Monday, February 16, 2015

ተሂዶበት ከሚፈለገው ቦታ ባላደረሰ መንገድ ተመላልሶ መጓዝ ችግሩ የመንገዱ ሣይሆን የተጓዡ ነው

ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት             ረቡዕ የካቲት ፭ ቀን ፪ሺህ፯  ዓ.ም.                       ቅፅ ፫ ፣ ቁጥር ፲   ሰሞኑን የትግሬ-ወያኔ እጀታ የሆነው የምርጫ ቦርድ፣ በመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና በአንድነት ለፍትሕና ዲሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) ላይ «ከምርጫ ውድድር የማገድ» ውሣኔ ማሣለፉን ሰምተናል። ይህም ምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤቶች፣ ፖሊስ፣ አቃቢ ሕግ፣ መከላከያ ሠራዊቱ እና መሰል በ«ሕገ-መንግሥቱ ተቋቋሙ» የተባሉት ተቋሞች በሞላ የወያኔ ሕዝባዊ ድርጅቶች መሆናቸውን በይፋ እና በማያሻማ መንገድ ከታዩባቸው አያሌ ተግባሮች መካከል አንዱ ሆኖ የሚጠቀስ ነው። የምርጫ ቦርዱ ውሣኔ በራሱ ምርጫ ቦርድ የወያኔ ሕዝባዊ ድርጅትና እጀታ ከመሆኑ የመነጨ ብቻ ሣይሆን፣ የተቃዋሚው ጎራ ደጋግሞ በሄደበት እና ምንም ዓይነት ውጤት ባላስመዘገበበት መንገድ መጓዙ ጭምር እንደሆነ ሊስተዋል ይገባል። የትግሬ-ወያኔ በምርጫ ተሸንፎ ሥልጣን እንደማይለቅ ያለፉት አራት የይስሙላ ምርጫዎች ከበቂ በላይ ነቃሾች ናቸው።
ይህን በተመለከተ የ1997ቱን የምርጫ ውጤት ተከትሎ የትግሬ-ወያኔ በወሰደው የድምፅ ነጠቃ፣ ታዛቢ የነበሩት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር አቶ መለስን ለማለስለስ ባደረጉት የማግባባት ሙከራ ያረጋገጡት ሃቅ ነው። አቶ መለስ በወቅቱ የሰጣቸው መልስ፦ «ኢሕአዴግ በምርጫም ሆነ በኃይል ሥልጣን ከለቀቀ የሚጠብቀን አንድ እና አንድ ብቻ ነው። ይኸውም በአገር ክህደት ተከሰን ወህኒ መውረድ ነው። በመሆኑም ለ፲፯(አሥራ ሰባት) ዓመታት አፈር ግጠን የጨበጥነውን ሥልጣን በሕዝብ ድምፅ አንለቅም።» ሲል ነበር እቅጩን እና የማይለወጠውን የትግሬ-ወያኔን ዓላማ የገለጸው። በተመሣሣይ ሁኔታ የሕወሓት እና የኢሕአዴግ የፖሊት ቢሮ አባል የነበረው አቶ ገብሩ አሥራትም «ሉዓላዊነትና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ» በሚለው መጽሐፉ የሚነግረን ይህንኑ ነው። ስለዚህ ምርጫ ቦርድ ሰሞኑን የሰጠውም ውሣኔ የዚሁ ተከታይ አካል በመሆኑ፣ ድርጊቱ አስገራሚም፣ አስደንጋጭም አይሆንም። ባለፉት ፳፬(ሃያ አራት) ዓመታት የኖርንበት ዓለም የታዘበው ዕውነታ ነውና። አስገራሚና አስደንጋጭ የሆነው ተቃዋሚው በወያኔ ሁለንተናዊ ፍላጎት ቁጥጥር ሥር መሆኑን አለመገንዘቡ ነው። እኒህ ተቃዋሚዎች ጉዟቸው ያልተለወጠ እና በየአምስት ዓመቱ በሚደረግ የምርጫ ዘመቻ የተገዛ ነው። ይህ ጉዞ ለውጤት ያላበቃ መሆኑ ተደጋግሞ እየታዬ፣ ውጤት እንደማያስገኝ በታወቀ መንገድ መጓዙ፣ ችግሩ ከመንገዱ ሣይሆን፣ ከተጓዡ እንደሆነ ትግሉ የሚገኝበት ሁኔታ ያሣያል። ስለሆነም ተቃዋሚ ኃይሎች ከ1997ቱ የምርጫ ሂደት እና ውጤት ከታዩት አዎንታዊ እና አሉታዊ የጉዞ አቅጣጫዎች ትምህር የቀሰሙ አይመስልም። ሁለተኛው