Wednesday, September 9, 2015

መልካም የድል ዓመት።

አራቱ ንቅናቄዎች በዚህ ፍጥነት የጋራ ድርጅት ይመሰርታሉ ብዬ አላሰብኩም ነበር። ሁሉም የድርጅት አመራሮች ምስጋና ይገባቸዋል፤ ፕ/ር ብርሃኑ ትግሉ ስርዓት ይዞ በጥሩ አቅጣጫ እንዲጓዝ እያደረገው እንደሆነ በመስማቴ እንደ ወትሮው ኮርቸበታለሁ። የደሚት መሪ ሞላ አሰግዶም ትሁት፣ ሰው አክባሪ፣ ተግባቢና አገሩን በጣም የሚወድ ሰው ነው። መአዛው ጊጡም እንዲሁ ደግ፣ቅን፣ ሰው አክባሪና አገሩን የሚወድ ሰው ነው። የአማራን ድርጅት መሪ በአካል አላገኘሁትም፣ ምክትሉንና ጸሃፊውን አነጋግሪያቸዋለሁ፤ በተለይ ጸሃፊውን በቅርበት አውቀዋለሁ፣ ገና ትግሉን በረሃ ወርዶ ሳይቀላቀል በአገር ቤት ብዙ ታሪክ የሰራና መስዋትነት የከፈለ ወጣት ነው። የአፋሩ ኢብራሂም ሙሳም ሆነ ዶ/ር ኮንቴ አገራቸውን የሚወዱ አሪፍ መሪዎች ናቸው። በሁሉም ድርጅቶች ውስጥ፣ በጣም ብዙ አገር ወዳድ ታጋዮች አሉ፤ አዲሱ ድርጅት የእነዚህ ታጋዮች ሁሉ ውጤት ነውና እነሱም ክብር ይገባቸዋል።

ከታዋቂ ድርጅቶች መካከል ሳይጣመር የቀረው ኦነግ ነው፤ ኦነግ በተለያዩ ቡድኖች በመከፋፈሉ አፋጣኝ ጥምረት ለመመስረት ሂደቱን አስቸጋሪ ሳያደርገው አልቀረም። በቅድሚያ ድርጅቱ አንድ ሆኖ ቢመጣ ለመጣመር ያመቻል፤ ይህንንም ያደርጋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ጄ/ል ከማል ገልቹም ሆነ ጄ/ል ሃይሉ ጎንፋ አገር ወዳድና ቅን አሳቢ ታጋዮች በመሆናቸው ጥምረቱን ለመቀላቀል አይከብዳቸውም። አቶ ዳውድ ኢብሳን ስለማላውቀው አስተያየት መስጠት አልችልም ። የኦጋዴኑ ኦብነግ ኤርትራ ውስጥ መቀመጫ እንዳለው አላውቅም። ግን አይመስለኝም።
የድርጅቶቹ መጣመር ስለ ድህረ-ኢህአዴግ ኢትዮጵያ የምንነጋገርበትን ጊዜ ካሰብነውም በላይ አቅርቦታል። እንግዲህ ነጻነቱን የሚናፍቅ ሁሉ አዲሱን ድርጅት በሚችለው አቅም በመደገፍ የነጻነቱ ተቋዳሽ ብቻ ሳይሆን የነጻነቱ ባለቤትም ለመሆን ይነሳ ። ሙያ በልብ ነው እንዲሉ ትግሉ በጉራ መንፈስ አይሁን፤ በትዕቢትና በበቀል ስሜት ሳይሆን በትህትናና በፍቅር ይካሄድ። ድርጅቱ አዳዲስ ሰዎችን የሚቀበል እንጅ ሰዎችን የሚገፋ አይሁን። ማንም ኢትዮጵያዊ በዚህ የነጻነት ትግል ያገባዋል። ኢህአዴጎችም ቢሆኑ ለሰሩት ጥፋት ህዝብን የመካሻ ጊዜ አግኝተዋልና ለትግሉ አስተዋጽኦ በማድረግ ህዝባቸውን ይካሱ። መረጃዎችን ከመስጠት ጀምሮ፣ ድርጅቱን ከውስጥ ሆኖ የማዳከም ዘመቻ ይጀምሩ። መልካም የድል ዓመት።

No comments:

Post a Comment