Wednesday, June 17, 2015

እነ ብርሃኑ ተ/ያሬድ የክስ መቃወሚያ አቀረቡ * ብርሃኑ “እንዴት ማረሚያ ቤቱን ትከሳለህ” ተብሎ ወረቀቱን ተነጥቋል

እነ ብርሃኑ ተ/ያሬድ የክስ መቃወሚያ አቀረቡ * ብርሃኑ “እንዴት ማረሚያ ቤቱን ትከሳለህ” ተብሎ ወረቀቱን ተነጥቋልbirhanu tekle

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
መንግስት የኢትዮ-ኤርትራ ድንበርን ተሻግረው ኤርትራ የሚገኘውንና በተወካዮች ም/ቤት በሽበርተኝነት የተፈረጀውን የግንቦት ሰባት ወታደራዊ ክንፍ ሊቀላቀሉ ሲሉ በጸጥታ ኃይሎች ማይካድራ ላይ በቁጥጥር ስር አውያቸዋለሁ ያላቸው እነ ብርሃኑ ተክለያሬድ አቃቤ ህግ ባቀረበባቸው ክስ ላይ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያቸውን አስገቡ፡፡
ዛሬ ሰኔ 9/2007 ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የቀረቡት በእነ ብርሃኑ ተክለያሬድ የክስ መዝገብ የተካተቱት አራት ተከሳሾች ማለትም፣ ብርሃኑ ተ/ያሬድ፣ እየሩሳሌም ተስፋው፣ ፍቅረማርያም አስማማውና ደሴ ካህሳይ በጋራ ያዘጋጁትን የክስ መቃወሚያ አስገብተዋል፡፡
አራቱ ተከሳሾች ጠበቃ ማቆም አንፈልግም በማለታቸው ያለጠበቃ የቀረቡ ሲሆን፣ ተከሳሾቹ በክስ መቃወሚያቸው ላይ ሁለት አብይት ነጥቦችን በመጥቀስ ክሱ ውድቅ ተደርጎ በነጻ እንዲሰናበቱ ጠይቀዋል፡፡
ተከሳሾቹ በክስ መቃወሚያቸው ላይ እንደጠቀሱት አቃቤ ህግ ያቀረበባቸው ክስ ከህገ መንግስቱ ጋር የሚጣረስና (ጸረ-ሽብር አዋጁ ከህገ መንግስቱ ጋር እንደሚጣረስ በመጥቀስ) በወ/መ/ሥ/ሥ/ህጉ መሰረት ያልቀረበ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ እንደ ህጉ ያልቀረበን ክስ ውድቅ በማድረግ በነጻ ያሰናብተን ብለዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በተከሳሾች የቀረበው አቤቱታ ላይ አቃቤ ህግ መልስ እንዲሰጥ በሚል ለሰኔ 19/2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በሌላ በኩል አንደኛ ተከሳሽ ብርሃኑ ተ/ያሬድ በተደጋጋሚ በእስር ቤት በሚደርስበት በደል ላይ አቤቱታ ማሰማቱን ቀጥሏል፡፡ በዚህም ፍርድ ቤቱ አቶ ብርሃኑ አለኝ የሚለውን አቤቱታ በጽሑፍ እንዲያቀርብ አዝዞ የነበር ቢሆንም አቶ ብርሃኑ የማዘጋጀውን አቤቱታ ‹‹እንዴት ማረሚያ ቤቱን ትከሳለህ›› በሚል ጽሑፉን እየተነጠቀ እንደሆነ በመግለጽ አቤቱታውን በጽሑፍ ማቅረብ እንዳልቻለ አስረድቷል፡፡
ይህን የአቶ ብርሃኑን አቤቱታ በተመለከተ የማረሚያ ቤቱ ተወካይ ችሎት ፊት እንዲቀርቡ ተደርገው ‹‹ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ያለውን አቤቱታ እንዲያቀርብ አዝዘናል፤ ስለዚህ እናንተ መልስ ካላችሁ መልሳችሁን እንቀበላለን፣ አሁን ግን ተከሳሹ የሚያዘጋጀውን አቤቱታ እንዲያቀርብ አድርጉ›› በማለት በፍርድ ቤቱ ተነግሯቸዋል፡፡ በመሆኑም አቶ ብርሃኑ በቀጣዩ ቀጠሮ በእስር ቤት አያያዝ ላይ ያለውን አቤቱታ በጽሑፍ ይዞ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

No comments:

Post a Comment