Monday, September 14, 2015

አስመራ ተጉዘው የነበሩት ሁለቱ የኢሳት ጋዜጠኞች ስለ ሞላ አስገዶም መክዳት ምን አሉ?

በአዲስ ዓመት ዋዜማ ኢሳት ያሰማው ሰበር ዜና አነጋጋሪ ሆኗል:: ውህደት ተፈጸመ የሚለው ዜና 3 ሌሊት ሳያልፍ ይህ ዜና ብዙዎችን እያነጋገረ ነው:: ስለታጋይ ሞላ አስገዶም አስመራ ሄደው አግኝተውት የነበሩት ሁለቱ የኢሳት ጋዜጠኞች ፋሲል የኔዓለም እና መሳይ መኮንን ምን ይላሉ? ያንብቡት:: ፋሲል የኔዓለም ስለ ሞላ አስገዶም:- የደሚህቱ ሞላ አስገዶም መክዳቱን ስሰማ በእጅጉ ተገርሜአለሁ። ከቀናት በፊት ሞላ ፣ ሰው አክባሪ፣ ተግባቢና አገሩን የሚወድ ሰው መሆኑን ጽፌ ነበር። ኤርትራ በነበርኩበት ጊዜ ደጋግሜ አግኝቸዋለሁ ፣ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ጊዜ ወስደን ተነጋግረናል። እስከዛሬዋ ቀን ድረስ ስለሞላ የነበረኝ አመለካከት ቀደም ብዬ የገለጽኩት ነው። ስለእውነት እመሰክራለሁ፣ ኤርትራ በነበርኩበት ወቅት አንድም ቀን በሰላይነት እንድጠረጥረው ወይም በወያኔነት እንድፈርጀው የሚያደርግ ነገር አላነበብኩም። ከህወሃት ጋር የሚጋራቸው አቋሞች ቢኖሩም፣ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የማይናወጽ አቋም እንዳለው፣ ህወሃት ኢትዮጵያን ታሪክ አልባ በማድረጉ በጣም እንደሚያዝን ነግሮኛል። ከእርሱ ጋር የተግባባንበት የመጨረሻው ነጥብም ይህ ነበር- ህወሃት ኢትዮጵያን ከመበታተኑ በፊት እንድረስላት።
ጥምረትን በተመለከተም በተወሰነ ደረጃ አስፈላጊነቱን ያምናል። ደሚት ያለውን የሰራዊት ብዛትና ሃብት ሲያስበው ደግሞ፣ ከደሚህት ያነሰ የሰራዊት ቁጥር ካላቸው ጋር ይጣመሩ የሚለውን ለመቀበል ሲቸግረው አይቻለሁ። በሌላ በኩል ደግሞ ወደ አማራው ክልል ዘልቆ ለመግባት አርበኞች አስፈላጊ ናቸው ብሎ ያምን ነበር፤ ለዚህም ሲል መጣመሩን ይፈልገዋል። እንደሰማሁት ከአርበኞች ግንቦት7ና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በነበረው ድርድር፣ መጀመሪያ ላይ ባይደግፈውም፣ በራሱ አመራሮች በድምጽ ብልጫ ከተሸነፈ በሁዋላ ውሳኔውን ተቀብሎ ነበር ። ሞላ ” ጥምረቱን የደገፉት ጓደኞቼ በሂደት ያባርሩኝ ይሆናል” የሚል ስጋት ሳይገባው አልቀረም። እነ ፕ/ር ብርሃኑ ወደ ኤርትራ ወርደው ተቃዋሚዎችን ያስተባብራሉ ብሎ የጠበቀም አይመስለኝም። ምንም ይሁን ምን ሞላ የከዳው ከስልጣን ጋር በተያያዘ መሆኑን አምናለሁ። እኔ ኤርትራ በነበርኩበት ወቅት ከደሚህት ጋር የሚደረግ ድርድር ስላልነበር፣ ስለ ስልጣን ፍላጎቱ ልናገር አልችልም ። እንደሰማሁት በደሚት ውስጥ በርካታ አመራሮች አሁንም አሉ። የወጣው ሰራዊት ጥሎት ከወጣው ሰራዊት ጋር ሲነጻጸር ኢምንት መሆኑን አንዳንድ ሰዎች ነግረውኛል። ይህ ሰራዊት የአገር አድን ሰራዊቱ አካል ሆኖ የሚቀጥል ይመስለኛል። በነገራችን ላይ የደሚህት ሰራዊት ኢትዮጵያዊ ቅርጽ አለው፤ ሁሉንም ብሄረሰቦች አቅፎ የያዘ ነው። እንዲያውም ትዝ አለኝ፣ ደሚህት የተለያዩ ብሄረሰቦችን በአባልነት ይዞ እያለ እንዴት የትግራይ ነጻ አውጭ ተብሎ መጠራቱ ትክክል አይመስለኝም፣ ስማችሁ እየጎዳችሁ ነው ብየዋለሁ። ለማንኛውም፣ ፖለቲካ እንዲህ ነው። እስከመጨረሻው የጸና ብቻ እርሱ ያሸንፋል። መልካም አዲስ አመት። መሳይ መኮንን ስለ ሞላ አስገዶም:- ትግሉ የምር መሆኑን የሚያመላክቱ ምልክቶች እየታዩ ነው:: በባህላዊ መንገድ ሲታገሉ ስንዝር መሄድ ያልቻሉ የዕውነቱ ቀን ሲመጣ መንገዋለላቸው የሚጠበቅ ነው:: አዲሱ ንቅናቄ የሚያራግፈውን እያራገፈ ወደፊት ማለቱ አይቀርም:: ህወሀቶች በዚህ ከፈነጠዙ: የነጻነት ታጋዮችን የሚደግፉ ኢትዮጵያውንም በዚህ ከተሰበሩ ሁለቱም ተሳስተዋል:: ከግለሰብ የወረደ በድርጅት የሚመራ ትግል መስመሩን ይዟል:: ነገ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ወደ ህወሀት ቢገባ የሚቆም ትግል አይደለም እየተካሄደ ያለው:: ህዝብ ልቡ ለነጻነት ከቆመ: ህይወቱን ለመስዋዕት ካዘጋጀ ማን ያቆመዋል? - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/46609#sthash.55HGqCym.VAWd7GS0.dpuf

No comments:

Post a Comment