Thursday, February 19, 2015

“ስኳር ለባለካርድ ብቻ” – ምርጫ ቦርድ

sugar and election board

የሥልጣን ተቀናቃኞቻቸውን ይሁን ባላንጣዎቻቸውን ወይም ከእርሳቸው የተለየ ሃሳብ የሚያመነጩትን “ስኳር ወዳድ”፣ “በስኳር የተታለለ”፣ … እያሉ ለእስር ሲዳርጉ የነበሩት አቶ መለስ፤ ሞት ሳይቀድማቸው በፊት ራሳቸው ያቋቋሙትና እርሳቸውን ደግሞ ደጋግሞ እያገላበጠ አንዴ ፕሬዚዳንት ሌላ ጊዜም ጠቅላይ እያደረገ ሲሾማቸው የኖረው “የምርጫ ቦርድ” ሕዝቡን በስኳር እየፈተነ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ “ስኳር” ቀምሰው ሳያውቁ ስለ ስኳር “አስከፊነት” ዘለግ ያለ መግለጫ በመስጠት ይታወቁ የነበሩት መለስ ለፓርቲያቸው መለያ “ንብ” መምረጣቸው በስኳር ላይ ያላቸውን ጥላቻ በትጋት ያሳየ እንደሆነ ታሪካቸው አሁንም ይመሰክራል፡፡ የሆነው ሆኖ ጓዶቻቸውን “በስኳር ወዳጅነት” ለእስር የዳረጉት መለስ እርሳቸው እየመላለሰ እንዲያነግሥ የመሠረቱት “የምርጫ ቦርድ” ሰሞኑን በ“አፍቅሮተ ስኳር” መጠመዱን ቢሰሙ ኖሮ ምን ይሉ ይሆን? ለማንኛውም እስካሁን በ“ስኳር” ተጠርጥሮ እስርቤት ያልወረደው “ምርጫ ቦርድ” ብቻ መሆኑ ሰሞኑን ነገረ ኢትዮጵያ በፌስቡክ ገጹ ላይ “የምርጫ ካርድ ያልወሰዱ ዜጎች ስኳር እንዳይወስዱ ተከለከሉ” በሚል ያስነበበው ዜና ያስረዳል፡፡ እንዲህ ቀርቧል፡-

በምስራቅ ጎጃም ዞን አነደድ ወረዳ የቦቀል ቀበሌ ነዋሪዎች የምርጫ ካርድ ስላልወሰዳችሁ ስኳር አይሰጣችሁም መባላቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ በአካባቢው ስኳርን ጨምሮ ሌሎች አቅርቦቶች በስፋት እንደሚጠፉ የተናገሩት ነዋሪዎቹ ትላንት ጠዋት የቀበሌ ካድሬዎች በድምጽ ማጉያ “ዛሬ ስኳር ስለመጣ ቀበሌ ድረስ መጥታችሁ እንድትወስዱ፡፡ የመጣው ስኳር ውስን በመሆኑ ሊያልቅ ስለሚችል ዛሬውኑ መጥታችሁ እንድትወስዱ እናሳስባለን፡፡ ከዛሬ ውጭ ላታገኙ ትችላላችሁ” እያሉ ሲለፉ እንዳረፈዱ ተናግረዋል፡፡
ሆኖም መጥቷል የተባለው ስኳር ለማግኘት ወደ ቀበሌው ያመሩት ነዋሪዎቹ ስኳሩን ለመውሰድ ሲጠይቁ “የምርጫ ካርድ ወስዳችኋል?” የሚል ጥያቄ እንደሚቀርብላቸው ግልጸዋል፡፡ የምርጫ ካርድ የሚያሳዩ ነዋሪዎች ስኳሩ ሲሰጣቸው፤ ያላወጡት በአስቸኳይ ምርጫ ካርድ አውጥተው እንዲመለሱና ስኳር እንዲወስዱ ተነግሯቸዋል ተብሏል፡፡ በአንጻሩ ስኳር ለመውሰድ የምርጫ ካርድ ማውጣት የለብንም ያሉት ነዋሪዎች ስኳር እንደማያገኙ የተነገራቸው ሲሆን “እንደዜጋ የምርጫ ካርድ ወሰድንም አልወሰድንም ስኳር የማግኘት መብት አለን” ያሉ ዜጎች በፖሊስ ተደብድበው እንደተባረሩ ከቦታው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡
በጠዋቱ የቀበሌ ነዋሪዎች ያሰሙት የነበረውን ለፈፋ ሰምቶ ወደ ቀበሌ ያመራ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ መምህር የምርጫ ካርድ ካላመጣ ስኳር እንደማይሰጠው ተነግሮት መመለሱን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡ መምህሩ “የምርጫ ካድር የመውሰድና ያለመውሰድ መብት አለኝ፡፡ የማምንበት ፓርቲ ሲኖር የምርጫ ካርድ እወስዳለሁ፡፡ ካልሆነ ግን አልወስድም፡፡ ብወስድም ስኳር ለማግኘት ብዬ አይደለም፡፡ እንደማንኛውም ዜጋ ስኳር የማግኘት መብት አለኝ” በሚል የቀበሌ ሰራተኞቹን ለማስረዳት ቢሞክርም “እኛ ስኳር ስጡ የተባልነው ካርድ ለወሰደ ብቻ ነው፡፡ ካርድ ካልወሰድክ አይሰጥህም” ተብሎ እንደተመለሰ ገልጾልናል፡፡ (ነገረ ኢትዮጵያ)

No comments:

Post a Comment