Tuesday, September 29, 2015

ትግሉ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ወይንስ ለምንይልክ ቤተ መንግሥት (ይገረም አለሙ)

ይገረም አለሙ
ፈጣሪ ዕድሜ ከጥንካሬ ጋር ያደላቸው በሀገር ጉዳይ የማይታክቱት ፕ/ር መስፍን ወልደ ማሪያም ሰሞኑን በምድረ አሜሪካ ነዋሪ ከሆኑ ኢትዮጵያውያን ጋር ያደረጉትን ውይይት ዘመነ ቴክኖሎጂ ምስጋን ይግባውና በያለንበት ሆነነን ተከታትለናል፡፡ ከውይይቱ ታዳሚዎቸች ከቀረቡ በርካታ ጥያቄዎች አንዱ በያ ትውልድ ላይ ጨከኑበት የሚል ነበር፡፡ ፕ/ር መስፍን ሲመልሱም አልጨከንኩበትም እውነቱን ነው የተናገርኩት አንዳንዶቹ እንደውም ተማሪዎቼ ነበሩና አነጋሬአቸዋለሁ፣ ፍላጎታቸው ለሀገርና ለሕዝብ ሳይሆን ሥልጣን ነበር ብለዋል፡፡
በዚሁ ሰሞን እጄ የገባው ባለ 96 ገጽ ሰነድ ውስጥ ፕ/ር የተናገሩትን የሚያረጋገጥ ከጉዳዩ ባለቤቶች አንዱ በሆነው የተነገረ አገኘሁ፡፡ ሰነዱ በእያንዳንዱ ገጽ ላይ“ በሀገርና ሕዝብ ደህንነት ጥበቃ ምኒስቴር የማዕከላዊ ምርመራ ድርጅት የወንጀል መዝገብ ቤት” የሚል ማኅተምና “ጥብቅ ምሥጢር” የሚል ማሳሰቢያ ያረፈበት ሲሆን ከኢህአፓ መሪዎች አንዱ የነበረው ብርሀነ መስቀል ረዳ በእስር ቤት የሰጠውን የምርመራ ቃል የያዘ ነው፡፡ ከአጀማመራቸው አንስቶ እስከ መንዝና መርሀ ቤት ቆይታው ይዘረዝራል፡፡

ምንም ዘመናዊ የግንኙነት ዘዴ ባልነበረበት ዘመን አፍሪካ አውሮፓና አሜሪካ ሆነው በደብዳቤ ግንኙነት ሰነድ ማዘጋጀት ድርጅት መመስረት አመራር መምረጥ መቻላቸው ብሎም ከተለያዩ ሀገራትና ድረጅቶች ጋር ግግንኙነት በመፍጠር ወታደራዊ ሥልጠና መውሰዳቸውና በኤርትራ እስከ አሲምባ መዝለቃቸው አዲስ አበባም ላይ በህቡዕ ያደረጉት አንቅስቃሴ በእውነቱ የሚያስደንቅ ነው፡፡ ግና ምን ዋጋ አለው ያንን ችሎታ፤ ያንን እውቀት፤ ያንን ድፍረትና ቁርጠኝነት የሥልጣን ጥም በላው፡፡ እንታገልለታለን ብለው የተነሱለትን ዓላማ የሥልጣን ፍላጎት በለጠውና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ቀርቶ ርስ በርሳቸውም መስማማት አንዳይችሉ አደረጋቸው፡፡ሁሉንም ሊደፈጥጥ የተዘጋጀው ደርግ አፍንጫቸው ስር እያለ የሥልጣን ጉጉት የሀሳብ ልዩነቶቻቸውን በውይይት ከማስታረቅ ይልቅ አጥፊና ጠፊ ሆነው አንዲሰለፉ አበቃቸውና፤ የአንድ ድርጅት አባላት ርስ በርሳቸው አንዲሁም አንዱ ድርጅት ከሌላው ያለምንም በቂ ምክንያት እየተጠፋፉ ለአጥፊያቸው ራሳቸውን አመቻቹ፡፡ ሊድን ያልቻለ በሽታም አስፋፉ፡፡
