Tuesday, June 30, 2015

የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት የፍርድ ቤት ቀጠሮ ወደዕረቡ መዘዋወሩ ተሰማ በፍርድ ቤቱ ቅጥር ግቢ እና ውጪ በርካታ የጸጥታ ሃይሎች ነበሩ

ዛሬ በጥዋት የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ላይ ሊሰጥ የተቀጠረውን ውሳኔ ተመልክቼ ለመዘገብ ልደታ በሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አምርቼ ነበር፡፡ 3፡30 ሰዓት ገደባ በታችኛው መግቢያ በር ጋር ስደርስ፣ ቁጥራቸው በዛ ያሉ፣ የሚሊተሪ ልብስ የለበሱ የጸጥታ ሃይሎች እና የአዲስ አበባ ፖሊሶች በፍርድ ቤቴ ቅጥር ግቢ በር ላይ ሆነው ሰዎችን በጥብቅ እየተፈሹ ሲያስገቡ አስተዋልኩ፡፡ በአጋጣሚ ከጠበቃ ተማም አባቡልጉ ጋር ተደዋውለን ተገናኝተን ነበር፡፡
‹‹እነአቡበከርን ከቂሊንጦ አላመጧቸውም፤ ቀጠሮው ለዕረቡ መዘዋወሩን የሚጠቁም መረጃ ሰምቻለሁ፡፡›› አለኝ፡፡ በዚህ ጊዜ ዳርማር አንበሳ ጫማ ቤት ፊትለፊት አንድ የፖሊስ አመራር አራት ሂጅብ የለበሱ ሴት ሙስሊሞችን ‹‹ከዚህ አካባቢ ሂዱ›› እያለ በመቆጣት ከአካባቢው እንዲርቁ ሲያደርጋቸው ተመልክቻለሁ፡፡
በርካታ የጸጥታ ሃይሎች በተሰበሰቡበት የፍርድ ቤት መግቢያ በር ጋር ተፈትሼ ወደውስጥ ዘለኩኝ፡፡ የኮሚቴዎቹ አንዷ ጠበቃ የሆነችውን ወ/ሮ አዲስን አገኘኋትና ስለጉዳዩ ጥያቄ አቀረብኩላት፡፡ ‹‹መደበኛ ባልሆነ መንገድ ዕረቡ የሚል መረጃ አግኝቻለሁ፤ ዕረቡ ችሎቱ ይሰየም አይሰየም ግን በእርግጠኝነት አላወኩም›› የሚል መልስ ሰጥታኛለች፡፡
እኔም የፍርድ ቤት ቅጥር ግቢውን ለቅቴ ስወጣም፣ ከውስጥም ሆነ በውጪ (በፍርድ ቤቱ) በርካታ የጸጥታ ሃይሎች፣ ፖሊሶችና የፍርድ ጉዳዩን ለመታዘብ የመጡ ወንድ እና ሴት ሙስሊሞች ቆመው ተመልክቻለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment