ግን ደግሞ የአንባቢያን ቀልብ ለመሳብ ይመቸኝ ዘንድ ግልፅ ደብዳቤ ለኢሳት/ESAT ልበል እንጅ ከላይ በተመሳሳይ ሁኔታ የተለያዩ ግለሰብ ስሞችን እያነሳሁ ችግሮችን ለማሳየት በመሞከሬ ኢሳት ተጠያቂ አይሆንም:: አጠር ባለ መልኩ ቀጥዬ ለማቅረብ የምሞክረው ግን በቀጥታ የኢሳት ታዳሚዎችን የሚመለት ይሆናል::
ባለፉት 21 ዓመታት የወያኔ አስከፊ አስተዳደር ውስጥ ተፈጥረው የነበሩ መልካም የትግል አጋጣሚዎች ነበሩ:: ሆኖም ግን ሁሉም እንደዋዛ ሳንጠቀምባቸው አምልጠውናል:: በዚህ ረገድ በዋና መልኩ ሊጠቀሱ ከሚችሉት ዋና ዋናዎቹ ውስጥ ወያኔ መላ አገሪቱን በ1983 ዓ.ም በተቆጣጠረ ግዜ በአገር ቤት ታማኝ በየነ ወጣት ኢትዮጵያውያንን አስተባብሮ ብዙ ቅርሶች በወያኔና ጀሌዎቹ እንዳይፈርሱ ሲከላከል በውጭው ዓለም ደግሞ ኢትዮጵያውያን በኢዴኃቅ ዙሪያ ተሰባስበው የተለያዩ የተቃውሞ ሰልፎችን ከማድረግ በተጨማሪ ኢዴኃቅ ወሳኙን ፀረ-ወያኔያዊ ትግል በብቃት የሚመራ መስሎ ይታይ ስለነበር ከፍተኛ ገንዘብ በየስብሰባው የተለገሰው ቢሆንም የኋላ ኋላ ግን ኢዴኃቅን ይመራው የነበር ግለሰብ ሱዳን በመጣ ግዜ ያንን ገንዘብ የተጠቀመበት በአባላቱና ደጋፊዎቹ ቆራጥ ጅማሮ ወሳጅነት ወሳኝ የትጥቅ ትግል ጀምሮ የነበረውን ማዘርላንድን ለማፍረስ ነበር:: ይህ ግለሰብ ሱዳን በመጣ ግዜ ከዚህ አሳፋሪ ድርጊቱ ተቆጥቦ ለኢሕአፓ አባላት ብቻ ሳይሆን ለሁላችንም አመራር በመስጠት ፀረ-ወያኔውን የትጥቅ ትግል እንዲያስተባብር ሻለቃ አጣናው ዋሴ ድንጋይ ይዘው አጎንብሰው ቢለምኑትም እሱ ግን ተልዕኮው አገርን አስተባብሮ ከማዳኑ ላይ ሳይሆን በአንድ ድርጅታዊ ስሜትና ዓላማ ተጠምዶ ስለነበር ልመናቸውን አሻፈረኝ ብሎ እጅግ በጣም አሳፋሪ ንትርክ በትግሉ ግንባር እንዲፈጠር በማድረጉ የሱዳን መንግሥት በሁኔታው ተገርሞና አዝኖ ይህንኑ ግለሰብ በ24 ሰዓት ውስጥ ወደ መጣበት እንዲመስ ሲያደርጉት እኛን ደግሞ በሂደት ለእስር ዳርገው ካቆዮን በኋላ በUNHCR ጣልቃ ገብነት ከአካባቢው እንድንለቅ በማድረግ ትግሉን እንዴት እንደጎዳው የሚያውቅ ያውቀዋል:: ሻለቃ አጣናው ዋሴ ግን ልጆቻቸው ውጭ እንዲወጡላቸው ቢለምናቸውም አገሬ ከወያኔ ነፃ ሳትመጣ ከአካባቢው አርቅም ብለው እምቢኝ ስላሉ ከቀሪ የማዘርላንድ አባላት ጋር ከሱዳን በወያኔ ታፍነው በቃሊቲ እስር ቤት ሕይወታቸው ሊያልፍ ችሏል::
ከዚያም ቀጥሎ ፓሪስ አንድ ፓሪስ ሁለት የሚባሉት በኢቶ-ኤርትራ ጦርነት ግዜ ከወያኔ ጋር ተደራድሮ ለመግባት ብዙ የጦርነት ቅስቀሳ በማድረግ የመሃሉ አገሩ ሕዝብ ወደ ጦር ግንባር እንዲዘምት በማደረግ እነ ስዬ አብርሃ ፈንጅ ረጋጭ አድርገው ሕዝባችን ካስጨረሱ በኋላ ‘ሕብረት’ ተብሎ ሲመሰረት በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ወገናችን ትግሉ መልሶ ሕይወት የዘራበት እየመሰለው ገንዘቡንና ግዜውን ቤዛ ከማድረጉ ባሻገር በተመሳሳይ ሁኔታ ቅንጅትን መርዳት ማለት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን እንደመሰለፍ ይቆጠራ ተብሎ ብዙ ገንዘብና ግዜ ያለብቃትና ሁነኛ አመራር ባከነ – - – በወቅቱ ለሁሉም ጠንካራ ድልድይ ሆኖ ያገለግል የነበረውና ብዙ ስራ የተሰራበት ተንሣኤ ራዲዎም ብዙም ሳይውል ሳያድር ልሳኑ ተዘጋ::