ብርሀነ መስቀል ከማዕከላዊ ኮሚቴ ከተባረረ በኋላ ክሊክ ብሎ ከሚጠራቸው የትግል አጋሮቹ ግድያ ሽሽት ድርጅቱ ካስቀመጠው ሰባ ደረጃ አካባቢ ለቆ እንደተሰወረና የእርማት ንቅናቄ የሚል ስራ እንደጀመረ ብዙም ሳይቆይ ደግሞ የደርግን አሰሳ በመሸሽ ከሌሎቹ አጋሮቹ ጋር ከአዲስ አበባ ወጥተው መንዝና መርሀቤት ጫካ ለመግባት እንደበቁ ይናገራል፡፡ በትግል አጋሮቻቸው የተገደሉ የአመራር አባላትን ስምም ይዘረዝራል፡፡ ግን ለምን መጠፋፋት መገዳደል! ይገኝ አይገኝ ላልታወቀ ገና ላም አለኝ በሰማይ ለሆነ ስልጣን በአንድ አላማ ስር ተሰልፈው በአንድ ድርጀት ታቅፈው ለትግል የተማማሉ የአንድ ሀገር ልጆች እስከመገዳደል መድረሳቸው ያሳዝናል፤ ይበልጥ የሚያሳዝነው ደግሞ የዛ ድርጊት መሪ ተዋናዮች ሲያዝኑም ሲያፍሩም ሲጸጸቱም አለመሰማቱ ነው፡፡
እንደ ብርሀነ መስቀል ገለጻ ከሆነ ኢህፓ ከውስጥ አመራሩ ርስ በርስ ይቆራቆሳል፣ ይህን መልክ ሳያሲዝ ከላይ ከደርግ ከጎን ደግሞ በተለይ ከመኢሶን ጋር ይታገላል፡፡ በወቅቱ የችግሮች ሁሉ ቁንጮ የነበረው የመኢሶንና የኢህአፓ ቅራኔያቸው አንቶ ፈንቶ ልዩነታቸው መሰረት የለሽ ጠባቸው የግለሰቦች የሥልጣን ጥም(ድርጅታዊ ያልሆነ) አንደነበረ በተለያየ ሁኔታ ተገልጹዋል፡፡ ይህንኑ የሚያሳይ ትንሽ ግን የትልቅ ነገር ምልክት ከብርሀነ መስቀልም ቃል ውስጥ እናገኛለን፡፡
“ሚያዚያ 13/68 የታወጀው የብሔራዊ ዴሞክራሲዊ አብዮት ፕሮግራምና በተቀዳሚ ም/ል ሊቀመንበሩ ለተራማጆች ሁሉ የተደረገውን አስቸኳይ የግንባር መቋቋም ጥሪ… በሳምንት ውስጥ ማ/ኮ ተሰብስቦ የግንባሩን ጥሪ አንቀበል የምንል ወገን የብዙሀኑን አባላት ደምጽ አግኝተን ክሊኩ በግልጽ ተሸነፈ”፣ ይልና ተሸናፊው ወገን የተለያየ ሰበብ እየፈጠረ አዘግይቶ ባወጣው መግለጫ “በኢትዮጵያ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ ለግንባሩ ብቁ ተብለው ሲዘረዘሩ ያኔ ፕሮግራሙን በይፋ አውጆ የነበረው መኢሶን ሳይጠቀስ ቀረ” ካለ በኋላ “ለግንባር ጥሪው ምላሽ የሚለው የፓርቲው መግለጫ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በተለይ የሰፊው ሕዝብ ድምጽ ጋዜጣ “ኢህአፓን ለግንባር ማን ጠራትና ተኳኩላ ቀረበች” ወዘተ የሚል የኩርፊያ ጽሁፍ አወጣ” ይላል፡፡ እስቲ ይታያችሁ ጋባዡ ተቀምጦ ተጋባዦቸ ሲጣሉ፡፡ ይህ ታዲያ የጤና ነው፡፡ በሽታው ተዛምቶ በቅርብ ግዜም እገሌ የሚባል ድርጅት ከተገኘ አንገኝም አገሌ የሚባል ሰው ከተጋበዘ አንካፈልም ሲባል ሰምተናል፡፡ መድሀኒት ያልተገኘለት መጥፎ በሽታ፡፡
