Friday, January 18, 2013

አስርቱ እኩኝ የወያኔ መንግስት ስትራተጂዎች



ከእለት ወደ እለት የወያኔ መንግስት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የሚያደርሰዉ ግፍ እየተባባሰ ሀይ የሚለዉ በመታጣቱ፤ ምንአልባትም ብዙዎች የወያኔን ክፋት ቢያዩት በሚል ብእሬን እንዳነሳ ተገደድኩኝ፡፡ ወያኔ ስልጣን ላይ ከመጣበት ከ 1983 አነስቶ እስካሁን የስልጣን ዘመን ድረስ የኢትዮጵያን ሕዝብ ምን አተረፈ ምንስ ጎደለበት፤ ወያኔስ የገባዉ የተስፋ ቃል ምን ላይ ወደቀ ምንስ ግቡን መታለት እያልኩ ሳሰላ፤ ሚዛን የሚደፋ ምንም መልካም አጣሁ፡፡ ስለዚህ የወያኔ መንግስት ስልጣን ላይ ለዘመናት ለመቆየት የዘረጋቸዉን እኩይ እስትራቴጂዎች ከእዚህ በታች እደተዘረዘሩት ተመለከትኳቸዉ፡፡

1. ህዝብ በተለያየ መንገዶች ትኩረቱን በመያዝ ስለመብቱ፤ ስለኢኮኖሚዉ ብሎም ሀገሪቱ ዉስጥ በመንግስት ስለሚደረጉ የክፋት ተግባራት እንዳያዉቅና እንዳይቃወም ማዘናጋት፡፡
2. ወጣቱን ከዕዉቀትና ከኢኮኖሚ ዕንዲርቅ በማድረግ በተጨማሪም የማሠብ ችሎታዉን እንዳይጠቀም፤ እንዳያሰፋ የተለያዩ ማዘናጊያዎችን ማድረግ፡፡ ለምሳሌ በአዉሮፓ ሀገራት ሰፖርቶች ማጥመድ፤ ወጣቱ 24 ሰዓት ስለ ማንችስተር፤ አርሰናል፤ ቼልሲ… ወዘተ የመሳሰሉትን እንዲያወራና ስለ መብቱ ወይም ስለ ኢኮኖሚ እንዳያነሳ ማድረግ፡፡
3. የተለያዩ ሚዲያ ተቋማትን በመጠቀም ስለ ሙዚቃ ኮንሰርት ማስታወቂያ በማስነገር ወጣቱ በእንደነዚህ አይነት ነገሮች እንዲጠመድ በማድረግ ጥያቄዎቹን ማዳፈን፡፡ ወያኔ ለራሱ አላማ ማስፈፀሚያ የሚጠቅሙትን ወጣት ካድሬዎች በጥቅም በመደለል መመልመልና አሠልጥኖ በህዝብ ዉስጥ በማስረግ ህዝቡን የማዘናጋት ስራ እንዲሰሩ ማድረግ፤ ከተሳካም አባላትን እየመለመሉ ደቀመዝሙር ማድረግ፡፡
4. በህዝብ ዉስጥ ሆንብሎ አደገኛ የሆኑ ችግሮችን መፍጠርና በፍጥነት መፍህትሄዎችን ማቅረብ፤ በዚህ ሁኔታ ዉስጥ የህዝቡን ምላሽ ደካማና ጠንካራ ጎኑን ማየት፡፡ በኢትዮጵያ ዉስጥ አስከ ዛሬ ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በህዝቡ ዉስጥ የተፈጠሩ ችግሮች ባለቤት ራሳቸዉ ወያኔዎች ናቸዉ፡፡ ወያኔዎች ችግሩን ፈጥረዉ የህዝቡን ደካማና ጠንካራ ጎኖች ከለዩ በኋላ፡ ጠንካራ አቌም ያላቸዉን ግለሰቦች፤ ህዝብን ሊመሩ፤ ስለመብት ጥያቄ ሊያነሡ ወይም የሚያነሡትን ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ይልካሉ፤ አኔ ግን ወደ ቃሊቲ ዩኒቨርስቲ ያጉሩና ቶርች በማድረግ ሰብዐዊ ያልሆኑ የስቃይ ትምህርት ይሰጡበታል፤ ያዋርዱበታል፤ ሞራልን ይገሉበታል ... ወዘተ፡፡