እናም ከዚህ መሰሉ ተደጋጋሚ ውድቀት ትግሉን ለማዳን የኢሳት ታዳሚዎች ኢሳት በሚያቀርበው ዜና ብቻ እየተቆጨን ከወሳኙ ትግል የምንሸሽ ከሆነ ኢሳትም ሕዝብን የማነሳሳት ጥረቱ ነግ እንደ ተንሣኤ ሬድዮ ሁሉ ከንቱ ሆኖ ይቀራል እኛንም ታሪክና ትውልድ ይፋረደናል – - – ሕሊናችን ይሞግተናል:: እዚህ ላይ አንድ በሚገባ መገንዘብ ያለብን በሕዝባችን ላይ የሚደረገውን ድርጊት አገር ውስጥ መልሶ ማቅረቡ ጉዳት ባይኖረውም በይዘቱ ግን ለቀባሪው አረዱት ነውና የኢሳት ሁነኛ ታዳሚ (Target Group) በሕዝቡ ላይ እየተፈፀመ ያለውን አበሳ ውጭ ያለው ወገኑ (የኢሳት ታዳሚ) እንዲያውቀው በማድረግ ከማንም በፊት ፊቱን ወደ ወሳኙ ትግል በማዞር አገርና ሕዝብን እንደዚያ ካለው አደጋ እንዲታደግ ማድረግ ነው:: ይህን መሰሉ የሰመረና የተቀናጀ የተግባር ሥራ የሚሰራ ከሆነ ኢሳት እስከመጨረሻው ድል ድረስ የትግሉን ውጤት እየተከታተለ ለሕዝብ ቢያደርስ ያምርበታል ለትግሉም ጠንካራ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል:: ሕዝቡም ድጋፉን እስከመጨረሻው ለኢሳት ይሰጣል::
“. . . በጀሮህ አተኛ. . .”
ቋንቋ ፖሊስ (አጋዚ) ሆኖ – ከቀዬ አፈናቅሎ ካማሳው አፈናቅሎ
ጎሣ ፖሊስ (አጋዚ) ሆኖ – ከእርስት አፈናቅሎ ከቤቱ አፈናቅሎ
ሕዝቤ ክፋኛ ተራበ – አገሬ ጭምር
ብቃያው ደስ አይል – አውድማው ጭምር
መሬቱ ደረቀ – ደኑ ተራቆተ
ቀየውን አያውቁት አየር ጠባዩን
እርሻውን አያውቁት በሬ አጠማመድን – ሞፈር ቀንበሩን
ምርጥ ዘር አለን ብለው ነጠቁት የሱን- አጠፈት የሱን::
ጀማሪው (ቀያሹ) ኢጣሊያ – የናዚ ጓደኛ
ቀጣዩ ወያኔ ጥርቅም ምንደኛ – የነሱ ድቅያ::
ቴዎድሮስን ተዋቸው – አትቀስቅሷቸው
አሉላን ተዋቸው – አትቀስቅሷቸው
ምኒሊክን ተዋቸው – አትቀስቅሷቸው
ባልቻንም ተዋቸው – አትቀስቅሷቸው
በላይን ተዋቸው – አትቀስቅሷቸው
ጀግኖችን ተዋቸው – አትቀስቅሷቸው
ለአገር ክብር ሲሉ – ለአገር እድገት ሲሉ
ብዙ ጉዞ ሄደው – ተራራውን ወጠው – ቁልቁለቱን ወርደው
ደክሟቸዋልና አርፈው ይተኙበት አትቀስቅሷቸው::
ፋኖ ተጠራራ ጎበዝ ተጠራራ ጀግና ተጠራራ
ገፍተውናልና ከተውናልና ለአሳር ለመከራ::
አዋጁ ይነገር እምቢልታ ይመታ
ገና አይቀርለትም እሰከ ግባተሞቱ ባፍጢሙ እስኪደፋ
እንግዲህ ምን ቀረን አቤ ከገፈፈው – አቤ ከቀደደው
የቆፈንን አድማስ የፍርሃትና ሸማ – የውርደትን ካባ::
ስብስበውን ተወው አትሁን መለኛ
ማነብነቡን ተወው ከንቱ ጥበበኛ
ወይ እንደ ቅንጅት ግዜ የድል አጥቢያ አርበኛ
ወይ እንደ ስም-አይጠሬ መጥፎ ከዳተኛ
ወይ እንደ ሕብረቱ መንታ መንገደኛ
ወይ እንደ አመራረ ቢሱ የስልጣን ጥመኛ
መድረክ አይፈይድም አትሁን ዜዴኛ አትሁን መንተኛ
ሌላ መንገድ የለም ሌላ ዘዴ የለም አትሁን ከዳተኛ
ትጥቁን ሳታስፈታው ለፍርድ ሳታቀርበው ያነን ጎጠኛ
እንግዲህ ነቃ በል የአበበን ቃል ስማ – በጀሮህ አተኛ – በጀሮህ – አተኛ::
በቀን አስር ግዜ በቁማቸው ለሚሞቱ ለነሆድ ባምላኩ የፍርሃት ማስታገሻና ለአበበ ገላው ደግሞ ለክብሩ የስንኝ ቋጠሮ ትሁንልኝ!! – አንተነህ ሽፈራው!!

No comments:

Post a Comment