የሀሳብ ልዩነትን በውይይት ማስታረቅ ሳይሆን በጉልበት መደፍለቅ፣ የተለየ ሀሳብ የሚያራምዱትን በማዳመጥ ሳይሆን በመርገጥ/በማስወገድ እኔ ብቻ ትክክል ማለትና አሻቅቦ ቤተ መንግሥትን እያዩ አባሉንና ተከታዩን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ እየጋቱ ለመስዋዕትት መዳረግ፤ተደጋጋፎ ሊታገሉ የሚገባን ድርጅት ስም እየሰጡ ወንጀል እየፈበረኩ ከቻሉ ለማጥፋት ካልሆነም ሽባ ለማድረግ እቅልፍ የሚነሳ በሽታ መቼ አንደጀመረ ባላውቅም ጎልቶ የታየውና ነጥሮ የወጣው በአብዮቱ ዘመን መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይሄው በሽታ መድሀኒት የሚፈልግለት ጠፍቶ፣ ሊያረጅም ሊዘምንም አልችል ብሎ እስካሁን የፖለቲካችንና የፖለቲከኞቻችን መታወቄያ እንደሆነ ይገኛል፡፡ ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም ሆኖብን አንደሁም አንጃ ዛሬም ከኢትየጰጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ መነሳት አለበት ከምንለው ሀይል ጋር ከሚደርገው ትግል ይልቅ የጎንዮሽ ርስ በርስ የሚደረገው ትግል የከፋ ሆኖ ነው ወያኔ ከሀያ አራት አመታት አገዛዙ በኋላ መቶ በመቶ በምርጫ አሸነፍኩ ብሎ ሊቀልድብን የበቃው፡፡
ሰሞኑን አሜሪካ ለንባብ የበቃው የሌ/ኮ ፍሰሀ ደስታ መጽሀፍ ሲተዋወቅ ጸኃፈው የኢህአፓ ቆራጥነት የመኢሶን ርዕዮተዓላመዊ ብቃት የደርግ ሀገር ወዳድነት ቢቀናጅ ተአምር ሊሰራ ይቻል እንደነበረ በቁጭት መግለጻቸውን ሰምተናል፡፡ኮረኔሉ ከዚህም አልፈው እስካሁን ማንም ያልደፈረውን ደፍረው አውቀው በድፍረት ሳያውቁ በስህተት ለፈጸሙት የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ በሁሉም ዘንድ ያለው የሥልጣን ጥም በምን ልጓም ተገቶ እንደምንስ ሰክኖ ለዚህ መብቃት ይቻላል፡፡ ጽድቁ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ እንዲሉ ይቅርታው ቀርቶ ባለፈ ስራ መጸጸትና ለአለቀው ወጣት ማዘንም አይታይም፡፡ ካለፈ መማር ቢኖር የቤተ መንግሥቱ ወንበር ለሁሉም ሊሆን አንደማይችል ነገር ግን የኢትዮጵያን ሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት የሚያረጋግጥ ሥርዓት መፍጠር ሁሉንም ንጎሶች እንደሚደርጋቸው አምነው እውቀት ልምዳቸውን ተሰጥኦ ተሞክሮአቸውን በማቀናጀት ትግሉ አንዴት፤ የት፤ በምን ሁኔታና በማን መካሄድ እንደሚችልና አንደሚገባው ሊመክሩ ሊያቅዱና ስትራቴጂ ነድፈው አንደ አቅም ችሎታው ተደጋግፈው በመታገል የግዞቱን ዘመን ባሳጠሩት ነበር፡፡ ግና አልታደልንምና ዛሬም ብዙዎቹ ራሳቸው ለሥልጣን ስለሚበቁበት ብቻ እያሰቡ የሚያውቁትን ያደጉበትንና አላረጅ ያለውን የጎንዮሽ ትግል የሙጢኝ አንዳሉ ናቸው፡፡ላያገኙት ሥልጣን ትግሉንና ታጋዩን በትንሹም ቢሆን ይጎዳሉ፤ለገዢው እድሜ መርዘም ይሰራሉ፡፡