በችግሩ የተለዩ ደካማ ጎኖች የአሸባሪ ስም ይለጠፍባቸዉና ጥሩ ወዳጅነት በዚሁ አሸባሪነት ምክንያት ከአሜሪካና መሰል ሀገሮች ሰላለ ሚሊዮኖች ዶላር እርዳታ ተቀብለዉ የህዝቡን ደካማ ጎኖች በደንብ እንዲሠፉ ያደርጋሉ፤ ሥርመሠረት ከሌላቸዉም በደንብ ስር እንዲይዙ አድርገዉ ያጎለብቷቸዋል፤ እንደአስፈላጊነቱ ሐዉልትም ሊያቆሙላቸዉ ይችላሉ፡፡
5. የከተሞች ምስቅልቅል ችግር እንዲያድጉ ማድረግ፡ ለምሳሌ በአንዳንድ ከተሞች የዉሀ ችግሮች ይኖራሉ፡ እነዚህ ችግሮች ጭራሹኑ እንዲባባሡ ማድረግ፤ መብራት እንዲጠፋ ማድረግ፤ እነዚህ መሰረታዊ ነገሮች እንዲሙዋሉለት ነዋሪዉ ሲጠይቅ፤ እነዚህን ፍላጎቶች ለማግኘት ሌሎች አገልግሎቶችን መቀነስ፤ ታክስ መጨመር ከአሁን በፊት የማይከፍልም ከሆነ እንዲከፍል ማስገደድ፤ህክምና ከአሁን በፊት በነፃ ያገኝ ከሆነ ከላይ የተጠቀሱትን ፍላጎት ለማሟላት ከዚህ በሗላ ለህክምና መክፈል አለብህ በማለት የሚፈልገዉን ነገር እንዳይጠይቅ በማድረግ፤ ከጠየቀም የተለያዩ ግዴታዎችን በማስገባት ማስፈረም፤ በዚህ ሁሉ ሂደት ዉስጥ ህዝብ ሲጮህ አመታት እንዲቆጠሩ በማድረግ የስልጣናቸዉን እድሜ ያራዝማሉ፡፡
6. ከባድ የሆነ የኢኮኖሚ ችግር በመፍጠር ዋናዋና (Basic) የሆኑ ፍጆታዎች ላይ ዋጋ መጨመር ወይም እጥረት እዲኖር ማድረግ፡፡ ሕዝብ በጣም የሚፈልጋቸዉን ለህይወቱ መሰረታዊ የሆኑ ነገሮችን ያሳጡታል፡፡ ለምሳሌ፡- የምግብ አቅርቦት እጥረት፤ የቤት ኪራይ ዉድነት፤ ነዳጅ እዲወደድ ማድረግ፤ የትራንስፖርት እጥረት መፍጠር፤ ሰዎች ከቦታ ቦታ፡ ወደ ስራ ገበታቸዉ በሰአታቸዉ ለመሄድ ትራንስፖርት ለማግኘት ሲጋፉ ሲቸገሩ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ በዝምታ ማየት፤ አንዳንድ ግለሰቦች ከዉጪ መኪኖች ለማስገባትና በትራንስፖርቱ ዘርፍ ለመሰማራት ሲሞክሩ መኪናዉ ከሚያወጣዉ ዋጋ በላይ ታክስ በመጠየቅ ተስፋ በማስቆረጥ ህዝቡ ምንም አይነት አማራጭ እዳያገኝ በማድረግ ያዳክሙታል፡፡
የእህል የጥራጥሬና የቀንድ ከብቶች እጥረት እንዲኖር ቢኖርም እንዲወደድ ያደርጋሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በህጋዊና በህገወጥ ከአገር የሚወጡ የቀንድ ከብቶች ቁጥር አገር ዉስጥ ከአለዉ አቅርቦት በምንም አይመጣጠንም፤ በዚህ ምክንያት ዜጎች በግ ወይም ፍየል ገዝተዉ ለመብላት የማይታሰብ ከሆነ ዉሎ አድሯል፡፡ እንደነዚህ ያሉ ችግሮች ሲፈጠሩ መንግስት እጁን ጣልቃ ሊያስገበና የግሉን ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ሊያደርግ ሲገባ ጉዳዩ ስር እየሰደደ ከችግሩ መዉጣት ወደማይቻልበት ደረጃ አድርሶታል፡፡