የተቃዋሚ ድርጅቶች መሠረታዊ ችግር በአደረጃጀታቸው ላይ ያጠነጠነ ነው። የትግሬ-ወያኔ በማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ብቻ ሣይሆን በዕድሮች ሣይቀር የራሱን ሥውር መዋቅር አስርጎ አደራጅቷል። ሰሞኑን በመኢአድ እና በአንድነት ላይ የተከሰተው ችግር ግን፣ ተቃዋሚ ድርጅቶች የትግሬ-ወያኔን የሤራ ስልት ባለመገንዘብ ከነ አየለ ጫሚሶ ዓይነት ሠጎ ገቦች ድርጅቶቻቸውን ማጽዳት አለመቻላቸውን ቁልጭ አድርጎ ያሣያል። ሰለዚህ የአደረጃጀት ሥልታቸው የወያኔን ሠርጎ ገቦች ሊያንተረትር በሚችል መልክ እስካልተቃኘ ድረስ፣ በምንም ሁኔታ የትግል ጉዞ አቅጣጫቸው በወያኔ እና በአጋሮቹ ላይ ተጽዕኖ ሊያሣድር አይችልም። ይህም ብቻ አይደለም፤ ተቃዋሚው የሙጥኝ ብሎ የያዘው «በሕጋዊ እና ሰላማዊ መንገድ ብቻ የትግሬ-ወያኔን በምርጫ አሸንፈን ሥልጣን እንይዛለን» የሚለውን ብቸኛ የትግል መሣሪያው አድርጎ መያዙ፣ ለትግሬ-ወያኔ ሠርጎ መግባት የተመቻቸ ሁኔታ ከመፍጠሩ ባሻገር፣ የነቁትን የኅብረተሰብ ክፍሎች በቀላሉ የአገዛዙ ዒላማ እንዲሆኑ አድርጓል። ይህም ትግሉን ተተኪ መሪዎች በማሣጣት መሪ አልባ በማድረጉ፣ የሕዝቡን  የወኔ ሥንቅ እንዳሟጠጠ በድርጅቶቹ ውስጥ በቂ ትኩረት የተሰጠው ያለመሆኑን ያመለክታል። የተቃዋሚው ኃይል የትግሬ-ወያኔን ባሕሪ የሚመጥን የትግል ሥልት መከተል ባለመቻላቸው፣ ወያኔ «ግሞ» ሲል «ጥንቦ» ማለት አልቻሉም። በተደጋጋሚ በአገር ቤት ካሉ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚደመጠው የትግል ስልት፦ «በሕጋዊ እና ሰላማዊ መንገድ ብቻ የትግሬ-ወያኔን በምርጫ አሸንፈን ሥልጣን እንይዛለን» የሚል ነው። ሆኖም የሰላማዊ ትግል ሥልት በምርጫ ዘመቻ ብቻ የተገደበ አይደለም። የምርጫ ዘመቻ ለሰላማዊ ትግል ጠቃሚ የሚሆነው ዲሞክራሲያዊ ተቋሞች የሚባሉት ማለትም፦ ነፃ እና ገለልተኛ የሆነ የምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤቶች፣ አቃቤ ሕግ፣ ፖሊስ፣ የመከላከያ ሠራዊት እና ወገንተኛ ያልሆኑ የብዙኃን መገናኛ ተቋሞች መኖር፣ ወዘተርፈ፣ በአጠቃላይ የሕግ የበላይነት ሰፍኖ ከማንም ተፅዕኖ ውጭ በነፃ የመሥራት የዜግነት መብት ሲረጋገጥ ነው። እነዚህ ተቋሞች በሌሉበት ሁኔታ ግን፣ በምርጫ ፖለቲካ ወያኔን ከሥልጣን እናወርዳለን ብሎ ምርጫን በብቸኛ የትግል መሣሪያነት የሙጢኝ ብሎ መያዝ፣ ታጋዩ ሕዝብ ሥቃይን እና በደልን ተለማምዶ የ፵(አርባ) ቀን ዕድሌ ነው ብሎ እንዲያምን እና ለወያኔ አገዛዝ ምቹ እንዲሆን ሠፊ በር የሚከፍት መሆኑ በግልፅ ሊታመንበት ይገባል። በተግባርም የሚታየው ይኼው ነው። የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚ መዋቅር፣ የፍትህ አካሎች እና የብዙሃን መገናኛ ተቋሞች በአንድ ዘረኛ ቡድን ፍላጎት እና ቁጥጥር ሥር በዋሉበት ሀገር፣ በምርጫ ሥልጣን እረከባለሁ ማለት ሸንበቆ ያፈራል፣ በቅሎ ትወልዳለች፣ ዝንብ ማር ትጋግራለች፣ ፀሐይ በምሥራቅ ትጠልቃለች እንደማለት ይቆጠራል። እንደሞረሽ-ወገኔ እምነት፣ ሰላማዊ ትግሉ የተለየ መንገድ መከተል ይኖርበታል። ወቅታዊ የትግሉ መፈክር «ለዲሞክራሲ፣ ለዕኩልነት እና ለብልጽግና» ሣይሆን ቅድሚያ ለነፃነት