በአብዮቱ ወቅት ከነበሩት ፓርቲዎች የአንዱ የወዝ ሊግ መሪ የነበሩት አቶ ተስፋየ መኮንን ይድረስ ለባለታሪኩ በተሰኘው መጽሐፋቸው “በሕዝባችን ፊት ተሰባስበን ችግሮቻችንን ለመፈታት ችሎታው ያልነበረን የኢትዮጵያ ልጆች የኮ/ል መንግሥቱ የግድያ ጉሮኖ ውስጥ ለመጨረሻ ግዜ ተገናኘን፡፡
ሁላችንም በተዘዋዋሪ መንገድና ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ ሲበዛ ለድርጅት ሲያንስ ለግል የሥልጣን ሽኩቻ ስንባላ ለዚያው ተመሳሳይ ዓላማ የቆሙት ኮ/ል መንግሥቱ በአሸናፊነት ሊበሉን በአንድ ቦታ አሰባሰቡን ፡፡ ክቡር በሆኑ የሕዝብ ጥያቄዎች ላይ ካደረስነው በደል አንጻር ከዚህ የበለጠ ምን የታሪክ ፍርድ ይኖራል፡፡” በማለት ነበር የወቅቱ አብይ ችግር የሥልጣን ጥም አንደነበረ ያሳዩት፡፡ ይሄው ድርጊት ነው እስከዛሬ የቀጠለው፣ ዛሬም ያለውና ወደፊትም የማይቆም የሚመስለው፡፡ ተባብሮ መስራት ቀርቶ ተከባብሮ መኖር የተሳናቸው ፓርቲዎች አባላት በወያኔ እስር ቤት በአንድ ላይ ይታሰራሉ፡፡ በመሪዎች የሥልጣን ጥም ምክንያት ትግሉ አንድ ርምጃ መራመድ ተስኖት አባላትና ደጋፊዎች ግን ሞት እስር ስደት ስቃይ እየደረሰባቸው ነው፡፡ይህንንም የዜጎች መስዋዕትነት ለእነርሱ ፍላጎት ማሳኪያ ሊጠቀሙበት የሚዳዳቸው ፖለቲከኞች እናያለን፡፡
በኢትጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር ይዘጋጅ በነበረው ርዕይ 2020 መድረክ ላይ ዶ/ር ታደሰ ብሩ ኬርሴሞ ሰላም ዴሞክራሲና ልማት የልሂቃን ሚና ዛሬና ነገ በኢትዮጵያ በሚል ርእስ ባቀረቡት ጽሁፍ «የኢትዮጵያ ልሂቃን በጣም መበታተናቸው ሳያንስ እርስ በርሳቸው በእጅጉ የሚጻረሩ አንዱ ሌላኛውን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ከመረረ ጥላቻ ጋር የተነሱ መሆናቸው አገራችን ዛሬ ለምትገኝበት አሳዛኝ ሁኔታ የዳረገን ይመስለኛል፡፡ የመጠፋፋቱ ትግል በደርግ ግዜ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረ ቢሆንም አሁንም መልኩን እየቀያየረ ቀጥሏል ፡፡ ኢትዮጵያዉያን ልሂቃን በአገራዊ ጉዳዮች የጋራ መግባባት