7. የ አስር (10) እና የ ሀያ (20) አመታት እቅዶችን በማዉጣት የህዝቡ ኑሮ እንዲያሽቆሎቅል ያደርጉታል፡፡እነዚህ እቅዶች ተራ ቁጥራቸዉን ጠብቀዉ በየጊዜያቸዉ በህዝቡ ላይ ሳይወድ በግድ ተፈፃሚ ይሆናሉ፡፡ በተጨማሪም እዲቀበላቸዉ፤ እንዲለምዳቸዉ በማድረግ የማሰብ ችሎታዉን ያዳክሙታል፡፡ የዛሬ መራራ የነገ ጠፋጭ ይሆናል የሚል እስትራቴጂ ያወጡለታል፤ ባዶ ተስፋም ይመግቡታል፡፡ ከጥቂት አመታት በኋላ መካከለኛ ገቢ ካላቻ ሀገሮች ተርታ ትገባለህም ይሉታል፤ አሁን ለአንተ ባይመችም ለሚቀጥለዉ ትዉልድ ጥሩ ተስፋ ይኖረዋል፤ ችግር ቢኖርም ተጋግዘን ለመወጣት እንሞክራለን፡ ቀጣዩ ትዉልድ ዛሬ ያቆምንለትን ያገኘዋል፤ ይኖረዋል እያሉ ባዶ ተስፋ ያሳቅፉታል፡፡
ብዙዉን ጊዜ የአንባገነን ባህሪ ያላቸዉ መንግስታቶች የሚያሥነግሩዋቸዉ ማስታወቂያዎች ልክ ህፃን ልጅን እንደሚያባብሉ እሹሩሩዎች ናቸዉ፡፡ ጥሩ ጥሩ ጣእመ ዜማ ያላቸዉና በጥንቅናቄ የተመረጡ ቃላትን ጨምረዉ ለህዝቡ ያዜሙለታል፡፡
ለምሳሌ የማስታዉሰዉ በመንግስቱ ኀይለማርያም ዘመን የጅማ ህፃናት ለቡና የዘመሩትን ያስታዉሰኛል፡፡
የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና፤
የገቢ ምንጫችን ቡና ቡና .... ወዘተ፡፡
የሚለዉን ዝማሬ መቼም የቱን ያክል በኢትዮጵያ ህዝብ ጆሮ ላይ እንዳሉ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነዉ፡፡ይህን ዝማሬ ማር የሚያዘንቡ በሚመስል ዝማሬ ህፃናቱ ሲዘምሩ ሲሰማ በዛን ወቅት በአለም ላይ በቡና አቅርቦት ታዋቂ ከነበሩት ከብራዚልና ከኮሎንቢያ በላይ አምራችና አቅራቢ እንደ ኢትዮጵያ ያለ አይመስልም ነበር፡፡ ነገሩ ግን ጉዳዩ የተገላቢጦሽ ነበር፤ በወቅቱ ሀገራችን በአለምላይ ጥራቱ እጅግ የወረደ እዚህ ግባ የማይባል የተበላሸ ቡና ነበር የምታቀርበዉ፡፡ ነገር ግን መንግስቱ ጥሩ መዝሙር እያዘመረ፤ አረንጏዴ ወርቃችን እያለ እየቀለደ ህዝቡ በመሬቱ በአግባቡ እንዳይሰራ እያደረገ ሲሻዉ መሬቱን እየወረሰ በድህነት አለንጋ እየገረፈ ሲያሰቃያቸዉ እደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነዉ፡፡
