Monday, May 11, 2015

ፖሊስ በሰማያዊ አባላት ላይ አለኝ የሚለውን መረጃ እንዲያቀርብ የ‹‹መጨረሻ›› አንድ ቀን ተሰጠው

ሚያዝያ 14/2007 ዓ.ም መንግስት አይ.ኤስ.አይ.ኤስ ሊቢያ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመውን የሽብር ድርጊት ለማውገዝ በጠራው ሰልፍ ላይ ‹‹ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳትና በመሳተፍ›› ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ሚያዝያ 30/2007 ዓ.ም ጠዋት በቄራ የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ቀርበው የ6000 ብር የሰው ዋስትና ተፈቅዶላቸው የነበር ቢሆንም ፖሊስ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ጥሶ በእስር ላይ እንዳቆያቸው ይታወቃል፡፡

የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ጥሶ አባላቱን በእስር ላይ ያቆየው ፖሊስ ዛሬ ሚያዝያ 3/2007 ዓ.ም ልደታ ፍርድ ቤት 11ኛ ምድብ ችሎት በማቅረብ ‹‹መረጃ ያጠፉብኝል፣ ከሀገር ይወጣሉ›› እና የመሳሰሉትን ከአሁን ቀደም ያቀረባቸውን ምክንያቶች በመዘርዘር 14 ቀን እንዲፈቀድለት ጠይቆ የነበር ቢሆንም ዳኛዋ አለኝ የሚለውን መረጃ ለማቅረብ ለነገ የ‹‹መጨረሻ›› ቀጠሮ እንዲሰጠው ወስነዋል፡፡
እነ ወይንሸት ፖሊስ የዋስትና መብታቸውን በመጣስ በህገ ወጥ መንገድ አስሯው እንደሚገኝ፣ ቋሚ መኖሪያ ያላቸውና ለኢሜግሬሽን ደብዳቤ በመላኩ ከሀገር የሚወጡበትና መረጃ የሚያጠፉበት መንገድ እንደሌለ በመግለጽ ተከራክረዋል፡፡ ዳኛዋም ‹‹ፍርድ ቤቱ በወሰነው መሰረት መፍታት ነበረባችሁ፡፡ ለምርመራ እስካሁን የታሰሩበት ቀን በቂ ነው፡፡ ሆኖም አሁንም የማቀርበው አዲስ ነገር አለ ካላችሁ ነገ የመጨረሻ ቀን እንዲሆን›› ብለዋል፡፡
ፖሊስ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ጥሶ በእስር ያቆያቸው በእነ ወይንሸት የምርመራ መዝገብ የተካተቱት አምስት ሰዎች ወይንሸት ሞላ፣ ዳንኤል ተስፋዬ፣ ኤርሚያስ ጸጋየ እና ማስተዋል ፈቃዱ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ሲሆኑ፣ በዚሁ መዝገብ ላይ ፖሊስ የፓርቲው አባል እንደሆነች የሚገልጸው፣ እሷ ግን አባል አለመሆኗን የገለጸች ቤተልሄም አቃለወርቅም ትገኛለች፡፡

No comments:

Post a Comment