ላይ ካልደረሱ በስተቀር ይህ የጥላቻና የመጠፋፋት ፖለቲካ በቀላሉ የሚቆም አይመስለኝም፡፡ ብለው ነበር ፡፡ ዶ/ር ታደሰ እንዲህ ብለው ብቻ አላበቁም፣የልሂቃኑ ለድርድር መዘጋጀት እጅግ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ሲገልጹ « እዚህ ላይ አጽንኦት ልሰጥበት የምፈልገው ጉዳይ ግን ጥሩ ሕገ መንግሥት፣ ጥሩ የምርጫ ሕግ እና ግልጽና ፍትሀዊ ምርጫ ወዘተ..ቢኖሩም እንኳን ልሂቃኑ ለድርድር የተዘጋጁ ካልሆኑ ዲሞክራሲ መኖር የማይችል መሆኑ ነው» ነበር ያሉት፡፡ ጽሁፉ ከቀረበ 10 አመታት ያለፉት ቢሆንም የተለወጠ ነገር የለም፤ እንደውም መሻል ቀርቶ ብሶበታል፡፡ዛሬስ ወደፊትስ…፤
ለውጥ ያለመታየቱ ምክንያትም ፕ/ር መስፍን በአሜሪካው የውይይት መድረክ ላይ የተናገሩትና በተለያዩ ጽሆፎቻቸው የገለጹት በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ ያለው የሥልጣን ጥም ነው፡፡ ከዚህ እንዴት መገላገል ይቻል ይሆን! ፕ/ር መስፍን ሥልጣን ባህልና አገዛዝ፣ፖለቲካና ምርጫ በሚለው መጽሀፋቸው አንዲህ ይላሉ ፡፡
“እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ወደ ፖለቲካ ሲገባ ከልጅነት እስከ እውቀት በውስጡ የተመረገውን የጌትነትና የሎሌነት ባህል ፍቆ ፈቅፍቆ ማርገፍ አለበት፡፡በግድ የአሰተሳሰብ የጽዳት ዘመቻ ያስፈልገናል፡፡ ዓላማን የማጥራት ዘመቻ ያስፈልግናል፡፡በግድ የነጻነትና የእኩልነት አራማጆች በቁርጠኝነት መነሳትና ማሳየት ያስፈልገናል፡፡ ብዙዎቹ የተቀናቃኝ መሪዎች ላይ የሚታየው የድሮው መኳንንትና መሳፍንት ለመምሰል የመሞከር ጠባይና ከዚህም ጋር ተያይዞ ሎሌዎችን በገንዘብ ሆነ በወደፊት ተስፋ እየገዙ የአገዛዝን ባህል ለማራማድ የሚደረገው ሙከራ የፖለቲካውን ሥርዓት አያራምድም ፡፡ ጥረቱ ሁሉ በሥልጣን ላይ ያሉትን ሰዎች ለመለወጥ እንጂ ሥርዓትን ለመለወጥ አይመስልም” (ገጽ 32)
ሎሬት ጸጋየ ገብረመድህን በአንድ ወቅት ከጦቢያ መጽሄት ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ በገለጸው ስጋት ልሰናበት“ኔልሰን ማንዴላ እንደ ስምጥ ሸለቆ ቁልቁል የጠለቀውን ‹የልዩነት›› መቀመቅ በዴሞክራሲ ድልድይ ገደሉን አስተካሎ የመቻቻልን ጥበብ ለወገኑ ሲታደግ የኛ ተቀዋሚዎች ፖለቲከኞች ግን በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል አዳስ ሰምጥ ሸለቆዎች አንዳይቆፍሩ እሰጋለሁ፡፡”

No comments:

Post a Comment