እንዲህና ይህንን የመሳሰሉ አዉዳሚ የሆኑ ማስታወቂያዎችን እየሰሩ የህዝብን የማስተዋል ችሎታ ያወርዱታል፡፡ ህዝብን የሚያኮስስ ተስፋ የሚያስቆርጡ ግራ ቀኙን በሰፊ ማየት እንዳይችሉ የሚያደርጉ ማስታወቂያዎችን ያስነግሩበታል፤ ባጠቃላይ እንደ ወያኔ ያሉ አንባገነኖች ህዝብን እንደሞኝ ምንም እንደማያዉቅ አድርገዉ ፤ንቀዉ፤ አዋርደዉ፤ ረግጠዉ ሊገዙት ይመኛሉ፡፡ ሕዝብን የሚያበረታቱ ተስፋን የሚሰጡ ለራሱ፤ ለቤተሰቡና ለሀገሩ እንዲያስብ ሊያነሳሱ የሚችሉ ሀላፊነት አለብኝ ብሎ በወኔ እንዲነሳ እንዲመራመር እንዲጠይቅ ከማድረግ ይልቅ በሞኖፖል በተቆጣጠሩት ቴሌቪዥን ተስፋ እንዲቆርጥ፤ እንዲኮስሰ፤ ነገን በተስፋ እንዳያይ፤ ማስተዋሉ እንዲሞት የሚያደርጉ ማስታወቂያዎችን ይነግሩታል፡፡ ለምሳሌ፡- በቅርቡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ ሞት ህዝቡን ሰብስበዉ የለቅሶ ቲያትር ሲያሰሩት መክረማቸዉን አይተናል፤ ሲፈልጉ ደግሞ ሰብስበዉ እንዲስቅ እያደረጉ በፈለጉት መንገድ ይነዱታል፡፡
8. ሕዝብ እውቀት እንዳይኖረዉ መሀይም ሆኖ እንዲኖር የጊዜዉን ቴክኖሎጂ እነዳያዉቅ፤ እንደያገኝ ያደርጉታል፡፡ እንደ ፓል ቶክ፤(paltalk) ፌስቡክ (facebook)የመሳሰሉትን ሊዘጉ ይሞክራሉ፡፡ የህዝብ ዕዉቀት በሀገር ዉስጥ ብቻ የተወሠነ እንዲሆን፤ ከአዲስ አበባ እነዳያልፍ፤ የጎረቤት ሀገሮችን እንኳን መረጃ እንዳያገኝ ያደርጉታል፡፡
9. ዜጎች የኢንተርኔት እውቀት እንዳይኖራቸዉ ቢኖርም እንኳን የተሻለ ኢንተርኔት አማራጭ እንዲያገኝ ከማድረግ ይልቅ ደካማዉን ያቀርቡለታል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ዉስጥ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ቁጥር ከ82 ሚሊዮን ህዝብ ዉስጥ 0.7 ፐርሰንት ብቻ ሲሆን፤ የፌስቡክ (facebook) ተጠቃሚ ደግሞ 946 ሰዎች ብቻ ናቸዉ፡፡ መረጃዉን ያገኘሁት ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የእሁድ መዝናኛ ፕሮግራም ላይ የኢንተርኔት መሀበራዊ ድህረ-ገፆች አሉታዊና አወንታዊ ጎናቸዉ በሚል እርዕስ ከባለሙያ ጋር አዘጋጁ በ28-04-2005 ዓም. ወይም በ 06-01-2013 እንዳቀረበዉ፡፡ እናም በዚህ መልኩ ዜጎች መረጃ የማግኘት መብታቸዉ ተነፍጎ፤ እዉቀት እንዳይኖራቸዉ የፈጠራ አድማሳቸዉን እንዳያሰፋ ያደርጉዋቸዋል፡፡
10. ዝቅተኛ መደቦች (Lower class) እና ከፍተኛ መደቦችን (Higher class) በመፍጠር ዝቅተኛዉን መደብ ደሀ በሆኑ እርባና በሌላቸዉ እዉቀቶች ያጨናንቁታል፡፡ ለምሳሌ፡- በመንግስት ትምህርት ቤቶች ዉስጥ የ12 ክፍል ተማሪን እና የከፍተኛ መደቡን ተማሪ በግል የተሻለ ትምህርት የሚያገኘዉን ለንፅፅር ብናቀርብ ዉጤቱ የዝቅተኛዉ መደብ ተማሪ ፍሬቢስ ነዉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እርባና በሌላቸዉ እዉቀቶች ጊዜዉን እና ገንዘቡን ብቻ እንዲያጠፋ ስለተደረገ ነዉ፡፡ ባጠቃላይ የትምህርቱ ካሪኩለሞች (Curriculums) የሀይማኖትን፤ የዘርን ልዩነት የሚያጎሉ እስትራቴጂዎች ናቸዉ፡፡