ትግል መሆን አለበት። አገር እና ሕዝብ ሳይኖሩ፣ ዲሞክራሲ እና ዕኩልነት ሊታሰቡ የሚችሉ ጉዳዮች አይደሉምና! በመሆኑም፣ የተቃዋሚው ጎራ፣ የትግሬ-ወያኔን እንደተኩላ ከብቦ የሚቦጫጭቅበትን፣ አጠቃላይ ሕዝባዊ እንቢተኝነትን የትግሉ መርህ አድርጎ ሊንቀሣቀስ ይገባዋል። ስለዚህ ቀዳሚው የትኩረት አቅጣጫ መሆን ያለበት በየአካባቢው ያለውን የትግሬ-ወያኔን የስለላ መዋቅር በመበጣጠስ፣ ሕዝቡ የራሱ አለቃ የሚሆንበትን ዘዴ በመሻት፣ የትግሬ-ወያኔን እና አጋሮቹን ለነፋስ በመስጠት፣ የአገዛዝ ዕድሜያቸውን ለማሳጠር መንቀሣቀስ ነው። ይህ ደግሞ ከገጠር እስከ ከተማ፣ ከመሀል እስከዳር ሕዝቡን በማደራጀት በእንቢተኝነት ስሜት እንዲነሣ ማነቃነቅ ያስፈልጋል። የትግሬ-ወያኔ አፋኝ ቡድን የኃይል መከፋፈል የሚፈጠርበት፣ ለቅልብ ጦሩ ሆድ መሙያ የሚከፍለው በጄት የሚያጣበት፣ በገዥው ቡድን መካከል የኃሣብ መከፋፈል የሚፈጠርበት፣ የማስፈጸም አቅሙ የሚሟሽሽበት፣ እርስ በርሳቸው የሚጠራጠሩበት ሁኔታን የሚፈጥር ሥራ መሠራት አለበት። ለዚህም በደህንነቱ፣ በሠራዊቱ፣ በፖሊሱ፣ በቢሮክራሲው መሀል ሠርጎ በመግባት ዓላማ እና ዕቅዳቸውን ማክሸፍ ያስፈልጋል። ሕዝቡም «ላልወከልነው አካል ግብር አንከፍልም፣ የእኛ ባልሆኑ ተቋሞች አንገዛም፣» የሚለውን ስሜት እና እምነቱን ሊያጎለብት ይገባል። በትግሬ-ወያኔ የተለያዩ የንግድ እና የአገልግሎት ተቋሞች፣ ማለትም፥ የትራንስፖርት፣ የሆቴል፣ የንግድ ቤቶች እንዳይጠቀም በልዩ ልዩ መንገዶች በማስተማር ወያኔ እና አባሎቹን ከማናቸውም ማህበራዊ እና ባህላዊ እንቅስቃሴዎች በማግለል ብቻቸው እንዲቆሙ መደረግ አለበት። «መጡብን» ሳይሆን፣ «መጣንባችሁ» ሊባሉ ይገባል። ከእንግዲህ ተቃዋሚው ጎራ ሙሾ ማውረዱን ማቆም አለበት። መርዶ የሽንፈት እንጂ፣ የድል ምልክት ባለመሆኑ፣ «እንዲህ ሆን፣ እንዲ,ህ ተደረገን» የሚሉት እሮሮዎች ሊገቱ ይገባል። ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት የትግሬ-ወያኔ በሁለቱ የሰላማዊ ትግል አራማጅ ድርጅቶች ላይ የወሰደውን እርምጃ የተመለከተው ከትግሬ-ወያኔ ጉዞ እና ዓላማ አንፃር የሚጠበቅ እንጂ፣ ዱብ ዕዳ እና እንግዳ ነገር አድርጎ አይደለም። በአንፃሩ «ማሽላ ሲያር ይስቃል» እንዲሉ፣ ይህ እርምጃ ለፀረ-ወያኔ ትግል እልህ፣ ቁጭትና የመጠቃት ስሜትን የሚፈጥር ነው ብለን እናምናለን። ስለሆነም የተቃዋሚው ጎራ በአንድ ብሔራዊ ዓላማ ዙሪያ እንኳን መሰባሰብ ባይችል፣ በፀረ-ወያኔ አቋሙ በአንድ ግንባር ወይም ኅብረት ሥር እንዲሰለፍ ሠፊ በር የከፈተ ያህል ይቆጥረዋል። ስለዚህ በአገር ቤትም ሆነ በውጭ የሚገኘው ተቃዋሚ ኃይል ከምንጊዜውም በበለጠ ተቀራርቦ በመነጋገር በትግሬ-ወያኔ አገዛዝ ላይ የተጠናከረ እና ሁሉን- አቀፍ ትግል እንዲያደርግ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያዊነት ስም ጥሪያችንን እ,ናቀርባለን።   ዐማራን ከፈጽሞ ጥፋት እንታደጋለን! ፈለገ አሥራት የትውልዳችን ቃል ኪዳን ነው! የትግሬ-ወያኔ ዘረኛ ቡድን ነው፤ በመሆኑም መወገድ አለበት! - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/38954#sthash.nApo4tfT.dpuf

No comments:

Post a Comment