ከፍተኛ መደቦች (Higher class) የተሻለ እዉቀት ወዳለባቸዉ ወደ ግል የትምህርት ተቓማት በመሄድ ዉጤት ያለዉ እዉቀት እንዲያገኙ በማድረግ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና የስራ አማራጮችንም ሆነ እስኮላር የእነሱ እንዲሆን ያደርጋሉ፡፡ በዚህ
መልኩ መሳፍንታዊ የሆነ መደብ ይፈጠራል፤ ስለዚህ በ 10 እና 20 አመታት ዉስጥ የገዢና የተገዢ መደብ ይፈጠራሉ፡፡ ይህ ደግሞ ህዝብን በአግባቡ የሚያስተዳድሩ ሳይሆን ህዝብን የሚገዙ የሚጨቁኑ ይሆናሉ፡፡ ህዝብ ከተገዛ ባሪያ ነዉ፤ ከተዳደረ ግን ነፃ ነዉ፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ዉስጥ እየታየ ያለዉ ማስተዳደር ሳይሆን መግዛት ነዉ፤ ምክንያቱም አሁን ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚታየዉ የአንድ በሄር የበላይነት ነዉ፤ የጦር ሀይሉን የሚመሩት ከአንድ ብሄር ከአንድ እምነት ነዉ፡፡
እነዚህንና ምናልባትም ሌሎች ብዙ ያልጠቀስኳቸዉ እስትራቴጂዎች አንባገነኑ ወያኔ የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ሊቀልድበት ሲሻዉ እኔ ፈቅጄና ወድጄ ከማወጣልህ እስትራቴጂና ህግ ዉልፊት ብትል የሚደርሰብህ ከህገመንግስቱ ጋር መላተም ይሆንብሀል ይለዋል፡፡ ከህገመንግስቱ ጋር መላተም ማለት ደግሞ የሚያስከትለዉን የህግ ዉጤት ከማስፈራራት ጋር ይነግረዋል፡፡ ሲሻዉ ደግሞ ህዝቤ ሆይ ከእኔ በላይ የሚያስብልህ ላሳር፡ በጎ ፈቃዴን የሰጠሁህ እያለ ይሳለቅበታል፡፡
ኧረ ለመሆኑ ወገኖቼ እንዲህ በህዝባችን ላይ፤ በምድራችን ላይ ወያኔን እንዲፈነጭ፤ እነዲያስር፤ እነዲገድል፤ ሴት እህቶቻችንን ለአረብ ሀገራት እነዲሸጥ፤ ህፃናት ልጆቻችንን ለምዕራብያን እነዲሸጥ፤ የአንዱን ብሄር በሌላዉ ላይ እነዲነሳ ሊያደርግ፤ መብት የሰጠዉ ማነዉ??
ዉድ ኢትዮጵያዊ ወገኖቼ ከዚህ በኋላ ጊዜ የለንም ወገኖቻችን የድረሱልን ጩኸት እያሰሙ ነዉ፣ ያለልዩነት እጅ ለ እጅ ተያይዘን እንቢ ለመብቴ፣ እንቢ ለወገኔ፣ እንቢ ለኢትዮጵያ ፣ ብለን አንባገነኑን ወያኔን ከህዝባችን ጫንቃ ላይ ልናነሳዉ ይገባል፡፡
                       ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!
                          ከሰብኣዊ

No comments:

Post a Comment